በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥቅምት 2013

በሚገባ ከታሰበበት ጸሎት የምናገኘው ትምህርት

በሚገባ ከታሰበበት ጸሎት የምናገኘው ትምህርት

“ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን።”—ነህ. 9:5

1. የአምላክ ሕዝቦች ስላደረጉት ስለ የትኛው ስብሰባ እንመረምራለን? ከዚህ ስብሰባ ጋር በተያያዘስ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

“ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ።” እነዚህ ቃላት፣ የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው ለይሖዋ ጸሎት እንዲያቀርቡ አነሳስተዋቸዋል፤ በዚያ ወቅት ያቀረቡት ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት ረጅም ጸሎቶች መካከል አንዱ ነው። (ነህ. 9:4, 5) ይህ ስብሰባ የተካሄደው በ455 ዓ.ዓ. በኢየሩሳሌም ሲሆን ዕለቱ ደግሞ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ቲሽሪ የተባለው ሰባተኛ ወር 24ኛ ቀን ነው። ከዚህ ልዩ ቀን በፊት የተከናወኑትን ነገሮች ስንመረምር እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ይህ ስብሰባ የተሳካ የሆነው ሌዋውያኑ ምን ዓይነት ጥሩ ልማድ ስለነበራቸው ነው? በዚያን ዕለት ከቀረበው በሚገባ የታሰበበት ጸሎት ምን ትምህርት አገኛለሁ?’—መዝ. 141:2

ልዩ ወር

2. እስራኤላውያን የኢየሩሳሌምን ግንብ እንደገና ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ምን ግሩም ምሳሌ ትተውልናል?

2 ከላይ የተጠቀሰው ስብሰባ ከመካሄዱ ከአንድ ወር በፊት አይሁዳውያን የኢየሩሳሌምን ግንብ እንደገና ሠርተው አጠናቅቀው ነበር። (ነህ. 6:15) የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራ ያጠናቀቁት በ52 ቀናት ውስጥ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ በመንፈሳዊ ረገድ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሟሟላት ላይ ልዩ ትኩረት አደረጉ። በመሆኑም ቲሽሪ በተባለው ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ በአደባባይ ተሰብስበው ዕዝራና ሌሎች ሌዋውያን የአምላክን ቃል ጮክ ብለው ሲያነቡና ሲያብራሩ አዳመጡ። ሁሉም የቤተሰብ አባላት ይኸውም “ማስተዋል የሚችሉ ሁሉ . . . ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር” ሕጉ ሲነበብ ቆመው ያዳምጡ ነበር። በዛሬው ጊዜ ምቹ በሆኑ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ለምንሰበሰብ ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አንዳንድ ጊዜ ስብሰባ ላይ እያለህ አእምሮህ መባዘንና ያን ያህል አስፈላጊ ስላልሆኑ ጉዳዮች ማሰብ ይጀምራል? ከሆነ የእነዚህን እስራኤላውያን ምሳሌ መለስ ብለህ አስብ፤ ሕዝቡ የሚሰጠውን ትምህርት በማዳመጥ ብቻ ሳይወሰኑ ትምህርቱ ወደ ልባቸው ጠልቆ እንዲገባ አድርገው ነበር፤ በዚህም የተነሳ በብሔር ደረጃ የአምላክን ሕግ ባለማክበር በሠሩት ስህተት ማልቀስ ጀመሩ።—ነህ. 8:1-9

3. እስራኤላውያን የተሰጣቸውን የትኛውን መመሪያ ታዝዘዋል?

 3 ይሁንና ሕዝቡ በዚያ ቀን የተሰባሰቡት ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ አልነበረም። ይህ ዕለት የበዓል ቀን እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡ በይሖዋ አምልኮ ደስ የሚሰኙበት ወቅት ሊሆን ይገባል። (ዘኍ. 29:1) በመሆኑም ነህምያ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለሆነ አትዘኑ።” ደስ የሚለው ነገር፣ ሕዝቡ የተባሉትን በታዛዥነት ስላደረጉ ቀኑ ‘የሐሤት’ ቀን ሆነ።—ነህ. 8:10-12

4. እስራኤላውያን የቤተሰብ ኃላፊዎች ምን አደረጉ? በዚህ የዳስ በዓል ላይ ከተከናወኑት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ ምንድን ነው?

4 በቀጣዩ ቀን የየቤተሰቡ ኃላፊዎች፣ ሕዝቡ የአምላክን ሕግ ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመመርመር አንድ ላይ ተሰባሰቡ። ሕጉን ሲመረምሩ፣ ቲሽሪ በተባለው በሰባተኛው ወር ከ15ኛው ቀን ጀምሮ የዳስ በዓል መከበር እንዳለበትና በዓሉ በ22ኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ በማድረግ እንደሚደመደም የሚገልጽ ሐሳብ አገኙ፤ ስለዚህ ለበዓሉ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። እስራኤላውያን፣ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካከበሯቸው የዳስ በዓሎች ሁሉ በላቀ መንገድ በዓሉን አከበሩ፤ በመሆኑም ‘ደስታቸው ታላቅ ነበር።’ በዚህ በዓል ላይ ከተካሄዱት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ የአምላክ ሕግ “ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ . . . በየዕለቱ” ይነበብ የነበረ መሆኑ ነው።—ነህ. 8:13-18

ኃጢአታቸውን የሚናዘዙበት ቀን

5. የአምላክ ሕዝቦች፣ ሌዋውያኑ እነሱን ወክለው ለይሖዋ ከመጸለያቸው በፊት ምን አደረጉ?

5 በዓሉ ካበቃ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ እስራኤላውያን፣ የአምላክን ሕግ ባለመጠበቃቸው ኃጢአታቸውን በሕዝብ ፊት ለመናዘዝ ተሰባሰቡ። ይህ ቀን በመብላት እና በመጠጣት የሚያሳልፉት የበዓል ቀን አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች ጾመው እና ሐዘናቸውን ለመግለጽ ማቅ ለብሰው ነበር። በዚህ ወቅትም የአምላክ ሕግ ጠዋት ላይ ለሦስት ሰዓት ያህል በሕዝቡ ፊት ተነበበ። የከሰዓት በኋላውን ጊዜ ደግሞ “ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአ[ብ]ሔር በመስገድ አሳለፉ።” ከዚያም ሌዋውያኑ፣ ሕዝቡን ወክለው በሚገባ የታሰበበት ጸሎት አቀረቡ። —ነህ. 9:1-4

6. ሌዋውያኑ፣ በደንብ የታሰበበት ጸሎት እንዲያቀርቡ የረዳቸው ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 ሌዋውያኑ፣ እንዲህ ያለ በደንብ የታሰበበት ጸሎት እንዲያቀርቡ የረዳቸው የአምላክን ቃል አዘውትረው ማንበባቸው እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በጸሎቱ ላይ የመጀመሪያዎቹ አሥር ቁጥሮች ያተኮሩት በይሖዋ ሥራዎችና ባሕርያት ላይ ነው። በቀሪው የጸሎቱ ክፍል ላይ ደግሞ የአምላክ ‘ርኅራኄ’ እና ‘ምሕረት’ ብዙ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን እስራኤላውያን እንዲህ ዓይነት ደግነት የሚገባቸው ሰዎች እንዳልሆኑ ሌዋውያኑ በጸሎታቸው ላይ በግልጽ ተናግረዋል። (ነህ. 9:19, 27, 28, 31) እኛም የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብ እና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ይሖዋ እንዲያነጋግረን  መፍቀድ ይኖርብናል፤ እንዲህ ካደረግን ለይሖዋ ረጅም ጸሎት በምናቀርብበት ወቅት እንደ ሌዋውያኑ ትርጉም ያለው እንዲሁም ተደጋጋሚ ያልሆነ ጸሎት ማቅረብ እንችላለን።—መዝ. 1:1, 2

7. ሌዋውያኑ አምላክን ምን ለመኑ? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ሌዋውያኑ በጸሎታቸው ላይ ያካተቱት አንድ ልመና ብቻ ነው። ይህ ትሕትና የሚንጸባረቅበት ልመና የሚገኘው በቁጥር 32 መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ።” ሌዋውያን ከተዉት ከዚህ ግሩም ምሳሌ እንደምንማረው በጸሎታችን ላይ፣ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ከመጠየቃችን በፊት ይሖዋን ማወደሳችንና ማመስገናችን ተገቢ ነው።

የአምላክን ክቡር ስም ማወደስ

8, 9. (ሀ) ሌዋውያኑ ጸሎታቸውን ሲጀምሩ ትሕትናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ሌዋውያኑ በጸሎታቸው የጠቀሷቸው ሁለት የሰማይ ሰራዊቶች የትኞቹ ናቸው?

8 ሌዋውያኑ ለአምላክ ያቀረቡት ጸሎት በደንብ የታሰበበት ቢሆንም እንኳ የተጠቀሙባቸው ቃላት፣ ለይሖዋ የሚገባውን ውዳሴ በበቂ ሁኔታ እንደማይገልጹ ተሰምቷቸው ነበር። በመሆኑም ጸሎታቸውን የጀመሩት ለአምላክ ሕዝብ የሚከተለውን ትሕትና የተንጸባረቀበት ሐሳብ በማቅረብ ነው፦ “የሰው ምስጋናና ውዳሴ ታላቅነቱን ሙሉ በሙሉ ለመግለጥ የሚበቃ ባይሆንም እንኳ የከበረ ግርማ ያለውን የእግዚአብሔርን ስም አወድሱ።”—ነህ. 9:5 የ1980 ትርጉም

9 ጸሎቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል።” (ነህ. 9:6) ይሖዋ አምላክ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጋላክሲዎችን ያቀፈውን አጽናፈ ዓለም ፈጥሯል። በተጨማሪም ውብ በሆነችው ፕላኔታችን ላይ የሚገኙትን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው እሱ ነው፤ እንዲሁም ምድራችንን የሠራት ለተለያዩ ፍጥረታት መኖሪያነት አመቺ እንድትሆን አድርጎ ሲሆን እነዚህ ፍጥረታትም እንደየወገናቸው መባዛት ይችላሉ፤ ይህ ሁሉ፣ ከግዑዙ አጽናፈ ዓለም ባልተናነሰ መልኩ የሚያስገርም ነው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲፈጠሩ የተመለከቱት ቅዱሳን የአምላክ መላእክትም “የሰማይ ሰራዊት” ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። (1 ነገ. 22:19፤ ኢዮብ 38:4, 7) ከዚህም ሌላ መላእክት “መዳን የሚወርሱትን” ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች በማገልገል የአምላክን ፈቃድ በትሕትና ይፈጽማሉ። (ዕብ. 1:14) እኛም፣ በሚገባ እንደሠለጠነ ሰራዊት ይሖዋን በአንድነት ስናገለግል እነዚህ መላእክት ግሩም ምሳሌ እንደሚሆኑን ጥርጥር የለውም!—1 ቆሮ. 14:33, 40

10. አምላክ ከአብርሃም ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን እንማራለን?

10 ሌዋውያኑ በመቀጠል አምላክ ከአብራም ጋር  ስለነበረው ግንኙነት አነሱ፤ አብራም 99 ዓመት እስኪሆነው ድረስ፣ መሃን ከነበረችው ከሚስቱ ከሦራ ልጅ አልወለደም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ የአብራምን ስም በመለወጥ “የብዙ ሕዝቦች አባት” የሚል ትርጉም ባለው አብርሃም በተባለው ስም እንዲጠራ አደረገው። (ዘፍ. 17:1-6, 15, 16) በተጨማሪም አምላክ የአብርሃም ዘር የከነዓንን ምድር እንደሚወርስ ቃል ገባ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ የገቡትን ቃል የሚረሱ ቢሆንም ይሖዋ ግን ፈጽሞ ቃሉን አይረሳም። ሌዋውያኑ በጸሎታቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳውያን ዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን . . . ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ።” (ነህ. 9:7, 8) እኛም ምንጊዜም በቃላችን ለመገኘት በመጣር ጻድቅ የሆነውን የአምላካችን ምሳሌ እንከተል።—ማቴ. 5:37

ይሖዋ ያከናወናቸውን ነገሮች ማውሳት

11, 12. ይሖዋ የሚለው ስም ምን ትርጉም እንዳለው እንዲሁም ይሖዋ ከአብርሃም ዘሮች ጋር ባለው ግንኙነት እንደ ስሙ መሆኑን ያሳየው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

11 ይሖዋ የሚለው ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም ይሖዋ ደረጃ በደረጃ በሚወስዳቸው እርምጃዎች አማካኝነት ቃል የገባቸውን ነገሮች እውን የሚያደርግ አምላክ እንደሆነ ያመለክታል። አምላክ በግብፅ በባርነት ከነበሩት የአብርሃም ዘሮች ጋር የነበረው ግንኙነት ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው። በወቅቱ መላው የእስራኤል ሕዝብ ነፃ መውጣትና ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት ፈጽሞ የሚችል አይመስልም ነበር። ያም ቢሆን አምላክ ደረጃ በደረጃ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ቃል የገባው ነገር እንዲፈጸም ያደረገ ሲሆን ይህም ይሖዋ በሚለው ልዩና ታላቅ ስም መጠራቱ የተገባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

12 በነህምያ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎት ስለ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ በግብፅ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ። ታምራታዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በፈርዖንና፣ በሹማምቱ ሁሉ፣ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ላክህ፤ ይህንም ያደረግኸው ግብፃውያን እንዴት በእብሪት እንዳስጨነቋቸው ስላወቅህ ነው። እስከ ዛሬም የሚጠራ ስም ለራስህ እንዲኖርህ አደረግህ። በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልህ፤ ያሳደዷቸውን ግን በኀይለኛ ውሃ ውስጥ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ውስጥ ወረወርሃቸው።” ከዚያም ጸሎቱ በመቀጠል ይሖዋ ለሕዝቡ ስላደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ . . . የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሰባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጕድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሰኙ።”—ነህ. 9:9-11, 24, 25

13. ይሖዋ፣ ለእስራኤላውያን በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸው እንዴት ነው? ሕዝቡ ግን ምን አደረጉ?

13 አምላክ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሌሎች በርካታ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ ወስዷል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ዝግጅት አድርጓል። ሌዋውያኑ ለአምላክ ባቀረቡት ጸሎት ላይ ያንን ጊዜ በማስታወስ እንዲህ ብለዋል፦ “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው።” (ነህ. 9:13) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ተስፋይቱን ምድር በሚወርሱበት ወቅት የእሱን ቅዱስ ስም ለመሸከም ብቁ ሆነው እንዲገኙ ሲል ሊያስተምራቸው ጥረት ቢያደርግም እነሱ ግን የተማሯቸውን መልካም ነገሮች ረሱ።—ነህምያ 9:16-18ን አንብብ።

የተግሣጽ አስፈላጊነት

14, 15. (ሀ) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ኃጢአት በሠሩበት ወቅት በምሕረት የያዛቸው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ፣ ከመረጣቸው ሕዝቦቹ ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን እንማራለን?

14 ሌዋውያኑ ባቀረቡት ጸሎት ላይ፣ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ በሲና ተራራ ቃል ከገቡ ብዙም ሳይቆይ የፈጸሟቸውን ሁለት ኃጢአቶች ለይተው ጠቅሰዋል። በዚህ በደላቸው የተነሳ ይሖዋ በምድረ በዳ እንዲሞቱ ቢተዋቸው ተገቢ  ቅጣት ነበር። ይሁንና ይሖዋ ይህን ባለማድረጉ ሌዋውያኑ በጸሎታቸው ላይ እንዲህ በማለት አወድሰውታል፦ “ከርኀራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ . . . አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።” (ነህ. 9:19, 21) ይሖዋ ዛሬም እሱን በታማኝነት ለማገልገል የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ያሟላልናል። ታዛዥ ባለመሆናቸውና እምነት በማጣታቸው በምድረ በዳ እንዳለቁት በሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ላለመሆን እንጠንቀቅ። እነዚህ ነገሮች “የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።”—1 ቆሮ. 10:1-11

15 የሚያሳዝነው ነገር፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ ብዙም ሳይቆይ የፆታ ብልግናንና ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን በሚያካትተው የከነዓናውያን አምልኮ መካፈል ጀመሩ። በመሆኑም ይሖዋ፣ ምርጥ ሕዝቦቹ በጎረቤቶቻቸው ጭቆና እንዲደርስባቸው ፈቀደ። ሕዝቡ ከኃጢአታቸው ንስሐ ሲገቡ ግን ይሖዋ፣ ምሕረት በማሳየት ይቅር ይላቸው እንዲሁም ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸው ነበር። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ “በየጊዜው” ይፈጠር ነበር። (ነህምያ 9:26-28, 31ን አንብብ።) ሌዋውያኑ እንዲህ ብለዋል፦ “ብዙ ዘመን ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህ አማካይነት በመንፈስህ አስጠነቀቅሃቸው። ነገር ግን አላደመጡህም፤ ከዚህም የተነሣ ጎረቤቶቻቸው ለሆኑ አሕዛብ አሳልፈህ ሰጠሃቸው።”—ነህ. 9:30

16, 17. (ሀ) ነህምያ 9:36, 37 እንደሚገልጸው እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የነበሩበት ሁኔታ አባቶቻቸው መጀመሪያ ተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ ከነበራቸው ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) እስራኤላውያን ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው የተቀበሉት እንዴት ነው? ምን ለማድረግስ ቃል ገቡ?

16 እስራኤላውያን ከምርኮ ከተመለሱ በኋላም እንደ ቀድሟቸው ያለመታዘዝን ጎዳና ተከትለዋል። ሆኖም የነበሩበት ሁኔታ አባቶቻቸው ምድሪቱን ሲወርሱ ከነበሩበት ሁኔታ ይለያል፤ እንዴት? ሌዋውያኑ ቀጥለው በጸሎታቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “እነሆ፤ ዛሬም ባሮች ነን፤ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ባሮች ነን። ከኀጢአታችን የተነሣ የተትረፈረፈው መኸር ሲሳይ የሆነው በላያችን ላስቀመጥሃቸው ነገሥታት ነው፤ . . . እኛም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንገኛለን።”—ነህ. 9:36, 37

17 ሌዋውያኑ፣ አምላክ እንዲህ ዓይነት መከራ እንዲደርስባቸው መፍቀዱ ትክክል እንዳልሆነ መግለጻቸው ነበር? በፍጹም! “በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ” በማለት ጥፋተኞች መሆናቸውን አምነዋል። (ነህ. 9:33) ሌዋውያኑ፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መንፈስ የተንጸባረቀበትን ይህን ጸሎት የደመደሙት ከዚያ ጊዜ በኋላ ብሔሩ የአምላክን ሕግ እንደሚያከብር ቃል በመግባት ነው። (ነህምያ 9:38ን አንብብ፤ 10:29) ከዚያም 84 የአይሁድ መሪዎች ይህን በሚገልጽ የውል ስምምነት ላይ ማህተሞቻቸውን አኖሩ።—ነህ. 10:1-27

18, 19. (ሀ) ከጥፋት ተርፈን አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም ለመግባት ምን ያስፈልገናል? (ለ) ስለ ምን ነገር መጸለያችንን ማቋረጥ አይኖርብንም? ለምንስ?

18 እኛም ከጥፋት ተርፈን ጽድቅ ወደሚሰፍንበት የይሖዋ አዲስ ዓለም ለመግባት ብቁ እንድንሆን የይሖዋ ተግሣጽ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አባቱ የማይገሥጸው ልጅ ማን ነው?” በማለት ጠይቋል። (ዕብ. 12:7) በአምላክ አገልግሎት በታማኝነት በመጽናት እንዲሁም መንፈሱ እንዲያጠራን በመፍቀድ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን አመራር እንደምንከተል እናሳያለን። ከባድ ኃጢአት ከሠራን ደግሞ ከልባችን ንስሐ በመግባትና የሚሰጠንን ተግሣጽ በትሕትና በመቀበል የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን።

19 በቅርቡ ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ ሲያወጣ ካተረፈው የበለጠ ታላቅ ስም ያተርፋል። (ሕዝ. 38:23) የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ተስፋይቱን ምድር እንደወረሱ ሁሉ ይሖዋን በታማኝነት በማምለክ የሚጸኑ ክርስቲያኖች በሙሉ አምላክ ወዳዘጋጀው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚገቡ ጥርጥር የለውም። (2 ጴጥ. 3:13) እንዲህ ያለ አስደናቂ ተስፋ ከፊታችን የተዘረጋልን ከመሆኑ አንጻር የአምላክ ታላቅ ስም እንዲቀደስ መጸለያችንን አናቋርጥ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ አሁንም ሆነ ለዘላለም የአምላክን በረከት ለማግኘት ከፈለግን ከየትኛው ጸሎት ጋር ተስማምተን መኖር እንደሚገባን እንመረምራለን።