በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2014

የማያምኑ ዘመዶቻችንን ልብ መንካት

የማያምኑ ዘመዶቻችንን ልብ መንካት

“ወደ ቤት ሄደህ ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ሁሉና ያሳየህን ምሕረት ለዘመዶችህ ንገራቸው።” ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ያለው እሱን ሊከተለው ለፈለገ አንድ ሰው ነበር፤ በወቅቱ ኢየሱስ ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ ምሥራቅ ባለችው በጋዳራ የነበረ ይመስላል። የሰው ልጆች ትኩረታቸውን የሚስቡና ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው ነገሮች ሲያገኙ ይህን ለዘመዶቻቸው ማካፈል እንደሚፈልጉ ኢየሱስ ተገንዝቦ ነበር።—ማር. 5:19

በዛሬው ጊዜም ሰዎች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው እናያለን፤ እርግጥ ከዘመዶቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደ ባሕሉ ይለያያል። አንድ ሰው የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አገልጋይ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ስለ አዲሱ እምነቱ ለዘመዶቹ መናገር ይፈልጋል። ይሁንና ይህን ማድረግ ያለበት በምን መንገድ ነው? ከእሱ የተለየ እምነት ያላቸውን ወይም ጨርሶ እምነት የሌላቸውን ዘመዶቹን ልብ መንካት የሚችለውስ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ጠቃሚና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ይሰጣል።

“መሲሑን . . . አገኘነው”

በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው እንድርያስ፣ ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ካስተዋሉት የመጀመሪያ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ታዲያ ያወቀውን ነገር ወዲያውኑ የተናገረው ለማን ነው? “እንድርያስ በመጀመሪያ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና ‘መሲሑን (ትርጉሙ ክርስቶስ ማለት ነው) አገኘነው’ አለው።” እንድርያስ ጴጥሮስን ወደ ኢየሱስ የወሰደው ሲሆን ይህን በማድረጉም ጴጥሮስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን አጋጣሚ ከፍቶለታል።—ዮሐ. 1:35-42

ይህ ከሆነ ከስድስት ዓመት ገደማ በኋላ ጴጥሮስ በኢዮጴ አርፎ ነበር፤ በዚህ ጊዜ፣ በስተ ሰሜን ወዳለችው ወደ ቂሳርያ ሄዶ ቆርኔሌዎስ የተባለውን የመቶ አለቃ እንዲያነጋግር ተጋበዘ። ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ ቤት ሲደርስ እነማንን አገኘ? መጽሐፍ ቅዱስ “ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ [ጴጥሮስንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች] እየጠበቃቸው ነበር” ይላል። ቆርኔሌዎስ እንዲህ በማድረግ፣ ዘመዶቹ የጴጥሮስን ንግግር የማዳመጥና በሰሙት ነገር ላይ ተመሥርተው ውሳኔ የማድረግ  አጋጣሚ እንዲያገኙ መንገድ ከፍቶላቸዋል።—ሥራ 10:22-33

እንድርያስና ቆርኔሌዎስ፣ ለዘመዶቻቸው ካደረጉት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

እንድርያስም ሆነ ቆርኔሌዎስ ዘመዶቻቸው እውነትን እንዲሰሙ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን ወስደዋል። እንድርያስ፣ ጴጥሮስን ወስዶ ከኢየሱስ ጋር አስተዋውቆታል፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹ የጴጥሮስን ንግግር እንዲያዳምጡ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይሁንና እንድርያስም ሆነ ቆርኔሌዎስ በዘመዶቻቸው ላይ ጫና አላሳደሩባቸውም፤ ወይም ደግሞ ብልጠት ተጠቅመው የክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ ለማድረግ አልሞከሩም። ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? እኛም እንደ እነሱ ብናደርግ የተሻለ ውጤት እናገኛለን። ለዘመዶቻችን አንዳንድ ሐሳቦችን ልናካፍላቸው እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንዲያውቁና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እንዲተዋወቁ አጋጣሚ ልናመቻችላቸው እንችላለን። ያም ቢሆን የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ መብታቸውን ማክበርና አላስፈላጊ ጫና ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል። ዩርገን እና ፔትራ የተባሉ በጀርመን የሚኖሩ ባልና ሚስት ተሞክሮ፣ ዘመዶቻችንን እንዴት መርዳት እንደምንችል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።

ፔትራ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናች ሲሆን ከጊዜ በኋላም ተጠመቀች። ባለቤቷ ዩርገን በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያገለግል ነበር። መጀመሪያ ላይ ዩርገን በባለቤቱ ውሳኔ ደስተኛ አልነበረም። ውሎ አድሮ ግን፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደሆነ ተገነዘበ። እሱም ራሱን ለይሖዋ ወስኖ የይሖዋ ምሥክር ሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። ዩርገን፣ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆነን ዘመድ ልብ መንካት ስለሚቻልበት መንገድ ምን ምክር ይሰጣል?

እንዲህ ብሏል፦ “ዘመዶቻችንን መጫን የለብንም፤ ያወቅናቸውን መንፈሳዊ ነገሮች በሙሉ በአንድ ጊዜ ልናዥጎደጉድባቸውም አይገባም። እንዲህ ማድረግ ከእውነት ይበልጥ ሊያርቃቸው ይችላል። የተሻለ የሚሆነው፣ በየጊዜው ስለ እውነት ትንሽ ትንሽ መናገሩ ነው። ከዚህም ሌላ ዘመዶቻችን በእነሱ ዕድሜ ካሉና እንደ እነሱ ዓይነት ዝንባሌ ካላቸው ወንድሞች ጋር እንዲገናኙ ማድረጉ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን እነሱን መርዳት ቀላል እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረክታል።”

“ዘመዶቻችንን መጫን የለብንም፤ ያወቅናቸውን መንፈሳዊ ነገሮች በሙሉ በአንድ ጊዜ ልናዥጎደጉድባቸውም አይገባም።”—ዩርገን

ሐዋርያው ጴጥሮስና የቆርኔሌዎስ ዘመዶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀበል ጊዜ አልወሰደባቸውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩና እውነትን የሰሙ ሌሎች ሰዎች ግን ውሳኔ ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ አስፈልጓቸው ነበር።

ስለ ኢየሱስ ወንድሞችስ ምን ማለት ይቻላል?

ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ያከናውን በነበረበት ወቅት ከዘመዶቹ መካከል የተወሰኑት በእሱ አምነው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የተባሉት ሐዋርያት እናት የሆነችው ሰሎሜ አክስቱ ሳትሆን አትቀርም፤ በመሆኑም ያዕቆብና ዮሐንስ የአክስቱ ልጆች የነበሩ ይመስላል። ሰሎሜ፣ ኢየሱስንና ሐዋርያቱን “በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር” ከተባለላቸው “ብዙ ሴቶች” አንዷ ሳትሆን አትቀርም።—ሉቃስ 8:1-3

ሌሎቹ የኢየሱስ የቅርብ ዘመዶች ግን በእሱ ያመኑት ከጊዜ በኋላ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከተጠመቀ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የሆነውን እንመልከት፤ እሱ ሲያስተምር ለመስማት ብዙ ሰዎች በአንድ ቤት ተሰብስበው ነበር። “ዘመዶቹ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ‘አእምሮውን ስቷል’ በማለት ሊይዙት መጡ።” ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ ወንድሞቹ ከጉዞው ጋር በተያያዘ ሐሳብ ባቀረቡለት ወቅት ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ወንድሞቹ . . . አላመኑበትም ነበር።”—ማር. 3:21፤ ዮሐ. 7:5

ኢየሱስ ዘመዶቹን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ዘመዶቹ “አእምሮውን ስቷል” ባሉት ወቅት ቅር አልተሰኘባቸውም። ኢየሱስ ከተገደለና ከሞት ከተነሳ በኋላም ለወንድሙ ለያዕቆብ በመገለጥ ዘመዶቹን አበረታቷቸዋል። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ ያዕቆብ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ ወንድሞቹም እሱ፣ መሲሕ መሆኑን እንዲያምኑ ሳይረዳቸው አልቀረም። በመሆኑም ከሐዋርያትና ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር በኢየሩሳሌም ደርብ ላይ በነበረው ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ መንፈስ  ቅዱስን ከተቀበሉት ደቀ መዛሙርት መካከል እነሱም የነበሩ ይመስላል። ከጊዜ በኋላም፣ ይሁዳ የተባለው ሌላው የኢየሱስ ወንድም እንዲሁም ያዕቆብ አስደናቂ መብት አግኝተዋል።—ሥራ 1:12-14፤ 2:1-4፤ 1 ቆሮ. 15:7

አንዳንዶች ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋሉ

“ምንጊዜም ታጋሽ መሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።”—ሮስቪታ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ የማያምኑ ዘመዶችም በሕይወት መንገድ መጓዝ እስኪጀምሩ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ሮስቪታን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ባለቤቷ በ1978 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር በሆነበት ወቅት ሮስቪታ አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበረች። ሮስቪታ ለእምነቷ ቅንዓት ስለነበራት መጀመሪያ ላይ ባሏን ትቃወመው ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን ተቃውሞዋ እየረገበ የመጣ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩም ተገነዘበች። በ2003 እሷም ተጠመቀች። ሮስቪታ ለውጥ እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው? ባለቤቷ መጀመሪያ ላይ ባደረሰችበት ተቃውሞ ከመናደድ ይልቅ አመለካከቷን ለመቀየር የሚያስችል አጋጣሚ የሰጣት መሆኑ ነው። ታዲያ ሮስቪታ ምን ምክር ትሰጣለች? “ምንጊዜም ታጋሽ መሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብላለች።

ሞኒካ የተጠመቀችው በ1974 ሲሆን ሁለት ወንዶች ልጆቿ ደግሞ ከአሥር ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ባለቤቷ ሃንስ እምነቷን ባይቃወምም እስከ 2006 ድረስ አልተጠመቀም ነበር። የቤተሰቡ አባላት ያለፈውን ጊዜ መለስ ብለው በማስታወስ ምን ምክር ይሰጣሉ? “ከይሖዋ ጋር በታማኝነት ተጣበቁ፤ ከእምነታችሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ፈጽሞ አቋማችሁን አታላሉ” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ ሃንስን ምንጊዜም እንደሚወዱት ያሳዩ ነበር። እንዲሁም ውሎ አድሮ የእነሱ ዓይነት እምነት እንደሚይዝ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጉ ነበር።

በእውነት ውኃ መርካት

በአንድ ወቅት ኢየሱስ የእውነትን መልእክት፣ የዘላለም ሕይወት ከሚያስገኝ ውኃ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐ. 4:13, 14) ዘመዶቻችን፣ ቀዝቃዛና ንጹሕ የሆነውን የእውነት ውኃ ጠጥተው እንዲረኩ እንፈልጋለን። ሆኖም ብዛት ያለው ውኃ በችኮላ እንዲጠጡ ብናስገድዳቸው ትን ይላቸዋል፤ ይህ እንዲሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ዘመዶቻችን የእውነትን ውኃ ሲጠጡ እንዲረኩ አሊያም ደግሞ ትን እንዲላቸው የሚያደርገው እኛ እውነትን የምናቀርብበት መንገድ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” እንዲሁም “የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤ ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ” ይላል። ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—ምሳሌ 15:28፤ 16:23

አንዲት ሚስት እምነቷን ለባሏ ማስረዳት ትፈልግ ይሆናል። ‘የምትሰጠውን መልስ አስቀድማ የምታመዛዝን’ ከሆነ የምትናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ ትመርጣለች እንዲሁም አትቸኩልም። ባለቤቷ እንደምትመጻደቅበት ወይም ከእሱ እንደምትበልጥ አድርጋ እንደምታስብ እንዳይሰማው ለማድረግ ትጠነቀቃለች። የምትናገረው ነገር በደንብ የታሰበበት ከሆነ መንፈስን የሚያድስና ሰላም የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። ባለቤቷ ዘና የሚለውና እሱን ማነጋገር የሚቀላት መቼ ነው? ማውራት ወይም ማንበብ የሚወደው ስለ ምን ነገር ነው? ሳይንሳዊ ነገሮች፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወይም ስፖርት ይወዳል? ስሜቱንና አመለካከቱን እያከበረች በሌላ በኩል ደግሞ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎቱ እንዲነሳሳ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዲት ሚስት ለእነዚህ ነጥቦች ትኩረት መስጠቷ ንግግሯም ሆነ ድርጊቷ ማስተዋል የታከለበት እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የቤተሰባችንን አባላት ልብ ለመንካት ስለ እምነታችን በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ከማዥጎድጎድ መቆጠባችን አስፈላጊ ቢሆንም ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። ምግባራችንም የምንናገረውን ነገር የሚደግፍ መሆን አለበት።

ምሳሌ የሚሆን ምግባር ይኑራችሁ

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዩርገን እንዲህ ብሏል፦ “በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ምንጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪዎችን ተግባራዊ አድርጉ። ይህን ማድረጋችሁ፣ የማያምነው የቤተሰብ አባል የተመለከተውን ለውጥ አፍ አውጥቶ ባይናገርም እንኳ ስለ ጉዳዩ በቁም ነገር እንዲያስብበት የሚያነሳሳ ጥሩ ዘዴ ነው።” ባለቤቱ ወደ እውነት ከመጣች ከ30 ዓመት በኋላ የተጠመቀው ሃንስም በዚህ ይስማማል። “አንድ ክርስቲያን ምሳሌ የሚሆን ሕይወት መምራቱ አስፈላጊ ነው፤ ይህም እውነት በሕይወታችን ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ የማያምነው የቤተሰብ አባል እንዲመለከት ያደርጋል” ብሏል። በእምነታችን ምክንያት ከሌሎች ሰዎች የተለየ አቋም በሚኖረን ጊዜ እንኳ እምነታችን የተሻሉ ባሕርያትን እንድናዳብር እንደረዳን እንጂ መጥፎ አካሄድ እንድንከተል እንዳላደረገን ዘመዶቻችን ከሕይወታችን እንዲመለከቱ ማድረግ ይገባናል።

“አንድ ክርስቲያን ምሳሌ የሚሆን ሕይወት መምራቱ አስፈላጊ ነው፤ ይህም እውነት በሕይወታችን ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ የማያምነው የቤተሰብ አባል እንዲመለከት ያደርጋል።”—ሃንስ

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የማያምን ባል ላላቸው ሚስቶች የሚከተለውን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል፦ “ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለገዛ ባሎቻችሁ ተገዙ፤ ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት በዓይናቸው ሲመለከቱ ነው። ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ የወርቅ ጌጣ ጌጦች በማድረግ ወይም በልብስ አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማያረጀውን ልብስ ይኸውም በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ጭምትና ገር መንፈስ የተላበሰ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።”—1 ጴጥ. 3:1-4

 ጴጥሮስ፣ አንድ ባል ሚስቱ በምታሳየው መልካም ምግባር ሊማረክ እንደሚችል ጽፏል። ክሪስታ የተባለች እህት በ1972 ከተጠመቀች በኋላ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በአእምሮዋ በመያዝ በመልካም ምግባሯ የባሏን ልብ ለመንካት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ባለቤቷ በአንድ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጥንቶ የነበረ ቢሆንም እውነትን የራሱ አላደረገም። አልፎ አልፎ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን በጉባኤ ውስጥ ካሉ አንዳንድ ወንድሞች ጋር ይቀራረባል። እነሱም በበኩላቸው የመምረጥ ነፃነቱን ያከብሩለታል። ታዲያ ክሪስታ፣ የባለቤቷን ልብ ለመንካት ምን አደረገች?

እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን መንገድ በጥብቅ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ባለቤቴን ‘ያለ ቃል’ ማለትም መልካም ባሕርያት በማሳየት ለመማረክ እጥራለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ እሱ የሚፈልገውን ለመፈጸም የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ከዚህም ሌላ የራሱን ምርጫ የማድረግ መብቱን የማከብርለት ሲሆን ጉዳዩን ለይሖዋ እተወዋለሁ።”

የክሪስታ ተሞክሮ፣ ምክንያታዊ መሆን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል። ክሪስታ አዘውትራ በስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በክርስቲያናዊው አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረግን ጨምሮ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ ጥሩ ልማድ አላት። በሌላ በኩል ደግሞ ለባለቤቷ ፍቅር የማሳየት እንዲሁም ጊዜና ትኩረት የመስጠት ግዴታ እንዳለባት ስለምትገነዘብ ይህን ታደርጋለች። የማያምኑ ዘመዶች ያሉን ሁሉ፣ ምክንያታዊ መሆናችንና ስሜታቸውን ለመረዳት መሞከራችን አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ይላል። ይህ ደግሞ እምነታችንን ከማይጋሩ የቤተሰባችን አባላት በተለይም ከትዳር ጓደኛችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንዳለብን ይጠቁመናል። አብረን ጊዜ ማሳለፋችን ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንድናደርግ አጋጣሚ ይፈጥራል። ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ መኖሩ፣ የማያምነው የትዳር ጓደኛ ብቸኝነት እንዳይሰማውና እንደተተወ እንዳያስብ ወይም ቅናት እንዳያድርበት አስተዋጽኦ ያደርጋል።—መክ. 3:1

ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ

የሆልገር አባት የተጠመቀው ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ወደ እውነት ከመጡ ከ20 ዓመት በኋላ ነው። ሆልገር “የማያምነውን የቤተሰብ አባል እንደምንወደውና ስለ እሱ እንደምንጸልይ ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው” ብሏል። ክሪስታም ‘ባለቤቷ ውሎ አድሮ እውነትን በመቀበል ከይሖዋ ጎን መቆሙ እንደማይቀር ሁልጊዜ ተስፋ እንደምታደርግ’ ተናግራለች። ከማያምኑ ዘመዶቻችን ጋር በተያያዘ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረንና አንድ ቀን እውነትን እንደሚቀበሉ ተስፋ ልናደርግ ይገባል።

ከማያምኑ የቤተሰባችን አባላት ጋር ምንጊዜም ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የማድረግ፣ እውነትን ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ የመፍጠር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልባቸውን እንዲነካው የማድረግ ግብ ሊኖረን ይገባል። ደግሞም ምንም ነገር ስናደርግ ‘የገርነት መንፈስና ጥልቅ አክብሮት’ እናሳይ።—1 ጴጥ. 3:15