በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2013

“የማመዛዘን ችሎታችሁ በቶሎ አይናወጥ”!

“የማመዛዘን ችሎታችሁ በቶሎ አይናወጥ”!

“ወንድሞች፣ . . . የማመዛዘን ችሎታችሁ በቶሎ አይናወጥ።”—2 ተሰ. 2:1, 2

1, 2. በዛሬው ጊዜ ማታለል የተለመደ ነገር የሆነው ለምንድን ነው? የማታለያ ሐሳቦች የሚሰራጩት በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ማታለልና ማጭበርበር በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ይህም ሊያስገርመን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ የተዋጣለት አታላይ እንደሆነና ይህን ዓለም የሚገዛውም እሱ መሆኑን በግልጽ ይናገራል። (1 ጢሞ. 2:14፤ 1 ዮሐ. 5:19) ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ በሄደ መጠን ሰይጣን የቀረው “ጥቂት ጊዜ” ብቻ እንደሆነ ስለሚገነዘብ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በቁጣ እየተሞላ ነው። (ራእይ 12:12) በመሆኑም በዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር ያሉት ሰዎች ይበልጥ አታላዮች እየሆኑ እንደሚሄዱ የሚጠበቅ ነው፤ በተለይ ደግሞ ንጹሑን አምልኮ የሚያራምዱትን ለማታለል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም።

2 አንዳንድ ጊዜ ስለ ይሖዋ አገልጋዮች እንዲሁም ስለሚያምኑባቸው ነገሮች የሚገልጹ አሳሳች ዘገባዎችና ዓይን ያወጡ ውሸቶች በመገናኛ ብዙኃን ይሰራጫሉ። በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ጥናታዊ ፊልሞችና በጋዜጦች እንዲሁም በኢንተርኔት ድረ ገጾች አማካኝነት ከእውነት የራቁ ወሬዎች ይናፈሳሉ። አንዳንዶች እነዚህን ውሸቶች አምነው ስለሚቀበሉ የይሖዋ አገልጋዮችን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት ሊያድርባቸው አልፎ ተርፎም ሊበሳጩ ይችላሉ።

3. በሰይጣን የማታለያ ዘዴ እንዳንሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?

3 ጠላታችን በሚጠቀምበት በዚህ ቅስም የሚሰብር ዘዴ እንዳንሸነፍ የሚረዳን መከላከያ ይኸውም የአምላክ ቃል ስላለን አመስጋኞች ነን፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ነገሮችን ለማቅናት . . . ይጠቅማል።” (2 ጢሞ. 3:16) ከሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤ መረዳት እንደምንችለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተሰሎንቄ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተታልለውና ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ተቀብለው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ “የማመዛዘን ችሎታችሁ በቶሎ አይናወጥ” በማለት መክሯቸዋል። (2 ተሰ. 2:1, 2) ጳውሎስ በፍቅር ተነሳስቶ ከሰጠው ከዚህ ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን? ያገኘነውን ትምህርት በሕይወታችን ውስጥ ልንሠራበት የምንችለውስ እንዴት ነው?

ወቅታዊ ማሳሰቢያዎች

4. የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ስለ ‘ይሖዋ ቀን’ መምጣት ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር? እኛስ ማሳሰቢያ እየተሰጠን ያለው እንዴት ነው?

4 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ  ወንድሞቹ ‘በይሖዋ ቀን’ መምጣት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስቦ ነበር። ወንድሞቹ በጨለማ ውስጥ ሆነው ይኸውም ምንም ሳይዘጋጁ ይህ ቀን እንዲመጣባቸው አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ‘እንደ ብርሃን ልጆች ነቅተው እንዲኖሩ እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲጠብቁ’ አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:1-6ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ፣ የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶችን የምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን የምትጠፋበትን ጊዜ እንጠባበቃለን። ታላቁ የይሖዋ ቀን የሚጀምረው በዚህ ክንውን ነው። ደስ የሚለው ነገር፣ ይሖዋ ዓላማውን ስለሚፈጽምበት መንገድ ያለን ግንዛቤ እያደገ መጥቷል። በተጨማሪም የማመዛዘን ችሎታችንን እንድንጠብቅ የሚረዱ ወቅታዊ ማሳሰቢያዎችን በጉባኤ አማካኝነት በየጊዜው እናገኛለን። በተደጋጋሚ የሚሰጠንን ይህንን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር መመልከታችን ‘የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ’ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—ሮም 12:1

ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ለክርስቲያኖች ወቅታዊ ማሳሰቢያዎችን ይዘዋል (አንቀጽ 4ን እና 5ን ተመልከት)

5, 6. (ሀ) ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ስለ የትኛው ጉዳይ ተናግሯል? (ለ) በቅርቡ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት ምን እርምጃ ይወስዳል? ራሳችንን ምን እያልን መጠየቅ አለብን?

5 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከጻፈ ብዙም ሳይቆይ ሌላ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። በዚህ ደብዳቤው ላይ፣ ጌታ ኢየሱስ ‘አምላክን በማያውቁትና ምሥራቹን በማይታዘዙት’ ላይ መለኮታዊ ፍርድ በሚያስፈጽምበት ወቅት ስለሚመጣው መከራ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (2 ተሰ. 1:6-8) በምዕራፍ 2 ላይ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው አንዳንድ የጉባኤው አባላት የይሖዋን ቀን በተመለከተ ‘በስሜት ስለተወሰዱ’ ይህ ቀን በዚያ ወቅት እንደሚመጣ እስከማመን ደርሰው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:1, 2ን አንብብ።) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የይሖዋ ዓላማ ስለሚፈጸምበት መንገድ ያላቸው ግንዛቤ ውስን ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ስለ ትንቢት የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ይህን የሚያሳይ ነው፦ “ያለን እውቀት ከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው፤ የተሟላው ሲመጣ ግን ከፊል የሆነው ይቀራል።” (1 ቆሮ. 13:9, 10) ጳውሎስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስና በወቅቱ የነበሩ ሌሎች ታማኝ ቅቡዓን ወንድሞች በመንፈስ መሪነት የጻፏቸው ማስጠንቀቂያዎች፣ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲጠብቁ ረድተዋቸዋል።

6 ጳውሎስ፣ የእነዚህን ክርስቲያኖች አመለካከት ለማስተካከል ሲል የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ታላቅ ክህደት እንደሚነሳና “የዓመፅ ሰው” እንደሚገለጥ በመንፈስ መሪነት ጻፈላቸው። * ከዚያም የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ጌታ ኢየሱስ በሰይጣን የተታለሉትን ሁሉ ‘እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል።’ ሐዋርያው  ጳውሎስ፣ እንዲህ ያለ የጥፋት እርምጃ የሚወሰድባቸው “ለእውነት ፍቅር ባለማሳየታቸው” እንደሆነ ገልጿል። (2 ተሰ. 2:3, 8-10) እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ለእውነት ያለኝ ፍቅር ምን ያህል ነው? በዚህ መጽሔትና በሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነት ለዓለም አቀፉ የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ የሚቀርበውን ትምህርት ተከታትዬ በማንበብ ወቅታዊ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረኝ ጥረት አደርጋለሁ?’

ወዳጆቻችሁን በጥበብ ምረጡ

7, 8. (ሀ) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸው ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በተለይ ሊጠነቀቁበት የሚገባው አደጋ የትኛው ነው?

7 እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ከከሃዲዎችና ከእነሱ ትምህርቶች በተጨማሪ ሌሎች አደገኛ ነገሮችም ያጋጥሟቸዋል። ጳውሎስ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር” እንደሆነ ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል። አክሎም “አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ብሏል። (1 ጢሞ. 6:10) ክርስቲያኖች ‘ከሥጋ ሥራዎችም’ ጋር ቢሆን ሁልጊዜ መታገል ያስፈልጋቸው ነበር።—ገላ. 5:19-21

8 ያም ቢሆን ጳውሎስ ከሃዲዎች የሚያስከትሉትን አደጋ በተመለከተ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን አጥብቆ ያሳሰባቸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፤ እነዚህን ከሃዲዎች በሌላ ቦታ ላይ “ሐሰተኛ ሐዋርያት” ብሎ ጠርቷቸዋል። ከተሰሎንቄ ክርስቲያኖች መካከል “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች” ነበሩ። (2 ቆሮ. 11:4, 13፤ ሥራ 20:30) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ፣ የኤፌሶን ጉባኤ አባላት ‘መጥፎ ሰዎችን ባለመታገሣቸው’ አመስግኗቸዋል። የኤፌሶን ክርስቲያኖች እነዚህን መጥፎ ሰዎች ‘ፈትነው’ ሐሰተኛ ሐዋርያት ማለትም ውሸታሞች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። (ራእይ 2:2) ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ የሚከተለውን ማሳሰቢያ መስጠቱ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “ወንድሞች፣ በሥርዓት ከማይሄድ . . . ማንኛውም ወንድም እንድትርቁ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።” አክሎም ‘መሥራት ስለማይፈልጉ’ ክርስቲያኖች ተናገረ። (2 ተሰ. 3:6, 10) መሥራት የማይፈልጉ ሰዎች በሥርዓት እንደማይሄዱ ተቆጥረው ክርስቲያኖች ከእነሱ መራቅ እንዳለባቸው ከተገለጸ የክህደት ጎዳና መከተል ከጀመሩ ሰዎችማ መራቅ እንዳለባቸው ምንም ጥያቄ የለውም! እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት በጣም አደገኛ በመሆኑ በዚያ ወቅት የነበሩት ክርስቲያኖች ሊርቋቸው ይገባ ነበር፤ ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—ምሳሌ 13:20

9. አንድ ሰው ግምታዊ ሐሳብ መሰንዘር ወይም ሌሎችን መንቀፍ ቢጀምር ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

9 የምንኖረው፣ ታላቁ መከራ የሚጀምርበትና ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያበቃበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት በመሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት የተሰጡት እነዚህ ማሳሰቢያዎች ለእኛ ይበልጥ ትርጉም ይኖራቸዋል። ይሖዋ ለእኛ ጸጋ ያሳየበትን ‘ዓላማ መሳት’ ይኸውም በሰማይ ወይም በምድር ያዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማጣት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። (2 ቆሮ. 6:1) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ አንድ ሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ሐሳብ በማይሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ ግምታዊ ሐሳብ እንድንሰነዝር ወይም ሌሎችን እንድንነቅፍ ሊያነሳሳን ቢሞክር ከእንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ መጠንቀቅ እንደሚኖርብን ጥርጥር የለውም።—2 ተሰ. 3:13-15

“የተማራችኋቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ያዙ”

10. በተሰሎንቄ የሚገኙ ክርስቲያኖች በጥብቅ መከተል የነበረባቸው የትኞቹን ወጎች ነው?

10 ጳውሎስ፣ በተሰሎንቄ የሚገኙ ወንድሞቹን ‘ጸንተው እንዲቆሙ’ እንዲሁም የተማሯቸውን ነገሮች አጥብቀው እንዲይዙ አሳስቧቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:15ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች የተማሯቸው “ወጎች” ምንድን ናቸው? የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያስተምሯቸውና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት ትምህርቶች እኩል ጠቃሚ እንደሆኑ አድርገው የሚያስፋፏቸው ትምህርቶች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አምላክ በእሱ በኩል ስላስተላለፋቸው እንዲሁም እሱና ሌሎች ክርስቲያኖች  ከኢየሱስ ስለተቀበሏቸው ትምህርቶች ነበር፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ከጊዜ በኋላ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተካትተዋል። ጳውሎስ፣ በቆሮንቶስ ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞቹን “በሁሉም ነገር ስለምታስቡኝና ለእናንተ ያስተላለፍኳቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ስለያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 11:2) እነዚህ ትምህርቶች፣ እምነት ከሚጣልበት ምንጭ የተገኙ በመሆናቸው ክርስቲያኖች እነዚህን ወጎች የሚጠራጠሩበት ምክንያት አልነበራቸውም።

11. አንዳንዶች በየትኞቹ መንገዶች ሊታለሉ ይችላሉ?

11 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንድ ክርስቲያን እምነቱን ሊያጣና ጸንቶ ላይቆም እንደሚችል ተናግሯል። (ዕብራውያን 2:1ን እና 3:12ን አንብብ።) ጳውሎስ ስለ ‘መራቅ’ ሁለት ጊዜ እንደተናገረ ልብ በል። አንድ ሰው በሁለት የተለያዩ መንገዶች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል። በወንዝ ዳርቻ ላይ ያለ አንድ ጀልባ ማንም ሳይነካው ቀስ በቀስ በውኃው ሊወሰድ እንደሚችል ሁሉ አንድ ክርስቲያንም ሳይታወቀው ቀስ በቀስ ከይሖዋ ሊርቅ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብሎ ጀልባውን ከወንዙ ዳርቻ እንደሚያርቅ ሰው ሁሉ አንድ ክርስቲያንም ከይሖዋ የሚያርቀውን አካሄድ ሆን ብሎ ሊከተል ይችላል። ሁለቱም ሁኔታዎች፣ በእውነት ላይ ያላቸው እምነት እንዲዳከም በመፍቀድ በማታለያ የሚወድቁ ሰዎችን አካሄድ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ።

12. በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊነታችንን ሊያዳክሙ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

12 በተሰሎንቄ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸው ይመስላል። በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል? ጊዜ የሚያባክኑ ነገሮች ብዙ ናቸው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች በመጠቀምና የኤሌክትሮኒክ መልእክቶችን በመለዋወጥ ረጅም ሰዓታት ማሳለፍ፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች መጠመድ ወይም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ዘወትር መከታተል ምን ያህል ጊዜ ሊያባክን እንደሚችል አስቡት። እነዚህ ነገሮች የአንድን ክርስቲያን ትኩረት ሊከፋፍሉና ቅንዓቱ እንዲቀዘቅዝ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ ምን ያስከትልበታል? ልባዊ ጸሎት ማቅረቡን፣ የአምላክን ቃል ማጥናቱን በስብሰባዎች ላይ መገኘቱንና ምሥራቹን መስበኩን ቸል እንዲል ያደርገዋል። ታዲያ በእነዚህ ነገሮች የተነሳ የማመዛዘን ችሎታችን በቶሎ እንዳይናወጥ ምን ሊረዳን ይችላል?

እንዳንናወጥ የሚረዱን ነገሮች

13. በትንቢት በተነገረው መሠረት ብዙዎች ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? እምነታችን እንዳይዳከም ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 እንዳንናወጥ ከሚረዱን ነገሮች መካከል ያለንበትን ጊዜ እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ እንዲሁም የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” መሆኑን ከማይቀበሉ ሰዎች ጋር መቀራረብ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አቅልሎ አለመመልከት ይገኙበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጨረሻውን ዘመን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የራሳቸውን ምኞት እየተከተሉ የሚያፌዙ ፌዘኞች እንደሚመጡ ታውቃላችሁ። እነዚህ ፌዘኞች ‘“እገኛለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል’ ይላሉ።” (2 ጴጥ. 3:3, 4) የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበባችንና አዘውትረን ማጥናታችን የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” መሆኑ ምንጊዜም ከአእምሯችን እንዳይጠፋ ይረዳናል። በትንቢት የተነገረለት ክህደት መታየት ከጀመረ የቆየ ሲሆን ዛሬም አለ። “የዓመፅ ሰው” በአሁኑ ጊዜም ያለ ሲሆን የአምላክን አገልጋዮች መቃወሙን ቀጥሏል። በመሆኑም የይሖዋ ቀን ምን ያህል እንደቀረበ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም።—ሶፎ. 1:7

ጥሩ ዝግጅት ማድረግና በአገልግሎት መካፈል ‘የማመዛዘን ችሎታችን በቶሎ እንዳይናወጥ’ ይረዳናል (አንቀጽ 14ን እና 15ን ተመልከት)

14. በአምላክ አገልግሎት መጠመዳችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

14 አንድ ሰው ምንጊዜም ንቁ እንዲሆንና የማመዛዘን ችሎታው እንዳይናወጥ የሚረዳው ዋነኛው ነገር የመንግሥቱን ምሥራች አዘውትሮ መስበኩ እንደሆነ በተሞክሮ ታይቷል። የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ፣ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን እሱ ያስተማራቸውን ነገሮች እንዲጠብቁ በማስተማር ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ተከታዮቹ ይህን መመሪያ መታዘዛቸው ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) እሱ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም በስብከቱ  ሥራ በቅንዓት መካፈል ይኖርብናል። በተሰሎንቄ የነበሩት ወንድሞቻችን፣ ግዴታ ስለሆነባቸው ብቻ በዘልማድ በመስበክና በማስተማር ይረኩ የነበረ ይመስልሃል? ጳውሎስ “የመንፈስን እሳት አታጥፉ። ትንቢትን አትናቁ” ብሎ እንደጻፈላቸው አስታውስ። (1 ተሰ. 5:19, 20) በዛሬው ጊዜም በጥናታችን ልናካትታቸው እንዲሁም ለሌሎች ልናካፍላቸው የምንችላቸው አስደናቂ ትንቢቶች አሉ!

15. በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ምን ነገሮችን ማካተታችን ጠቃሚ ነው?

15 የቤተሰባችን አባላት የአገልግሎት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ብዙ ወንድሞችና እህቶች በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት የተወሰነውን ጊዜ ለአገልግሎት ለመዘጋጀት ይጠቀሙበታል። የቤተሰባችሁ አባላት፣ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰው ለመጠየቅ ሲሄዱ ምን ማድረግ እንደሚችሉ መወያየታችሁ ጠቃሚ ነው። ሰዎቹን በቀጣዩ ጊዜ ሲያገኟቸው ምን ይሏቸዋል? የሰዎቹን ትኩረት ይበልጥ የሚስቡት የትኞቹ ርዕሶች ናቸው? ሰዎቹን ለማነጋገር የተሻለ የሚሆነው ጊዜ መቼ ነው? በርካታ ወንድሞች ደግሞ በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት የተወሰነውን ጊዜ ለጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ያውሉታል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ለመዘጋጀት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ትችሉ ይሆን? ተሳትፎ ማድረጋችሁ እምነታችሁን የሚያጠናክርላችሁ ሲሆን ይህም የማመዛዘን ችሎታችሁ እንዳይናወጥ ጥበቃ ይሆንላችኋል። (መዝ. 35:18) በእርግጥም የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ ግምታዊ ሐሳብ የመሰንዘር ልማድ እንዳይኖረን እንዲሁም ጥርጣሬ እንዳይፈጠርብን ይረዳናል።

16. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የማሰብ ችሎታቸውን እንዲጠብቁ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?

16 ይሖዋ ባለፉት ዓመታት ሕዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ይበልጥ መረዳት እንዲችሉ በማድረግ ባርኳቸዋል፤ ይህም ወደፊት አስደናቂ ሽልማት እንደሚሰጠን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመሆን ተስፋ አላቸው። ይህ የማሰብ ችሎታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያነሳሳቸው ምንም ጥርጥር የለውም! ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የጻፈው የሚከተለው ሐሳብ ለእነሱም ይሠራል፦ “በይሖዋ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ እናንተን በመንፈስ በመቀደስ እንዲሁም በእውነት ላይ ባላችሁ እምነት አማካኝነት . . . ስለመረጣችሁ አምላክን ስለ እናንተ ሁልጊዜ ለማመስገን እንገፋፋለን።”—2 ተሰ. 2:13

17. በ2 ተሰሎንቄ 3:1-5 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምን ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ?

17 በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ ክርስቲያኖችም የማመዛዘን ችሎታቸው በቶሎ እንዳይናወጥ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። አንተም በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያለህ ክርስቲያን ከሆንህ ጳውሎስ፣ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ቅቡዓን ባልንጀሮቹ ለጻፈው ፍቅራዊ ማበረታቻ ትኩረት ስጥ። (2 ተሰሎንቄ 3:1-5ን አንብብ።) ፍቅር ለሚንጸባረቅበት ለዚህ ሐሳብ ሁላችንም አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። በእርግጥም ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የተጻፉት ደብዳቤዎች፣ ግምታዊ ሐሳቦችን ወይም ጥርጣሬ እንዲፈጠር የሚያደርጉ አመለካከቶችን በተመለከተ ጠቃሚ ማሳሰቢያ ይዘዋል። በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች የምንኖረው ይህ ሥርዓት ሊጠፋ በጣም በተቃረበበት ጊዜ ላይ በመሆኑ እነዚህን ማሳሰቢያዎች በቁም ነገር ልንመለከታቸው ይገባል።

^ አን.6 በሐዋርያት ሥራ 20:29, 30 ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከክርስቲያን ጉባኤ መካከል “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች” እንደሚነሱ ተናግሯል። ቀስ በቀስ በክርስቲያኖች መካከል ቀሳውስትና ምዕመናን የሚል ልዩነት እንደተፈጠረ ታሪክ ያረጋግጣል። በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. “የዓመፅ ሰው” ተገለጠ፤ ይህ “የዓመፅ ሰው” የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትን በቡድን ደረጃ ያመለክታል።—የየካቲት 1, 1990 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 10-14 (መ.ግ. 3-111 ከገጽ 10-14) ተመልከት።