‘ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ የይሖዋ በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።’—ዘፀ. 12:14

1, 2. የሁሉንም ክርስቲያኖች ትኩረት ሊስብ የሚገባው ዓመታዊ በዓል የትኛው ነው? ለምንስ?

ስለ ዓመታዊ በዓላት ስታስብ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንድ ያገባ ሰው የጋብቻ በዓሉን ይጠቅስ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ፣ ታሪካዊ ክንውኖችን በማስታወስ በስፋት የሚከበሩ በዓላትን ይጠቅሳሉ፤ ለምሳሌ ያህል፣ አገራቸው ነፃ የወጣችበት ቀን ሊሆን ይችላል። ከ3,500 ለሚበልጡ ዓመታት ሲከበር የኖረ ብሔራዊ ክብረ በዓል እንዳለ ታውቃለህ?

2 ይህ በዓል ፋሲካ ነው። በዓሉ የሚከበረው እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበትን ዕለት ለማስታወስ ነው። ይህ በዓል የአንተንም ትኩረት ሊስብ ይገባል። ለምን? በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምትሰጣቸው ነገሮች ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩት አይሁዳውያን ናቸው፤ እኔ ደግሞ አይሁዳዊ አይደለሁም። ታዲያ ይህ ዓመታዊ በዓል ለእኔ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል?’ “ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቷል” የሚለው ጥቅስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። (1 ቆሮ. 5:7) የዚህን ጥቅስ ሐሳብ ለመረዳት አይሁዳውያን ስለሚያከብሩት የፋሲካ በዓል ማወቅና ይህ በዓል ለክርስቲያኖች ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ መመርመር ይኖርብናል።

ፋሲካ ይከበር የነበረው ለምንድን ነው?

3, 4. ከመጀመሪያው ፋሲካ በፊት ምን ነገሮች ተከናወኑ?

3 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች፣ ከመጀመሪያው ፋሲካ በፊት ስለተከናወኑት ነገሮች የተወሰነ እውቀት አላቸው። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የዘፀአት መጽሐፍ አንብበው፣ ታሪኩን ሰዎች ሲናገሩ ሰምተው ወይም በታሪኩ ላይ የተመሠረተ ፊልም ተመልክተው ሊሆን ይችላል።

4 እስራኤላውያን ለበርካታ ዓመታት በግብፅ ባሪያዎች ሆነው ከኖሩ በኋላ ይሖዋ፣ ሙሴንና ወንድሙን አሮንን ወደ ፈርዖን ላካቸው፤ እነሱም እስራኤላውያንን እንዲለቅቅ ፈርዖንን ጠየቁት። እብሪተኛ የነበረው ይህ የግብፅ መሪ ግን ሊለቃቸው ፈቃደኛ አልነበረም፤ በመሆኑም ይሖዋ ምድሪቱን በተለያዩ አስከፊ መቅሰፍቶች  መታ። በመጨረሻም አምላክ፣ አሥረኛውን መቅሰፍት ሲያመጣ የግብፃውያን በኩራት በሙሉ ሞቱ፤ በዚህም የተነሳ ፈርዖን ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሆነ።—ዘፀ. 1:11፤ 3:9, 10፤ 5:1, 2፤ 11:1, 5

5. እስራኤላውያን ነፃ ከመውጣታቸው በፊት ምን እንዲያደርጉ ታዝዘው ነበር? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ነፃ ከመውጣታቸው በፊት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ታሪኩ የተከናወነው በ1513 ዓ.ዓ. የጸደይ ወቅት ላይ አቢብ ተብሎ በሚጠራው የአይሁዳውያን ወር ነበር፤ ይህ ወር ከጊዜ በኋላ ኒሳን ተብሏል። * እስራኤላውያን ከዚያ ወር አሥረኛ ቀን ጀምሮ ለኒሳን 14 ማድረግ ያለባቸውን አንዳንድ ዝግጅቶች አምላክ ነገራቸው። በዕብራውያን የጊዜ አቆጣጠር መሠረት አንድ ቀን የሚባለው ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ እንደገና እስከምትጠልቅበት ድረስ ያለው ጊዜ ስለሆነ ይህ ቀን የጀመረው ጀምበር ስትጠልቅ ነው። ኒሳን 14 ላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ የበግ (ወይም የፍየል) ጠቦት ማረድና ደሙን በበሩ መቃኖችና በጉበኑ ላይ መርጨት አለበት። (ዘፀ. 12:3-7, 22, 23) እስራኤላውያን በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው የተጠበሰ የበግ ሥጋ ካልቦካ ቂጣና ከተለያዩ ቅጠሎች ጋር ይመገባሉ። የአምላክ መልአክ በምድሪቱ ላይ እየተዘዋወረ የግብፃውያንን በኩራት ይገድላል፤ ታዛዥ የሆኑ እስራኤላውያን ጥበቃ የሚያገኙ ሲሆን በኋላ ላይም ነፃ ይወጣሉ።—ዘፀ. 12:8-13, 29-32

6. የአምላክ ሕዝቦች፣ የፋሲካ በዓልን በየዓመቱ ማክበር የነበረባቸው ለምንድን ነው?

6 ነገሮቹ የተከናወኑትም ልክ በዚህ መልኩ ነው፤ እስራኤላውያን ነፃ የወጡበትን ቀን በቀጣዮቹ ዓመታትም ማስታወስ ይጠበቅባቸው ነበር። ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።” ከኒሳን 14 ቀጥሎ ለሰባት ቀን ያህል የቂጣ በዓል ያከብራሉ። ፋሲካ የምንለው በዋነኝነት ኒሳን 14 የሚከበረውን በዓል ቢሆንም መጠሪያው እነዚህ በዓላት በአጠቃላይ ለሚቆዩባቸው ስምንት ቀናትም ያገለግላል። (ዘፀ. 12:14-17፤ ሉቃስ 22:1፤ ዮሐ. 18:28፤ 19:14) እስራኤላውያን እንዲያከብሯቸው ከታዘዙት “የዓመት በዓላት” መካከል አንዱ ፋሲካ ነው።—2 ዜና 8:13

7. ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባከበረው የመጨረሻ ፋሲካ ላይ የትኛውን በዓል አቋቋመ?

7 ኢየሱስና ሐዋርያቱ፣ በሙሴ ሕግ ሥር ያሉ አይሁዳውያን እንደመሆናቸው መጠን ዓመታዊውን የፋሲካ በዓል አክብረዋል። (ማቴ. 26:17-19) ይህን በዓል ለመጨረሻ ጊዜ ባከበሩበት ወቅት ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ማክበር ያለባቸውን በዓል ማለትም የጌታ ራትን አቋቋመ። ይሁን እንጂ በዓሉን ማክበር ያለባቸው መቼ ነው?

የጌታ ራት መከበር ያለበት መቼ ነው?

8. ፋሲካንና የጌታ ራትን አስመልክቶ ምን ጥያቄ ይነሳል?

8 ኢየሱስ፣ የጌታ ራትን ያቋቋመው ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን የፋሲካ በዓል አክብሮ ሲጨርስ ስለሆነ ይህ በዓል መከበር ያለበት የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ዕለት ነው። ይሁን እንጂ አሁን ያሉት አይሁዳውያን የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩበት ቀን እኛ የክርስቶስን ሞት ከምናከብርበት ዕለት ጋር የአንድ ወይም የጥቂት ቀናት ልዩነት ሊኖረው እንደሚችል ሳትገነዘብ አልቀረህም። እንዲህ ያለ ልዩነት የተፈጠረው ለምንድን ነው? አምላክ፣ የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ ለእስራኤላውያን የሰጠው ትእዛዝ የዚህን ጥያቄ መልስ በተወሰነ መጠን ይጠቁመናል። ሙሴ “የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ [በጎቹን] ይረዷቸው” በማለት ከመናገሩ በፊት ኒሳን 14 ላይ በምን ሰዓት እንዲህ ሊያደርጉ እንደሚገባ ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል።ዘፀአት 12:5, 6ን አንብብ።

9. በዘፀአት 12:6 መሠረት የፋሲካው በግ የሚታረደው ስንት ሰዓት ላይ ነው? (በተጨማሪም  “ስንት ሰዓት ላይ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

9 ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር በተዘጋጀው አዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ የዘፀአት 12:6 የግርጌ ማስታወሻ፣ በጉ መታረድ ያለበት “በሁለት ምሽት መካከል” እንደሆነ ይናገራል። አንዳንድ የመጽሐፍ  ቅዱስ ትርጉሞች በዋናው ጽሑፍ ላይ ይህንን ጥቅስ የተረጎሙትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው። በአንዳንድ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይህ አገላለጽ “ምሽት ላይ” እና “ጀምበር ስትጠልቅ” ተብሎ ተተርጉሟል። በመሆኑም በጉ የሚታረደው ኒሳን 14 መጀመሪያ ላይ ይኸውም ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ሆኖም ሙሉ በሙሉ ከመጨለሙ በፊት ነው።

10. አንዳንዶች የፋሲካ በግ መታረድ ያለበት መቼ ነው ይላሉ? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

10 ከጊዜ በኋላ አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡትን በጎች በሙሉ ለማረድ ብዙ ሰዓት ሊፈጅ እንደሚችል ይሰማቸው ጀመር። በመሆኑም በዘፀአት 12:6 ላይ የተጠቀሰው ወቅት ኒሳን 14 ሊያበቃ ሲል ያለውን ጊዜ ይኸውም ፀሐይ ማዘቅዘቅ ከምትጀምርበት ጊዜ (ከእኩለ ቀን) አንስቶ ጀምበር ጠልቃ ቀኑ እስከሚያበቃበት ድረስ ያለውን ጊዜ እንደሚያመለክት ማሰብ ጀመሩ። ይሁን እንጂ በጎቹ የሚታረዱት ኒሳን 14 ማብቂያ ላይ ከሆነ ፋሲካው የሚበላው መቼ ነው? የጥንት የአይሁድ እምነት ሊቅ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆናታን ክላዋንስ እንዲህ ብለዋል፦ “አዲስ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ነው፤ በመሆኑም መሥዋዕቱ የሚቀርበው በ14ኛው ቀን ቢሆንም ፋሲካ የሚጀምረውና የሚበላው በ15ኛው ቀን ነው፤ እርግጥ የዘፀአት መጽሐፍ በዓሉ በዚህ ቀን መከበር እንዳለበት የሚናገረው ነገር የለም።” አክለውም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የረቢዎች ጽሑፍ ቤተ መቅደሱ [በ70 ዓ.ም.] ከመጥፋቱ በፊት ሴደር [የፋሲካ ምግብ] እንዴት ይበላ እንደነበር እንኳ አይገልጽም።”—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

11. (ሀ) ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. በዋለው የፋሲካ በዓል ቀን ምን ደረሰበት? (ለ) በ33 ዓ.ም. የዋለው ኒሳን 15 “ታላቅ ሰንበት” የተባለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

11 ከዚህ አንጻር ‘በ33 ዓ.ም. ፋሲካ የተከበረው መቼ ነው?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ኒሳን 13 ላይ ‘የፋሲካ መሥዋዕት የሚሠዋበት’ ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “ሄዳችሁ ፋሲካን እንድንበላ አዘጋጁልን” አላቸው። (ሉቃስ 22:7, 8) “ከጊዜ በኋላም” ፋሲካ የሚበላበት ‘ሰዓት ደረሰ’፤ ይህ የሆነው ሐሙስ ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነበር። ኢየሱስ ይህንን ፋሲካ ከሐዋርያቱ ጋር ከበላ በኋላ የጌታ ራትን አቋቋመ። (ሉቃስ 22:14, 15) ኢየሱስ የታሰረውና ለፍርድ የቀረበው በዚያው ምሽት ነው። ኒሳን 14 እኩለ ቀን አካባቢ ኢየሱስ ተሰቀለ፤ የሞተውም በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው። (ዮሐ. 19:14) በመሆኑም ‘ፋሲካችን ክርስቶስ የተሠዋው’ የፋሲካ በግ በሚታረድበት ቀን ነው። (1 ቆሮ. 5:7፤ 11:23፤ ማቴ. 26:2) በአይሁዳውያን አቆጣጠር መሠረት፣ ኒሳን 14 ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ማለትም ኒሳን 15 ከመጀመሩ በፊት ኢየሱስ ተቀበረ። *ዘሌ. 23:5-7፤ ሉቃስ 23:54

 ለአንተ ትርጉም ያለው መታሰቢያ

12, 13. የፋሲካ በዓል ለአይሁዳውያን ልጆች ምን ትርጉም ነበረው?

12 አሁን ደግሞ በግብፅ ወደተከበረው የፋሲካ በዓል መለስ እንበል። ሙሴ፣ የአምላክ ሕዝቦች ፋሲካን እንዲያከብሩና ይህም “ቋሚ ሥርዐት” ሊሆናቸው እንደሚገባ ነገራቸው። በየዓመቱ ይህ በዓል ሲከበር ልጆች የበዓሉ ትርጉም ምን እንደሆነ ወላጆቻቸውን መጠየቃቸው አይቀርም። (ዘፀአት 12:24-27ን አንብብ፤ ዘዳ. 6:20-23) በመሆኑም ፋሲካ ልጆችም ትምህርት የሚያገኙበት ‘የመታሰቢያ’ በዓል ሆኖ ያገለግል ነበር።—ዘፀ. 12:14

13 አባቶች ለልጆቻቸው የበዓሉን ትርጉም ስለሚያስረዱ መጪዎቹ ትውልዶች አስፈላጊ ትምህርቶች እያገኙ ይሄዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ይማራሉ። እስራኤላውያን ልጆች ስለ ይሖዋ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ይሖዋ፣ ለሕዝቦቹ የሚያስብና እነሱን ለመታደግ እርምጃ የሚወስድ እውን እና ሕያው የሆነ አምላክ ነው። ይሖዋ “ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ” ለእስራኤላውያን በኩራት ጥበቃ በማድረግ እንዲህ ዓይነት አምላክ መሆኑን አሳይቷል። በዚህ ወቅት የእስራኤል በኩራት በሕይወት እንዲተርፉ አድርጓል።

14. ክርስቲያን ወላጆች ስለ ፋሲካ የሚናገረውን ዘገባ ተጠቅመው ልጆቻቸውን ምን ማስተማር ይችላሉ?

14 ክርስቲያን ወላጆች፣ የአይሁዳውያን ፋሲካ ያለውን ትርጉም በየዓመቱ ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ አይጠበቅባቸውም። ይሁን እንጂ ወላጆች፣ ከበዓሉ የሚገኘውን ትምህርት ይኸውም አምላክ ሕዝቦቹን እንደሚጠብቅ ለልጆቻችሁ ታስተምሯቸዋላችሁ? ይሖዋ እውን እንደሆነና አሁንም ቢሆን ለሕዝቦቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ ያላችሁን ጠንካራ እምነት ልጆቻችሁ በግልጽ ማየት ይችላሉ? (መዝ. 27:11፤ ኢሳ. 12:2) ለልጆቻችሁ ይህን ስታስተምሩ እናንተ ብቻ በመናገር ልጆቹ እንዲሰለቹ ከማድረግ ይልቅ ውይይቱ አስደሳች እንዲሆን ትጥራላችሁ? ከፋሲካ በዓል የሚገኙ ትምህርቶችን በመጠቀም ቤተሰባችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት ጥረት አድርጉ።

ስለ ፋሲካ በዓል ከልጆቻችሁ ጋር በመወያየት ምን ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ? (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

15, 16. ከዘፀአት ምዕራፍ 12 እስከ 15 ላይ ያለው ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

15 ስለ ፋሲካ የሚናገረው ዘገባ የሚያስተምረን፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ብቻ አይደለም። አምላክ ሕዝቡን ‘ከግብፅ በማውጣት’ ታድጓቸዋል። ይህ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለአንድ አፍታ አስብ። አምላክ፣ በደመናና በእሳት ዓምድ መርቷቸዋል። እስራኤላውያን፣ ቀይ ባሕር በግራቸውና በቀኛቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ በደረቅ ምድር ተጉዘዋል። እንዲሁም ባሕሩን በሰላም ከተሻገሩ በኋላ ውኃው የግብፅን ሠራዊት ሲያጠፋ ተመልክተዋል። በመሆኑም ሕዝቡ ይሖዋ ስለታደጋቸው እንዲህ ብለው ለመዘመር ተገፋፍተዋል፦ “ለይሖዋ እዘምራለሁ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው። አዳኜ ስለሆነልኝ ያህ ብርታቴና ኃይሌ ነው።”—ዘፀ. 13:14, 21, 22፤ 15:1, 2 NW፤ መዝ. 136:11-15

16 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚታደግ ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉ እየረዳችኋቸው ነው? እንዲህ ዓይነት ጠንካራ እምነት እንዳላችሁ ከንግግራችሁና ከምታደርጓቸው ውሳኔዎች መመልከት ይችላሉ? ከዘፀአት ምዕራፍ 12 እስከ 15 ላይ ያለው ታሪክ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚታደግ የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ወቅት ልትወያዩ ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 7:30-36 አሊያም  በዳንኤል 3:16-18, 26-28 ላይ የሚገኘውን ዘገባ በመጠቀም ይህንኑ ሐሳብ ማስተላለፍ ትችሉ ይሆናል። አዎን፣ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ይሖዋ ሕዝቡን የታደገው በጥንት ዘመን ብቻ እንዳልሆነ እምነት ሊጥሉ ይገባል። ይሖዋ፣ በሙሴ ዘመን ሕዝቡን እንደታደገው ሁሉ ወደፊትም ይታደገናል። 1 ተሰሎንቄ 1:9, 10ን አንብብ።

ልናስታውሰው የሚገባ ነገር

17, 18. በመጀመሪያው ፋሲካ ላይ ደም ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ ምን ነገር ያስታውሰናል?

17 እውነተኛ ክርስቲያኖች የአይሁዳውያንን ፋሲካ አያከብሩም። ይህ ዓመታዊ በዓል እንዲከበር የሚያዝዘው የሙሴ ሕግ ነው፤ እኛ ደግሞ በዚህ ሕግ ሥር አይደለንም። (ሮም 10:4፤ ቆላ. 2:13-16) ከዚህ ይልቅ የምናከብረው የአምላክን ልጅ ሞት መታሰቢያ ነው። ያም ቢሆን በግብጽ የተቋቋመው ፋሲካ ላይ ይከናወኑ የነበሩ አንዳንድ ነገሮች ለእኛም ትርጉም አላቸው።

18 በበሩ መቃኖችና በጉበኑ ላይ የሚረጨው የበጉ ደም ሕይወት ያድን ነበር። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ በፋሲካ ዕለትም ሆነ በሌላ ወቅት ለአምላክ የእንስሳ መሥዋዕት አናቀርብም። ይሁን እንጂ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ የሚችል የተሻለ መሥዋዕት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሰማያት ስለተመዘገበው የበኩራት ጉባኤ’ ጽፎ ነበር። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሕይወት ማግኘት የሚችሉት ‘በተረጨው የኢየሱስ ደም’ አማካኝነት ነው። (ዕብ. 12:23, 24) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ሕይወት የሚያገኙት በዚሁ ደም አማካኝነት ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች የሚከተለውን ሐሳብ ዘወትር ማስታወስ አለባቸው፦ “በአምላክ የተትረፈረፈ ጸጋ መሠረት ልጁ ቤዛውን በመክፈል በደሙ አማካኝነት ነፃ እንድንወጣ ማለትም ለበደላችን ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።”—ኤፌ. 1:7

19. ከኢየሱስ አሟሟት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ነገር በትንቢቶች ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?

19 እስራኤላውያን፣ ፋሲካን ሲያከብሩ በጉን ካረዱ በኋላ አንዱንም አጥንት እንዳይሰብሩ ታዝዘዋል። (ዘፀ. 12:46፤ ዘኍ. 9:11, 12) ታዲያ ቤዛውን ለመክፈል ስለመጣው “የአምላክ በግ” ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐ. 1:29) ኢየሱስ የተሰቀለው በሁለት ወንጀለኞች መካከል ነበር። አይሁዳውያን፣ የተሰቀሉት ሰዎች አጥንት እንዲሰበር ጲላጦስን ጠየቁ። አጥንታቸው መሰበሩ ቶሎ እንዲሞቱ ያደርጋል፤ አይሁዳውያን ይህን ያደረጉት ድርብ ሰንበት በሆነው በኒሳን 15 ዕለት ሰዎቹ በእንጨት ላይ ተሰቅለው እንዲውሉ ስላልፈለጉ ነው። በመሆኑም ወታደሮቹ የሁለቱን ወንጀለኞች እግር ሰበሩ፤ “ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ቀደም ብሎ መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም።” (ዮሐ. 19:31-34) ይህም ከፋሲካ በግ ጋር በተያያዘ ከተሰጠው መመሪያ ጋር ይስማማል፤ ከዚህ አንጻር በጉ፣ ኒሳን 14 ቀን 33 ዓ.ም. ለሆነው ነገር “ጥላ” ሆኗል ሊባል ይችላል። (ዕብ. 10:1) ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ የተከናወኑት ነገሮች መዝሙር 34:20 ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጋቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ያለንን እምነት ሊያጠናክርልን ይገባል።

20. በፋሲካና በጌታ ራት መካከል ምን ጉልህ ልዩነት አለ?

20 ይሁን እንጂ በፋሲካ እና በጌታ ራት መካከል ልዩነቶች አሉ። አይሁዳውያን ፋሲካን የሚያከብሩበት መንገድ ክርስቶስ ተከታዮቹ የሞቱን መታሰቢያ ሲያከብሩ እንዲያደርጉ ካዘዛቸው ነገር ጋር አንድ ዓይነት አይደለም። በግብፅ የነበሩት የጥንቶቹ እስራኤላውያን ፋሲካን ሲያከብሩ የበጉን ሥጋ የበሉ ቢሆንም ደሙን ግን አልጠጡም። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ካዘዛቸው ነገር ጋር ልዩነት አለው። “በአምላክ መንግሥት” ገዢ የሚሆኑት በሙሉ፣ የኢየሱስን ሥጋና ደም ከሚወክሉት ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል እንዳለባቸው ኢየሱስ ተናግሯል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት እንመረምራለን።—ማር. 14:22-25

21. ስለ ፋሲካ ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

21 ያም ቢሆን ፋሲካ፣ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክንውን ሲሆን ለእያንዳንዳችን የሚሆን ጠቃሚ ትምህርቶችንም እንደያዘ ጥርጥር የለውም። ፋሲካ ክርስቲያኖች ሳይሆን አይሁዳውያን የሚያከብሩት ‘የመታሰቢያ’ በዓል ነው፤ ያም ቢሆን ስለ በዓሉ የሚናገረው ዘገባ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት’ ክፍል እንደመሆኑ መጠን እኛ ክርስቲያኖች ስለ በዓሉ ማወቅና ከበዓሉ የምናገኛቸውን ግልጽ የሆኑ ትምህርቶች ማስተዋል ይኖርብናል።—2 ጢሞ. 3:16

^ አን.5 ይህ ወር ኒሳን ተብሎ የተጠራው አይሁዳውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ቢሆንም ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል የአይሁዳውያንን የመጀመሪያ ወር የምንጠራው ኒሳን ብለን ነው።

^ አን.11 ኒሳን 15 የጀመረው ፀሐይ ስትጠልቅ ነው፤ በመሆኑም ሳምንታዊው ሰንበት (ቅዳሜ) እንዲሁም ሁልጊዜም እንደ ሰንበት የሚከበረው ያልቦካ ቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን አንድ ላይ ተገጣጠሙ ማለት ነው። እነዚህ ሁለት ሰንበቶች በአንድ ቀን ላይ በመዋላቸው ኒሳን 15 “ታላቅ ሰንበት” ሊባል ችሏል።ዮሐንስ 19:31, 42ን አንብብ።