በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በወጣትነት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ ማድረግ

በወጣትነት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ ማድረግ

“እናንተ ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች፣ . . . የይሖዋን ስም [አወድሱ]።”—መዝ. 148:12, 13 NW

1. ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች በየትኞቹ ግሩም አጋጣሚዎች እየተጠቀሙ ነው?

የምንኖረው ታሪካዊ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እየጎረፉ ነው። (ራእይ 7:9, 10) ብዙ ወጣቶች ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች በማስተማር አስደሳች ተሞክሮ እያገኙ ነው። (ራእይ 22:17) አንዳንድ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ በመርዳት ላይ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የሌላ አገር ቋንቋ በሚነገርባቸው ክልሎች ውስጥ ምሥራቹን በቅንዓት እያዳረሱ ነው። (መዝ. 110:3፤ ኢሳ. 52:7) የይሖዋ ሕዝቦች እያከናወኑ ባሉት በዚህ አስደሳች ሥራ ይበልጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

2. ይሖዋ ለወጣቶች ኃላፊነት እንደሚሰጥ የጢሞቴዎስ ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው? (የመጀመሪያውን ሥዕል ተመልከት።)

2 ወጣት እንደመሆንህ መጠን ዛሬ የምታደርጋቸው ምርጫዎች ወደፊት ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ሊያስገኙልህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በልስጥራ ይኖር የነበረው ጢሞቴዎስ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ በማድረጉ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ በሚስዮናዊነት ማገልገል ችሏል። (ሥራ 16:1-3) ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ካጋጠመው ኃይለኛ ተቃውሞ የተነሳ አዲሱን የተሰሎንቄ ጉባኤ ትቶ ለመሄድ በተገደደ ጊዜ ወደ ተሰሎንቄ ተመልሶ ወንድሞችን እንዲያበረታታ ኃላፊነት የሰጠው ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ነበር። (ሥራ 17:5-15፤ 1 ተሰ. 3:1, 2, 6) ጢሞቴዎስ የተሰጠው ኃላፊነት ምን ስሜት አሳድሮበት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ!

በፊትህ የተደቀነው ከሁሉ የላቀ ምርጫ

3. በሕይወትህ ውስጥ ልታደርገው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ምርጫ ምንድን ነው? ይህን ምርጫ ለማድረግስ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው?

3 የወጣትነት ዕድሜ ትላልቅ ውሳኔዎች የሚደረጉበት ወቅት ነው። ይሁንና ከሌሎቹ ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው አንድ ምርጫ አለ፤ ይህም ይሖዋን ለማገልገል የምታደርገው ውሳኔ ነው። ይህን ውሳኔ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? ይሖዋ “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” ብሏል። (መክ. 12:1) ይሖዋን ‘ማሰብ’ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ እሱን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ነው። (ዘዳ. 10:12) በሙሉ ልብህ አምላክን ለማገልገል የምታደርገው ውሳኔ በሕይወትህ ልታደርገው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ምርጫ ነው። በወደፊት ሕይወትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።—መዝ. 71:5

4. ይሖዋን ለማገልገል ከምታደርገው ምርጫ ሌላ ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ወሳኝ ምርጫዎች ምንድን ናቸው?

4 እርግጥ በወደፊት ሕይወትህ ላይ ለውጥ የሚያመጣው ይሖዋን ለማገልገል የምታደርገው ምርጫ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ትዳር መመሥረትን፣ የትዳር ጓደኛ ምርጫንና መተዳደሪያ ማግኘትን የመሳሰሉ ጉዳዮችም ያሳስቡህ ይሆናል። እነዚህ ትላልቅ ውሳኔዎች ናቸው፤ ይሁንና ከምንም በፊት ይሖዋን አቅምህ በሚፈቅደው መጠን ማገልገል ትፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ይኖርብሃል። (ዘዳ. 30:19, 20) ለምን? ምክንያቱም የምታደርጋቸው ምርጫዎች እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። ትዳርንና ሥራን በተመለከተ የምታደርገው ውሳኔ ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት ላይ ለውጥ ያመጣል። (ከሉቃስ 14:16-20 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን ለማገልገል ያለህ ፍላጎት፣ ትዳርንና ሥራን በተመለከተ በምታደርገው ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በመሆኑም የላቀ ቦታ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አስቀድመህ መወሰን ይኖርብሃል።—ፊልጵ. 1:10

በወጣትነትህ ምን ለማድረግ አስበሃል?

5, 6. ትክክለኛ ውሳኔዎችን ማድረግ የኋላ ኋላ አስደሳች ተሞክሮዎች ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (በተጨማሪም በዚህ እትም ላይ የወጣውን “በልጅነቴ ያደረግኩት ምርጫ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።)

5 አምላክን ለማገልገል ከመረጥክ በኋላ አምላክ ምን እንድታደርግ እንደሚፈልግ ማሰብ ትችላለህ፤ ደግሞም እሱን እንዴት እንደምታገለግለው መወሰን ትችላለህ። አንድ ጃፓናዊ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የ14 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ቀን ከጉባኤያችን ሽማግሌ ጋር ሳገለግል ወንድም አገልግሎቱ ብዙም እንዳላስደሰተኝ አስተዋለ። በደግነት መንፈስ ‘ዩኢቺሮ፣ ወደ ቤት ተመለስና ቁጭ ብለህ ይሖዋ ስላደረገልህ ነገር በጥሞና አስብ’ አለኝ። እኔም ልክ እንዳለኝ አደረግኩ። እንዲያውም ለተወሰኑ ቀናት በጉዳዩ ላይ ማሰቤንና መጸለዬን ቀጠልኩ። ቀስ በቀስ አመለካከቴ ተለወጠ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋን ማገልገል ያስደስተኝ ጀመር። የሚስዮናውያንን ተሞክሮ ማንበብ ያስደስተኝ ነበር፤ እንዲሁም አምላክን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ስለምችልበት መንገድ ማሰብ ጀመርኩ።”

6 ዩኢቺሮ እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል፦ “ወደፊት ይሖዋን በሌላ አገር ለማገልገል የሚያስችሉኝን ምርጫዎች ማድረግ ጀመርኩ። ለዚህም ስል እንግሊዝኛ ለመማር ወሰንኩ። ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ አቅኚ ሆኜ ማገልገል እንድችል የተወሰነ ሰዓት እንግሊዝኛ አስተምር ነበር። ሃያ ዓመት ሲሞላኝ የሞንጎሊያ ቋንቋ መማር የጀመርኩ ሲሆን ይህን ቋንቋ ከሚናገሩ አስፋፊዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አገኘሁ። ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በ2007 ሞንጎሊያን ለመጎብኘት ሄድኩ። ከአንዳንድ አቅኚዎች ጋር ሳገለግል ብዙ ሰዎች እውነትን ማወቅ እንደሚፈልጉ ስለተገነዘብኩ ወደዚያ ተዛውሬ እነሱን ለመርዳት ተነሳሳሁ። አስፈላጊውን ዕቅድ ለማውጣት ወደ ጃፓን ተመለስኩ። ከሚያዝያ 2008 ጀምሮ በሞንጎሊያ በአቅኚነት እያገለገልኩ ነው። በሞንጎሊያ ኑሮው ከባድ ነው። ሆኖም ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ ይሰጣሉ፤ እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ የመርዳት አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና እንደመረጥኩ ይሰማኛል።”

7. እኛ ራሳችን ልናደርጋቸው የሚገቡ ምርጫዎች የትኞቹ ናቸው? ሙሴስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

7 ሕይወታችንን በይሖዋ አገልግሎት እንዴት እንደምንጠቀምበት የመወሰኑ ጉዳይ ለእያንዳንዳችን የተተወ ምርጫ ነው። (ኢያሱ 24:15) ትዳር መመሥረትንና የትዳር ጓደኛ ምርጫን በተመለከተ ሌላ ሰው ሊወስንልህ አይችልም። በተጨማሪም ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንዳለብህ የምትወስነው አንተ ነህ። ብዙ ሥልጠና የማይጠይቅ ሥራ ለመያዝ ትመርጥ ይሆን? አንዳንዶቻችሁ የምትኖሩት ድህነት በተንሰራፋባቸው  መንደሮች ውስጥ ነው፤ ሌሎቻችሁ ደግሞ የምትኖሩት በበለጸጉ ከተሞች ውስጥ ነው። ያላችሁ ባሕርይ፣ ችሎታ፣ ልምድ፣ ፍላጎትና መንፈሳዊ ግብ በጣም የተለያየ ነው። በመካከላችሁ ያለው ልዩነት፣ በጥንቷ ግብፅ በነበሩት ዕብራውያን ወጣቶችና በወጣቱ ሙሴ መካከል የነበረውን ልዩነት ያህል ሰፊ ሊሆን ይችላል። ሙሴ በቤተ መንግሥት ተንደላቆ የመኖር አጋጣሚ የነበረው ሲሆን ሌሎቹ ዕብራውያን ግን በባርነት ይማቅቁ ነበር። (ዘፀ. 1:13, 14፤ ሥራ 7:21, 22) እንደ እናንተ ሁሉ እነሱም የኖሩት ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነበር። (ዘፀ. 19:4-6) እያንዳንዳቸው ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙበት መወሰን ነበረባቸው። ሙሴ ትክክለኛ ምርጫ አድርጓል።ዕብራውያን 11:24-27ን አንብብ።

8. ወጣቶች ጥሩ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል እርዳታ ከየት ማግኘት ይችላሉ?

8 ይሖዋ በወጣትነት ዕድሜያችሁ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ እንድታደርጉ ይረዳችኋል። ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያስተምራችኋል። (መዝ. 32:8) በተጨማሪም አማኝ የሆኑ ወላጆቻችሁና የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት በሥራ ማዋል እንደምትችሉ እንድትገነዘቡ ሊረዷችሁ ይችላሉ። (ምሳሌ 1:8, 9) ከዚህ ቀጥሎ፣ የወደፊት ሕይወታችሁን ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሊቀርጹ የሚችሉ ጥበብ የታከለባቸው ምርጫዎች እንድታደርጉ የሚረዷችሁን ሦስት ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።

መመሪያ የሚሆኗችሁ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

9. (ሀ) ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት እንደሚያከብረን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት መፈለጋችን’ ምን አጋጣሚ ይከፍትልናል?

9 ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ። (ማቴዎስ 6:19-21, 24-26, 31-34ን አንብብ።) ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት እንደሚያከብረን አሳይቷል። አምላክ ከወጣትነት ዕድሜህ ምን ያህሉን ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ ልታውል እንደሚገባ አልወሰነም። ይሁንና ኢየሱስ ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት መፈለግ እንዳለብን የሚገልጽ ጠቃሚ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቶናል። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ የምታደርግበት መንገድ ለአምላክ ያለህን ፍቅር፣ ለሰዎች ያለህን አሳቢነትና ለዘላለም ሕይወት ተስፋ ያለህን አድናቆት ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልሃል። ከትዳርና ከሥራ ጋር በተያያዘ የምታደርገው ምርጫ ስለ ቁሳዊ ነገሮች ይበልጥ እንድትጨነቅ ያደርግሃል? ወይስ ለአምላክ መንግሥትና ጽድቅ ያለህን ቅንዓት የሚያሳይ ይሆናል?

10. ኢየሱስ ደስተኛ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምንድን ነው? አንተስ ደስተኛ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

10 ሌሎችን በማገልገል ደስታ ለማግኘት ጣሩ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20, 21, 24, 35ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን መሠረታዊ የሆነ የሕይወት መመሪያ አስተምሮናል። የራሱን ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ ያደርግ ነበር፤ ይህም በጣም ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ኢየሱስ ገር የሆኑ ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ ሲሰጡ ማየት ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:21፤ ዮሐ. 4:34) እናንተም ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ቀምሳችሁ ይሆናል። በሕይወታችሁ ውስጥ የምታደርጓቸውን ትላልቅ ውሳኔዎች ኢየሱስ ባስተማራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርታችሁ የምታደርጉ ከሆነ ደስተኞች እንደምትሆኑ ጥርጥር የለውም፤ ይሖዋም በዚህ ይደሰታል።—ምሳሌ 27:11

11. ባሮክ ደስታውን አጥቶ የነበረው ለምንድን ነው? ይሖዋስ ምን ምክር ሰጠው?

11 ከሁሉ የላቀ ደስታ ልናገኝ የምንችለው ይሖዋን በማገልገል ነው። (ምሳሌ 16:20) የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ይህን እውነታ ዘንግቶ የነበረ ይመስላል። በአንድ ወቅት በይሖዋ አገልግሎት ያገኝ የነበረውን ደስታ አጥቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ ብሎታል፦ “ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥፋት አመጣለሁና አትፈልገው፤ . . . በሄድህበት ሁሉ ሕይወትህ እንዲተርፍልህ አደርጋለሁ።” (ኤር. 45:3, 5) ባሮክን ደስተኛ እንዲሆን ሊያደርገው የሚችለው ነገር ምንድን ነው ትላለህ? ታላቅ ነገር መሻት ወይስ የአምላክ አገልጋይ ሆኖ ከኢየሩሳሌም ጥፋት መትረፍ?—ያዕ. 1:12

12. ራሚሮ ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ያስቻለው ምን ምርጫ ማድረጉ ነው?

12 ሌሎችን ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ከቀመሱት ወንድሞች መካከል አንዱ ራሚሮ ነው። ራሚሮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የተወለድኩት በአንዲስ ተራሮች በምትገኝ አንዲት መንደር ሲሆን ቤተሰቦቼ ድሆች ነበሩ። ታላቅ ወንድሜ ዩኒቨርሲቲ እየከፈለ  ሊያስተምረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። ይሁንና ወንድሜ ይህን ሐሳብ ያቀረበልኝ የይሖዋ ምሥክር ሆኜ እንደተጠመቅኩ አካባቢ ነበር፤ በዚሁ ጊዜ አንድ አቅኚ ከእሱ ጋር በአንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረበልኝ። ወደዚያ ሄጄ ፀጉር ማስተካከል የተማርኩ ሲሆን መተዳደሪያ ለማግኘት ፀጉር ቤት ከፈትኩ። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የምናቀርብላቸውን ግብዣ በደስታ ይቀበሉ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ በተወለድኩበት አካባቢ በሚነገር ቋንቋ በተቋቋመ አዲስ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተሰማራሁ አሥር ዓመት ሆኖኛል። ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ምሥራቹን እንዲሰሙ በመርዳት ያገኘሁትን ዓይነት ደስታ ሊሰጠኝ የሚችል ሌላ ሥራ የለም።”

ራሚሮ ከወጣትነቱ ጀምሮ ይሖዋን በማገልገል ደስተኛ መሆን ችሏል (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

13. ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ወጣትነት ከሁሉ የተሻለ ጊዜ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

13 በወጣትነታችሁ ይሖዋን በማገልገል እርካታ አግኙ። (መክብብ 12:1ን አንብብ።) ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል መጀመሪያ ጥሩ ሥራ መያዝ አለብኝ ብላችሁ አታስቡ። ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ለመጀመር ከወጣትነት የተሻለ ጊዜ አይኖርም። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ወጣቶች የቤተሰብ ኃላፊነት የለባቸውም፤ በተጨማሪም ተፈታታኝ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ጥሩ ጤንነትና ብርታት አላቸው። ታዲያ በወጣትነትህ ጊዜ ለይሖዋ ምን ለማድረግ አስበሃል? ምናልባት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ግብ አውጥተህ ይሆናል። የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት ክልል ማገልገል ትፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ አሁን ባለህበት ጉባኤ ውስጥ ይበልጥ ማገልገል የምትችልባቸው መንገዶች እንዳሉ ተገንዝበህ ይሆናል። አምላክን ለማገልገል ያወጣኸው ግብ ምንም ይሁን ምን መተዳደሪያ ማግኘት ያስፈልግሃል። ‘ምን ዓይነት ሥራ ብመርጥ ይሻላል? የምወስደው ሥልጠናስ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል።

በመሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ ማድረግ

14. አንድ ሰው የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ዕቅድ ሲያወጣ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል?

14 ከላይ የተመለከትናቸው ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያሏችሁን የሥራ አማራጮች  ለመገምገም ሊረዷችሁ ይችላሉ። በትምህርት ቤታችሁ ያሉ አማካሪዎች ባላችሁበት አካባቢ ያሉትን የሥራ አማራጮች ሊጠቁሟችሁ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ወይም ደግሞ በአካባቢያችሁ አሊያም ልታገለግሉ ባሰባችሁበት ቦታ ተፈላጊ የሆነው ሙያ ምን እንደሆነ መረጃ ሊሰጣችሁ የሚችል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይኖር ይሆናል። እንዲህ ካሉ ምንጮች የምታገኙት መረጃ ሊጠቅማችሁ ይችላል፤ ሆኖም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይሖዋን የማይወዱ ሰዎች ዓለምን እንድትወዱ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባችሁ ይሞክሩ ይሆናል። (1 ዮሐ. 2:15-17) ይህ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች ስትመለከቱ ልባችሁ በቀላሉ ሊያታልላችሁ እንደሚችል አትዘንጉ።ምሳሌ 14:15ን አንብብ፤ ኤር. 17:9

15, 16. ሥራን በተመለከተ ጥሩ ምክር ሊሰጣችሁ የሚችለው ማን ነው?

15 ያሏችሁን የሥራ አማራጮች ከተገነዘባችሁ በኋላ ጥሩ ምክር ማግኘት ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 1:5) የሥራ አማራጮችን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመዘን እንድትችሉ ማን ሊረዳችሁ ይችላል? ይሖዋንና እናንተን የሚወዱ እንዲሁም እናንተንም ሆነ ያላችሁበትን ሁኔታ በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች የሚሰጧችሁን ምክር አዳምጡ። ዝንባሌያችሁንና የውስጥ ስሜታችሁን መመርመር እንድትችሉ ይረዷችኋል። የሚሰጧችሁ ሐሳብ ግባችሁን መለስ ብላችሁ እንድታስቡበት ይረዳችሁ ይሆናል። ይሖዋን የሚወዱ ወላጆች ካሏችሁ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱላችሁ ይችላሉ። በተጨማሪም በጉባኤያችሁ የሚገኙ ሽማግሌዎች ለእናንተ ጥሩ ምክር ለመስጠት የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት አላቸው። ከዚህም ሌላ አቅኚዎችንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ማማከር ትችላላችሁ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሰማራት የመረጡት ለምንድን ነው? የአቅኚነት አገልግሎት የጀመሩት እንዴት ነው? የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች የሚያሟሉትስ እንዴት ነው? አገልግሎታቸው ምን እርካታ አስገኝቶላቸዋል?—ምሳሌ 15:22

16 በሚገባ የሚያውቋችሁ ሰዎች ማስተዋል የተሞላበት ምክር ሊለግሷችሁ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ትምህርት ስለከበዳችሁ ብቻ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችሁን አቋርጣችሁ አቅኚ መሆን አሰባችሁ እንበል። በዚህ ጊዜ ከልቡ የሚወዳችሁ ሰው ዝንባሌያችሁን ሊረዳና የትምህርቱ ዓለም በቀላሉ እጅ ያለመስጠትን ባሕርይ ሊያስተምራችሁ እንደሚችል ሊያስገነዝባችሁ ይችላል፤ ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል የምትፈልጉ ከሆነ ደግሞ ይህን ባሕርይ ማዳበራችሁ ወሳኝ ነው።—መዝ. 141:5፤ ምሳሌ 6:6-10

17. ምን ዓይነት ውሳኔ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል?

17 ይሖዋን የሚያገለግል ማንኛውም ሰው እምነቱን የሚያዳክሙና ከይሖዋ እንዲርቅ ሊያደርጉት የሚችሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል። (1 ቆሮ. 15:33፤ ቆላ. 2:8) ይሁንና አንዳንድ ሥራዎች ከሌሎቹ ይበልጥ ለመንፈሳዊ አደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ። በአንድ ዓይነት የሥራ መስክ ከተሰማሩ በኋላ “አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው” የጠፋ ሰዎች በአካባቢያችሁ ይኖሩ ይሆናል። (1 ጢሞ. 1:19) ከአምላክ ጋር ያላችሁን ዝምድና አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ከማድረግ መቆጠብ የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 22:3

ወጣት ክርስቲያን መሆን በሚያስገኛቸው አጋጣሚዎች ተጠቀሙ

18, 19. አንድ ወጣት በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ ከፍ የማድረግ ተነሳሽነት ባይኖረው ምን ማድረግ ይኖርበታል?

18 ይሖዋን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት ካላችሁ ወጣት የአምላክ አገልጋይ መሆን የሚያስገኛቸውን አጋጣሚዎች ልትጠቀሙባቸው ይገባል። በዚህ አስደሳች ወቅት ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችላችሁን ምርጫ አድርጉ።—መዝ. 148:12, 13

19 ይሁንና በይሖዋ አገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ ይበልጥ ከፍ የማድረግ ተነሳሽነት ባይኖራችሁስ? ተስፋ ሳትቆርጡ እምነታችሁን ለማጠናከር ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን በረከት የሚያስገኘውን የሕይወት ጎዳና ለመከተል የሚያደርገውን ጥረት ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በማንኛውም ረገድ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ቢኖራችሁ አምላክ ትክክለኛውን አስተሳሰብ ይገልጥላችኋል። ያም ሆነ ይህ ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ ልማድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።” (ፊልጵ. 3:15, 16) ይሖዋ እንደሚወዳችሁ አስታውሱ። እሱ የሚሰጠው ምክር ከሁሉ የተሻለ ነው። በወጣትነታችሁ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ እንድታደርጉ ከማንም በተሻለ ሊረዳችሁ የሚችለው ይሖዋ ነው።