“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ክብር . . . ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11

1. እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ብዙዎች ‘ማየት ማመን ነው’ ሲሉ ይሰማል፤ በሌላ አባባል በዓይናቸው ያላዩትን ነገር ማመን እንደማይችሉ መግለጻቸው ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች በይሖዋ እንዲያምኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱም “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” ይላል። (ዮሐ. 1:18) ታዲያ እኛ ራሳችንስ “የማይታየው አምላክ” በተባለው በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ቆላ. 1:15) የመጀመሪያው እርምጃ ስለ ይሖዋ እውነቱ እንዳይታወቅ እንቅፋት የሚሆኑ ትምህርቶችን ለይቶ ማወቅ ነው። ከዚያም “የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችን” ለማፍረስ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መጠቀም አለብን።—2 ቆሮ. 10:4, 5

2, 3. ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ እንቅፋት የሚሆኑ ሁለት ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

2 ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን እንዳያውቁ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ የሐሰት ትምህርቶች አንዱ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ነው። በሰብዓዊ ጥበብ ላይ የተመሠረተው ይህ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች ተስፋ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። የዚህ ትምህርት መሠረታዊ ሐሳብ፣ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ወደ ሕልውና የመጣው በአጋጣሚ እንደሆነ ይገልጻል፤ ከዚህ አንጻር የሰው ልጆች ሕይወት ዓላማ አይኖረውም።

3 በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የሃይማኖት ሰዎች ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉንም ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ አጽናፈ ዓለም የተፈጠረው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነ ያስተምራሉ። ክሪኤሽኒዝም በመባል የሚታወቀውን ይህን መሠረተ ትምህርት የሚያራምዱ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ይኖራቸው ይሆናል፤ ሆኖም አምላክ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነና ይህንንም ያደረገው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነ ይገልጻሉ። እነዚህ ሰዎች ከእነሱ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አሳማኝ የሆነ ሳይንሳዊ ማስረጃን ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም። በመሆኑም ይህ መሠረተ ትምህርት፣ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲያጡ ያደርጋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ ከሆኑ ማስረጃዎች ጋር የሚጋጭና የተሳሳተ መረጃ የያዘ መጽሐፍ ያስመስለዋል። የክሪኤሽኒዝም ደጋፊዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩ አንዳንድ ሰዎች ናቸው፤ እነዚያ ሰዎች ለአምላክ ቅንዓት ቢኖራቸውም ቅንዓታቸው “በትክክለኛ  እውቀት ላይ የተመሠረተ” አልነበረም። (ሮም 10:2) ታዲያ እንደ ዝግመተ ለውጥ እና ክሪኤሽኒዝም ያሉትን እንደ “ምሽግ” ያሉ ትምህርቶች በአምላክ ቃል ተጠቅመን መደርመስ የምንችለው እንዴት ነው? * ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት በግለሰብ ደረጃ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው።

ማስረጃውን በመመርመርና የማሰብ ችሎታን በመጠቀም እምነት ማዳበር

4. እምነታችን በምን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል?

4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውቀትን እንደ ውድ ነገር አድርገን እንድንመለከት ያበረታታናል። (ምሳሌ 10:14) ይሖዋ፣ በሰብዓዊ ፍልስፍና ወይም በሃይማኖታዊ ወጎች ላይ ተመሥርተን ሳይሆን ማስረጃውን በመመርመርና የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም በእሱ ላይ እምነት እንድናዳብር ይፈልጋል። (ዕብራውያን 11:1ን አንብብ።) በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን በመጀመሪያ ይሖዋ መኖሩን ማመን ይኖርብናል። (ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።) አምላክ እንዳለ የምናምነው ማስረጃውን ስለመረመርንና ‘የማሰብ ችሎታችንን’ ስለተጠቀምን እንጂ እንዲሁ በሆነ ነገር ማመን ስለፈለግን አይደለም።—ሮም 12:1

5. አምላክ መኖሩን እንድናምን የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክን ባናየውም እንኳ መኖሩን እንድናምን የሚያደርገንን አንዱን ምክንያት ጠቅሷል። ጳውሎስ ይሖዋን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) ይህ ሐሳብ ትክክል መሆኑን፣ አምላክ መኖሩን ለሚጠራጠር ሰው ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን የፈጣሪያችንን ኃይልና ጥበብ የሚያሳዩ የፍጥረት ሥራዎች እንደ ማስረጃ መጥቀስ እንችላለን።

በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀው የአምላክ ኃይል

6, 7. ለምድር ጋሻ ሆነው የሚያገለግሉት ሁለት ከለላዎች የይሖዋን ኃይል የሚገልጡት እንዴት ነው?

6 የይሖዋ ኃይል ከተገለጠባቸው ነገሮች መካከል ጉዳት እንዳይደርስብን እንደ ጋሻ ሆነው የሚጋርዱን ሁለት ከለላዎች ይገኙበታል፤ እነሱም የምድር ከባቢ አየር እና የምድር መግነጢሳዊ መስክ ናቸው። ከባቢ አየርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ከባቢ አየር፣ የምንተነፍሰው አየር እንድናገኝ ከማድረግ የበለጠ ጥቅም አለው። በጠፈር ውስጥ ያሉ ነገሮች በምድር ላይ የሚያደርሱትን አብዛኛውን ውርጅብኝ ይከላከልልናል። ከፍተኛ ውድመት ሊያስከትሉ የሚችሉ ትላልቅ የድንጋይ ስብርባሪዎች ወደ ምድር ከባቢ አየር ሲደርሱ ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ በዚህ ጊዜ በምሽት ሰማይ ላይ የሚታይ ውብ የሆነ ደማቅ ብርሃን ይፈጥራሉ።

7 የምድር መግነጢሳዊ መስክም ጉዳት እንዳይደርስብን ይከላከልልናል። ይህ መከላከያ የሚመነጨው ከምድር እምብርት ነው። የምድር መካከለኛ ክፍል የቀለጠ ብረት ይዟል፤ ይህም በፕላኔታችን ዙሪያ የሚገኝና ከፍተኛ ኃይል ያለው እንዲሁም እስከ ጠፈር የተዘረጋ መግነጢሳዊ መስክ ይፈጥራል። ይህ መግነጢሳዊ መስክ የፀሐይ ወላፈኖችና (ሶላር ፍሌር) በፀሐይ ውጨኛ ክፍል ላይ የሚፈጠሩ ፍንዳታዎች የሚያስከትሏቸው ጨረሮች ጉዳት እንዳያደርሱብን ይከላከልልናል። በመሆኑም ከፍተኛ ኃይል ያላቸው እነዚህ ጨረሮች በምድር ላይ ያለውን ሕይወት አቃጥለው አያጠፉትም። ከዚህ ይልቅ የምድር መግነጢሳዊ መስክ ላይ ነጥረው ይመለሳሉ፤ አሊያም ይህ መግነጢሳዊ መስክ ውጦ ያስቀራቸዋል። በሰሜንና በደቡብ ዋልታዎች አካባቢ ሰማይ ላይ በቀለማት ያሸበረቀ ደማቅ ብርሃን (አውሮራ) የሚታየው በዚህ የተነሳ ነው። በእርግጥም ይሖዋ ‘ኃይሉ ታላቅ ነው።’—ኢሳይያስ 40:26ን አንብብ።

በፍጥረት ላይ የሚታየው የአምላክ ጥበብ

8, 9. ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑት የተፈጥሮ ዑደቶች የይሖዋን ጥበብ የሚገልጡት እንዴት ነው?

8 በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር አስፈላጊ የሆኑት የተፈጥሮ ዑደቶች የይሖዋን ጥበብ ይገልጣሉ። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ዙሪያዋን በቅጥር በተከበበችና በሕዝብ በተጨናነቀች አንዲት ከተማ ውስጥ እንደምንኖር እናስብ። ይህች ከተማ ንጹሕ ውኃ ለማግኘትና ቆሻሻ ለማስወገድ የሚያስችል መንገድ ባይኖራት በቆሻሻ መዋጧና ለመኖሪያ የማትሆን ቦታ መሆኗ አይቀርም። በአንዳንድ መንገዶች ምድራችንም በቅጥር ከተከበበች ከተማ ጋር ትመሳሰላለች። በምድር ላይ ያለው ንጹሕ ውኃ የተወሰነ ነው፤ እንዲሁም ቆሻሻ ነገሮችን ወደ ሕዋ መጣል አንችልም። ያም ቢሆን በቅጥር እንደተከበበች ከተማ በሆነችው ምድራችን ላይ በቢሊዮን  የሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት ለበርካታ ዘመናት መኖር ችለዋል። እንዴት? ምድራችን፣ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ አስደናቂ ችሎታ ስላላት ነው።

9 የኦክስጅን ዑደትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በቢሊዮን የሚቆጠሩ ፍጥረታት ኦክስጅንን ወደ ሰውነታቸው አስገብተው ካርቦን ዳይኦክሳይድን ያስወጣሉ። ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ የኦክስጅን እጥረት አላጋጠመም፤ ከባቢ አየርም ቢሆን እነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት በሚያስወግዱት የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ ተጥለቅልቆ አያውቅም። ለምን? ፎቶሲንተሲስ የሚባል አስደናቂ ሂደት ስላለ ነው። ይህ ሂደት ዕፅዋት ካርቦን ዳይኦክሳይድን፣ ውኃን፣ የፀሐይ ብርሃንን እንዲሁም የተለያዩ ማዕድናትን በመጠቀም ካርቦሃይድሬትና ኦክስጅን ለማምረት ያስችላቸዋል። እኛ ኦክስጅኑን ወደ ሰውነታችን ስናስገባ ዑደቱ ዙሩን ይጨርሳል። ይሖዋ “ሕይወትንና እስትንፋስን . . . ለሰው ሁሉ” ለመስጠት ቃል በቃል በዕፅዋት ይጠቀማል ሊባል ይችላል። (ሥራ 17:25) በእርግጥም ይሖዋ በጥበቡ ተወዳዳሪ የለውም!

10, 11. ሞናርክ የተባለው ቢራቢሮና የውኃ ተርብ የይሖዋን ጥበብ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

10 አስደናቂ በሆነችው ፕላኔታችን ላይ የሚኖሩ በርካታ ሕያዋን ፍጥረታትም የይሖዋን ጥበብ ይገልጣሉ። በምድር ላይ ከ2 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን የሚደርሱ ዝርያዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። (መዝሙር 104:24ን አንብብ።) እስቲ ከእነዚህ ፍጥረታት በአንዳንዶቹ ንድፍ ላይ የሚታየውን የአምላክ ጥበብ እንመልከት።

የውኃ ተርብ ዓይን ንድፍ የአምላክን ጥበብ ይገልጣል የውስጠኛው ምስል፦ ዓይኑ በአጉሊ መነጽር ሲታይ (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11 ለምሳሌ ያህል፣ ሞናርክ የተባለው ቢራቢሮ አንጎሉ ከጤፍ አይበልጥም። ያም ቢሆን ይህ ቢራቢሮ ከካናዳ ተነስቶ ሜክሲኮ ወደሚገኝ ደን ለመድረስ 3,000 ኪሎ ሜትር ገደማ የመጓዝ ችሎታ አለው፤ ይህ ቢራቢሮ በሚጓዝበት ወቅት አቅጣጫውን የሚያውቀው ፀሐይዋ ያለችበትን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ነው። ታዲያ የፀሐይዋ አቅጣጫ በሚቀየርበት ወቅት ይህ ቢራቢሮ አቅጣጫውን የሚያውቀው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ ቅንጣት የሚያህለውን የዚህን ቢራቢሮ አንጎል የፈጠረው በፀሐይ አቅጣጫ ላይ ያለውን ለውጥ ግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንዲችል አድርጎ ነው። እስቲ አሁን ደግሞ የውኃ ተርብ የተባለውን ነፍሳት ዓይን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የዚህ ነፍሳት ሁለት ዓይኖች የተሠሩበት መንገድ አስደናቂ ነው። በአንዱ ዓይኑ ላይ ብቻ 30,000 የሚያህሉ ሌንሶች አሉት። ያም ቢሆን በጣም ትንሽ የሆነው የዚህ ተርብ አንጎል እነዚህ ሁሉ ሌንሶች የሚያስተላልፉትን መልእክት ማስተናገድና በአካባቢው የሚደረገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መለየት ይችላል።

12, 13. ይሖዋ፣ ሰውነታችን የተገነባባቸውን ሴሎች ከሠራበት መንገድ ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስደንቅህ ምንድን ነው?

12 ከዚህ ሁሉ ይበልጥ የሚያስደንቀው ግን ይሖዋ፣ ሕያዋን ፍጡራን በሙሉ የተገነቡባቸውን ሴሎች የሠራበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የሰው ልጆች አካል 100 ትሪሊዮን በሚያህሉ ሴሎች የተገነባ ነው። በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) የተባለ ገመድ የሚመስል ረቂቅ ነገር አለ። ዲ ኤን ኤ አጠቃላይ ሰውነታችን በምን መንገድ እንደሚዋቀር የሚገልጸውን አብዛኛውን መመሪያ ይዟል።

13 ዲ ኤን ኤ ምን ያህል መረጃ መያዝ ይችላል? አንድ ግራም ዲ ኤን ኤ የሚይዘውን መረጃ አንድ ሲዲ ከሚይዘው መረጃ ጋር እስቲ እናወዳድር። አንድ ሲዲ በአንድ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያሉ መረጃዎችን  በሙሉ መያዝ ይችላል፤ ሲዲው ምን ያህል ስስ እንደሆነ ስናስብ ይህን ሁሉ መረጃ መያዝ መቻሉ አስደናቂ ነው። ይበልጥ የሚገርመው ግን አንድ ግራም ዲ ኤን ኤ አንድ ትሪሊዮን ሲዲዎች የሚይዙትን ያህል መረጃ መያዝ መቻሉ ነው! በሌላ አባባል፣ አንድ የሻይ ማንኪያ ዲ ኤን ኤ በዛሬው ጊዜ በሕይወት ያሉትን ሰባት ቢሊዮን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የዚህን ቁጥር 350 እጥፍ የሚያህሉ ሰዎችን ለመሥራት የሚያስችል መረጃ የመያዝ አቅም አለው!

14. የሳይንስ ሊቃውንት ያገኟቸውን መረጃዎች መመርመርህ ስለ ይሖዋ ምን ዓይነት ስሜት እንዲያድርብህ ያደርጋል?

14 ንጉሥ ዳዊት የሰው ልጆችን አካል ለመሥራት የሚያስፈልገውን መረጃ፣ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሲገልጽ በመጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ ተናግሯል። ዳዊት ስለ ይሖዋ አምላክ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ።” (መዝ. 139:16 NW) ዳዊት፣ ሰውነቱ የተፈጠረበትን መንገድ ሲመለከት ይሖዋን ለማወደስ መነሳሳቱ ምንም አያስገርምም። የሳይንስ ሊቃውንት በቅርቡ ያገኟቸው አዳዲስ መረጃዎች፣ ይሖዋ አካላችንን የሠራበትን መንገድ ይበልጥ እንድናደንቅ ያደርጉናል። እነዚህን ግኝቶች ስንመረምር “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች” በማለት እንደጻፈው መዝሙራዊ ይሖዋን ለማወደስ የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት እናገኛለን። (መዝ. 139:14) በእርግጥም ሰዎች፣ በፍጥረት ላይ የሚታየውን ይህን ሁሉ ማስረጃ እየተመለከቱ አምላክ መኖሩን አለማመናቸው የሚያስገርም ነው!

ሌሎች ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያከብሩ እርዷቸው

15, 16. (ሀ) ጽሑፎቻችን፣ በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀውን የይሖዋን ችሎታ ይበልጥ እንድናደንቅ የሚረዱን እንዴት ነው? (ለ) “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚለው ዓምድ ሥር ከወጡት ርዕሶች መካከል አንተን የበለጠ የነካህ የቱ ነው?

15 ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ንቁ! መጽሔት፣ ፍጥረት ሕያው ስለሆነው አምላካችን የሚገልጠውን እውነት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሲያሳውቅ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የመስከረም 2006 ንቁ! “በእርግጥ ፈጣሪ አለ?” የሚል የሽፋን ርዕስ ነበረው። ይህ እትም የተዘጋጀበት ዓላማ በክሪኤሽኒዝም እና በዝግመተ ለውጥ ትምህርት የታወሩ ሰዎችን ዓይን መክፈት ነው። አንዲት እህት ይህን ልዩ እትም በተመለከተ ለዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ይህን ልዩ እትም ለማሰራጨት የተደረገው ዘመቻ በጣም የተሳካ ነበር። አንዲት ሴት 20 ቅጂዎች እንዲሰጧት ጠየቀች። ሴትየዋ የባዮሎጂ መምህርት ስትሆን ተማሪዎቿ በሙሉ መጽሔቱ እንዲደርሳቸው ፈልጋ ነበር።” አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዕድሜዬ ወደ 75 ዓመት እየተጠጋ ነው፤ ከ1940ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ በአገልግሎት ስካፈል ቆይቻለሁ፤ ያም ቢሆን በዚህ ወር ይህን የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም በማሰራጨት ስካፈል የተደሰትኩትን ያህል በአገልግሎት የተደሰትኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም።”

16 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በብዙዎቹ የንቁ! እትሞች ላይ “ንድፍ አውጪ አለው?” የሚል ዓምድ እየወጣ ነው። በዚህ ዓምድ ሥር የሚወጡት አጫጭር ርዕሶች በፍጥረት ላይ የሚታየውን እጅግ አስገራሚ ንድፍ የሚያጎሉ ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆች የታላቁን ንድፍ አውጪ ሥራ ለመኮረጅ የሞከሩባቸውን መንገዶች ይጠቁማሉ። ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባለው ብሮሹር በ2010 ሲወጣ ደግሞ ለአምላክ ክብር ለመስጠት የሚረዳ ሌላ መሣሪያ አግኝተናል። በብሮሹሩ ላይ ያሉት ውብ ሥዕሎችና ትምህርት ሰጪ ሰንጠረዦች በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀውን የይሖዋን ችሎታ ይበልጥ እንድናደንቅ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። በእያንዳንዱ ክፍል መጨረሻ ላይ ያሉት ጥያቄዎች ባነበብነው ነገር ላይ ቆም ብለን እንድናስብ ይረዱናል። ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይ ላይ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክሩ በዚህ ብሮሹር ለመጠቀም ሞክራችኋል?

17, 18. (ሀ) ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ስለ እምነታቸው ለሚቀርብላቸው ጥያቄ በልበ ሙሉነት መልስ እንዲሰጡ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? (ለ) ስለ ፍጥረት የሚናገሩትን ብሮሹሮች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ወቅት የተጠቀማችሁባቸው እንዴት ነው?

17 ወላጆች የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ወቅት ውብ ሥዕሎች ባሉት በዚህ ብሮሹር ላይ ከትናንሽ ልጆቻችሁ ጋር ተወያይታችሁ ታውቃላችሁ? እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ ሕያው ስለሆነው አምላካችን አድናቆት እንዲያድርባቸው ትረዷቸዋላችሁ። ምናልባትም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑ ልጆች ይኖሯችሁ ይሆናል። ሐሰት ለሆነው የዝግመተ ለውጥ ትምህርት በዋነኝነት የተጋለጡት እነዚህ ወጣቶች ናቸው። የሳይንስ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ስለ ተፈጥሮ የሚዘጋጁ ጥናታዊ ፊልሞች ወይም ጽሑፎች ሌላው ቀርቶ በመዝናኛው ዓለም የሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች እንኳ የዝግመተ ለውጥን  ጽንሰ ሐሳብ እንደ እውነት አድርገው ያቀርቡታል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ልጆቻችሁ ይህን ፕሮፓጋንዳ መቋቋም እንዲችሉ ለመርዳት በ2010 የወጣውን የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ሌላውን ብሮሹር ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እንደተባለው ብሮሹር ሁሉ ይህ ብሮሹርም ወጣቶች “የመለየት” ወይም የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያበረታታል። (ምሳሌ 2:10, 11) በትምህርት ቤት የሚማሩት ነገር ምክንያታዊ መሆኑን እንዲመረምሩ ይረዳቸዋል።

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ስለ እምነታቸው መልስ መስጠት እንዲችሉ አዘጋጇቸው (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

18 በዝግመተ ለውጥ ሂደት ላይ ያለውን “ክፍተት እንደሚሞሉ” የሚታሰቡ ቅሪተ አካላትን የሳይንስ ሊቃውንት እንዳገኙ የሚገልጹ የዜና ዘገባዎችን እንሰማለን፤ የሕይወት አመጣጥ የተባለው ብሮሹር ተማሪዎች፣ የእነዚህ ቅሪተ አካላት መገኘት ዝግመተ ለውጥን ይደግፍ እንደሆነ እንዲገመግሙ ይረዳቸዋል። ብሮሹሩ፣ ከላይ ያሉት ዘገባዎች የሰው ልጆች ዝንጀሮ መሰል ከሆኑ ፍጥረታት እንደመጡ የሚገልጸውን ሐሳብ ይደግፉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመመርመርም ይረዳል። በተጨማሪም የሳይንስ ሊቃውንት፣ ሕይወት በአጋጣሚ ሊገኝ እንደሚችል በቤተ ሙከራ ውስጥ እንዳረጋገጡ ለሚገልጹ ሰዎች እንዴት መልስ መስጠት እንዳለባቸው ወጣቶችን ያሠለጥናቸዋል። ወላጆች፣ እነዚህን ብሮሹሮች የምትጠቀሙ ከሆነ ልጆቻችሁ በፈጣሪ ላይ ስላላቸው እምነት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ በልበ ሙሉነት መልስ መስጠት እንዲችሉ ትረዷቸዋላችሁ።—1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።

19. ሁላችንም ምን የማድረግ መብት አለን?

19 ከይሖዋ ድርጅት የምናገኛቸው ብዙ ምርምር የተደረገባቸው ሐሳቦች በዙሪያችን ባሉት ነገሮች ላይ የሚታዩትን የይሖዋን ግሩም ባሕርያት እንድንገነዘብ ይረዱናል። እነዚህን ሐሳቦች ስናነብብ የምናገኛቸው አሳማኝ ማስረጃዎች አምላካችንን እንድናወድስ ይገፋፉናል። (መዝ. 19:1, 2) በእርግጥም የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ የሚገባውን ታላቅ ክብር የመስጠት አጋጣሚ ማግኘታችን ምንኛ ከፍተኛ መብት ነው!—1 ጢሞ. 1:17

^ አን.3 በክሪኤሽኒዝም ከሚያምኑ ሰዎች ጋር ለመወያየት የሚያስችሉ ሐሳቦችን ለማግኘት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የሚለውን ብሮሹር ከገጽ 24 እስከ 28 ተመልከት።