አንዲት ድሃ መበለት አንድያ ልጇን እቅፍ አድርጋ ይዛዋለች። ዓይኗን ማመን አቅቷታል። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የልጇን በድን አካል አቅፋ በሰቀቀን ስትመለከተው ነበር። አሁን ግን ከሞት የተነሳውንና ፊቱ በፈገግታ የፈካውን ልጇን ዓይን ዓይኑን እያየችው ነው። በቤቷ የነበረው እንግዳ “ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!” አላት።

ይህ አስደናቂ ትንሣኤ የተከናወነው ከዛሬ 3,000 ዓመት ገደማ በፊት ነው። ይህን ታሪክ 1 ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ ማንበብ ትችላለህ። ቤቷ ውስጥ በእንግድነት ተቀምጦ የነበረው ግለሰብ የአምላክ ነቢይ የሆነው ኤልያስ ነው። የልጁስ እናት ማን ነች? በሰራፕታ ከተማ የምትኖር በስም ያልተጠቀሰች አንዲት መበለት ነች። ልጇ ከሞት መነሳቱ በሕይወቷ ውስጥ ከተፈጸሙ እምነቷን ካጠናከሩላት ነገሮች መካከል ዋነኛው ነው። ይህች መበለት ያጋጠማትን ሁኔታ በትኩረት መመርመራችን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል።

ኤልያስ እምነት ያላት አንዲት መበለት አገኘ

ይሖዋ ክፉ በነበረው በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ግዛት ረጅም ጊዜ የዘለቀ ድርቅ እንዲከሰት አድርጎ ነበር። ኤልያስ ድርቁ እንደሚከሰት ካወጀ በኋላ አምላክ፣ ኤልያስን ከአክዓብ የሸሸገው ሲሆን ቁራዎች እንጀራና ሥጋ እያመጡ በተአምር እንዲመግቡት አድርጎ ነበር። ከዚያም ይሖዋ ኤልያስን እንዲህ አለው፦ “ተነሥና ሲዶና ውስጥ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሄደህ ተቀመጥ፤ በዚያም አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ።”—1 ነገ. 17:1-9

ኤልያስ ሰራፕታ ሲደርስ አንዲት ድሃ መበለት ጭራሮ ስትለቃቅም አየ። ታዲያ ነቢዩን የምትመግበው ይህች ሴት ትሆን? እሷ ራሷ ድሃ ሆና ሳለ እሱን ልትመግብ የምትችለው እንዴት ነው? ኤልያስ ጥርጣሬ አድሮበት ሊሆን ቢችልም ሴትየዋን ቀርቦ አነጋገራት። ከዚያም “የምጠጣው ውሃ በዕቃ ታመጪልኛለሽን?” ሲል ለመናት። ውኃ ልታመጣለት ስትሄድም “እባክሽን፣ ቍራሽ እንጀራም ይዘሽልኝ ነይ” አላት። (1 ነገ. 17:10, 11) ይህች መበለት ለሰውየው የሚጠጣ ነገር መስጠት አያቅታትም፤ ምግብ ማቅረብ ግን የማይታሰብ ነገር ነው።

 “አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! [“ይሖዋን፣” NW] በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር ምንም የለኝም። እነሆ፤ ለራሴና ለልጄ ምግብ አዘጋጅቼ በልተን እንድንሞት ጭራሮ ለቃቅሜ ወደ ቤት ልወስድ ነው” አለችው። (1 ነገ. 17:12) እስቲ የተነጋገሩት ነገር ምን ትርጉም እንዳለው እንመልከት።

ይህች መበለት ኤልያስ አምላክን የሚፈራ እስራኤላዊ መሆኑን ተገንዝባለች። “አምላክህን ሕያው ይሖዋን” ብላ መናገሯ ይህን ይጠቁማል። የእስራኤል አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ የተወሰነ እውቀት ያላት ቢመስልም ይሖዋን “አምላኬ” ብላ ለመጥራት የሚያስችላት እውቀት ግን አልነበራትም። ይህች ሴት ትኖር የነበረው በሰራፕታ ሲሆን ከተማዋ ደግሞ የፊንቄያውያን ከተማ የሆነችው የሲዶና ክፍል ወይም በሥሯ የምትተዳደር ከተማ የነበረች ይመስላል። ሰራፕታ የበአል አምላኪዎች የሚኖሩባት ከተማ ሳትሆን አትቀርም። ያም ሆኖ ይሖዋ በዚህች መበለት ውስጥ ያየው አንድ ልዩ ነገር አለ።

በሰራፕታ የምትኖረው ይህች ድሃ መበለት በጣዖት አምላኪዎች የተከበበች ብትሆንም በይሖዋ ላይ እምነት ነበራት። ይሖዋ ኤልያስን ወደ እሷ የላከው ለሴትየዋም ሆነ ለነቢዩ ጥቅም ብሎ ነው። ከዚህ ታሪክ አንድ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን።

በሰራፕታ የሚኖሩት የበአል አምላኪዎች በሙሉ ምግባረ ብልሹዎች አልነበሩም። ይሖዋ ኤልያስን ወደዚህች መበለት መላኩ እሱን የማያገለግሉትን ሆኖም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንደሚመለከት ያስገነዝበናል። በእርግጥም “ከየትኛውም ብሔር ቢሆን [አምላክን] የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—ሥራ 10:35

አንተ በምታገለግልበት ክልል ውስጥ ከሰራፕታዋ መበለት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ምን ያህል ሰዎች ያሉ ይመስልሃል? እነዚህ ሰዎች በሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የተከበቡ ቢሆኑም የተሻለ ነገር ለማግኘት ይናፍቁ ይሆናል። ስለ ይሖዋ ያላቸው እውቀት ውስን ስለሚሆን ወይም ምንም ነገር ሰምተው ስለማያውቁ እውነተኛውን አምልኮ እንዲያውቁ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን ለማግኘት ጥረት እያደረግህና እየረዳሃቸው ነው?

‘በመጀመሪያ ትንሽ እንጎቻ ጋግረሽ አምጪልኝ’

ኤልያስ መበለቲቷን ምን እንድታደርግ እንደጠየቃት እስቲ ልብ በል። የቀራትን አሟጥጣ በማዘጋጀት እሷና ልጇ ከበሉ በኋላ ሌላ የሚላስ የሚቀመስ ነገር ስለሌላቸው ሞታቸውን ከመጠበቅ ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ነግራዋለች። ሆኖም ኤልያስ ምን አላት? “አይዞሽ አትፍሪ፤ ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ፤ በመጀመሪያ ግን ከዚያችው ካለችሽ ትንሽ እንጎቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ ከዚያም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’”—1 ነገ. 17:11-14

አንዳንድ ሰዎች እንዲያ ዓይነት ጥያቄ ቢቀርብላቸው ‘ያለህን ምግብ አምጣ? ትቀልዳለህ!’ ሊሉ ይችላሉ። ይሁንና ይህች መበለት እንዲህ ያለ ምላሽ አልሰጠችም። ስለ ይሖዋ ያላት እውቀት ውስን ቢሆንም ኤልያስን በማመን የጠየቀውን ነገር አደረገችለት። ይህ እንዴት እምነት የሚፈትን ነገር ነው? ያም ሆኖ ይህች መበለት ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ አድርጋለች!

የሰራፕታዋ መበለት በኤልያስ አምላክ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላት በማሳየት የራሷንም ሆነ የልጇን ሕይወት መታደግ ችላለች

አምላክ ይህችን ድሃ መበለት አልተዋትም። ኤልያስ ቃል እንደገባላት ሁሉ ይሖዋ ሊያልቅ የተቃረበውን ዱቄትና ዘይት በመባረክ የረሃቡ ዘመን እስኪያበቃ ድረስ ኤልያስን፣ መበለቲቷንና ልጇን መግቧቸዋል። በእርግጥም “በኤልያስ በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም ነበር።” (1 ነገ. 17:16፤ 18:1) ይህች ሴት ከዚህ ተቃራኒ የሆነ እርምጃ ወስዳ ቢሆን ኖሮ የቀራትን ጥቂት ዱቄትና ዘይት ተጠቅማ የምታዘጋጀው ምግብ የመጨረሻዋ  ይሆን ነበር። እሷ ግን በይሖዋ ታምና መጀመሪያ ኤልያስን በመመገብ እምነቷን በተግባር አሳይታለች።

ይህ ታሪክ አምላክ እምነት ያላቸውን ሰዎች እንደሚባርክ ያስተምረናል። ንጹሕ አቋምህን የሚፈትን ነገር ሲያጋጥምህ እምነት እንዳለህ የምታሳይ ከሆነ ይሖዋ ይረዳሃል። ያጋጠመህንም ፈተና መወጣት እንድትችል አስፈላጊውን ነገር በመስጠት የሚንከባከብህና የሚጠብቅህ ወዳጅህ ይሆናል።—ዘፀ. 3:13-15

የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በ1898 እትሙ ላይ የመበለቲቷ ታሪክ የያዘውን ትምህርት አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይህች ሴት ለመታዘዝ የሚያበቃ እምነት ካላት ጌታ በነቢዩ አማካኝነት እሷን በመርዳት ያከብራታል፤ ይህች ሴት እምነት ባታሳይ ኖሮ ግን ይህን የምታደርግ ሌላ መበለት መገኘቷ አይቀርም ነበር። እኛም በሕይወት መንገድ ስንጓዝ ጌታ እምነታችንን የሚፈትኑ ነገሮች እንዲያጋጥሙን ይፈቅዳል፤ ሆኖም ውጤቱ የተመካው በእኛ ላይ ነው። እምነት ካሳየን በረከቱን እናገኛለን፤ እምነት ካላሳየን ግን በረከቱ ይቀርብናል።”

የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ከቅዱሳን መጻሕፍትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ከዚያም የይሖዋን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የቱንም ያህል ከባድ መስሎ ቢታየንም ከመመሪያው ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ እንባረካለን፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

‘እዚህ የመጣኸው ልጄን ለመግደል ነው?’

ይህች መበለት እምነቷን የሚፈትን ሌላ መከራ አጋጠማት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከጥቂት ጊዜ በኋላም የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ሕመሙ እየጠናበት ሄደ፣ በመጨረሻም ትንፋሹ ቀጥ አለ።” ይህ አሳዛኝ ክስተት የደረሰባት ለምን እንደሆነ ለማወቅ የፈለገችው ይህች እናት ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ እኔ ምን አደረግሁህ? እዚህ የመጣኸው ኀጢአቴን አስታውሰህ ልጄን ለመግደል ነውን?” አለችው። (1 ነገ. 17:17, 18) በምሬት የተናገረችው ይህ ሐሳብ ምን ይጠቁማል?

ይህች ሴት ሕሊናዋን የሚረብሻት ቀደም ሲል የሠራችው አንድ ኃጢአት ትዝ ብሏት ይሆን? ልጇ የሞተው በአምላክ ቅጣት እንደሆነና ኤልያስ ደግሞ ቅጣቱን የሚያስፈጽም የአምላክ መልእክተኛ እንደሆነ ተሰምቷት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚነግረን ነገር የለም፤ አንድ ነጥብ ግን ግልጽ ነው፦ መበለቲቱ፣ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደፈጸመባት አድርጋ በማሰብ አምላክን አልወቀሰችውም።

ኤልያስ የመበለቲቱ ልጅ መሞት እንዲሁም መበለቲቱ ለዚህ ከባድ ሐዘን የዳረጋት የእሱ ወደ ቤቷ መምጣት እንደሆነ አድርጋ መናገሯ አስደንግጦት መሆን አለበት። ኤልያስ የተዝለፈለፈውን የልጁን በድን ይዞ ወደ ሰገነቱ ከወጣ በኋላ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ልጇን እንዲሞት በማድረግ ተቀብላ በምታስተናግደኝ በዚህች መበለት ላይም መከራ ታመጣባታለህን?” ብሎ ጮኸ። ነቢዩ፣ ይሖዋ በዚህች ደግና እንግዳ ተቀባይ ሴት ላይ እንዲህ ያለ መከራ እንዲደርስ መፍቀዱ በአምላክ ስም ላይ ምን ያህል ነቀፋ ሊያስከትል እንደሚችል በማሰብ ተጨንቆ መሆን አለበት። በመሆኑም ኤልያስ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ የዚህ ልጅ ነፍስ ትመለስለት” በማለት ለመነ።—1 ነገ. 17:20, 21

“ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!”

ይሖዋ ይህን ጸሎት እያዳመጠ ነበር። ይህች መበለት ለነቢዩ እንክብካቤ አድርጋለት የነበረ ከመሆኑም ሌላ እምነት አሳይታለች። አምላክ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ትንሣኤ ለወደፊቱ ትውልድ ምን ያህል ተስፋ ሊሰጥ እንደሚችል በማሰብ ልጁ ያደረበት ሕመም ለሞት እንዲያበቃው ፈቅዷል። ኤልያስ በለመነው ጊዜ ይሖዋ ልጁ ከሞት እንዲነሳ አድርጓል። ኤልያስ “ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!” ብሎ ለመበለቲቱ ልጇን ሲሰጣት ምን ያህል ተደስታ ሊሆን እንደሚችል ገምት! በዚህ ጊዜ መበለቲቱ ኤልያስን “አሁን የእግዚአብሔር ሰው መሆንህን፣ ከአንደበትህም የወጣው የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን ዐወቅሁ” አለችው።—1 ነገ. 17:22-24

በ1 ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ የሚገኘው ዘገባ ስለዚህች መበለት ከዚህ ውጪ የሚለው ነገር የለም። ኢየሱስ ይህችን መበለት ጠቅሶ አዎንታዊ ነገር መናገሩ ቀሪ ሕይወቷን ይሖዋን በታማኝነት አገልግላ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። (ሉቃስ 4:25, 26) ስለ እሷ የሚናገረው ታሪክ አምላክ ለአገልጋዮቹ መልካም ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚባርክ ያስተምረናል። (ማቴ. 25:34-40) አምላክ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮቹ ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው ያረጋግጥልናል። (ማቴ. 6:25-34) በተጨማሪም ይህ ዘገባ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን የማስነሳት ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳለው ማስረጃ ይሆነናል። (ሥራ 24:15) በእርግጥም እነዚህ ግሩም ነጥቦች የሰራፕታዋን መበለት ሁልጊዜ እንድናስታውሳት የሚያደርጉ አይደሉም?