“ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”—1 ዮሐ. 3:18

1, 2. (ሀ) ብዙ ቤተሰቦች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይደቀኑባቸዋል? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ? (ለ) ወላጆችም ሆኑ ልጆች የሁኔታዎች መለዋወጥ የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

በአንድ ወቅት ጠንካራና ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ ሰዎች የነበሩት ወላጆቻችን ራሳቸውን መርዳት ሲያቅታቸው ማየት ልብ የሚሰብር ነገር ነው። ምናልባትም ወላጆቻችን፣ በመውደቃቸው ምክንያት እግራቸው ተሰብሮ፣ መርሳትና መንገድ ስተው መጥፋት ጀምረው አሊያም ከባድ የጤና ችግር ገጥሟቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አረጋውያኑ ራሳቸው፣ አካላቸው በመድከሙ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ እንደ ድሯቸው የማንንም እርዳታ ሳይሹ መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን መቀበል ይከብዳቸው ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል? እነሱን መንከባከብ የሚቻለውስ እንዴት ነው?

2 አረጋውያንን ስለ መንከባከብ የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “እርጅናን ተከተለው ስለሚመጡ ችግሮች መወያየቱ ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቤተሰቡ ምን አማራጮች እንዳሉት መነጋገሩና ስለሚወሰደው እርምጃ ስምምነት ላይ መድረሱ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር በተሻለ መንገድ ለመወጣት ያስችለዋል።” ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ማስወገድ እንደማይቻል አምነን መቀበላችን እንዲህ ያለ ውይይት የማድረጉን ጥቅም እንድንገነዘብ ይረዳናል። በመሆኑም አስቀድመን አንዳንድ ዝግጅቶችንና ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን። ቤተሰቦች በፍቅር ተባብረው በመሥራት፣ ተፈታታኝ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመወጣት የሚረዳቸውን እቅድ ማውጣት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

 ‘ለጭንቀት ጊዜ’ እቅድ ማውጣት

3. በዕድሜ የገፉ ወላጆች ተጨማሪ እገዛ ሲያስፈልጋቸው የቤተሰባቸው አባላት ምን ማድረግ ሊኖርባቸው ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

3 በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያለ ማንም እርዳታ ራሳቸውን ችለው መኖር የማይችሉበት ጊዜ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ በዚህ ጊዜ በተወሰነ መጠን የሌሎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (መክብብ 12:1-7ን አንብብ።) በዕድሜ የገፉ ወላጆች ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ሲቸግራቸው፣ ለእነሱ የሚስማማቸውና አቅማቸውን ያገናዘበ እንክብካቤ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ከልጆቻቸው ጋር ተነጋግረው መወሰን ያስፈልጋቸዋል። ቤተሰቡ በዕድሜ የገፉትን ወላጆች በመንከባከብ ረገድ እንዴት መተባበር እንደሚቻልና የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ እንዲሁም መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ለመወሰን አንድ ላይ ተሰባስቦ መወያየቱ ጥሩ ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በተለይ ደግሞ ወላጆች ስሜታቸውን በግልጽ መናገርና እውነታውን ያገናዘቡ መፍትሔዎችን መፈለግ ይኖርባቸዋል። የቤተሰቡ አባላት፣ አረጋውያኑ ወላጆች ተጨማሪ እገዛ እየተደረገላቸው በራሳቸው ቤት መኖር ይችሉ እንደሆነ ሊወያዩ ይችላሉ። * አሊያም ደግሞ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ምን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል መነጋገር ይችሉ ይሆናል። (ምሳሌ 24:6) ለምሳሌ፣ አንዳንዶች አረጋውያን ወላጆቻቸው በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ መስጠት የሚችሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በገንዘብ ረገድ ለመርዳት አቅሙ ይኖራቸው ይሆናል። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የየራሱ ድርሻ እንዳለው መገንዘብ ይኖርበታል፤ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቤተሰቡ አባላት ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ሊለዋወጡ ይችላሉ።

4. የአረጋውያን ቤተሰብ አባላት እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ?

4 ወላጆቻችሁን መንከባከብ ስትጀምሩ ስለ ሁኔታቸው ለማወቅ የተቻላችሁን ያህል ጥረት አድርጉ። በጊዜ ሂደት እየተባባሰ የሚሄድ ሕመም ካለባቸው በሽታው ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማወቅ ሞክሩ። (ምሳሌ 1:5) ለአረጋውያን እርዳታ የሚሰጡ መንግሥታዊ ተቋማትን አነጋግሩ። ወላጆቻችሁን የመንከባከቡን ኃላፊነት ሳትቸገሩ ለመወጣት ብሎም ለእነሱ የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በአካባቢያችሁ ካሉ ይህን ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በቤተሰባችሁ ውስጥ የሚኖረው ለውጥ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል፤ ለምሳሌ ወላጆቻችሁን ልታጧቸው እንደሆነ በማሰብ ታዝኑ፣ ትደናገጡ ወይም ግራ ትጋቡ ይሆናል። ለምታምኑት ወዳጃችሁ ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋ የልባችሁን ንገሩት። እሱም ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል የአእምሮ ሰላም ይሰጣችኋል።—መዝ. 55:22፤ ምሳሌ 24:10፤ ፊልጵ. 4:6, 7

5. አረጋውያን እንክብካቤ ማግኘት ስለሚችሉባቸው የተለያዩ አማራጮች ቀደም ብሎ መረጃ ለመሰብሰብ ጥረት ማድረጉ የጥበብ አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?

5 አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው፣ አረጋውያን እንክብካቤ ማግኘት ስለሚችሉባቸው የተለያዩ አማራጮች ቀደም ብለው መረጃ ለማግኘት ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ ከአንዱ ልጃቸው ጋር ከመኖር ወይም ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚያደርግ ተቋም ውስጥ ከመግባት አሊያም በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች አማራጮችን ከመጠቀም የተሻለው የትኛው እንደሆነ አረጋውያኑ ከልጆቻቸው ጋር ይነጋገራሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች፣ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም የሚችለውን “ድካምና መከራ” አስቀድመው በማሰብ ዝግጅት አድርገዋል። (መዝ. 90:10) አብዛኞቹ ቤተሰቦች ግን አስቀድመው እቅድ ስለማያወጡ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ከባድ ውሳኔዎችን በጥድፊያ ለመወሰን ይገደዳሉ። አንድ ባለሞያ እንደገለጸው ይህ ወቅት “እንዲህ ያለ ውሳኔ ለማድረግ በጣም መጥፎ ጊዜ ነው።” የቤተሰብ አባላት በዚህ ጊዜ በአፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ውጥረት ሊፈጠርና አለመግባባት ሊነሳ ይችላል። በሌላ በኩል ግን አስቀድሞ እቅድ ማውጣት ወደፊት የሚከሰቱ ለውጦችን ማስተናገድ ከባድ እንዳይሆን ያደርጋል።—ምሳሌ 20:18

በዕድሜ ለገፉ ወላጆች ስለሚያስፈልገው እንክብካቤ ቤተሰቡ አንድ ላይ ተሰባስቦ መወያየት ሊያስፈልገው ይችላል (ከአንቀጽ 6-8ን ተመልከት)

6. ወላጆች እንዲኖሩበት ስለታሰበው ቦታ ከልጆቻቸው ጋር አስቀድመው መነጋገራቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ወላጆቻችሁ እንዲኖሩበት ስለታሰበው ቦታ እንዲሁም ሊኖሩ ስለሚችሉት ለውጦች ከእነሱ ጋር መነጋገር ይከብዳችሁ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረጋቸው በኋላ ላይ በጣም እንደጠቀማቸው ብዙዎች ተናግረዋል። እንዴት? መተሳሰብና መግባባት ባለበት ሁኔታ ጥሩ እቅድ ለማውጣት የሚያስችል አጋጣሚ ስለሚፈጥር ነው። ሁሉም ፍቅርና ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሐሳባቸውን አስቀድመው መግለጻቸው በኋላ ላይ ውሳኔ ማድረግ ቀላል እንዲሆን ይረዳል። አረጋውያኑ ሁኔታቸው እስከፈቀደ ድረስ ራሳቸውን ችለው ለመኖርና የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ በሚመርጡበት ጊዜም እንኳ፣ ወደፊት እርዳታ ቢያስፈልጋቸው ምን ዓይነት ዝግጅት ቢደረግላቸው እንደሚመርጡ  ከልጆቻቸው ጋር አስቀድመው መወያየታቸው ጠቃሚ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።

7, 8. ቤተሰቦች ስለ የትኞቹ ጉዳዮች መወያየታቸው ጠቃሚ ነው? ለምንስ?

7 ወላጆች፣ ከቤተሰባችሁ ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት በምታደርጉበት ወቅት ወደፊት ምን እንዲደረግላችሁ እንደምትፈልጉ፣ የገንዘብ አቅማችሁ ምን ያህል እንደሆነ እንዲሁም የትኞቹን አማራጮች እንደምትመርጡ ግለጹ። ይህ ደግሞ እናንተ ውሳኔ ማድረግ የማትችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ልጆቻችሁ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። ቤተሰባችሁ በተቻለ መጠን እናንተ የምትፈልጉትን ነገር ለማድረግና ራሳችሁን ችላችሁ የመኖር መብታችሁን ለማክበር እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 6:2-4) ለምሳሌ፣ አንደኛው ልጃችሁ ቤት ለመኖር ነው የምትፈልጉት ወይስ ሌላ የምትሹት ነገር አለ? በዚህ ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ፤ ሁሉም ሰው እንደ እናንተ ዓይነት አመለካከት ላይኖረው እንደሚችል እንዲሁም እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ በአመለካከታችሁ ላይ ለውጥ ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልጋችሁ አስታውሱ።

8 አስቀድሞ እቅድ ማውጣትና መወያየት ችግሮችን ለማስወገድ ሊረዳ እንደሚችል ሁሉም ሰው መገንዘብ ይኖርበታል። (ምሳሌ 15:22) ይህም ከሕክምና ጋር ስለተያያዙ ነገሮች መወያየትን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት ውይይት ስታደርጉ የይሖዋ ምሥክሮች በሚጠቀሙበት የሕክምና መመሪያ ካርድ ላይ በሰፈሩት ነጥቦች ላይም መነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ሰው ስለሚሰጠው ሕክምና የማወቅ እንዲሁም ሕክምናውን የመቀበል ወይም ያለመቀበል መብት አለው። አንድ ሰው የሕክምና መመሪያ ካርዱን መሙላቱ በዚህ ረገድ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል። አረጋውያኑ የሕክምና ጉዳዮች ወኪል ከመረጡ (እንዲህ ማድረግ በሕግ ተቀባይነት ካለው) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ይህ እምነት የሚጥሉበት ሰው ተገቢውን ውሳኔ ማድረግ ይችላል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ፣ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በሚፈለጉበት ጊዜ ማቅረብ እንዲችሉ ፎቶ ኮፒ አድርገው ሊይዟቸው ይገባል። አንዳንዶች የእነዚህን ሰነዶች ቅጂ፣ ከኑዛዜያቸው እና ከሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች (ለምሳሌ ከኢንሹራንስ፣ ከገንዘብና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር ከተያያዙ ሰነዶች) ጋር አብረው ያስቀምጣሉ።

ከሚመጡት ለውጦች ጋር ራስን ማስማማት

9, 10. ለአረጋውያን በሚደረግላቸው እንክብካቤ ላይ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉት ከአቅማቸው ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩት የትኞቹ ለውጦች ናቸው?

9 አብዛኛውን ጊዜ አረጋውያኑ አቅማቸውና ሁኔታቸው እስከፈቀደ ድረስ ራሳቸውን ችለው መኖር ይፈልጋሉ፤ ቤተሰቦቻቸውም ቢሆን የሚፈልጉት ይህን ሊሆን ይችላል። አረጋውያኑ ምግባቸውን ማብሰል፣ ቤታቸውን ማጽዳት፣ መድኃኒታቸውን በአግባቡ መውሰድ ይችሉ ይሆናል፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር መገናኘት አያስቸግራቸው ይሆናል። በመሆኑም አረጋውያኑ፣ ልጆቻቸው የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን መከታተል እንደማያስፈልጋቸው ይገልጹ ይሆናል። ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ ካስቸገራቸው ለምሳሌ ገበያ መውጣት ከከበዳቸው ወይም የማስታወስ ችሎታቸው በጣም እየደከመ ከመጣ ልጆቻቸው እነዚህን ነገሮች ከግምት በማስገባት አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

10 ከእርጅና ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ችግሮች መካከል ግራ መጋባት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ በተገቢው መንገድ መጸዳዳት አለመቻል እንዲሁም የመስማት፣ የማየትና የማስታወስ ችሎታን ማጣት ይገኙበታል፤ ወላጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት የጤና ችግር ካጋጠማቸው ሁኔታውን በአግባቡ መወጣት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። በዚህ ረገድ ልጆች ቅድሚያውን መውሰድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻቸው በራሳቸው ያደርጓቸው የነበሩ ነገሮችን ልጆቹ ኃላፊነቱን ወስደው ማከናወን መጀመር ይኖርባቸው ይሆናል። ወላጆች  የተሻለ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ ልጆች እነሱን ወክለው አንዳንድ ነገሮችን ማከናወን እንዲሁም ጸሐፊያቸው ወይም ሹፌራቸው መሆን አሊያም እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ሚናዎችን መጫወት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።—ምሳሌ 3:27

11. ለውጥ ማድረግ ሊያስከትል የሚችለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቀነስ ምን ማድረግ ይቻላል?

11 ወላጆቻችሁ ያጋጠሟቸው ችግሮች መስተካከል የማይችሉ ከሆኑ ከሚደረግላቸው እንክብካቤ ወይም ከሚኖሩበት ቦታ ጋር በተያያዘ ለውጥ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። በዚህ ጊዜ የምታደርጉት ለውጥ አነስተኛ ከሆነ ለውጡን መቀበሉ ብዙም ላይከብድ ይችላል። ለምሳሌ የምትኖሩት ወላጆቻችሁ ካሉበት ርቃችሁ ከሆነ በአቅራቢያቸው ያለ አንድ የእምነት ባልንጀራችሁ ወይም ጎረቤታቸው በየጊዜው እየሄደ እንዲያያቸውና ያሉበትን ሁኔታ እንዲነግራችሁ ዝግጅት ማድረጉ በቂ ይሆን? እርዳታ የሚፈልጉት ምግብ ከማብሰል ወይም ከጽዳት ጋር በተያያዘ ብቻ ይሆን? ቤት ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ፣ መታጠቢያ ቤት ሲጠቀሙ ወይም ሌሎች ነገሮችን ሲያከናውኑ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ቤቱ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይቻል ይሆን? ምናልባትም አረጋውያኑ ቤታቸው እየመጣ አንዳንድ ነገሮችን የሚያከናውንላቸው ሰው ካገኙ እንደ ቀድሞው ራሳቸውን ችለው መኖር ይችሉ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ብቻቸውን መኖራቸው አስጊ ከሆነ ከበፊቱ የበለጠ ቋሚ እርዳታ የሚያገኙበት ዝግጅት ማመቻቸት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን በአካባቢያቸው ምን ዓይነት እርዳታ ማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ ጥረት አድርጉ። *ምሳሌ 21:5ን አንብብ።

አንዳንዶች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን የተወጡበት መንገድ

12, 13. አንዳንድ ልጆች የሚኖሩት ከወላጆቻቸው ርቀው ቢሆንም ወላጆቻቸውን እንደሚያከብሩ የሚያሳዩትና የሚንከባከቡት እንዴት ነው?

12 አፍቃሪ የሆኑ ልጆች፣ ወላጆቻቸው ተደስተው እንዲኖሩ ይፈልጋሉ። ወላጆቻቸው ጥሩ እንክብካቤ እያገኙ መሆኑን ማወቃቸው ለልጆቹ የአእምሮ ሰላም ይሰጣቸዋል። ይሁንና ብዙ ልጆች፣ ባሉባቸው ሌሎች ኃላፊነቶች የተነሳ የሚኖሩት ወላጆቻቸው ካሉበት አካባቢ ርቀው ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ልጆች እረፍት ወስደው ወላጆቻቸውን ይጠይቃሉ፤ እንዲሁም ወላጆቻቸው በአሁኑ ወቅት ማከናወን የማይችሏቸውን የቤት ውስጥ ሥራዎች ያከናውኑላቸዋል። ልጆች ለወላጆቻቸው አዘውትረው ከተቻለም በየዕለቱ ስልክ መደወላቸው ወይም ደብዳቤ አሊያም ኢ-ሜይል መጻፋቸው ወላጆች ልጆቻቸው እንደሚወድዷቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል።—ምሳሌ 23:24, 25

13 ወላጆቻችሁን ለመንከባከብ ያደረጋችሁት ዝግጅት ምንም ይሁን ምን ለወላጆቻችሁ በየዕለቱ የሚደረገውን እንክብካቤ በየተወሰነ ጊዜ መለስ ብላችሁ ማጤን ያስፈልጋችኋል። ከወላጆቻችሁ ርቃችሁ የምትኖሩ ከሆነና ወላጆቻችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ የጉባኤያቸው ሽማግሌዎች ሐሳብ እንዲሰጧችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። በተጨማሪም ጉዳዩን በጸሎታችሁ ላይ ማካተታችሁን አትርሱ። (ምሳሌ 11:14ን አንብብ።) ወላጆቻችሁ የይሖዋ ምሥክር ባይሆኑም እንኳ “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለውን መመሪያ መታዘዝ ይኖርባችኋል። (ዘፀ. 20:12፤ ምሳሌ 23:22) እርግጥ ነው፣ ሁሉም ቤተሰብ አንድ ዓይነት ውሳኔ አያደርግም። አንዳንድ ቤተሰቦች አረጋዊ ወላጆቻቸው እነሱ ቤት መጥተው ወይም በአቅራቢያቸው እንዲኖሩ ያደርጋሉ። ይሁንና እንዲህ ማድረግ የሚቻለው ሁልጊዜ አይደለም። አንዳንድ ወላጆች ራሳቸውን መቻል ስለሚፈልጉና ለልጆቻቸው ሸክም መሆን ስለማይሹ ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መኖርን አይመርጡም። ሌሎች ወላጆች ደግሞ በቂ ገንዘብ ስላላቸው የሚንከባከባቸው ሰው ቀጥረው በራሳቸው ቤት መኖርን ይመርጣሉ።—መክ. 7:12

14. አረጋዊ ወላጆችን በዋነኝነት የሚንከባከቡ ሰዎች ምን ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

14 በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ አረጋዊ ወላጆችን የመንከባከቡ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው በወላጆቹ አቅራቢያ በሚኖረው ልጅ ላይ ነው። ይሁንና ወላጆቹን በዋነኝነት የሚንከባከበው ሰው፣ ይህን ኃላፊነቱን በመወጣትና የራሱን ቤተሰብ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ሚዛኑን መጠበቅ አለበት። እያንዳንዱ ሰው ያለው ጊዜና ጉልበት ውስን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆቹን የሚንከባከበው ሰው ያለበት ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ወላጆችን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ዝግጅት እንደገና መለስ ብሎ መገምገም ያስፈልጋል። አብዛኛው ኃላፊነት የወደቀው በአንደኛው የቤተሰብ አባል ላይ ይሆን? ሌሎቹ ልጆች ተራ ገብተው ወላጆቻቸውን በመንከባከብ ኃላፊነቱን መጋራት ይችሉ ይሆን?

15. ለአረጋውያን በዋነኝነት እንክብካቤ የሚያደርገው ሰው እንዳይዝል ምን ማድረግ ይቻላል?

 15 አረጋዊው ወላጅ ያልተቋረጠ እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነ የሚንከባከበው ሰው ሊዝል ይችላል። (መክ. 4:6) አፍቃሪ የሆኑ ልጆች፣ ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ቢሆኑም የማያቋርጥ እርዳታ መስጠት በጣም ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሰዎች፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማቸው ምክንያታዊ መሆንና የሌሎችን እገዛ መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚያግዛቸው ሰው ቢያገኙ ይጠቀማሉ፤ አለዚያ ግን ወላጆቻቸውን የመንከባከቡ ኃላፊነት ሊከብዳቸውና ወላጆቹ፣ ቤት ሆነው እንክብካቤ ማግኘት የሚችሉ ቢሆንም ወደ አረጋውያን መጦሪያ ተቋም እንዲገቡ ለማድረግ ሊገደዱ ይችላሉ።

16, 17. በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የሚንከባከቡ ልጆች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ? ይህንንስ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? (“በአመስጋኝነት ተነሳስቶ መንከባከብ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

16 የምንወዳቸው ወላጆቻችን በእርጅና ምክንያት በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ሲሠቃዩ መመልከት ሊረብሸን ይችላል። ሌሎችን የሚንከባከቡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሐዘን፣ የጭንቀት፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የብስጭትና የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው አልፎ ተርፎም ሊማረሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ በዕድሜ የገፋው ወላጅ ደግነት የጎደለው ነገር ይናገር ወይም የሚደረግለትን ነገር አያደንቅ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠማችሁ ቶሎ ቅር አትሰኙ። አንድ የአእምሮ ጤና ባለሙያ እንዲህ ብሏል፦ “ማንኛውም ዓይነት ስሜት በተለይም የማትፈልጉት ዓይነት ስሜት ሲመጣባችሁ የተሻለው ነገር እንዲህ ዓይነቱ ስሜት መፈጠሩ የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ አምኖ መቀበል ነው፤ ያደረባችሁን ስሜት ላለመቀበል መታገል ወይም እንዲህ ስለተሰማችሁ ራሳችሁን መኮነን የለባችሁም።” በዚህ ጊዜ ለትዳር ጓደኛችሁ፣ ለሌላ የቤተሰባችሁ አባል ወይም ለምታምኑት ወዳጃችሁ ስሜታችሁን አውጥታችሁ ንገሩ። እንዲህ ማድረጋችሁ፣ ስላደረባችሁ ስሜት ተገቢ አመለካከት እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል።

17 አንዳንድ ጊዜ የአረጋውያኑ ቤተሰብ፣ አረጋውያኑን በቤት ውስጥ መንከባከባቸውን ለመቀጠል የሚያስችል የገንዘብ አቅም ወይም አስፈላጊው ችሎታ አይኖራቸው ይሆናል። በመሆኑም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸው ወደ አረጋውያን መጦሪያ ተቋም እንዲገቡ ለማድረግ ይገደዳሉ። አንዲት እህት በአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ያሉ እናቷን እየሄደች የምትጠይቃቸው በየቀኑ ነው ማለት ይቻላል። ቤተሰቧን ወክላ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ የ24 ሰዓት ክትትል ያስፈልጋታል፤ እኛ ደግሞ ይህንን ማድረግ አልቻልንም። ወደ አረጋውያን መጦሪያ ተቋም እንድትገባ መወሰኑ ቀላል አልነበረም። ነገሩን መቀበል እጅግ በጣም ከብዶን ነበር። ይሁን እንጂ ከመሞቷ በፊት በነበሩት የመጨረሻ ወራት የተሻለው ነገር በዚያ መኖሯ ነበር፤ እሷም በዚህ ተስማምታለች።”

18. አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሰዎች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

18 ወላጆቻችሁ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ እነሱን መንከባከቡ ከባድና በስሜት ላይ ጫና የሚፈጥር ኃላፊነት ሊሆን ይችላል። አረጋውያንን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ የተሻለው አካሄድ የትኛው እንደሆነ ወጥ የሆነ መመሪያ መስጠት አይቻልም። ያም ቢሆን ጥበብ የታከለበት እቅድ ማውጣታችሁ፣ ተሳስባችሁና ተባብራችሁ መሥራታችሁ፣ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችሁ ከሁሉ በላይ ደግሞ ልባዊ ጸሎት ማቅረባችሁ የምትወዷቸውን ወላጆቻችሁን የመንከባከብ ኃላፊነታችሁን ለመወጣት ያስችላችኋል፤ በዚህ መንገድ እንደምታከብሯቸው ማሳየት ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ወላጆቻችሁ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤና ትኩረት እንዳገኙ ስለምታውቁ እርካታ ታገኛላችሁ። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8ን አንብብ።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ወላጆቻቸውን ለሚያከብሩ ሰዎች የሚሰጠውን የአእምሮ ሰላም እንደምታገኙ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—ፊልጵ. 4:7

^ አን.3 ወላጆችም ሆኑ ልጆች በዚህ ረገድ የሚያደርጉት ምርጫ በአካባቢው ሁኔታ ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች አያቶች፣ ወላጆችና ልጆች አንድ ላይ መኖራቸው ወይም በየጊዜው መገናኘታቸው የተለመደ አሊያም የሚፈለግ ነገር ነው።

^ አን.11 ወላጆቻችሁ በራሳቸው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ፣ ድንገተኛ ሁኔታ ቢከሰት አስፈላጊውን እርዳታ መስጠት እንዲቻል እንክብካቤ የሚያደርግላቸው ታማኝ ሰው የቤቱ ቁልፍ እንዲኖረው ማድረጉ ተገቢ ነው።