በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ከታሪክ ማኅደራችን

“ቤቴ ምንጊዜም ከእኔ ጋር ነበር”

“ቤቴ ምንጊዜም ከእኔ ጋር ነበር”

በ1929 ነሐሴ/መስከረም ወር ላይ በተካሄደው የዘጠኝ ቀን የስብከት ዘመቻ ከ10,000 በላይ የሚሆኑ ሰባኪዎች መላዋን ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ጎርፍ አጥለቅልቀዋት ነበር። በዚህ ጊዜ ሩብ ሚሊዮን መጻሕፍትንና ቡክሌቶችን ማበርከት ችለዋል። ከእነዚህ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች መካከል አንድ ሺህ ገደማ የሚሆኑት ኮልፖርተሮች ነበሩ። ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት አድጎ ነበር! ቡለቲን * የተሰኘው ጽሑፍ የአቅኚዎች ቁጥር ከ1927 እስከ 1929 ባለው ጊዜ ውስጥ ሦስት እጥፍ ማደጉ “ለማመን የሚያዳግት” እንደነበር ገልጿል።

በ1929 መገባደጃ ላይ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከስቶ ነበር። ጥቅምት 29, 1929 ጨለማ ባጠላበት ማክሰኞ ቀን በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ የተከሰተው የዋጋ ማሽቆልቆል በዓለም አቀፍ ደረጃ አስደንጋጭ የሆነ ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት አስከትሏል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ባንኮች ከሰሩ። የግብርና ሥራ ቆመ። ትላልቅ ፋብሪካዎች ተዘጉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥራ ተባረሩ። በ1933 በዩናይትድ ስቴትስ በብድር ከተገዙ ቤቶች ውስጥ በየቀኑ በአበዳሪዎች የሚወረሱት ቤቶች ቁጥር 1,000 ደርሶ ነበር።

ታዲያ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች እንዲህ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተቋቁመው መኖር የቻሉት እንዴት ነው? ችግሩን ለመቋቋም የተጠቀሙበት አንዱ ዘዴ በተሽከርካሪ ቤት መኖር ነበር። ተሽከርካሪ ቤት ወይም ተጎታች ቤት ከኪራይም ሆነ ከቀረጥ ነፃ ስለነበረ ብዙ አቅኚዎች እጅግ አነስተኛ በሆነ ወጪ የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል። * በትላልቅ ስብሰባዎች ወቅት ደግሞ ተንቀሳቃሽ ቤት ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሆቴል መኝታ ክፍል ሆኖ አገልግሏል። በ1934 የወጣው ቡለቲን ውኃ፣ ምድጃ፣ ታጣፊ አልጋ፣ ለቅዝቃዜ ወቅት የሚያገለግል ማሞቂያና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ያሉት አነስተኛ ሆኖም ምቾት ያለው መኖሪያ እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል የሚያብራራ ዝርዝር መግለጫ ይዞ ነበር።

በዓለም ዙሪያ የነበሩ ብልሃተኛ የሆኑ ሰባኪዎች ተሽከርካሪ ቤቶችን መሥራቱን ተያይዘውት ነበር። ቪክቶር ብላክዌል “ኖኅ መርከብ የመሥራት ልምድ አልነበረውም፤ እኔም ብሆን ተጎታች ቤት የመሥራት ልምድም ሆነ እውቀት አልነበረኝም” ሲል ተናግሯል። ይሁንና ቪክቶር ቤቱን መሥራት ችሏል።

በሕንድ ኃይለኛ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ለመኖሪያነት የሚያገለግልን አንድ መኪና ጀልባ ላይ ጭነው ሲያሻግሩ

ኤቨሪ እና ሎቪንያ ብሪስቶ የተባሉ ባልና ሚስት ተሽከርካሪ ቤት ነበራቸው። ኤቨሪ “ከጠንካራ ቅርፊት የተሠራውን ሽፋኗን ተሸክማ እንደምትዞር ኤሊ ነበርኩ፤ ቤቴ ምንጊዜም ከእኔ ጋር ነበር” ብሏል። ኤቨሪ እና ሎቪንያ ከሃርቪ እና ከአን ኮንሮው ጋር ሆነው በአቅኚነት ያገለግሉ የነበረ ሲሆን የነሃርቪ ተንቀሳቃሽ ቤት ግድግዳው በቅጥራን በተሠራ ወረቀት ተሸፍኖ ነበር። ቤታቸውን ባንቀሳቀሱ ቁጥር ወረቀቱ እየተቆራረጠ ይወድቅ ነበር። ኤቨሪ “ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ እንደዚህ ያለ ተጎታች ቤት ታይቶ አያውቅም!” በማለት ተናግሯል። ይሁንና ሃርቪ እና ባለቤቱ እንዲሁም ሁለት ወንዶች ልጆቻቸው “እጅግ ደስተኞች ነበሩ” ሲል አክሎ ገልጿል። ሃርቪ ኮንሮው “አንዳች ነገር ጎድሎን አያውቅም፤ ደግሞም ይሖዋን ማገልገላችንና የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ ማግኘታችን የደህንነት ስሜት እንዲሰማን አድርጎናል” በማለት ጽፏል። ከጊዜ በኋላ ሃርቪ እና አን እንዲሁም ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው በጊልያድ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ሲሆን ሚስዮናውያን ሆነው በፔሩ አገልግለዋል።

የባታይኖ ቤተሰብም በአቅኚነት ያገለግሉ ነበር። ጁስቶ እና ቪንቼንሳ ልጅ ሊወልዱ መሆናቸውን ሲገነዘቡ የ1929 ሞዴል የሆነን ፎርድ የጭነት መኪና ወደ መኖሪያነት ለወጡ፤ ይህ ቤት ከዚያ በፊት ይኖሩባቸው ከነበሩ ድንኳኖች ጋር ሲወዳደር “ምርጥ  ሆቴል ያረፉ ያህል” ሆኖላቸው ነበር። ከትንሿ ሴት ልጃቸው ጋር ሆነው በሚወዱት የሥራ ምድብ ማገልገላቸውን የቀጠሉ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ ጣሊያናውያን ይሰብኩ ነበር።

በርካታ ሰዎች ለምሥራቹ ጆሯቸውን የሰጡ ቢሆንም ድሃና ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የገንዘብ መዋጮ ማድረግ የሚችሉት ከስንት አንዴ ነበር። በመሆኑም የተለያዩ ሸቀጦችን በመስጠት ጽሑፎችን ይወስዱ ነበር። ሁለት አቅኚዎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሰጧቸውን 64 ዓይነት ነገሮች በዝርዝር መዝግበዋል። የመዘገቡት ዝርዝር ሲታይ “የአንድ ሱቅ ዕቃ ዝርዝር ይመስል ነበር።”

ፍሬድ አንደርሰን ሲያገለግል አንድ ገበሬ አግኝቶ የነበረ ሲሆን ገበሬው መጽሐፎቻችንን መውሰድ ስለፈለገ የእናቱን መነጽር መዋጮ አድርጎ ሰጠ። በዚያው አካባቢ ባለ አንድ እርሻ ላይ ያገኘው ሰው ደግሞ ጽሑፎቻችንን መውሰድ ቢፈልግም “የማነብበት መነጽር የለኝም” ሲል ገለጸለት። ይሁንና የጎረቤቱን መነጽር ሲያደርግ መጽሐፎቹን በሚገባ ማንበብ የቻለ ሲሆን ለመጽሐፎቹና ለመነጽሩም መዋጮ አድርጓል።

ኸርበርት አቦት በመኪናው ውስጥ ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤት ይዞ ይጓዝ ነበር። ጽሑፍ ሲያበረክት ሰዎች በመዋጮ መልክ የሚሰጡትን ሦስት ወይም አራት ዶሮዎች ወደ ገበያ ወስዶ ይሸጣቸውና ነዳጅ ይቀዳል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ገንዘብ ጨርሰን የተቸገርንበት ጊዜ ነበር? አዎ፣ የተቸገርንባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ይህ አገልግሎታችንን እንድናቆም አላደረገንም። የመኪናችን ነዳጅ እስካላለቀ ድረስ እምነታችንንና ትምክህታችንን በይሖዋ ላይ ጥለን አገልግሎታችንን እንቀጥል ነበር።”

የይሖዋ ሕዝቦች እነዚያን አስቸጋሪ ጊዜያት ተቋቁመው መኖር የቻሉት በይሖዋ ስለተማመኑና ቆራጥ አቋም ስለነበራቸው ነው። ማክስዌል እና ኤሚ ሉዊስ የተባሉ ባልና ሚስት በአንድ ወቅት ዶፍ ዝናብ ሲዘንብ ይኖሩበት ከነበረው ተጎታች ቤት ውስጥ በፍጥነት ወጥተው የሸሹ ሲሆን እነሱ እንደወጡ ቤታቸው ዛፍ ወድቆበት ለሁለት ተገመሰ። ማክስዌል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነዚህ ነገሮች እንቅፋት አልሆኑብንም፤ በአጋጣሚ የተከሰቱ ነገሮች ስለነበሩ አገልግሎታችንን የማቋረጥ ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሯችን አልመጣም። መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ ነበር፤ የእኛም ሐሳብ ይህን ማከናወን ነበር።” ማክስዌል እና ኤሚ በገጠማቸው ሁኔታ ሳይሸበሩ በወዳጆቻቸው እርዳታ ተሽከርካሪ ቤታቸውን መልሰው ሠሩ።

ተፈታታኝ ችግሮች ባሉበት በዚህ ዘመንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ የሆነ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያሳያሉ። ደግሞም ይሖዋ በቃ እስኪል ድረስ ከላይ እንደተጠቀሱት የቀድሞ ዘመን አቅኚዎች በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል ቆርጠናል።

^ አን.3 በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት አገልግሎታችን ተብሎ ይጠራል።

^ አን.5 በዚያን ጊዜ አብዛኞቹ አቅኚዎች ሰብዓዊ ሥራ አይሠሩም ነበር። ከዚህ ይልቅ በቅናሽ ዋጋ የወሰዷቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሲያበረክቱ የሚያገኙትን መዋጮ አነስተኛ የሆነውን የኑሮ ወጪያቸውን ለመሸፈን ይጠቀሙበት ነበር።