በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥቅምት 2013

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ፊሊፒንስ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ፊሊፒንስ

ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ግሬጎሪዮ እና ማሪሉ የተባሉ ባልና ሚስት በማኒላ የሙሉ ቀን ሥራ እየሠሩ በአቅኚነት ያገለግሉ ነበር። ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም ተሳክቶላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ማሪሉ የደረጃ እድገት አግኝታ የምትሠራበት ባንክ ሥራ አስኪያጅ ሆነች። ማሪሉ “ጥሩ ሥራ ስለነበረን በጣም የተመቻቸ ሕይወት እንመራ ነበር” ብላለች። እንዲያውም ገቢያቸው በመጨመሩ ከማኒላ በስተ ምሥራቅ 19 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ምርጥ የሚባል ቦታ ላይ የሚመኙት ዓይነት ቤት ለመሥራት ወሰኑ። ቤቱን እንዲሠራላቸው ከአንድ ኩባንያ ጋር የተዋዋሉ ሲሆን በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ እየከፈሉ በአሥር ዓመት ውስጥ ክፍያውን ለመጨረስ ተስማሙ።

“ከይሖዋ እየሰረቅሁ እንዳለሁ ሆኖ ተሰማኝ”

ማሪሉ እንዲህ ትላለች፦ “አዲሱ ሥራዬ ጊዜዬንና ጉልበቴን በሙሉ ያሟጥጥብኝ ስለነበረ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ያለኝ ፍላጎት እየቀነሰ መጣ። ከይሖዋ እየሰረቅሁ እንዳለሁ ሆኖ ተሰማኝ።” አክላም “ለይሖዋ አገልግሎት የመደብኩትን ጊዜ ለእሱ መስጠት እያቃተኝ መጣ” ትላለች። ግሬጎሪዮ እና ማሪሉ ሁኔታው ስላላስደሰታቸው ሕይወታቸው ወዴት እያመራ እንዳለ ቁጭ ብለው ተነጋገሩ። ግሬጎሪዮ እንዲህ ይላል፦ “ለውጥ ለማድረግ  ፈልገን ነበር፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ግን አልመጣልንም። በሕይወታችን፣ በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተወያየን፤ በተለይ ልጆች ስለሌሉን ይህን የማድረግ አጋጣሚ ነበረን። ይሖዋ እንዲመራን ጸለይን።”

በዚህ ጊዜ አካባቢ፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ስለ ማገልገል የሚገልጹ በርካታ ንግግሮች ቀርበው ነበር። ግሬጎሪዮ “ይሖዋ በእነዚህ ንግግሮች አማካኝነት ለጸሎታችን ምላሽ እንደሰጠን ተሰማን” ይላል። ባልና ሚስቱ፣ ትክክለኛውን ውሳኔ በድፍረት ማድረግ እንዲችሉ ይሖዋ እምነት እንዲጨምርላቸው ጸለዩ። አንዱ ትልቅ እንቅፋት በግንባታ ላይ ያለው ቤታቸው ነበር። የሦስት ዓመት ክፍያ ከፍለዋል። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? ማሪሉ እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ውሉን ብናፈርስ እስከዚያ ጊዜ የከፈልነውን ገንዘብ በሙሉ እናጣለን፤ ገንዘቡ ደግሞ ትንሽ አልነበረም። ይሁን እንጂ ውሳኔው የይሖዋን ፈቃድ ወይም የራሳችንን ፍላጎት የማስቀደም ጉዳይ እንደሆነ ተሰማን።” ባልና ሚስቱ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሁሉንም ነገር ስለ ማጣት’ የተናገረውን በማስታወስ የቤት ግንባታውን ውል ሰረዙ፤ ሥራቸውን ለቀቁ፤ እንዲሁም አብዛኛውን ንብረታቸውን በመሸጥ ከማኒላ በስተ ደቡብ 480 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በፓላዋን ደሴት ወዳለ የገጠር መንደር ተዛወሩ።—ፊልጵ. 3:8

‘ሚስጥሩን ተምረዋል’

ግሬጎሪዮ እና ማሪሉ ወደ ገጠራማ አካባቢ ከመዛወራቸው በፊት ኑሯቸውን ቀላል በማድረግ ራሳቸውን ለማዘጋጀት ሞክረው ነበር፤ ይሁን እንጂ አዲሱ ሕይወታቸው ከቀድሞው ምን ያህል የተለየ እንደሚሆን የተገነዘቡት እዚያ ከደረሱ በኋላ ነው። “ሁኔታው ጨርሶ ያልጠበቅነው ነበር” ትላለች ማሪሉ። “የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም ኑሮን አመቺ የሚያደርጉ ሌሎች ነገሮች አልነበሩም። ሩዝ ለመቀቀል እንደ ድሯችን በኤሌክትሪክ ማብሰያ መጠቀም ስለማንችል እንጨት ፈልጠን እሳት ማቀጣጠል ነበረብን። ወደ ትላልቅ የገበያ ማዕከሎች መሄድ፣ ምግብ ቤት ሄዶ መብላትና የመሳሰሉት ትልቅ ከተማ ውስጥ ስንኖር የምናደርጋቸው ነገሮች ይናፍቁኝ ነበር።” ቢሆንም ባልና ሚስቱ ወደዚህ አካባቢ የመጡበትን ዓላማ ሁልጊዜ ለማስታወስ ጥረት ያደርጉ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ኑሮውን ለመዱት። ማሪሉ እንዲህ ትላለች፦ “አሁን አሁን፣ ማታ ላይ ደምቀው የሚታዩትን ከዋክብት ጨምሮ የተፈጥሮን ውበት በማየት እደሰታለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በምንሰብክላቸው ሰዎች ፊት ላይ የሚነበበውን ደስታ መመልከት በጣም ያስደስተኛል። እዚህ በማገልገላችን ባለን ነገር ረክተን የመኖርን ‘ሚስጥር ተምረናል።’”—ፊልጵ. 4:12

“ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ መመልከት የሚያስገኘው ደስታ ከምንም ነገር ጋር የሚወዳደር አይደለም። አሁን፣ ሕይወታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትርጉም እንዳለው ይሰማናል።”—ግሬጎሪዮ እና ማሪሉ

ግሬጎሪዮ እንዲህ ይላል፦ “እዚህ ስንመጣ አራት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። በየሳምንቱ የሕዝብ ንግግር መስጠት ስጀምርና የመንግሥቱን መዝሙር በምንዘምርበት ጊዜ በጊታር ሳጅባቸው በጣም ደስ አላቸው።” እነዚህ ባልና ሚስት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ አነስተኛ ቡድን አድጎ 24 አስፋፊዎች ያሉት እድገት የሚያደርግ ጉባኤ ሲሆን ማየት ችለዋል። ግሬጎሪዮ “የጉባኤው አባላት የሚያሳዩን ፍቅር ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል” ይላል። ግሬጎሪዮ እና ማሪሉ ርቆ በሚገኘው በዚህ አካባቢ ማገልገል ከጀመሩ ስድስት ዓመታት አልፈዋል፤ ያሳለፉትን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡ እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ መመልከት የሚያስገኘው ደስታ ከምንም ነገር ጋር የሚወዳደር አይደለም። አሁን፣ ሕይወታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትርጉም እንዳለው ይሰማናል።”

 “ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን ቀምሼ አይቻለሁ’!”

በፊሊፒንስ፣ ወደ 3,000 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚፈለጉባቸው አካባቢዎች ተዛውረዋል። ከእነዚህ መካከል 500 የሚያህሉት ነጠላ እህቶች ናቸው። ካረንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ካረን

አሁን በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ካረን ያደገችው በባጋኡ፣ ካጋያን ነው። ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች አገልግሎቷን ማስፋት ስለምትችልበት መንገድ አዘውትራ ታስብ ነበር። እንዲህ ትላለች፦ “የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነና ሁሉም ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት መስማት እንደሚያስፈልጋቸው ስለማውቅ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለማገልገል ፈለግሁ።” አንዳንድ የቤተሰቧ አባሎች ሩቅ አካባቢ ሄዳ ከማገልገል ይልቅ ከፍተኛ ትምህርት እንድትከታተል ቢያበረታቷትም ካረን ይሖዋ እንዲመራት ጸለየች። በገለልተኛ አካባቢዎች የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችንም አነጋገረች። ከዚያም 18 ዓመት ሲሆናት ካደገችበት ከተማ 64 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ገለልተኛ አካባቢ ተዛወረች።

ካረን ለማገልገል የሄደችበት ትንሽ ጉባኤ ክልል፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ተራራማ አካባቢዎችን ያካትታል። ካረን እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ከባጋኡ ተነስተን ወደ አዲሱ ጉባኤ ለመድረስ ብቻ አቀበትና ቁልቁለት ባለው መንገድ ላይ ለሦስት ቀን በእግራችን የተጓዝን ሲሆን ከ30 ጊዜ በላይ ወንዞችን አቋርጠናል።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼን ለማስጠናት ለስድስት ሰዓት በእግሬ እጓዛለሁ፤ ከዚያም እነሱ ጋር ካደርኩ በኋላ በማግሥቱ ወደ ቤቴ ለመመለስ እንደገና ለስድስት ሰዓት ያህል እጓዛለሁ።” ታዲያ ይህን ሁሉ ጥረት ማድረጓ የሚክስ እንደሆነ ይሰማታል? “አንዳንድ ጊዜ እግሮቼ በጣም ይዝላሉ” ብላለች፤ አክላ ግን “18 የሚያህሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሁበት ጊዜ አለ። ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን ቀምሼ አይቻለሁ’!” በማለት በደስታ ተናግራለች።—መዝ. 34:8

“በይሖዋ መታመንን ተማርኩ!”

ሱኪ

በ40ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ሱኪ የተባለች አንዲት ነጠላ እህት ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ፊሊፒንስ ሄዳ በዚያ ለመኖር ወሰነች፤ ይህን እንድታደርግ ያነሳሳት ምንድን ነው? በ2011 በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ አንድ ባልና ሚስት ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው አዳምጣ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ወደ ሜክሲኮ ሄደው በስብከቱ ሥራ እገዛ ለማበርከት ሲሉ አብዛኞቹን ንብረቶቻቸውን እንደሸጡ ተናግረዋል። ሱኪ “ይህን ቃለ መጠይቅ ካዳመጥኩ በኋላ ከዚያ በፊት አስቤባቸው ስለማላውቃቸው ግቦች ማሰብ ጀመርኩ” በማለት ትናገራለች። የሕንድ ዝርያ ያላት ሱኪ፣ በፊሊፒንስ ላሉ የፑንጃብ ሕዝቦች ምሥራቹን በመስበክ ረገድ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ስታውቅ ወደዚያ ለመሄድ ወሰነች። ሱኪ ያጋጠሟት እንቅፋቶች ነበሩ?

ሱኪ እንዲህ ትላለች፦ “የትኞቹን ነገሮች መሸጥና የትኞቹን ነገሮች ማስቀመጥ እንዳለብኝ መወሰን ካሰብኩት በላይ ከብዶኝ ነበር። ከዚህም ሌላ ለ13 ዓመት ያህል የኖርኩበትን ምቹ ቤቴን ትቼ ለጊዜው ከቤተሰቦቼ ጋር መኖር ጀመርኩ። እንዲህ ማድረግ ከባድ ቢሆንብኝም ወደፊት ቀለል ያለ ሕይወት ለመምራት ከወዲሁ ራሴን ለማዘጋጀት የሚያስችል ጥሩ መንገድ ነበር።” ሱኪ በፊሊፒንስ መኖር ከጀመረች በኋላስ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች  አጋጥመዋታል? “አንዳንድ ነፍሳትን በጣም እፈራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ናፍቆት ያስቸግረኝ ነበር፤ ከሁሉ በላይ የከበዱኝ እነዚህ ነገሮች ናቸው። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በይሖዋ መታመንን ተማርኩ!” ታዲያ የከፈለችው መሥዋዕት ክሷታል? ሱኪ በፈገግታ እንዲህ ትላለች፦ “ይሖዋ ‘ፈትኑኝ፤ በረከትንም የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ’ ብሎናል። አገልግሎት ላይ የማነጋግራቸው ሰዎች ‘ተመልሰሽ የምትመጪው መቼ ነው? ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ’ ሲሉኝ ይሖዋ የተናገረውን ነገር እውነተኝነት እየተመለከትሁ እንደሆነ ይሰማኛል። በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎችን መርዳት ይህ ነው የማይባል ደስታና እርካታ አስገኝቶልኛል!” (ሚል. 3:10) ሱኪ አክላም እንዲህ ትላለች፦ “ወደ ሌላ አገር ለመሄድ መወሰኑ በጣም ከብዶኝ ነበር። አንዴ ውሳኔውን ካደረግሁ በኋላ ግን ይሖዋ በሚያስገርም መንገድ ነገሮችን አመቻችቶልኛል።”

‘ፍርሃቴን አሸነፍኩ’

አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኝ ሲሜ የተባለ አንድ ባለትዳር ወንድም በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኝ አገር ውስጥ ጥሩ ሥራ ስላገኘ ከፊሊፒንስ ወደዚያ ሄደ። ሲሜ በዚያ እያለ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች የሰጠው ማበረታቻ እንዲሁም የበላይ አካል አባል የሆነ አንድ ወንድም ያቀረበው ንግግር፣ በሕይወቱ ውስጥ ይሖዋን እንዲያስቀድም አነሳሳው። ሲሜ “ሥራዬን ማቆም ግን በጣም አስፈርቶኝ ነበር” በማለት ይናገራል። ያም ቢሆን ሥራውን ትቶ ወደ ፊሊፒንስ ተመለሰ። በአሁኑ ጊዜ፣ ሲሜ እና ባለቤቱ ሃይዲ በአገሪቱ በስተ ደቡብ በሚገኝ ዳቫዉ ዴል ሱር በተባለ አካባቢ ያገለግላሉ፤ በዚህ አካባቢ ያለውን ሰፊ ክልል ለመሸፈን ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ያስፈልጋሉ። ሲሜ እንዲህ ይላል፦ “መለስ ብዬ ሳስበው፣ ሥራዬን የመልቀቅ ፍርሃቴን አሸንፌ ይሖዋን በማስቀደሜ በጣም ደስተኛ ነኝ። ካለን ነገር ሁሉ ምርጡን ለይሖዋ ከመስጠት የበለጠ በሕይወት ውስጥ የሚያረካ ነገር የለም!”

ሲሜ እና ሃይዲ

“ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልናል!”

ራሚሎ እና ጁልዬት የተባሉ በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ አቅኚ ባልና ሚስት ከሚኖሩበት ቦታ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኝ ጉባኤ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሲያውቁ ወደዚያ ለመሄድ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። ራሚሎ እና ጁልዬት የአየሩ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ሲሉ በሞተር ብስክሌታቸው ተሳፍረው በየሳምንቱ በተደጋጋሚ ወደዚህ አካባቢ ይሄዳሉ። ወጣ ገባ በሆኑ መንገዶች ላይ መጓዝ እንዲሁም ተንጠልጣይ ድልድዮችን ማቋረጥ በራሱ ፈታኝ ቢሆንም አገልግሎታቸውን በማስፋታቸው ደስተኞች ናቸው። ራሚሎ እንዲህ ይላል፦ “እኔና ባለቤቴ በአጠቃላይ 11 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን! የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ማገልገል መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልናል!”—1 ቆሮ. 15:58

ጁልዬት እና ራሚሎ

በምትኖርበት ወይም በሌላ አገር የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ስለ ማገልገል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ የወረዳ የበላይ ተመልካችህን አነጋግር፤ እንዲሁም በነሐሴ 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን “‘ወደ መቄዶንያ መሻገር’ ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።