በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ፍቅር ከተንጸባረቀበት የኢየሱስ ጸሎት ጋር ተስማምቶ መኖር

ፍቅር ከተንጸባረቀበት የኢየሱስ ጸሎት ጋር ተስማምቶ መኖር

“አባት ሆይ፣ . . . ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው።”—ዮሐ. 17:1

1, 2. ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር የፋሲካን በዓል ካከበረ በኋላ ምን እንዳደረገ ግለጽ።

ዕለቱ ኒሳን 14 ቀን 33 ዓ.ም. ሲሆን ምሽቱ ገፍቷል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፋሲካን በዓል አክብረው መጨረሳቸው ነው፤ በዓሉን ሲያከብሩ አምላክ አባቶቻቸውን ከግብፅ ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው አስታውሰው መሆን አለበት። ታማኝ የሆኑት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ደግሞ ከዚያ እጅግ የላቀውን “ዘላለማዊ መዳን” ሊያገኙ ነው። ኃጢአት የሌለበት መሪያቸው በቀጣዩ ቀን በጠላቶቹ እጅ ይገደላል። ይሁንና ይህ የክፋት ድርጊት በረከት ያመጣል። የኢየሱስ ደም መፍሰሱ የሰው ልጆች ከኃጢአት እና ከሞት እንዲድኑ መንገድ ይከፍታል።—ዕብ. 9:12-14

2 ኢየሱስ፣ ፍቅር የተንጸባረቀበትን ይህን ዝግጅት እንዳንረሳ ሲል በፋሲካ በዓል ምትክ በየዓመቱ የሚከበር አዲስ በዓል አቋቋመ። ኢየሱስ፣ እርሾ የሌለበትን ቂጣ አንስቶ ከቆረሰ በኋላ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያቱ በማከፋፈል እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።” ቀይ ወይን ያለበትን ጽዋም አንስቶ ልክ እንደዚሁ አደረገ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው።”—ሉቃስ 22:19, 20

3. (ሀ) የኢየሱስ ሞት ምን ትልቅ ለውጥ አምጥቷል? (ለ) በዮሐንስ 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢየሱስ ያቀረበውን ጸሎት ስንመረምር የትኞቹን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል?

3 አምላክ ቀደም ሲል ከሥጋዊ እስራኤላውያን ጋር የገባው የሕጉ ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው ሊመጣ ተቃርቧል። ይህ ቃል ኪዳን፣ ይሖዋ ከኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ጋር በሚገባው አዲስ ቃል ኪዳን ይተካል። ኢየሱስ የዚህ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ደኅንነት በጣም አሳስቦት ነበር። ሥጋዊ እስራኤላውያን በሃይማኖታቸው ውስጥ ክፍፍል የነበረ ከመሆኑም ሌላ በማኅበራዊ ሁኔታ ልዩነት ያደርጉ ነበር፤ ይህም በአምላክ ቅዱስ ስም ላይ ትልቅ ነቀፋ አምጥቷል። (ዮሐ. 7:45-49፤ ሥራ 23:6-9) ከዚህ በተለየ መልኩ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በአንድነት ተባብረው በመሥራት የአምላክን  ስም ማስከበር እንዲችሉ ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው ይፈልግ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? በጽሑፍ ተመዝግበው ከምናገኛቸው ጸሎቶች ሁሉ እጅግ የላቀውን ልብ የሚነካ ጸሎት አቀረበ። (ዮሐ. 17:1-26፤ መግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) ይህን ጸሎት ስንመረምር “አምላክ ለኢየሱስ ጸሎት መልስ ሰጥቶ ይሆን?” የሚለውን ጉዳይ ማሰብ እንችላለን። በተጨማሪም ራሳችንን መመርመርና “ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተመላለስኩ ነው?” በማለት መጠየቅ ይኖርብናል።

ኢየሱስ ቅድሚያ የሰጣቸው ነገሮች

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ጸሎቱን ከጀመረበት መንገድ ምን እንማራለን? (ለ) ኢየሱስ ስለ ወደፊት ሕይወቱ ላቀረበው ልመና ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጥቷል?

4 ሌሊቱ ቢገፋም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከአምላክ ያገኘውን ውድ እውቀት እያካፈላቸው ነው። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ምክንያቱም አንተ ለሰጠኸው ሰው ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ በሰዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋል። . . . እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ በነበረኝ ክብር አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።”—ዮሐ. 17:1-5

5 ኢየሱስ በጸሎቱ መጀመሪያ ላይ ቅድሚያ የሰጣቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ልብ በል። በዋነኝነት የሚያሳስበው ነገር በሰማይ ያለው አባቱ መከበር ነው፤ እሱ ራሱ ባስተማረው የጸሎት ናሙና መግቢያ ላይ “አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ማለቱም ይህን ያሳያል። (ሉቃስ 11:2) ኢየሱስ ቀጥሎ ትኩረት ያደረገው ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ ነው፤ ለደቀ መዛሙርቱ “የዘላለም ሕይወት” ስለ መስጠት ጠቅሷል። ከዚያም ኢየሱስ፣ እንደሚከተለው በማለት ራሱ የሚፈልገውን ነገር ጠየቀ፦ “ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ በነበረኝ ክብር አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።” ይሖዋም፣ ኢየሱስ ከጠየቀው የበለጠ ነገር ይኸውም ከመላእክት ሁሉ “እጅግ የላቀ ስም” በመስጠት ታማኝ ልጁን አክብሮታል።—ዕብ. 1:4

‘ብቻውን እውነተኛ የሆነውን አምላክ ማወቅ’

6. ሐዋርያት የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ይህን ማድረግ እንደቻሉ እንዴት እናውቃለን?

6 ኢየሱስ፣ ኃጢአተኛ የሆንነው የሰው ልጆች የጸጋ ስጦታ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ስለሚኖርብን ነገርም በጸሎቱ ላይ ጠቅሷል። (ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።) ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ ‘እውቀት መቅሰማችንን መቀጠል’ እንዳለብን ተናግሯል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከምናየውና ከምንሰማው ነገር ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ የቻልነውን ያህል ለመማር ጥረት ማድረግ ነው። ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ስለ እሱ የተማርነውን በተግባር ማዋል የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ነው። ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነሱም ተቀብለዋል” በማለት ስለተናገረ ሐዋርያቱ፣ ሕይወት የሚያስገኙትን እነዚህን ነገሮች እንዳደረጉ ግልጽ ነው። (ዮሐ. 17:8) ይሁን እንጂ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ስለ አምላክ ባወቁት ነገር ላይ ማሰላሰላቸውንና ያወቋቸውን ነገሮች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረጋቸውን መቀጠል ይጠበቅባቸው ነበር። ታዲያ እነዚህ ታማኝ ሐዋርያት ምድራዊ ሕይወታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ይህን ማድረግ ችለዋል? አዎን። የእነዚህ ሐዋርያት ስም በሰማያዊቷ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም 12 የመሠረት ድንጋዮች ላይ በማይፋቅ ሁኔታ መስፈሩ ይህን ያረጋግጣል።—ራእይ 21:14

7. አምላክን “ማወቅ” ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

7 የግሪክኛ ቋንቋ ምሁራን እንደገለጹት “እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ማወቃቸውን መቀጠል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እነዚህ ሁለት ሐረጎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ ሲሆን ሁለቱንም ነገሮች ማድረግ አስፈላጊ ነው። በባለ ማጣቀሻው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም (እንግሊዝኛ) ላይ የዮሐንስ 17:3 የግርጌ ማስታወሻ፣ ይህ ሐሳብ “አንተን ማወቅ” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ያሳያል። በመሆኑም ‘እውቀት መቅሰምን መቀጠል’  የማይቋረጥ ሂደት ሲሆን ይህም አምላክን ወደ “ማወቅ” ደረጃ ያደርሰናል፤ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው። ይሁንና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ የሆነውን አካል ማወቅ ስለ እሱ ባሕርያትና ዓላማ የአእምሮ እውቀት ከማካበት ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ይሖዋን ማወቅ፣ ከእሱና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝምድና መፍጠርንም ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም” ይላል። (1 ዮሐ. 4:8) አምላክን ማወቅ እሱን መታዘዝንም ይጨምራል። (1 ዮሐንስ 2:3-5ን አንብብ።) ይሖዋን ከሚያውቁት እንደ አንዱ ሆኖ መቆጠር እንዴት ያለ ክብር ነው! ይሁን እንጂ ከአስቆሮቱ ይሁዳ ሁኔታ መመልከት እንደምንችለው አንድ ሰው ይህን ውድ ዝምድና ሊያጣ ይችላል። በመሆኑም ይህንን ዝምድና እንዳናጣ ከፍተኛ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችንን ከቀጠልን የጸጋ ስጦታ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን።—ማቴ. 24:13

“ስለ ራስህ ስም ስትል”

8, 9. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው በምን ላይ ነው? የትኛውን ሃይማኖታዊ ልማድ አልተከተለም?

8 በዮሐንስ 17 ላይ ከተመዘገበው የኢየሱስ ጸሎት አንጻር ኢየሱስ፣ በወቅቱ አብረውት ለነበሩ ሐዋርያቱ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የእሱ ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑት ሰዎችም ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 17:20) ያም ቢሆን ግን ኢየሱስን በዋነኝነት የሚያሳስበው የእኛ መዳን እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልገናል። ምድራዊ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ዋነኛ ዓላማው የአባቱ ስም እንዲቀደስ እና እንዲከበር ማድረግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በናዝሬት ምኩራብ ውስጥ ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ የሚከተለውን ሐሳብ በማንበብ የተሰጠውን ተልዕኮ ገልጿል፦ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ምሥራች እንዳውጅ ቀብቶኛል።” ኢየሱስ ይህን ጥቅስ ባነበበበት ወቅት የይሖዋን ስም በትክክለኛው መንገድ እንደጠራ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 4:16-21

9 የአይሁዳውያን ወግ እንደሚገልጸው የሃይማኖት መሪዎች፣ ሕዝቡ የአምላክን ስም እንዳይጠቀሙ ማስተማር የጀመሩት ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ነበር። ኢየሱስ፣ እንዲህ ዓይነቱን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ልማድ እንዳልተከተለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ተቃዋሚዎቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው ግን በራሱ ስም ቢመጣ ትቀበሉታላችሁ።” (ዮሐ. 5:43) ከመሞቱ  ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ብሎ በመጸለይ በዋነኝነት የሚያሳስበውን ጉዳይ ገልጿል። (ዮሐ. 12:28) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ አሁን እየመረመርን ባለነው ጸሎቱ ላይ ስለ አባቱ ስም ደጋግሞ መጥቀሱ አያስገርምም።

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ፣ የአባቱን ስም ለማሳወቅ ምን አድርጓል? (ለ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የትኛውን ዓላማ ለማሳካት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል?

10 ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። እነሱ የአንተ ነበሩ፣ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነሱም ቃልህን ጠብቀዋል። በተጨማሪም፣ ከእንግዲህ እኔ በዓለም ውስጥ አልኖርም፤ እነሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው።”—ዮሐ. 17:6, 11

11 ኢየሱስ፣ የአባቱን ስም ለደቀ መዛሙርቱ ሲያሳውቅ ስሙን ከመናገር ያለፈ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ፣ የአምላክ ስም የሚወክላቸውን ነገሮች ይኸውም የአምላክን ድንቅ ባሕርያትና እኛን የሚይዝበትን መንገድ እንዲገነዘቡም ረድቷቸዋል። (ዘፀ. 34:5-7) ኢየሱስ ክብር አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ በመላው ምድር የይሖዋን ስም እንዲያሳውቁ መርዳቱን ቀጥሏል። ይህን የሚያደርግበት ዓላማ ምንድን ነው? ይህ ክፉ ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት እንዲሰበሰቡ ስለሚፈልግ ነው። ይህ ሥርዓት ሲጠፋ ይሖዋ፣ ታማኝ ምሥክሮቹን ለማዳን እርምጃ ይወስዳል፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ ለራሱ ታላቅ ስም ያተርፋል!—ሕዝ. 36:23

“ዓለም . . . እንዲያምን”

12. ሕይወት አድን በሆነው ሥራችን ስኬታማ እንድንሆን የሚያስፈልጉን ሦስት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

12 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ድክመቶቻቸውን ማሸነፍ እንዲችሉ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ደቀ መዛሙርቱ፣ እሱ የጀመረውን ሥራ ለማጠናቀቅ እንዲችሉ ይህ አስፈላጊ ነበር። ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ “አንተ ወደ ዓለም እንደላክኸኝ ሁሉ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ” ብሏል። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሕይወት አድን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ እንዲሳካላቸው የሚያስፈልጓቸውን ሦስት ነገሮች ጠቅሷል። አንደኛ፣ ደቀ መዛሙርቱ ርኩስ የሆነው የሰይጣን ዓለም ክፍል እንዳይሆኑ ጸልዮአል። ሁለተኛ፣ ከአምላክ ቃል ላይ የተማሩትን እውነት በሥራ ላይ በማዋል እንዲቀደሱ ጠይቋል። ሦስተኛ ደግሞ ኢየሱስ፣ በእሱና በአባቱ መካከል ያለው ዓይነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ አንድነት በደቀ መዛሙርቱ መካከል እንዲኖር በተደጋጋሚ ለምኗል። ይህ ቆም ብለን ራሳችንን እንድንመረምር የሚያነሳሳ ነው። ሁላችንም ‘ኢየሱስ ካቀረባቸው ሦስት ልመናዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እየተመላለስኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እነዚህን ነገሮች ካደረጉ ‘አባቱ እሱን እንደላከው ዓለም እንደሚያምን’ ያለውን እምነት ገልጿል።—ዮሐንስ 17:15-21ን አንብብ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አንድነታቸውን መጠበቅ ችለዋል (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

13. የኢየሱስ ጸሎት፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መልስ ያገኘው እንዴት ነው?

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአራቱ ወንጌሎች ቀጥሎ የሚገኘውን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስናጠና የኢየሱስ ጸሎት መልስ እንዳገኘ መረዳት እንችላለን። አይሁዳውያንንና አሕዛብን፣ ሀብታሞችንና ድሆችን እንዲሁም ባሪያዎችንና ጌቶችን ባቀፈው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በቀላሉ መከፋፈል ሊፈጠር ይችል ነበር። ይሁንና በመካከላቸው የጠበቀ አንድነት ስለነበረ ከአንድ አካል ክፍሎች ጋር ሊመሳሰሉ ችለዋል፤ የዚህ አካል ራስ ኢየሱስ ነው። (ኤፌ. 4:15, 16) በእርግጥም በተከፋፈለው የሰይጣን ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ አንድነት ማግኘት ተአምር ነው! ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው በታላቅ ኃይሉ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ይሖዋ ነው።—1 ቆሮ. 3:5-7

በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት አላቸው (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14. ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት በዘመናችን መልስ ያገኘው እንዴት ነው?

14 የሚያሳዝነው ነገር፣ እንደ ተአምር ሊቆጠር የሚችለው ይህ አንድነት ከሐዋርያቱ ሞት በኋላ አልቀጠለም። ከዚህ ይልቅ አስቀድሞ እንደተነገረው ታላቅ ክህደት የተነሳ ሲሆን ይህም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚታየው ክፍፍል እንዲፈጠር  አድርጓል። (ሥራ 20:29, 30) ይሁን እንጂ በ1919 ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹን ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ አውጥቶ ‘ፍጹም በሆነ የአንድነት ማሰሪያ’ ሰበሰባቸው። (ቆላ. 3:14) እነዚህ ቅቡዓን ያከናወኑት የስብከት ሥራ ምን ውጤት አስገኝቷል? ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” የተውጣጡ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ከአምላክ ቅቡዓን ጋር አንድ መንጋ እንዲሆኑ አድርጓል። (ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9) ይህም ኢየሱስ “ዓለም አንተ [ይሖዋ] እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው” በማለት ያቀረበው ጸሎት አስደናቂ ምላሽ እንዳገኘ የሚያሳይ ነው።—ዮሐ. 17:23

ግሩም የሆነ መደምደሚያ

15. ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ምን ልዩ ልመና አቅርቧል?

15 ኒሳን 14 ምሽቱ ሲጀምር ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ በመንግሥቱ ከእሱ ጋር አብረው እንዲገዙ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ክብር ሰጥቷቸው ነበር። (ሉቃስ 22:28-30፤ ዮሐ. 17:22) በመሆኑም ኢየሱስ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹ የሚሆኑትን በሙሉ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ እነዚህን የሰጠኸኝን በተመለከተ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እመኛለሁ፤ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር ያዩ ዘንድ ነው።” (ዮሐ. 17:24) የኢየሱስ ሌሎች በጎች፣ ቅቡዓኑ እንዲህ ያለ ሽልማት በማግኘታቸው ይደሰታሉ እንጂ አይቀኑም፤ ይህም በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ባሉት በሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል አንድነት እንዳለ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ በጸሎቱ መደምደሚያ ላይ፣ ምን ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጿል? (ለ) እኛስ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

16 በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች፣ ይሖዋ እሱን በሚገባ የሚያውቅና አንድነት ያለው ሕዝብ እንዳለው የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ አይቀበሉም፤ ለዚህም አስተዋጽኦ ያደረገው የሃይማኖት መሪዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ነው። በኢየሱስ ዘመንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። በመሆኑም በጸሎቱ መደምደሚያ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጻድቅ አባት ሆይ፣ በእርግጥ ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን አውቅሃለሁ፤ እነዚህ ደግሞ አንተ እንደላክኸኝ አውቀዋል። እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”—ዮሐ. 17:25, 26

17 ኢየሱስ ከዚህ ጸሎት ጋር የሚስማማ እርምጃ እንደወሰደ ማን ሊክድ ይችላል? የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን የአባቱን ስምና ዓላማ እንድናሳውቅ ሁልጊዜም ይረዳናል። ኢየሱስ እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ በቅንዓት በመፈጸም ለእሱ ሥልጣን እንደምንገዛ ማሳየታችንን እንቀጥል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 10:42) በተጨማሪም ውድ የሆነውን አንድነታችንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እናድርግ። እነዚህን ነገሮች የምናደርግ ከሆነ ከኢየሱስ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ እንኖራለን፤ ይህ ደግሞ የይሖዋን ስም የሚያስከብር ከመሆኑም ሌላ ዘላለማዊ ደስታ ያመጣልናል።