በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥር 2014

በልጅነቴ ያደረግኩት ምርጫ

በልጅነቴ ያደረግኩት ምርጫ

ልጅ ሳለሁ

በ1985 ከካምቦዲያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ልጆች በኦሃዮ፣ ኮለምበስ በሚገኘው ትምህርት ቤታችን አብረውን መማር ጀመሩ፤ ያኔ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከእነሱ አንዱ ጥቂት የእንግሊዝኛ ቃላት ያውቅ ነበር። የተለያዩ ሥዕሎችን እየተጠቀመ በሰዎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ድብደባና ግድያ እንዲሁም አንዳንዶች እንዴት እንዳመለጡ የሚገልጹ የሚዘገንኑ ታሪኮችን ይነግረኝ ጀመር። ማታ ማታ እነዚህን ልጆች ሳስብ አለቅስ ነበር። ምድር ገነት እንደምትሆንና ሙታን እንደሚነሱ የሚገልጸውን ተስፋ መንገር ብፈልግም በቋንቋ መግባባት አልቻልንም። በወቅቱ ትንሽ ልጅ የነበርኩ ብሆንም ለክፍል ጓደኞቼ ስለ ይሖዋ መንገር እንድችል የካምቦዲያ ቋንቋ ለመማር ወሰንኩ። ይህን ምርጫ ማድረጌ ወደፊት በሕይወቴ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ በወቅቱ የተገነዘብኩት ነገር አልነበረም።

የካምቦዲያን ቋንቋ መማር በጣም ከባድ ነው። ተስፋ ቆርጬ ከአንዴም ሁለቴ ልተወው ወስኜ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ በወላጆቼ አማካኝነት አበረታታኝ። ከጊዜ በኋላ አስተማሪዎቼና አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንድመርጥ ይገፋፉኝ ጀመር። የእኔ ፍላጎት ግን አቅኚ መሆን ነበር፤ እዚህ ግብ ላይ መድረስ እንድችል የተወሰነ ሰዓት ብቻ መሥራት የሚያስችሉኝን ኮርሶች ለመውሰድ ወሰንኩ። ከትምህርት ሰዓት በኋላ ከአንዳንድ አቅኚዎች ጋር ተቀጣጥሬ አገለግል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚማሩ ልጆችን አስተምር ነበር፤ እንዲህ ማድረጌ የኋላ ኋላ በጣም ጠቅሞኛል።

የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ሎንግ ቢች ከተማ በካምቦዲያ ቋንቋ ስብሰባ የሚያደርግ ቡድን መኖሩን ሰማሁ። እኔም ከቡድኑ ጋር ለመተዋወቅ ወደዚያ የሄድኩ ሲሆን ቋንቋውን እንዴት ማንበብ እንደምችል ተማርኩ። ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ አቅኚ ሆኜ በሰፈሬ ለማገኛቸው ካምቦዲያውያን መስበኬን ቀጠልኩ። አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ በካምቦዲያ ለመኖር አሰብኩ። በዚያ ወቅት በካምቦዲያ መኖር አደገኛ ሊሆን ቢችልም አሥር ሚሊዮን ከሚሆኑት የአገሪቱ ነዋሪዎች መካከል የመንግሥቱን ምሥራች የሰሙት ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ አውቅ ነበር። በዚያን ጊዜ ካምቦዲያ ውስጥ አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ሲሆን የአስፋፊዎቹ ብዛት 13 ነበር። በ19 ዓመቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ካምቦዲያ ሄድኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደዚያ ተዛውሬ ለመኖር ወሰንኩ። ራሴን ችዬ እየኖርኩ ማገልገል እንድችል እንግሊዝኛ በማስተማርና በመተርጎም የተወሰነ ሰዓት እሠራ ነበር። ከጊዜ በኋላ እንደ እኔ ዓይነት ግብ ያላት ሚስት አገባሁ። እኔና ባለቤቴ ብዙ ካምቦዲያውያን ሕይወታቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ የመርዳት አጋጣሚ አግኝተናል።

ይሖዋ ‘የልቤን መሻት’ ሰጥቶኛል። (መዝ. 37:4) ደቀ መዛሙርት ማፍራት ከየትኛውም ሙያ የሚበልጥ አርኪ ሥራ ነው። በካምቦዲያ በኖርኩባቸው 16 ዓመታት 13 የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈችው ትንሿ ጉባኤ አድጋ ዛሬ 12 ጉባኤዎችና 4 ገለልተኛ ቡድኖች ተቋቁመዋል!—ጄሰን ብላክዌል እንደተናገረው