“የይሖዋ ማሳሰቢያ እምነት የሚጣልበት ነው፤ ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል።”—መዝ. 19:7 NW

1. የአምላክ ሕዝቦች የትኞቹን ርዕሰ ጉዳዮች በተደጋጋሚ አጥንተዋል? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ጥቅም አስገኝቶልናል?

ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጅ ‘ይህን ትምህርት ከዚህ በፊት አጥንተነው የለም እንዴ?’ ብለህ ታውቃለህ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርክ የተወሰኑ ጊዜያትን ካስቆጠርክ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች በተደጋጋሚ እንደተጠኑ አስተውለህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ስለ ቤዛው፣ ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ እንዲሁም እንደ ፍቅርና እምነት ስላሉ ባሕርያት የሚቀርቡት ትምህርቶች በየጊዜው ከሚቀርቡልን መንፈሳዊ ማዕዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህን ትምህርቶች በተደጋጋሚ ማጥናታችን በእምነት ጤናሞች እንድንሆን አልፎ ተርፎም ‘ቃሉን የምናደርግ እንጂ ሰሚዎች ብቻ እንዳንሆን’ ረድቶናል።—ያዕ. 1:22

2. (ሀ) የአምላክ ማሳሰቢያዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክቱት ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ማሳሰቢያዎች ከሰብዓዊ ሕጎች የሚለዩት በምንድን ነው?

2 “ማሳሰቢያ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው አምላክ ለሕዝቡ የሚሰጣቸውን ሕጎች፣ ትእዛዛት እና ሥርዓቶች ነው። ማስተካከያና ማሻሻያ ከሚያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ሕጎች በተቃራኒ የይሖዋ ሕጎችና ሥርዓቶች ምንጊዜም እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ማሳሰቢያዎች የተሰጡት ለተወሰነ ጊዜ ወይም አንድን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ስለሆነ በዛሬው ጊዜ ማሳሰቢያዎቹን ተግባራዊ ማድረግ አይጠበቅብንም፤ ይህ ማለት ግን ማሳሰቢያዎቹ እንከን አለባቸው ማለት አይደለም። መዝሙራዊው “ማሳሰቢያህ ለዘላለም ጽድቅ ነው” ብሏል።—መዝ. 119:144 NW

3, 4. (ሀ) የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ምን ነገር ሊያካትቱ ይችላሉ? (ለ) እስራኤላውያን ማሳሰቢያዎቹን ተግባራዊ ካደረጉ ምን ጥቅም ማግኘት ይችሉ ነበር?

3 የይሖዋ ማሳሰቢያዎች አንዳንድ ጊዜ የማስጠንቀቂያ መልእክቶችንም እንደሚያካትቱ ሳታስተውል አልቀረህም። አምላክ በነቢያቱ በኩል ለእስራኤል ብሔር በየጊዜው ማስጠንቀቂያ ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ ሙሴ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ተታላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም። ከዚያም የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነዳል።” (ዘዳ. 11:16, 17)  አምላክ ለሕዝቡ አሌ የማይባሉ ጠቃሚ ማሳሰቢያዎችን እንደሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል።

4 ይሖዋ በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎችም እሱን እንዲፈሩ፣ ድምፁን እንዲሰሙና ስሙን እንዲቀድሱ እስራኤላውያንን አጥብቆ መክሯቸዋል። (ዘዳ. 4:29-31፤ 5:28, 29) ሕዝቡ እነዚህን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ካደረጉ ብዙ በረከቶችን ያገኙ እንደነበር የተረጋገጠ ነው።—ዘሌ. 26:3-6፤ ዘዳ. 28:1-4

እስራኤላውያን ለአምላክ ማሳሰቢያዎች ምን ምላሽ ሰጡ?

5. ይሖዋ ለንጉሥ ሕዝቅያስ የተዋጋው ለምንድን ነው?

5 አምላክ፣ የእስራኤል ሕዝብ ደጉንም ሆነ ክፉውን ባሳለፈበት ዘመን ሁሉ ለእነሱ የገባውን ቃል ጠብቋል። ለምሳሌ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ይሁዳን በመውረር ንጉሥ ሕዝቅያስን ከሥልጣን ለማውረድ በዛተበት ጊዜ ይሖዋ አንድ መልአክ በመላክ ጣልቃ ገብቷል። መልአኩ በአንድ ምሽት ብቻ በአሦር ሠራዊት ውስጥ የነበሩትን ‘ጽኑዓንና ኃያላን’ በሙሉ በመግደሉ፣ ሰናክሬም የኀፍረት ማቅ ተከናንቦ ወደ አገሩ ለመመለስ ተገድዷል። (2 ዜና 32:21 የ1954 ትርጉም፤ 2 ነገ. 19:35) ይሖዋ ለንጉሥ ሕዝቅያስ የተዋጋው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሕዝቅያስ ‘ከአምላክ ጋር ተጣብቆ ነበር፤ እንዲሁም እሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም።’—2 ነገ. 18:1, 5, 6

የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ኢዮስያስ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲያሳይ አነሳስተውታል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)

6. ንጉሥ ኢዮስያስ በይሖዋ መታመኑን ያሳየው እንዴት ነው?

6 የይሖዋን መመሪያ በመታዘዝ ረገድ ምሳሌ የሚሆነን ሌላው ሰው ደግሞ ንጉሥ ኢዮስያስ ነው። ገና በለጋ ዕድሜው ማለትም ከስምንት ዓመቱ አንስቶ በይሖዋ “ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም” አላለም። (2 ዜና 34:1, 2) ኢዮስያስ ምድሪቱን ከጣዖት አምልኮ በማንጻትና እውነተኛውን አምልኮ መልሶ በማቋቋም በይሖዋ እንደሚታመን አሳይቷል። እንዲህ በማድረጉ እሱ ብቻ ሳይሆን መላው ብሔርም ተባርኳል።—2 ዜና መዋዕል 34:31-33ን አንብብ።

7. እስራኤላውያን የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ችላ ሲሉ ምን ያጋጥማቸው ነበር?

7 የሚያሳዝነው ግን የአምላክ ሕዝቦች በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያልታመኑባቸው ጊዜያት ነበሩ። አንዴ ሲታዘዙ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሲያምፁ ለብዙ ዘመናት ቆይተዋል። እምነታቸው መዳከም ሲጀምር በአብዛኛው ልክ ጳውሎስ እንደተናገረው ‘በማንኛውም የትምህርት ነፋስ የሚንገዋለሉና ወዲያና ወዲህ የሚሉ’ ይሆናሉ። (ኤፌ. 4:13, 14) በመሆኑም በአምላክ ማሳሰቢያዎች ላይ እምነት መጣል ሲያቆሙ አስቀድሞ በተነገራቸው መሠረት አስከፊ መዘዝ ያጭዱ ነበር።—ዘሌ. 26:23-25፤ ኤር. 5:23-25

8. ከእስራኤላውያን ምሳሌ ምን እንማራለን?

8 ታዲያ ከእስራኤላውያን ምሳሌ ምን እንማራለን? እንደ እስራኤላውያን ሁሉ በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም ምክርና ተግሣጽ ይሰጣቸዋል። (2 ጴጥ. 1:12) በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ባነበብን ቁጥር ማሳሰቢያ እናገኛለን። የመምረጥ ነፃነት ያለን ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን የይሖዋን መመሪያዎች ለመታዘዝ አሊያም  ቀና መስሎ የሚታየንን መንገድ ለመከተል መምረጥ እንችላለን። (ምሳሌ 14:12) እስቲ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ላይ እምነት መጣል ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም እነዚህን ማሳሰቢያዎች በሥራ ላይ ማዋል ምን ጥቅም እንዳለው እንመልከት።

በሕይወት እንድትኖሩ ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ

9. እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚጓዙበት ወቅት ይሖዋ ከጎናቸው መሆኑን ያረጋገጠላቸው እንዴት ነው?

9 እስራኤላውያን “ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ” ውስጥ ያደረጉትን 40 ዓመት የፈጀውን አድካሚ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ይሖዋ እንዴት እንደሚመራቸው፣ እንደሚጠብቃቸውና እንደሚንከባከባቸው በዝርዝር አልነገራቸውም። ያም ሆኖ በእሱም ሆነ በሚሰጣቸው መመሪያዎች መታመን እንዳለባቸው የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን በተለያዩ ጊዜያት አሳይቷቸዋል። ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመምራት በቀን የዳመና ዓምድ በማታ ደግሞ የእሳት ዓምድ መጠቀሙ፣ አስቸጋሪ በሆነው የምድረ በዳ ጉዟቸው ወቅት ምንጊዜም ከጎናቸው እንደሆነ አስታውሷቸዋል። (ዘዳ. 1:19፤ ዘፀ. 40:36-38) ከዚህም በተጨማሪ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን አሟልቶላቸዋል። “ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።” በእርግጥም “ምንም ያጡት [ነገር] አልነበረም።”—ነህ. 9:19-21

10. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቡን እየመራ ያለው እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜ የምንኖር የአምላክ ሕዝቦች ወደ አዲሱ ዓለም ለመግባት ተቃርበናል። ታዲያ ከመጪው “ታላቅ መከራ” በሕይወት ለመትረፍ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያሟላልን እንተማመናለን? (ማቴ. 24:21, 22፤ መዝ. 119:40, 41) እውነት ነው፣ ይሖዋ እኛን ወደ አዲሱ ዓለም ለመምራት የዳመና ወይም የእሳት ዓምድ አላዘጋጀም። ይሁንና ምንጊዜም ንቁዎች እንድንሆን ለማሳሰብ ድርጅቱን ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን በማንበብ፣ የቤተሰብ አምልኮ በማድረግ እንዲሁም በስብሰባና በአገልግሎት አዘውትረን በመካፈል መንፈሳዊነታችንን እንድናጠናክር በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጠን ቆይቷል። ታዲያ እነዚህን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርገናል? እንዲህ ማድረጋችን በሕይወት ተርፈን ወደ አዲሱ ዓለም ለመግባት የሚያስችል እምነት እንድናዳብር ይረዳናል።

የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ማድረጋችን የመንግሥት አዳራሻችን ምቹና ለአደጋ የማያጋልጥ እንዲሆን የበኩላችንን ሚና እንድንጫወት ያነሳሳናል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. አምላክ ለእኛ እንደሚያስብ ካሳየባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

11 የምናገኛቸው ማሳሰቢያዎች በመንፈሳዊ ንቁ እንድንሆን ከመርዳት ባሻገር ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይጠቅሙናል። ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበርና አጥርቶ የሚያይ ዓይን መያዝ ጭንቀትን ለመቀነስ እንደሚረዳ የተሰጠንን ምክር እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም ስለ አለባበስና አጋጌጥ፣ ጤናማ መዝናኛ ስለ መምረጥ ብሎም ዓለማዊ ትምህርትን እስከ ምን ድረስ መከታተል እንዳለብን ከተሰጡን መመሪያዎች ጥቅም አግኝተናል። ከቤታችን፣ ከመኪናችን፣ ከመንግሥት አዳራሽና ለአደጋ ጊዜ ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ጋር በተያያዘ የተሰጡን የደኅንነት ማሳሰቢያዎችም ቢሆኑ ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። ይሖዋ እነዚህን ማሳሰቢያዎች መስጠቱ የእኛ ደኅንነት እንደሚያሳስበው ያሳያል።

ማሳሰቢያዎች የጥንት ክርስቲያኖች ምንጊዜም ታማኝ እንዲሆኑ ረድተዋቸዋል

12. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በተደጋጋሚ ከመከራቸው ጉዳዮች አንዱ የትኛው ነው? (ለ) ለጴጥሮስ የማይረሳ ትምህርት የሰጠው የትኛው የትሕትና ተግባር ነው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?

12 አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለሕዝቦቹ በየጊዜው ማሳሰቢያዎችን ይሰጥ ነበር። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የትሕትናን ባሕርይ እንዲኮተኩቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት ነግሯቸዋል። ትሑት መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በቃል ብቻ ከመንገር ባለፈ በተግባር አሳይቷቸዋል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ የፋሲካ በዓልን ለማክበር ከሐዋርያቱ ጋር ተሰብስቦ ነበር። ሐዋርያቱ በመመገብ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ከገበታ ላይ ተነስቶ እግራቸውን በማጠብ ብዙውን ጊዜ አንድ አገልጋይ የሚያከናውነውን ተግባር ፈጽሟል። (ዮሐ. 13:1-17) በዚህ መንገድ ስለ ትሕትና ከአእምሯቸው የማይፋቅ ትምህርት ሰጣቸው። በዚያ ዕለት በቦታው ተገኝቶ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ለእምነት ባልንጀሮቹ ስለ ትሕትና ትምህርት ሰጥቷቸው ነበር። (1 ጴጥ. 5:5)  የኢየሱስ ምሳሌነት እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ ሁላችንም ትሑቶች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል።—ፊልጵ. 2:5-8

13. ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የትኛውን አስፈላጊ ባሕርይ እንዲያዳብሩ አሳስቧቸዋል?

13 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ከነገራቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ሌላኛው ጠንካራ እምነት የማዳበር አስፈላጊነት ነው። ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ልጅ ውስጥ ያደረውን ጋኔን ማስወጣት ባቃታቸው ጊዜ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። እሱም ሲመልስ “እምነታችሁ ስላነሰ ነው። እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል እምነት ካላችሁ [የሚሳናችሁ] ነገር አይኖርም” ብሏቸዋል። (ማቴ. 17:14-20) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ እምነት በጣም አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ መሆኑን አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 21:18-22ን አንብብ።) እኛስ በአውራጃ፣ በወረዳ፣ በልዩ ብሎም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡልን መመሪያዎች አማካኝነት እምነታችንን እንድናጠናክር ከተደረገልን ዝግጅት በሚገባ እየተጠቀምን ነው? እነዚህ ስብሰባዎች አብረን አስደሳች ጊዜ እንድናሳልፍ ብቻ ታስበው የተደረጉ ዝግጅቶች አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት የምናሳይባቸው አጋጣሚዎች ናቸው።

14. በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ያሳየው ዓይነት ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ በሚያበረታቱ ማሳሰቢያዎች የተሞሉ ናቸው። ኢየሱስ ሁለተኛው ታላቅ ትእዛዝ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 22:39) የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብም ፍቅርን “ንጉሣዊ ሕግ” በማለት ጠርቶታል። (ያዕ. 2:8) ሐዋርያው ዮሐንስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የምጽፍላችሁ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበራችሁን የቆየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም” ብሏል። (1 ዮሐ. 2:7, 8) ዮሐንስ ‘የቆየ ትእዛዝ’ በማለት የተናገረው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ዮሐንስ እየተናገረ ያለው የፍቅርን ትእዛዝ አስመልክቶ ነው። “የቆየ” የተባለው ኢየሱስ ትእዛዙን የሰጠው “ከመጀመሪያ ጀምሮ” ማለትም ከአሥርተ ዓመታት በፊት ስለነበረ ነው። “አዲስ” የተባለው ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀውን ይህን ፍቅር ማሳየት ስለሚያስፈልጋቸው ነው። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን፣ ይህን ዓለም ለይቶ የሚያሳውቀውንና ለሰዎች ያለን ፍቅር እንዲጠፋ የሚያደርገውን የራስ ወዳድነት መንፈስ ከማዳበር እንድንጠበቅ የሚረዳ ማስጠንቀቂያ በማግኘታችን አድናቂዎች ልንሆን አይገባም?

15. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?

15 ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች አሳቢነት ያሳይ ነበር። የታመሙትን መፈወሱና የሞቱትን ማስነሳቱ ይህን ያሳያል። ይሁንና ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ ሰዎችን ከበሽታ ለመፈወስ አይደለም። ለሰዎች የላቀ ጥቅም ያስገኘው በስብከቱና በማስተማሩ  ሥራ መጠመዱ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የፈወሳቸውና ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ውሎ አድሮ አርጅተው ከመሞት አላመለጡም፤ ለሚሰብከው መልእክት ጆሮ የሰጡት ግን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።—ዮሐ. 11:25, 26

16. የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ምን ያህል በስፋት እየተከናወነ ነው?

16 ኢየሱስ በአንደኛው መቶ ዘመን የጀመረው የስብከቱ ሥራ በዛሬው ጊዜ በስፋት እየተከናወነ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ በማለት አዟቸው ነበር። (ማቴ. 28:19) ደቀ መዛሙርቱም ይህን ትእዛዝ ፈጽመዋል፤ እኛም ብንሆን አፋችንን ሞልተን ትእዛዙን ፈጽመናል ማለት እንችላለን! ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እያወጁ ነው፤ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠኑ ነው። ይህ የስብከቱ ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመኖራችን ማስረጃ ነው።

በዛሬው ጊዜም በይሖዋ መታመን

17. ጳውሎስና ጴጥሮስ ምን ምክር ሰጥተዋል?

17 የጥንት ክርስቲያኖች ማሳሰቢያ ማግኘታቸው በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ እንደረዳቸው በግልጽ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ጢሞቴዎስ በሮም እስረኛ ከነበረው ከሐዋርያው ጳውሎስ “ከእኔ የሰማሃቸውን ጤናማ ቃላት ንድፍ . . . አጥብቀህ ያዝ” የሚል መልእክት ሲደርሰው ምን ያህል ተበረታትቶ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። (2 ጢሞ. 1:13) ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹ እንደ ጽናት፣ ወንድማዊ መዋደድና ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ካበረታታቸው በኋላ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በውስጣችሁ በሚገኘው እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም።”—2 ጴጥ. 1:5-8, 12

18. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ማሳሰቢያ ሲሰጣቸው ምን ይሰማቸው ነበር?

18 አዎ፣ ጳውሎስና ጴጥሮስ ለጉባኤዎች የጻፏቸው መልእክቶች “ቀደም ሲል ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃል” የሚያስተላልፉ ናቸው። (2 ጴጥ. 3:2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንድሞቻችን እነዚህን መመሪያዎች በማግኘታቸው ቅር ተሰኝተው ይሆን? በፍጹም፣ ‘በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ’ የሚረዷቸው ስለሆኑ የአምላክ ፍቅር መገለጫ እንደሆኑ አውቀው ነበር።—2 ጴጥ. 3:18

19, 20. ይሖዋ በሚሰጠን ማሳሰቢያዎች ላይ እምነት መጣል የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

19 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ እንከን በማይወጣለት ቃሉ ውስጥ ባሰፈራቸው ማሳሰቢያዎች ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። (ኢያሱ 23:14ን አንብብ።) በሺህ በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ አምላክ ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች እንዴት እንደያዘ የሚናገሩ ታሪኮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ታሪካዊ ዘገባዎች ለጥቅማችን ሲባል ተመዝግበው ተቀምጠዋል። (ሮም 15:4፤ 1 ቆሮ. 10:11) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙም ተመልክተናል። እነዚህን ትንቢቶች፣ አስቀድሞ እንደተነገሩ ማሳሰቢያዎች ልናያቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ጎርፈዋል፤ ይህ ደግሞ ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ እንደሚፈጸም አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኢሳ. 2:2, 3) የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እያገኘ እንዳለ የሚጠቁም ነው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰውም በዓለም ዙሪያ ሰፊ የስብከት ዘመቻ መካሄዱ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ቀጥተኛ ፍጻሜ እያገኘ እንደሆነ ያሳያል።—ማቴ. 24:14

20 ፈጣሪያችን እምነት ልንጥልበት የምንችል ዘገባ በቃሉ ውስጥ እንዲቀመጥልን አድርጓል። ታዲያ በቃሉ ውስጥ ከሰፈረው ዘገባ ጥቅም እያገኘን ነው? በማሳሰቢያዎቹ ላይ እምነት መጣል ይገባናል። ሮሰሊን የተባለች አንዲት እህት ያደረገችው ይህንን ነው። እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት መጣል ስጀምር በፍቅር ተነሳስቶ እኔን ለመመገብና ለማበርታት እጁን እንደዘረጋልኝ ይበልጥ ግልጽ ሆነልኝ።” እኛም ይሖዋ ከሚሰጠን ማሳሰቢያ ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።