በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

አቅኚነት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክርልናል

አቅኚነት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክርልናል

“አምላካችንን . . . ማወደስ እንዴት መልካም ነው።”—መዝ. 147:1

1, 2. (ሀ) ስለምንወደው ሰው ማሰባችንና ማውራታችን ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ስለምንወደው ሰው ማሰባችንና ማውራታችን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደርጋል። ከይሖዋ አምላክ ጋር ካለን ዝምድና ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ዳዊት በእረኝነት ባሳለፋቸው ጊዜያት ምሽት ላይ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ የመመልከትና ተወዳዳሪ ስለሌለው ፈጣሪ የማሰላሰል ልማድ ነበረው። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ. 8:3, 4) ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን ይሖዋ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ እንዴት አስደናቂ በሆነ መንገድ እየፈጸመ እንደሆነ ካሰላሰለ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!”—ሮም 11:17-26, 33

2 እኛም በአገልግሎት ስንካፈል ስለ ይሖዋ ማሰባችንና ስለ እሱ ለሰዎች መናገራችን አይቀርም። ይህ በራሱ በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እየተካፈሉ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች በመንግሥቱ ሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ ማድረጋቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ጥልቀት ያለው እንዲሆን እንደረዳቸው ይሰማቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈልክ ከሆነ አሊያም ወደዚህ ግብ ለመድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ከሆንክ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ማሰላሰልህ ተገቢ ነው፦ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና የሚያጠናክረው እንዴት ነው? አቅኚ ከሆንክ ደግሞ ‘ከፍተኛ ወሮታ በሚያስገኘው በዚህ የአገልግሎት መስክ ለመቀጠል የሚረዳኝ ምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ገና በአቅኚነት መካፈል ካልጀመርክ ደግሞ ‘በዚህ የአገልግሎት መስክ ለመካፈል ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

 የሙሉ ጊዜ አገልግሎትና ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና

3. መንግሥቱ ስለሚያመጣቸው በረከቶች በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች መናገራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

3 መንግሥቱ የሚያመጣቸውን በረከቶች ለሰዎች መናገራችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ብዙ ጊዜ የምትጠቀመው የትኛውን ጥቅስ ነው? ምናልባት ከምትወዳቸው ጥቅሶች መካከል መዝሙር 37:10, 11፤ ዳንኤል 2:44፤ ዮሐንስ 5:28, 29 ወይም ራእይ 21:3, 4 ይገኙበት ይሆናል። እንዲህ ያሉ ተስፋዎችን ለሰዎች በተናገርን ቁጥር ለጋሱ አምላካችን ‘የመልካም ስጦታና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ መሆኑን እንድናስታውስ ያደርገናል። ይህ ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።—ያዕ. 1:17

4. ሰዎች በመንፈሳዊ እየተራቡ እንደሆነ መመልከታችን የአምላክን ጥሩነት ይበልጥ እንድናደንቅ የሚያደርገን እንዴት ነው?

4 በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ምን ያህል በመንፈሳዊ እንደተራቡ ስንመለከት ለእውነት ያለን አድናቆት ይጨምራል። በዓለም ያሉ ሰዎች ስኬታማና ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችላቸው አስተማማኝ መመሪያ የላቸውም። ብዙዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚጨነቁ ከመሆኑም ሌላ ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ ለማወቅም ጥረት ያደርጋሉ። ሃይማኖተኛ የሆኑ አብዛኞቹ ሰዎችም እንኳ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ምንም እውቀት የላቸውም ማለት ይቻላል። ያሉበት ሁኔታ በጥንቷ ነነዌ ከነበሩ ሰዎች ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። (ዮናስ 4:11ን አንብብ።) በስብከቱ ሥራ የምናሳልፈው ጊዜ ከፍ ያለ ከሆነ በአገልግሎት የምናገኛቸው ሰዎች ያሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ የይሖዋ ሕዝቦች ካሉበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው በግልጽ ማየት እንችላለን። (ኢሳ. 65:13) እርግጥ ይሖዋ የሚንከባከበው ሕዝቦቹን ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው መንፈሳዊ ማጽናኛና እውነተኛ ተስፋ እንዲያገኝ አጋጣሚውን ሰጥቷል፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ ምን ያህል ጥሩ አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል።—ራእይ 22:17

5. ሌሎችን በመንፈሳዊ መርዳት የራሳችንን ችግር ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

5 ሌሎችን በመንፈሳዊ መርዳት ስለ ራሳችን ችግሮች በማሰብ እንዳንዋጥ ያደርገናል። ትሪሻ የተባለች አንዲት የዘወትር አቅኚ ወላጆቿ በተፋቱበት ጊዜ የዚህን እውነተኝነት በሕይወቷ ተመልክታለች። “በሕይወቴ ውስጥ ስሜቴ በጣም ከተጎዳባቸው ወቅቶች አንዱ ነበር” በማለት ተናግራለች። አንድ ቀን ትሪሻ በጣም ከማዘኗ የተነሳ ቤት ለመዋል ፈልጋ ነበር፤ ይሁንና እንደምንም ብላ ጥናት ለመምራት ሄደች። የምታስጠናቸው ሦስት ልጆች በቤት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ነበረባቸው። አባታቸው ጥሏቸው የሄደ ሲሆን ታላቅ ወንድማቸው ደግሞ ብዙ በደል ያደርስባቸው ነበር። ትሪሻ እንዲህ ብላለች፦ “የደረሰብኝ መከራ ከእነሱ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የሚችል አይደለም። እያጠናን ሳለ ጭፍግግ ብሎ የነበረው ፊታቸው በደስታ አበራ፤ እንዲሁም ፍንድቅድቅ ማለት ጀመሩ። እነዚያ ልጆች በተለይ በዚያ ቀን ለእኔ ከይሖዋ እንደተሰጠኝ ስጦታ ሆነውልኛል።”

6, 7. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ስናስተምር እምነታችንን የሚጠናከረው እንዴት ነው? (ለ) ጥናቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ሕይወታቸው እንደተሻሻለ ስንመለከት ለአምላክ ጥበብ ያለን አድናቆት ምን ይሆናል?

6 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ማስተማር እምነታችንን ያጠናክረዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚሰብኩትን ነገር በሥራ ላይ ሳያውሉ ስለቀሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ሲጽፍ “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም?” ብሏል። (ሮም 2:21) በዛሬው ጊዜ ያሉ አቅኚዎች ከእነዚህ ሰዎች እጅግ የተለዩ ናቸው! በአብዛኛው እውነትን ለሌሎች የሚያስተምሩባቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሏቸው። ይህን ኃላፊነታቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት ለእያንዳንዱ ጥናት በሚገባ መዘጋጀት ምናልባትም ጥያቄዎችን ለመመለስ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ጄኒን የተባለች አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ለሌሎች ባስተማርኩ ቁጥር እነዚህ እውነቶች በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ ይበልጥ ሥር እየሰደዱ እንደሚሄዱ ይሰማኛል። ከዚህም የተነሳ እምነቴ ባለበት ከመቀጠል ይልቅ እያደገ መሄድ ችሏል።”

7 ጥናቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ሕይወታቸው ሲሻሻል መመልከታችን የአምላክን ጥበብ ይበልጥ እንድናደንቅ ያደርገናል። (ኢሳ. 48:17, 18) ይህ ደግሞ እኛም  እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ለማዋል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። አድሪያና የተባለች አንዲት አቅኚ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች በራሳቸው ጥበብ የሚመሩ ከሆነ ሕይወታቸው ሊመሰቃቀል ይችላል። በይሖዋ ጥበብ መመካት ሲጀምሩ ግን ወዲያውኑ ጥቅም ማግኘታቸው አይቀርም።” ፊል የተባለ አቅኚም ቢሆን በተመሳሳይ እንዲህ ብሏል፦ “በራሳቸው ለመለወጥ ጥረት አድርገው ያልተሳካላቸውን ሰዎች ይሖዋ እንዴት እንደሚለውጣቸው ማየት ትችላላችሁ።”

8. ከሌሎች ጋር በአገልግሎት ጥሩ ጊዜ ማሳለፋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

8 ከሌሎች ጋር በአገልግሎት ጥሩ ጊዜ ማሳለፋችን በመንፈሳዊ እንድንበረታታ ያደርገናል። (ምሳሌ 13:20) አብዛኛውን ጊዜ አቅኚዎች ከሌሎች ጋር በወንጌላዊነቱ ሥራ በመካፈል ሰፋ ያለ ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህ ደግሞ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የተሻለ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (ሮም 1:12፤ ምሳሌ 27:17ን አንብብ።) ሊሳ የተባለች አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “በሥራ ቦታ መፎካከርና መቀናናት የተለመደ ነገር ነው። ሁልጊዜ የምትውሉት ሐሜትና ጸያፍ ንግግር ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ነው። ዓላማቸው የተከፈለው መሥዋዕት ተከፍሎ ሌላውን ቀድሞ መሄድ ነው። አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያናዊ ምግባራችሁ ምክንያት ሊሾፍባችሁ ወይም ሊቀለድባችሁ ይችላል። ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ማገልገል ግን በጣም ያበረታታል። አገልግሎት ውዬ ወደ ቤት ስመለስ በጣም ቢደክመኝም እንኳ ከፍተኛ እርካታ ይሰማኛል።”

9. ከትዳር ጓደኛችን ጋር በአቅኚነት አብረን መካፈላችን በሦስት የተገመደውን የጋብቻ ትስስር ምን ያደርገዋል?

9 ከትዳር ጓደኛችን ጋር በአቅኚነት መካፈላችን በሦስት የተገመደውን የጋብቻ ትስስር ያጠናክረዋል። (መክ. 4:12) ከባለቤቷ ጋር በአቅኚነት የምታገለግለው ማደሊን እንዲህ ትላለች፦ “እኔና ባለቤቴ በአገልግሎት ያሳለፍነውን ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ያገኘነውን በአገልግሎት ልንሠራበት የምንችል አንድ ነጥብ አንስተን እንጫወታለን። በየዓመቱ በአቅኚነት አብረን ስናገለግል ይበልጥ እንቀራረባለን።”  በተመሳሳይም ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ትሪሻ እንዲህ ብላለች፦ “ትኩረታችን ያረፈው ዕዳ ውስጥ በሚጨምሩን ነገሮች ላይ ባለመሆኑ ስለ ገንዘብ አንጨቃጨቅም። የአገልግሎት ፕሮግራማችን አንድ ዓይነት ስለሆነ አብረን ተመላልሶ መጠየቅ እናደርጋለን፤ እንዲሁም ጥናት እንመራለን። ይህ ደግሞ በስሜትም ሆነ በመንፈሳዊ እኩል እየበሰልን እንድንሄድ ረድቶናል።”

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በቅንዓት መካፈል አርኪ ሕይወት ለመኖር ይረዳል (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

10. ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ስናስቀድምና የይሖዋን እጅ በሕይወታችን ስንመለከት በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ምን ይሆናል?

10 ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ስናስቀድም፣ የይሖዋን እጅ በሕይወታችን ስንመለከትና ለጸሎታችን ምላሽ እንደሚሰጠን ስንገነዘብ በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ይጨምራል። ሁሉም ክርስቲያኖች በአምላክ ላይ ትምክህት እንዳላቸው የተረጋገጠ ነው። በተለይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በይሖዋ ላይ መታመናቸው በአቅኚነት አገልግሎት እንዲቀጥሉ ኃይል ይሰጣቸዋል። (ማቴዎስ 6:30-34ን አንብብ።) ከርት የተባለ በአቅኚነትና በተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግል አንድ ወንድም ከቤቱ ሁለት ሰዓት ተኩል የሚያስኬድ አንድ ጉባኤ እንዲጎበኝ ተጠየቀ። በዚህ ጊዜ፣ እንደ እሱ አቅኚ ከሆነችው ሚስቱ ጋር ወደተመደበበት ጉባኤ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነ፤ ይሁንና የመኪናቸው ነዳጅ እንደምንም ቢያደርሳቸውም ሊመልሳቸው ግን አይችልም ነበር፤ ደሞዙን የሚያገኘው ደግሞ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር። ከርት “ውሳኔዬ ትክክል መሆኑን መጠራጠር ጀመርኩ” በማለት ተናግሯል። በጉዳዩ ላይ ከጸለዩበት በኋላ ይሖዋ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ስለተማመኑ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚችሉ ተሰማቸው። ከቤት ሊወጡ ሲሉ አንዲት እህት ደውላ ስጦታ እንዳዘጋጀችላቸው ነገረቻቸው። ስጦታው ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በትክክል የሚሸፈን ነበር። ከርት እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ የመሰሉ ተሞክሮዎች በየጊዜው ሲያጋጥሟችሁ በይሖዋ መታመን ቀላል ይሆንላችኋል።”

11. አቅኚዎች ከሚያገኟቸው በረከቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

11 አቅኚዎች ለይሖዋ አገልግሎት ራሳቸውን ሲያቀርቡና ከእሱ ጋር የመሠረቱትን የጠበቀ ዝምድና ሲያጠናክሩ ማለቂያ የሌለው በረከት ያገኛሉ። (ዘዳ. 28:2) ያም ሆኖ አቅኚነት የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። ማናችንም ብንሆን የአዳም ዓመፅ ካስከተላቸው ችግሮች ነፃ አይደለንም። አንዳንዶች አቅኚነታቸውን ለጊዜው ማቋረጥ እንዳለባቸው ቢሰማቸውም አብዛኛውን ጊዜ ችግሮቹን ተቋቁሞ መቀጠል አልፎ ተርፎም ማስወገድ ይችሉ ይሆናል። ታዲያ አቅኚዎች ይህን ውድ መብታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል

12, 13. (ሀ) አንድ አቅኚ የሰዓት ግቡ ላይ መድረስ ካቃተው ምን ማድረግ ይኖርበታል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ፣ የግል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 አብዛኞቹ አቅኚዎች ፕሮግራማቸው የተጣበበ ነው። ከዚህ አንጻር ያቀዱትን ሁሉ ማከናወን ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ስለሚችል በሚገባ የተደራጁ መሆናቸው አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) በመሆኑም አንድ አቅኚ የሰዓት ግቡ ላይ መድረስ ካቃተው ጊዜውን እንዴት እየተጠቀመበት እንዳለ ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል። (ኤፌ. 5:15, 16) ራሱን እንዲህ በማለት ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘በመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ አጠፋለሁ? ራሴን በመግዛት ረገድ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆን? ከሥራ ሰዓቴ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ማድረግ እችላለሁ?’ አንድ ሰው ሳይታወቀው ፕሮግራሙን በሚያጣብቡ እንቅስቃሴዎች ሊጠመድ እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ስለዚህ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ሁሉ በየጊዜው ፕሮግራማቸውን መመርመርና አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

13 በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ የግል ጥናት ማድረግና ማሰላሰል አንድ አቅኚ በፕሮግራሙ ውስጥ ሊያካትታቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ከዚህ አንጻር አንድ አቅኚ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች፣ ከላይ እንደተዘረዘሩት ላሉ ይበልጥ አስፈላጊ ነገሮች የመደበውን ጊዜ እንዳይሻሙበት ከፈለገ ራሱን መግዛቱ አስፈላጊ ነው። (ፊልጵ. 1:10) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አቅኚ ረጅም ሰዓት በአገልግሎት አሳልፎ ወደ ቤት ተመለሰ እንበል። ምሽት ላይ የጉባኤ ዝግጅት ሊያደርግ አስቧል። በቅድሚያ ግን የተላኩለትን ደብዳቤዎች መመልከት ጀመረ። ከዚያም ኮምፒውተሩን ከፍቶ ኢ-ሜይሉን ያነብብና መልስ ይጽፋል። አንዴ ኢንተርኔት መጠቀም ከጀመረ  አይቀር በዚያው ለመግዛት የሚፈልገው አንድ ዕቃ ዋጋው ቀንሶ እንደሆነ ይመለከታል። በዚህ ሁኔታ ምንም ሳያስበው ሁለት ሰዓት አለፈ፤ ለዚያ ምሽት ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ግን ጥናቱን አልጀመረም። ይሁንና ይህ ምን ችግር አለው? ፕሮፌሽናል አትሌቶች በስፖርቱ ረጅም ጊዜ መቆየት ከፈለጉ ሰውነታቸውን መንከባከብ ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይም አቅኚዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጽናት ከፈለጉ ጥሩ የግል ጥናት ልማድ በማዳበር መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል።—1 ጢሞ. 4:16

14, 15. (ሀ) አቅኚዎች አኗኗራቸውን ቀላል ማድረግ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ አቅኚ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

14 ስኬታማ የሆኑ አቅኚዎች አኗኗራቸውን ቀላል ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ኢየሱስ አጥርቶ የሚያይ ዓይን እንዲኖራቸው ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 6:22) እሱ ራሱም አገልግሎቱን ሲያከናውን ምንም ነገር ትኩረቱን እንዳይከፋፍልበት ሲል አኗኗሩን ቀላል አድርጓል። በዚህም የተነሳ “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም መስፈሪያ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 8:20) የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚፈልግ አንድ አቅኚ ቁሳዊ ነገሮችን ባበዛ ቁጥር እነሱን ለመንከባከብ፣ ለመጠገን ወይም በሌላ ለመተካት የሚያጠፋው ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር ማስታወስ አለበት።

15 አቅኚዎች ይህን የአገልግሎት መብት ያገኙት ከሌሎች የተሻሉ ስለሆኑ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ከዚህ ይልቅ ማናችንም ብንሆን ስጦታ ወይም የአገልግሎት መብት ስንቀበል በይሖዋ ጸጋ እንዳገኘነው ማሰብ ይኖርብናል። በመሆኑም አንድ አቅኚ በዚህ የአገልግሎት መስክ ለመቀጠል በይሖዋ ላይ ትምክህት ማሳደር ይኖርበታል። (ፊልጵ. 4:13) እርግጥ ነው፣ አቅኚዎች አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው የታወቀ ነው። (መዝ. 34:19) በዚህ ጊዜ አቅኚዎች ይህን የአገልግሎት መብታቸውን ለመተው ከመቸኮል ይልቅ ይሖዋ አመራር እንዲሰጣቸውና እንዲረዳቸው አጋጣሚውን መስጠት ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 37:5ን አንብብ።) አምላክ የሚያደርግላቸውን ፍቅራዊ እንክብካቤ በሕይወታቸው እየተመለከቱ ሲሄዱ ደግሞ አፍቃሪ ወደሆነው የሰማዩ አባታቸው ይበልጥ ይቀርባሉ።—ኢሳ. 41:10

አቅኚ መሆን ትችላለህ?

16. አቅኚ መሆን ከፈለግክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

16 አንተም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚያጣጥሙትን የተትረፈረፈ በረከት ማግኘት ከፈለግክ ይህን ፍላጎትህን ለይሖዋ በጸሎት ንገረው። (1 ዮሐ. 5:14, 15) በአሁኑ ጊዜ በአቅኚነት የሚያገለግሉትን አማክራቸው። ወደ አቅኚነት የሚያሸጋግሩ ግቦችን አውጣ። ኪትና ኤሪካ ያደረጉት ይህንኑ ነው። የሙሉ ቀን ሠራተኞች የነበሩ ሲሆን በእነሱ ዕድሜ እንደሚገኙ በርካታ ባለትዳሮች ሁሉ ልክ እንደተጋቡ ቤትና አዲስ መኪና ገዙ። እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህን ነገሮች እርካታ ያስገኙልናል ብለን አስበን ነበር፤ ሆኖም እንዳሰብነው አልሆነም።” ኪት ከሥራ ሲቀነስ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። እንዲህ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል፦ “አቅኚነት፣ በአገልግሎት መካፈል ምን ያህል ደስታ እንደሚያስገኝ አስገንዝቦኛል።” ኪትና ኤሪካ አቅኚ ከሆኑ አንድ ባልና ሚስት ጋር ጓደኛ ሆኑ፤ እነሱም አኗኗርን ቀላል በማድረግ በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ እንዲመለከቱ ረዷቸው። ኪትና ኤሪካ ምን አደረጉ? “መንፈሳዊ ግቦቻችንን በዝርዝር ከጻፍን በኋላ ማቀዝቀዣችን ላይ ለጠፍነው፤ ከዚያም እያንዳንዱ ግብ ላይ ስንደርስ ምልክት እናደርግበት ነበር።” ከጊዜ በኋላ ኪትና ኤሪካ አቅኚ መሆን ቻሉ።

17. አቅኚ ለመሆን ስትል በፕሮግራምህ ወይም በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?

17 አንተስ አቅኚ መሆን ትችል ይሆን? አሁን ባለህ ሁኔታ እዚህ መብት ላይ መድረስ እንደማትችል ሆኖ ከተሰማህ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር። ጉዳዩን በጸሎት ካሰብክበት በኋላ በፕሮግራምህ ወይም በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ አቅኚ መሆን ትችል ይሆናል። አቅኚ መሆን ከቻልክ ደግሞ የምታገኘው ደስታ ከምትከፍለው ማንኛውም መሥዋዕትነት የላቀ እንደሚሆን አትዘንጋ። ከራስህ ፍላጎት ይልቅ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደምህ ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልሃል። (ማቴ. 6:33) ለሌሎች መስጠት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ደስታም ማጣጣም ትችላለህ። ከዚህም በላይ ስለ ይሖዋ የማሰብና የመናገር ሰፊ አጋጣሚ ታገኛለህ፤ ይህ ደግሞ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ ጥልቀት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፤ ይሖዋም ቢሆን በአንተ ይደሰታል።