በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2014

የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ

የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ

“[አብርሃም] ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ለመባል በቃ።”ያዕ. 2:23

1. በአምላክ አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን ምን ችሎታዎች አሉን?

ብዙ ጊዜ ሰዎች “ቁርጥ አባቱን ይመስላል” ሲሉ እንሰማለን። በእርግጥም ብዙ ልጆች ወላጆቻቸውን ይመስላሉ። ደግሞም አንድ ልጅ ከአባቱም ሆነ ከእናቱ በዘር የሚወርሰው ነገር ይኖራል። በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ የሕይወት ምንጭ ነው። (መዝ. 36:9) ሰብዓዊ ልጆቹ የሆንነው እኛ ደግሞ በተወሰነ መጠን ከእሱ ጋር እንመሳሰላለን። በእሱ አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን የማመዛዘንና ውሳኔ የማድረግ እንዲሁም ወዳጅነት የመመሥረት ችሎታ አለን።—ዘፍ. 1:26

2. ይሖዋ ወዳጃችን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

2 ይሖዋ የቅርብ ወዳጃችን ሊሆን ይችላል። አምላክ ለእኛ ያለው ፍቅር እንዲሁም እኛ በእሱና በልጁ ላይ ያለን እምነት እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የነበራቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።

‘ወዳጄ አብርሃም’

3, 4. ከይሖዋ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት በተመለከተ በአብርሃምና በዘሮቹ መካከል ምን ልዩነት ነበር?

3 ይሖዋ የእስራኤላውያን አባት የነበረውን ሰው ‘ወዳጄ አብርሃም’ ብሎ ጠርቶታል። (ኢሳ. 41:8) በተጨማሪም 2 ዜና መዋዕል 20:7 ላይ አብርሃም የአምላክ ወዳጅ እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ታማኝ ሰው ከፈጣሪው ጋር ዘላቂ ወዳጅነት እንዲመሠርት ያስቻለው ምን ነበር? አብርሃም የነበረው እምነት እንዲህ  ዓይነት ወዳጅነት እንዲመሠርት አስችሎታል።—ዘፍ. 15:6፤ ያዕቆብ 2:21-23ን አንብብ።

4 የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ያስገኙት የአብርሃም ዘሮች መጀመሪያ ላይ ይሖዋ አባታቸውና ወዳጃቸው ሆኖ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ከአምላክ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት ተቋረጠ። ለምን? ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ የነበራቸው እምነት ስለተዳከመ ነው።

5, 6. (ሀ) ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት የመሠረትከው እንዴት ነው? (ለ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች ትኩረት መስጠት ይኖርብናል?

5 ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቃችሁ መጠን በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል እንዲሁም ለእሱ ያላችሁ ፍቅር ሥር እየሰደደ ይሄዳል። አምላክ በእውን ያለ አካል መሆኑንና ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንደምትችሉ የተረዳችሁበትን ጊዜ መለስ ብላችሁ አስቡ። በተጨማሪም በአዳም አለመታዘዝ የተነሳ ሁላችንም ኃጢአትን እንደወረስን ተገነዘባችሁ። ደግሞም መላው የሰው ዘር ከአምላክ የራቀ መሆኑን ተረዳችሁ። (ቆላ. 1:21) ከዚያም በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ለእኛ ግድ የማይሰጠው፣ የማይቀረብ አካል አለመሆኑን ተገነዘባችሁ። ኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንደሰጠን ባወቅንና በዚህ ዝግጅት ላይ እምነት ባሳደርን ጊዜ ከአምላክ ጋር መወዳጀት ጀመርን።

6 ይሖዋን ስላወቅንበት መንገድ መለስ ብለን ስናስብ ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ከአምላክ ጋር የመሠረትኩት ወዳጅነት እየጎለበተ ነው? በእሱ ላይ ያለኝ እምነት ጠንካራ ነው? ለምወደው ወዳጄ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር በየቀኑ እያደገ ነው?’ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የነበረው በጥንት ዘመን የኖረው ሌላው ሰው ደግሞ ጌዴዎን ነው። ቀጥሎ እሱ የተወውን ግሩም ምሳሌ እንመረምራለን፤ ይህም አርዓያውን እንድንከተል ያስችለናል።

‘ይሖዋ ሰላም ነው’

7-9. (ሀ) ጌዴዎን ምን አስደናቂ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? ምን ስሜትስ አሳደረበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው?

7 መስፍኑ ጌዴዎን ይሖዋን ያገለገለው የእስራኤል ብሔር ተስፋይቱ ምድር ከገባ በኋላ በብሔሩ ታሪክ ከፍተኛ አለመረጋጋት በታየበት ወቅት ነበር። መሳፍንት ምዕራፍ 6 የይሖዋ መልአክ በዖፍራ ጌዴዎንን እንዳነጋገረው ይገልጻል። በዚያን ወቅት ጎረቤቶቻቸው የነበሩት ምድያማውያን በእስራኤላውያን ላይ ከባድ ስጋት ፈጥረው ነበር። ከዚህ የተነሳ ጌዴዎን ስንዴ እየወቃ የነበረው ሜዳ ላይ ሳይሆን እህሉን በቶሎ መደበቅ በሚችልበት በወይን መጭመቂያ ውስጥ ነበር። ጌዴዎን መልአኩ ሲገለጥለትና “ኀያል ጦረኛ” ብሎ ሲጠራው በጣም በመገረም እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣው ይሖዋ በዚህ ጊዜም በእርግጥ ይረዳቸው እንደሆነ ጠየቀ። ፈጣሪን ወክሎ ያናገረው መልአክ ይሖዋ በእርግጥ ድጋፍ እየሰጠው እንደሆነ በመግለጽ ጌዴዎንን አበረታታው።

8 ጌዴዎን ‘እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ ማውጣት’ የምችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበር። ይሖዋ እንዲህ የሚል ቀጥተኛ መልስ ሰጠው፦ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ።” (መሳ. 6:11-16) ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ስለተፈጠረበት ሳይሆን አይቀርም፣ ጌዴዎን ምልክት እንዲሰጠው ጠየቀ። በዚህ ውይይት ላይ ጌዴዎን ይሖዋን እንደ እውን አካል አድርጎ እንደተመለከተው ምንም ጥያቄ የለውም።

9 ከዚያ በመቀጠል የተከሰተው ነገር የጌዴዎንን እምነት ያጠናከረለት ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲቀርብ አስችሎታል። ጌዴዎን ምግብ አዘጋጅቶ ለመልአኩ አቀረበለት። መልአኩ በያዘው በትር ምግቡን ሲነካው በተአምራዊ ሁኔታ እሳት በላው፤ ጌዴዎን ይህን ሲያይ መልአኩ በእርግጥ ይሖዋን ወክሎ እንደመጣ ተገነዘበ። ጌዴዎን በሁኔታው ተደናግጦ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” ብሎ ጮኸ። (መሳ. 6:17-22) ሆኖም ይህ ሁኔታ ጌዴዎን ከአምላክ ጋር በነበረው ወዳጅነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ ጌዴዎን ስለ ይሖዋ የነበረው ግንዛቤ ማደጉ ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዳለው ሆኖ እንዲሰማው አድርጎታል። ጌዴዎን በዚያ ስፍራ ላቆመው መሠዊያ “ይሖዋ ሻሎም” የሚል ስያሜ መስጠቱ ይህን እንድንገነዘብ ያስችለናል። ይህ ስም ‘ይሖዋ ሰላም ነው’ የሚል ትርጉም አለው። (መሳፍንት 6:23, 24ን አንብብ።) ይሖዋ በየዕለቱ በሚያደርግልን ነገር ላይ ስናሰላስል እሱ  እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን እንገነዘባለን። አዘውትረን ወደ አምላክ መጸለያችን ከበፊቱ ይበልጥ ውስጣዊ ሰላም እንዲሰማን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያጠናክረዋል።

በይሖዋ ‘ድንኳን ውስጥ የሚያድረው’ ማን ነው?

10. የይሖዋ ወዳጆች መሆን ከፈለግን በመዝሙር 15:3, 5 መሠረት ከእኛ ምን ይጠበቃል?

10 ይሖዋ የእኛ ወዳጅ እንዲሆን ልናሟላቸው የሚገቡ አንዳንድ መሥፈርቶች አሉ። በመዝሙር 15 ላይ እንደሰፈረው ዳዊት በይሖዋ ‘ድንኳን ውስጥ ለማደር’ በሌላ አባባል የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን ስለሚያስፈልጉት ብቃቶች በመዝሙሩ ላይ ጠቅሷል። (መዝ. 15:1) ከእነዚህ ብቃቶች መካከል ሁለቱ ስም ከማጥፋት መቆጠብና በምናደርገው ነገር ሁሉ ሐቀኛ መሆን ናቸው፤ እስቲ በእነዚህ ብቃቶች ላይ ትኩረት እናድርግ። ዳዊት እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ሲናገር “በምላሱ የማይሸነግል [‘ስም የማያጠፋ፣’ NW] . . . በንጹሐን ላይ ጕቦ የማይቀበል” ሰው በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንደሚያድር ገልጿል።—መዝ. 15:3, 5

11. የሰውን ስም ከማጥፋት መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?

11 ዳዊት በሌላ መዝሙር ላይ “አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (መዝ. 34:13) በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ይህን ምክር አለመከተል በእኛና በሰማይ በሚኖረው ጻድቅ አባታችን መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ያደርጋል። እንዲያውም ስም ማጥፋት የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የሰይጣን መለያ ባሕርይ ነው። “ዲያብሎስ” የሚለው ስም ከግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው። ስለ ሌሎች በምናወራው ነገር ረገድ ጠንቃቆች መሆናችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ቅርርብ ጠብቀን እንድንኖር ያስችለናል። በተለይ በጉባኤ ውስጥ ላሉ የተሾሙ ወንዶች ባለን አመለካከት ረገድ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል።ዕብራውያን 13:17ን እና ይሁዳ 8ን አንብብ።

12, 13. (ሀ) በሁሉም ነገር ሐቀኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ሐቀኛ መሆናችን ምን ውጤት ያመጣል?

12 ሐቀኝነት የይሖዋ አገልጋዮች የሚታወቁበት ሌላው ባሕርይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእኛ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር ስለምንመኝ ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 13:18) “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ቁርጥ ውሳኔ ስላደረግን ክርስቲያን ወንድሞቻችንን መጠቀሚያ አናደርግም። ለምሳሌ፣ ቀጥረን የምናሠራቸው ከሆነ በተገቢው መንገድ እንዲያዙና በተዋዋልነው ውል ላይ የሰፈረውን ክፍያ እንዲያገኙ እናደርጋለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ቀጥረን ከምናሠራቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት በሐቀኝነት እንመላለሳለን። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ጋር ተቀጥረን የምንሠራ ከሆነ ልዩ አስተያየት እንዲያደርግልን በመጠበቅ መጠቀሚያ ልናደርገው አይገባም።

13 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በሥራ ጉዳይ የሚገናኙ በዓለም ያሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ አድናቆታቸውን ሲገልጹ እንሰማለን። ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ትልቅ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች ቃላቸውን የሚጠብቁ ሰዎች መሆናቸውን አስተውለዋል። ዳይሬክተሩ “ምንጊዜም ቢሆን የገባችሁትን ቃል ታከብራላችሁ” ሲሉ ተናግረዋል። (መዝ. 15:4) እንዲህ ዓይነቱ ምግባር ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። ከዚህ በተጨማሪ በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ውዳሴ ያመጣል።

ሌሎች ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች እንዲሆኑ እርዷቸው

ሌሎች ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች እንዲሆኑ እንረዳለን (አንቀጽ 14, 15ን ተመልከት)

14, 15. በአገልግሎት የምናገኛቸውን ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

14 በአገልግሎት የምናገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች በአምላክ መኖር የሚያምኑ ቢሆኑም እንኳ አምላክን የቅርብ ወዳጃቸው አድርገው አይመለከቱትም። ታዲያ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ ለስብከት በላካቸው ጊዜ የሰጣቸውን መመሪያ እንመልከት፦ “ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ በቅድሚያ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ። በዚያም ሰላም ወዳድ ሰው ከሌለ ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። ሰላም ወዳድ ሰው ካለ ግን ሰላማችሁ ያርፍበታል።” (ሉቃስ 10:5, 6) ሰዎችን ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ የምናነጋግራቸው ከሆነ እውነትን ለመማር ሊነሳሱ ይችላሉ።  እንዲህ ማድረጋችን ተቃዋሚዎች ያደረባቸውን የጥላቻ ስሜት እንዲያስወግዱ ሊረዳ የሚችል ከመሆኑም በተጨማሪ በሌላ አጋጣሚ የተሻለ ምላሽ እንዲሰጡ መንገዱን ሊያመቻች ይችላል።

15 በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ የተዘፈቁ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችን የሚከተሉ ሰዎች ሲያጋጥሙን ወዳጃዊ በሆነ መንፈስና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እናነጋግራቸዋለን። በተለይ በዚህ ዓለም ተስፋ የቆረጡና እኛ ስለምናመልከው አምላክ ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡ ሞቅ ያለ አቀባበል እናደርግላቸዋለን። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ርዕሶች ብዙ ግሩም ምሳሌዎች ይዘዋል።

ከቅርብ ወዳጃችን ጋር አብሮ መሥራት

16. የይሖዋ ወዳጆች ብቻ ሳንሆን ‘ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

16 አብረው የሚሠሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠርታሉ። ሕይወታቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ሁሉ የእሱ ወዳጆች ከመሆናቸውም ሌላ ‘ከእሱ ጋር አብረው ይሠራሉ።’ (1 ቆሮንቶስ 3:9ን አንብብ።) በእርግጥም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል በሰማይ የሚኖረው አባታችን ያሉትን ድንቅ ባሕርያት ይበልጥ እንገነዘባለን። በተጨማሪም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምሥራቹን እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ እንድንፈጽም እንዴት እንደሚረዳን እናስተውላለን።

17. በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋ ወዳጃችን እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

17 ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ እየጨመረ ሲሄድ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ይሰማናል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የተቃዋሚዎችን ዕቅድ እንዴት እንደሚያከሽፍ እንመለከታለን። እስቲ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት መለስ ብለን እንመልከት። በእነዚህ ጊዜያት አምላክ እንዴት እየመራን እንዳለ በግልጽ አልተመለከትንም? የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ የሚቀርብልን መሆኑ በአድናቆት ስሜት እንድንሞላ ያደርገናል። በየዓመቱ በምናደርጋቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡት ትምህርቶች አፍቃሪው አባታችን ችግሮቻችንንና የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚረዳ ያሳያሉ። የአንድ ቤተሰብ አባላት በአንድ አውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ የተሰማቸውን አድናቆት ለመግለጽ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ትምህርቱ ልባችንን ነክቶታል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳችንን በጣም እንደሚወደንና ስኬታማ እንድንሆን እንደሚፈልግ ተሰምቶናል።” በጀርመን የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ደግሞ በአየርላንድ በተደረገ ልዩ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ለተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልና መስተንግዶ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፤ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይሁንና ከሁሉ በላይ የምናመሰግነው ይሖዋንና እሱ የሾመውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። እውነተኛ አንድነት ያለው የዚህ ሕዝብ አባል እንድንሆን ጋብዘውናል። ይህን እውነታ በአንደበት ከመናገር ባለፈ በራሳችን ሕይወት ማየት ችለናል። በደብሊን በተካሄደው ልዩ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በመገኘት ያሳለፍነው ጊዜ፣ ታላቁን አምላካችንን ከእናንተ ጋር በአንድነት የማገልገል ውድ መብታችንን ምንጊዜም እንድናስታውስ ያደርገናል።”

 ጓደኛሞች የሐሳብ ልውውጥ ያደርጋሉ

18. ከይሖዋ ጋር የምናደርገውን የሐሳብ ልውውጥ በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን?

18 ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ በሚኖርበት ጊዜ ወዳጅነት እየተጠናከረ ይሄዳል። የኢንተርኔትና የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በጣም በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀምና በሞባይል ስልኮች የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ የተለመደ ነገር ሆኗል። ይሁንና ከዚህ አንጻር ሲታይ የቅርብ ወዳጃችን ከሆነው ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ ስለምናደርገው የሐሳብ ልውውጥ ምን ማለት እንችላለን? እርግጥ እሱ ‘ጸሎት ሰሚ’ አምላክ ነው። (መዝ. 65:2) ሆኖም እኛ ቅድሚያውን ወስደን እሱን ምን ያህል እናነጋግረዋለን?

19. በሰማይ ለሚኖረው አባታችን የልባችንን አውጥተን መናገር በሚከብደን ጊዜ በየትኛው ዝግጅት መጠቀም እንችላለን?

19 አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ልባቸውን ከፍተው በጥልቅ የሚያሳስቧቸውን ነገሮች መናገር ይከብዳቸዋል። ይሁንና ይሖዋ ወደ እሱ ስንጸልይ እንዲህ እንድናደርግ ይፈልጋል። (መዝ. 119:145፤ ሰቆ. 3:41) የልባችንን አውጥተን መናገር በሚከብደን ጊዜ እንኳ እርዳታ የምናገኝበት ዝግጅት አለ። ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ችግሩ መጸለይ በሚያስፈልገን ጊዜ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤ ሆኖም በቃላት መግለጽ ተስኖን በምንቃትትበት ጊዜ መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። ይሁንና ልብን የሚመረምረው አምላክ የመንፈስን ትርጉም ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ ለቅዱሳን የሚማልደው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።” (ሮም 8:26, 27) እንደ ኢዮብ፣ መዝሙርና ምሳሌ የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በያዟቸው ሐሳቦች ላይ ማሰላሰላችን የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ እንድንናገር ይረዳናል።

20, 21. በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ሊያጽናኑን የሚችሉት እንዴት ነው?

20 አስጨናቂ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የሚከተለውን ምክር እንከተል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” የቅርብ ወዳጃችን ለሆነው አምላክ ሐሳባችንን በግልጽ መናገራችን ማጽናኛና ማበረታቻ እንደሚያስገኝልን የተረጋገጠ ነው፤ ጳውሎስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) ልባችንንና አእምሯችንን ለሚጠብቀው አቻ የማይገኝለት “የአምላክ ሰላም” ምንጊዜም አመስጋኞች መሆን አለብን።

ጸሎት ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ሊያጠናክርልን የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 21ን ተመልከት)

21 ጸሎት ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት እየጎለበተ እንዲሄድ ይረዳናል። እንግዲያው ‘ያለማቋረጥ እንጸልይ።’ (1 ተሰ. 5:17) ይህ የጥናት ርዕስ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድናና ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምተን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንዲያጠናክርልን ምኞታችን ነው። በእርግጥም ይሖዋ አባታችን፣ አምላካችንና ወዳጃችን ስለሆነ ጊዜ ወስደን ባገኘናቸው በረከቶች ላይ እናሰላስል።