በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥር 2014

“መንግሥትህ ይምጣ”—ግን መቼ?

“መንግሥትህ ይምጣ”—ግን መቼ?

“እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደቀረበ እወቁ።”ማቴ. 24:33

1, 2. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ የሆነ ዓይነት የመታወር ችግር የሚከሰተው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

አንድ ነገር ሲከናወን በቦታው የነበሩ የዓይን ምሥክሮች አብዛኛውን ጊዜ ዝርዝር ጉዳዮቹን የሚያስታውሱት በተለያየ መንገድ እንደሆነ ሳታስተውሉ አትቀሩም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ምርመራ ካደረገ በኋላ ዶክተሩ የነገረውን ነገር እንዳለ አስታውሶ መናገር ሊከብደው ይችላል። አሊያም አንድ ሰው ቁልፉ ወይም መነጽሩ አጠገቡ እያለ ለማግኘት ሊቸገር ይችላል። እንዲህ ያሉ ነገሮች የሚያጋጥሙት ለምንድን ነው? ተመራማሪዎች በአንድ ጊዜ ከአንድ ነገር በላይ ለማከናወን ስንሞክር የሆነ ዓይነት የመታወር ችግር እንደሚከሰት ይናገራሉ። አእምሯችን በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ማድረግ የሚችለው በአንድ ነገር ላይ ብቻ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

2 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ ከሚከሰቱት ነገሮች ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ የመታወር ችግር አጋጥሟቸዋል። ከ1914 አንስቶ ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ መለወጡን ያምኑ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ክስተቶች ያላቸውን ትርጉም አያስተውሉም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በመሾሙ ከዚህ አንጻር የአምላክ መንግሥት መጥቷል ሊባል እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” የሚለው ጸሎት ገና የተሟላ ምላሽ አላገኘም። (ማቴ. 6:10) ጸሎቱ የተሟላ ምላሽ የሚያገኘው አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት ሲወገድ እንደሆነ ግልጽ  ነው። የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ሊሆን የሚችለው ይህ ሁኔታ ሲፈጸም ብቻ ነው።

3. የአምላክን ቃል ማጥናታችን የጠቀመን እንዴት ነው?

3 የአምላክን ቃል አዘውትረን ስለምናጠና ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ እንዳለ መገንዘብ እንችላለን። አብዛኞቹ ሰዎች ግን ይህን አይገነዘቡም! ስለ ኑሯቸውና ስለሚያከናውኗቸው ነገሮች በማሰብ የተጠመዱ በመሆናቸው ክርስቶስ ከ1914 አንስቶ እየገዛ እንዳለ፣ በቅርቡ ደግሞ የአምላክን ፍርድ እንደሚያስፈጽም የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ቸል ብለዋል። ይሁን እንጂ የሚከተለውን ጥያቄ በግለሰብ ደረጃ ልታስቡበት ይገባል፦ አምላክን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስታገለግሉ ቆይታችሁ ከሆነ ከዓመታት በፊት ታደርጉ እንደነበረው በምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንኖር በንቃትና በትኩረት ታስባላችሁ? የይሖዋ ምሥክር የሆናችሁት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቢሆንም እንኳ ትኩረታችሁ ያረፈው ምን ላይ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን፣ አምላክ የሾመው ንጉሥ መለኮታዊው ፈቃድ በምድር ላይ በተሟላ መልኩ እንዲፈጸም በቅርቡ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወስድ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያስችሉንን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

ፈረሰኞቹ ተገልጠዋል

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ከ1914 አንስቶ ምን ሲያደርግ ቆይቷል? (የመጀመሪያውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) የሦስቱ ፈረሰኞች ግልቢያ ምን ያመለክታል? ትንቢቱስ የተፈጸመው እንዴት ነው?

4 ነጭ ፈረስ እየጋለበ እንዳለ ተደርጎ የተገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ አክሊል ተሰጥቶታል። በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ የተሟላ ድል ለመቀዳጀት ወዲያውኑ ግስጋሴውን ጀምሯል። (ራእይ 6:1, 2ን አንብብ።) በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ የተገለጸው ትንቢት የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ በፍጥነት እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ያመለክታል፤ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ ቸነፈር እንዲሁም ሞት የሚያስከትሉ ሌሎች ነገሮች ይከሰታሉ። ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርብ ርቀት እየተከተሉ የሚጋልቡት ሦስት ፈረሰኞች እነዚህን ክስተቶች የሚያመለክቱ ናቸው።—ራእይ 6:3-8

5 ሰዎች፣ ብሔራትን በማስተባበርና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት አማካኝነት ሰላም ለማስፈን ቃል ቢገቡም በትንቢት በተገለጸው መሠረት ‘ሰላም ከምድር ተወስዷል።’ አንደኛው የዓለም ጦርነት የታላላቅ ጦርነቶች መባቻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ በቅርቡ በዓለም ላይ የታዩት ክስተቶች ይህን ያረጋግጣሉ። ከ1914 አንስቶ በኢኮኖሚም ሆነ በሳይንስ መስክ ከፍተኛ እድገት የታየ ቢሆንም እንኳ በዛሬው ጊዜም የምግብ እጥረት የዓለምን ደህንነት ስጋት ላይ እንደጣለ ነው። በተጨማሪም ልዩ ልዩ ዓይነት ወረርሽኞች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎች ‘ገዳይ መቅሰፍቶች’ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፉ ማን ሊክድ ይችላል? የእነዚህ ክስተቶች ስፋትና ድግግሞሽ እንዲሁም የሚያስከትሉት እልቂት በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ ምን ትርጉም እንዳለው ልብ ብለሃል?

ፈረሰኞቹ ግልቢያቸውን በቀጠሉበት በዚህ ዘመን በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸውን ቀጥለዋል (አንቀጽ 4ንና 5ን ተመልከት)

6. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያገኘውን ፍጻሜ ያስተዋሉት እነማን ነበሩ? ይህስ ምን እንዲያደርጉ አነሳሳቸው?

6 አንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳቱና የኅዳር በሽታ መከሰቱ ብዙዎች ትኩረታቸው እንዲሰረቅ አድርጓል። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ግን ለብሔራት የተቀጠረው ጊዜ ወይም “የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 እንደሚያበቃ በመገንዘብ ይህን ወቅት በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። (ሉቃስ 21:24) እነዚህ ክርስቲያኖች ምን እንደሚከሰት ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች አልነበሩም። ያም ሆኖ 1914 ከመለኮታዊ አገዛዝ ጋር በተያያዘ አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት ዓመት እንደሚሆን ተገንዝበው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ሲረዱ ወዲያውኑ የአምላክ አገዛዝ መጀመሩን ለሌሎች በድፍረት አወጁ። ይሁንና መንግሥቱን ለማወጅ ያደረጉት ጥረት ከባድ ስደት አስከትሎባቸዋል። ይህ በብዙ አገሮች ውስጥ መከሰቱ በራሱ የትንቢቱን መፈጸም የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ‘ዐመፃን ሕጋዊ በማድረግ’ ጥቃት ለማድረስ ጥረት ያደርጉ ጀመር። በተጨማሪም ወንድሞቻችንን መደብደብ፣ ማሰር አልፎ ተርፎም በስቅላት፣ በጥይት አሊያም አንገታቸውን በመቅላት  መግደል ጀመሩ።—መዝ. 94:20፤ ራእይ 12:15

7. አብዛኛው ሕዝብ በዓለም ላይ የሚታዩት ክስተቶች ያላቸውን ትርጉም ማስተዋል ያልቻለው ለምንድን ነው?

7 የአምላክ መንግሥት በሰማይ እንደተቋቋመ የሚያረጋግጥ ብዙ ማስረጃ እያለ አብዛኛው ሕዝብ ይህን ማስተዋል የተሳነው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ የሚታየውን ሁኔታ፣ የአምላክ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ ሲያውጁት ከነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ማዛመድ ያቃታቸው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ ሰዎች ትኩረት የሚሰጡት በዓይናቸው ማየት ለሚችሉት ነገር ብቻ ስለሆነ ይሆን? (2 ቆሮ. 5:7) በሰብዓዊ ጉዳዮች ከልክ በላይ መጠመዳቸው አምላክ የሚያከናውነው ነገር እንዳይታያቸው አድርጎ ይሆን? (ማቴ. 24:37-39) አንዳንዶቹ በሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ ተዘናግተው ይሆን? (2 ቆሮ. 4:4) በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ነገር ለመመልከት እምነትና መንፈሳዊ ማስተዋል ያስፈልጋል። እየተከናወነ ያለውን ነገር ማየት የተሳነን ባለመሆናችን እጅግ ደስተኞች ነን!

ክፋት እየተባባሰ ሄዷል

8-10. (ሀ) ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-5 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ክፋት እየተባባሰ ሄዷል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

8 የአምላክ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች በቅርቡ እንደሚቆጣጠር ማወቅ የምንችልበት ሁለተኛው ምክንያት በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚታየው ክፋት እየተባባሰ መሄዱ ነው። ለአንድ መቶ ዓመት ገደማ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ በትንቢት የተነገሩት ሁኔታዎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። እንዲያውም እነዚህ ባሕርያት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም ዙሪያ እየተስፋፉ ነው። ይህ ትንቢት በሰፊው እየተፈጸመ እንዳለ አላስተዋልክም? ይህን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13ን አንብብ።

9 በ1940ዎቹ ወይም በ1950ዎቹ ዓመታት አሳፋሪ ተደርገው ይታዩ የነበሩትን ነገሮች በዛሬው ጊዜ በሥራ ቦታ እንዲሁም በመዝናኛው፣ በስፖርቱና በፋሽኑ ዓለም ከሚፈጸመው ነገር ጋር ለማነጻጸር ሞክር። እጅግ የከፋ ዓመፅና አስነዋሪ ብልግና በአሁኑ ጊዜ በየትም ቦታ የሚታዩ ነገሮች ሆነዋል። ሰዎች በኃይለኝነት፣ በብልግና ወይም በጭካኔ ከማንኛውም ሰው በልጠው መገኘት ይፈልጋሉ። በ1950ዎቹ መጥፎ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተደርጎ ይታይ የነበረው በዛሬው ጊዜ ለቤተሰብ ተስማሚ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ግብረ ሰዶማውያን በመዝናኛውና በፋሽኑ ዓለም ከፍተኛ ተደማጭነት እንዳላቸው ብዙዎች መገንዘብ ችለዋል፤ እንዲያውም የአኗኗር ዘይቤያቸውን በአደባባይ ያራምዳሉ። አምላክ ስለ እነዚህ ነገሮች  ያለውን አመለካከት በማወቃችን በጣም አመስጋኞች ነን!ይሁዳ 14, 15ን አንብብ።

10 በተጨማሪም በ1950ዎቹ ዓመታት ወጣቶች ዓመፀኛ ተደርገው እንዲታዩ በሚያደርጋቸው ምግባርና ዛሬ በሚታየው ሁኔታ መካከል ያለውን ልዩነት ለማሰብ ሞክር። ወላጆች፣ ‘ልጆቼ ሲጋራ ማጨስ፣ መጠጥ መጠጣት ወይም መጥፎ ዓይነት ጭፈራ መጨፈር ጀምረው ይሆን’ ብለው ይጨነቁ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን እንደሚከተለው ያሉ የሚዘገንኑ ሪፖርቶችን መስማት የተለመደ ሆኗል፦ የ15 ዓመት ልጅ በክፍል ጓደኞቹ ላይ ተኩስ ከፍቶ 2ቱን ገደለ፤ 13ቱን ደግሞ አቆሰለ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ የሰከሩ ወጣቶች ዘጠኝ ዓመት የሆናትን ልጅ በጭካኔ ገድለው አባቷንና የአክስቷን ልጅ ደበደቡ። በአንድ የእስያ አገር ባለፉት አሥር ዓመታት ከተፈጸሙት ወንጀሎች መካከል ግማሽ ያህሉን የፈጸሙት ወጣቶች ናቸው። ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸውን መካድ የሚችል ይኖራል?

11. ብዙ ሰዎች ነገሮች እየተበላሹ መሄዳቸውን ያልተገነዘቡት ለምንድን ነው?

11 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በትክክል ትንቢት ተናግሯል፦ “በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ምኞት እየተከተሉ የሚያፌዙ ፌዘኞች እንደሚመጡ ታውቃላችሁ። እነዚህ ፌዘኞች ‘“እገኛለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል’ ይላሉ።” (2 ጴጥ. 3:3, 4) አንዳንዶች እንዲህ የሚሉት ለምን ሊሆን ይችላል? አንድ ሁኔታ ይበልጥ እየተለመደ በመጣ ቁጥር ሰዎች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸው እየቀነሰ የሚመጣ ይመስላል። በጥቅሉ ሲታይ የኅብረተሰቡ ሥነ ምግባር ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ መሄዱ፣ በቅርብ ጓደኛችን ላይ የምናየውን ድንገተኛና ያልተጠበቀ የባሕርይ ለውጥ ያህል አስደንጋጭ አይሆንብንም። ይሁንና በዓለም ላይ የሚታየው የሥነ ምግባር ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሄዱ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል አይደለም።

12, 13. (ሀ) በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ለመቋቋም አስቸጋሪ’ የሆነውን ሁኔታ መወጣት እንድንችል የሚረዳን ምን መገንዘባችን ነው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ያለው ሁኔታ “ለመቋቋም የሚያስቸግር” እንደሚሆን አስጠንቅቋል። (2 ጢሞ. 3:1) ሆኖም ለመቋቋም የማይቻል አይደለም፤ በመሆኑም እውነታውን መጋፈጥ ይኖርብናል። ከይሖዋ፣ ከመንፈሱና ከክርስቲያን ጉባኤ በምናገኘው እርዳታ አማካኝነት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም አሳዛኝ ወይም አስደንጋጭ ሁኔታ በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን። ደግሞም በታማኝነት መጽናት እንችላለን። “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል” ምንጭ እኛ ሳንሆን አምላክ ነው።—2 ቆሮ. 4:7-10

13 ጳውሎስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የሚናገረውን ትንቢት የጀመረው “ይህን እወቅ” በማለት እንደሆነ ማስተዋል ይገባል። እነዚህ ቃላት ከዚያ በመቀጠል የተዘረዘሩት ነገሮች በእርግጥ እንደሚፈጸሙ ዋስትና ይሰጣሉ። ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እስኪያቆመው ድረስ ከአምላክ የራቀው ኅብረተሰብ እየተበላሸ እንደሚሄድ ምንም ጥያቄ የለውም። የታሪክ ምሑራን፣ በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ አንዳንድ ኅብረተሰቦች ወይም ብሔራት በደረሰባቸው ከባድ የሥነ ምግባር ውድቀት የተነሳ ለጥፋት መዳረጋቸውን ዘግበዋል። ይሁንና የመላው ዓለም አጠቃላይ የሥነ ምግባር አቋም የአሁኑን ያህል ያሽቆለቆለበት ዘመን በታሪክ ታይቶ አያውቅም። ብዙ ሰዎች ይህ ሁኔታ የሚያስተላልፈውን መልእክት በቸልታ ቢያልፉም ከ1914 አንስቶ የተከናወኑት ነገሮች የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል የሚል እምነት እንዲያድርብን ያደርጉናል።

ይህ ትውልድ አያልፍም

14-16. የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ‘ይመጣል’ ብለን እንድናምን የሚያስችለን ሦስተኛ ምክንያት ምንድን ነው?

14 መጨረሻው እንደቀረበ እንድንተማመን የሚያስችለን ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የተከናወነው ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከመቋቋሙ በፊት ታማኝ ቅቡዓንን ያቀፈ አንድ ቡድን አምላክን በትጋት እያገለገለ ነበር። በ1914 ይፈጸማሉ ብለው የጠበቋቸው አንዳንድ ነገሮች ሳይፈጸሙ ሲቀሩ ምን አደረጉ? አብዛኞቹ የሚደርስባቸውን ፈተናና ስደት ተቋቁመው በአቋማቸው ጸንተዋል፤ ይሖዋን ማገልገላቸውንም ቀጥለዋል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ  አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት አጠናቅቀዋል።

15 ኢየሱስ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በተናገረው፣ ዝርዝር ሐሳቦችን በያዘው ትንቢት ላይ “እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪከሰቱ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:33-35ን አንብብ።) ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ስላቀፉ ሁለት ቡድኖች እየተናገረ እንደነበር እንረዳለን። የመጀመሪያው ቡድን በ1914 በሕይወት ይገኝ ነበር፤ ደግሞም ክርስቶስ በዚያ ዓመት ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ አስተውሏል። የዚህ ቡድን አባላት በ1914 በሕይወት የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር በዚያ ዓመት ወይም ከዚያ በፊት በመንፈስ ተቀብተው የአምላክ ልጆች ሆነው ነበር።—ሮም 8:14-17

16 “ይህ ትውልድ” ያቀፈው የሁለተኛው ቡድን አባላት ከመጀመሪያው ቡድን ጋር በተመሳሳይ ወቅት የኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። ከዚህም ሌላ የመጀመሪያው ቡድን አባላት በምድር ላይ በሕይወት እያሉ የሁለተኛው ቡድን አባላት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ነበር። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያለ እያንዳንዱ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል በተናገረው ውስጥ አይካተትም። በዛሬው ጊዜ በዚህ በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ያሉ ቅቡዓን ሳይቀር በዕድሜ እየገፉ መጥተዋል። ይሁንና ኢየሱስ በማቴዎስ 24:34 ላይ “ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም” በማለት የተናገረው ሐሳብ ከእነሱ መካከል ቢያንስ የተወሰኑት ታላቁ መከራ ሲጀምር እንደሚያዩ እርግጠኞች እንድንሆን ያስችለናል። ይህ ጉዳይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ክፉዎችን ለማጥፋት እርምጃ የሚወስድበትና ጽድቅ የሰፈነበትን አዲስ ዓለም የሚያመጣበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ ያለንን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልናል።—2 ጴጥ. 3:13

ክርስቶስ በቅርቡ ድሉን ያጠናቅቃል

17. እስካሁን ከተመለከትናቸው ሦስት ማስረጃዎች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?

17 እስካሁን ከተመለከትናቸው ሦስት ማስረጃዎች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ኢየሱስ ትክክለኛውን ቀን ወይም ሰዓት ማወቅ እንደማንችል አስጠንቅቋል። (ማቴ. 24:36፤ 25:13) ይሁንና ጳውሎስ እንደገለጸው “ዘመኑን” ማወቅ እንችላለን፤ ደግሞም እናውቃለን። (ሮም 13:11ን አንብብ።) የምንኖረው በዚያ ዘመን ይኸውም በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲሁም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ እያከናወኑት ላለው ነገር የተሟላ ትኩረት ከሰጠን ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም መቃረባችንን የሚጠቁሙ አሳማኝ ማስረጃዎችን ማየት አይሳነንም።

18. የኢየሱስ ክርስቶስን ንግሥና ለመቀበል እምቢተኞች የሆኑ ምን ይጠብቃቸዋል?

18 ነጩን ፈረስ የሚጋልበው ድል አድራጊው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን ከፍተኛ ሥልጣን ለመቀበል እምቢተኛ የሆኑ ሁሉ የፈጸሙትን ስህተት በቅርቡ አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ። በዚያን ጊዜ ማምለጫ ቀዳዳ አያገኙም። እንዲያውም ብዙዎች በፍርሃት ተውጠው ‘ማን ሊቆም ይችላል?’ ብለው ይጮኻሉ። (ራእይ 6:15-17) ይሁንና በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ቀጣዩ ምዕራፍ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል። በዚያን ቀን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ‘የሚቆሙት’ በመንፈስ የተቀቡትና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ናቸው። የሌሎች በጎች ክፍል የሆነ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከታላቁ መከራ በሕይወት ይተርፋል።—ራእይ 7:9, 13-15

19. የመጨረሻዎቹ ቀኖች በቅርቡ እንደሚያበቁ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ የተገነዘብክ፣ አምነህ የተቀበልክና ተገቢውን ምላሽ የሰጠህ እንደመሆንህ መጠን ወደፊት ምን ለማግኘት ትጠባበቃለህ?

19 በዚህ አስደናቂ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሲፈጸም በንቃት የምንከታተል ከሆነ በሰይጣን ዓለም ፕሮፓጋንዳ ትኩረታችን አይከፋፈልም ወይም ደግሞ በዓለም ላይ የሚታዩት ክስተቶች የያዙትን እውነተኛ ትርጉም ማስተዋል አይሳነንም። ክርስቶስ የመጨረሻውን የጽድቅ ውጊያ በማካሄድ ከአምላክ በራቀው በዚህ ኅብረተሰብ ላይ የሚቀዳጀውን ድል ያጠናቅቃል። (ራእይ 19:11, 19-21) ከዚህ በኋላ በጣም አስደሳች ሕይወት እንደሚጠብቀን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ራእይ 20:1-3, 6፤ 21:3, 4