በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2013

ከንጽጽሮች ጥቅም ማግኘት

ከንጽጽሮች ጥቅም ማግኘት

በምድር ላይ ከኢየሱስ የሚበልጥ አስተማሪ አልተነሳም ቢባል አትስማማም? አንዳንድ የማስተማሪያ ዘዴዎቹን ምናልባትም ጥያቄዎችንና ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ የእሱን አርዓያ ለመከተል ጥረት አድርገህ ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ ንጽጽሮችን በተደጋጋሚ ይጠቀም እንደነበረ አስተውለህ ታውቃለህ?

ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት ንግግራቸው ንጽጽሮችን ይጠቀማሉ። አንተም ሳይታወቅህ እንዲህ ታደርግ ይሆናል። ምናልባትም እንዲህ ብለህ ታውቅ ይሆናል፦ “ሁሉም ሙዝ የበሰለ ነው ብለውኝ ነበር፤ እነዚህ ግን ጥሬ ናቸው።” ወይም “አንድ ፍሬ ልጅ ነበረች፤ አሁን ግን ትልቅ ሰው ሆናለች።”

እንዲህ ዓይነት አነጋገር ስንጠቀም በመጀመሪያ አንድን እውነታ ወይም ሐሳብ እንናገራለን፤ ከዚያም አንዳንድ ማያያዣዎችን በመጠቀም ተቃራኒውን ሐሳብ እናስከትላለን። ከእነዚህ ማያያዣዎች መካከል ከዚህ ይልቅ፣ ይሁን እንጂ፣ ግን እና በሌላ በኩል የሚሉት ይገኙበታል። አሊያም ደግሞ መጀመሪያ የተናገርነውን ሐሳብ ባይቃረንም ተጨማሪ መረጃ በመስጠት ወይም የሚያጠናክር ሐሳብ በመናገር ንጽጽር መጠቀም እንችላለን። ይህን ዘዴ መጠቀም ለዛ ያለው ከመሆኑም በላይ አድማጮች ነጥቡ ግልጽ እንዲሆንላቸው ያደርጋል።

ንጽጽሮችን መጠቀም በአንዳንድ ቋንቋዎችና ባሕሎች የተለመደ ባይሆንም ያላቸውን ጠቀሜታ መረዳታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ንጽጽሮች በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ንጽጽሮችን ይጠቀም ነበር። ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እናንሳ፦ “ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል።” “ሕግን . . . ልፈጽም እንጂ ልደመስስ አልመጣሁም።” “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ . . .።” “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉ ለሚያደርግባችሁ ሰው አጸፋ አትመልሱ፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።”—ማቴ. 5:15, 17, 27, 28, 38, 39

በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ላይ ተመሳሳይ ንጽጽሮች አሉ። እነዚህ ንጽጽሮች ሊተላለፍ የተፈለገውን ነጥብ በቀላሉ ለመረዳት አሊያም አንድን ነገር በላቀ መንገድ እንድታከናውን ሊያነሳሱህ ይችላሉ። ወላጅ ከሆንክ እስቲ የሚከተለውን ንጽጽር ቆም ብለህ አስብ፦ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።” (ኤፌ. 6:4) ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ አባት (ወይም እናት) ልጁን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ እንዳለበት ብቻ ቢገልጽ ኖሮ የተፈለገውን ሐሳብ ማስተላለፍ ይችል ይሆናል። ይሁንና ‘ልጆችን ከማስመረር ይልቅ የይሖዋ አስተሳሰብ በውስጣቸው እንዲቀረጽ በማድረግ ማሳደግ’ የሚለው ንጽጽር መልእክቱን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።

ጳውሎስ በዚያው ምዕራፍ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ትግል የምንገጥመው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን . . . በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።” (ኤፌ. 6:12) ይህ ንጽጽር ትግሉ ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለመገንዘብ እንደሚያስችልህ የታወቀ ነው። የምንዋጋው ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከመንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።

 ከንጽጽሮች ጥቅም ማግኘት

በዚያው የኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ ጳውሎስ የተጠቀመባቸውን ሌሎች በርካታ ንጽጽሮች ማግኘት ትችላለህ። በእነዚህ ንጽጽሮች ላይ ማሰላሰልህ ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ነጥብ ለመረዳት የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ ልትወስደው የሚገባህን እርምጃ ይበልጥ ግልጽ ያደርግልሃል።

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 እና ምዕራፍ 5 ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ንጽጽሮችን የሚያሳየውን ሠንጠረዥ መመርመሩን አስደሳችና ጠቃሚ ሆኖ እንደምታገኘው እርግጠኞች ነን። እያንዳንዱን ንጽጽር ስታነብ ስለ ራስህ ሕይወት አስብ። እንዲሁም እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በሐቀኝነት ውስጤን ስመረምር ዝንባሌዬ ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ምን አደርጋለሁ? ሰዎች ከሁለቱ ንጽጽሮች የትኛው ጋ ይመድቡኛል?’ ከንጽጽሮቹ መካከል በአንዱ ላይ ይበልጥ ልትሠራበት እንደምትችል ከተሰማህ ያወቅከውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርግ። በዚህ መንገድ ከንጽጽሩ ጥቅም እንድታገኝ እናበረታታሃለን።

ወይም ደግሞ ሠንጠረዡን በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ውስጥ ልታካትቱት ትችሉ ይሆናል። በመጀመሪያ ሁሉም የቤተሰባችሁ አባላት ንጽጽሮቹን ሊያነቧቸው ይችላሉ። ከዚያም አንዳችሁ የንጽጽሩን የመጀመሪያ ክፍል ስትናገሩ ሌሎቻችሁ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን ነጥብ አስታውሳችሁ ለመናገር ሞክሩ። በዚህ መንገድ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን ሐሳብ በተሟላ ሁኔታ በሥራ ላይ ለማዋል እንድትችሉ የሚረዳ ግሩም ውይይት ማድረግ ትችላላችሁ። አዎ፣ እንዲህ ያሉ ንጽጽሮችን መመርመር፣ ልጅ አዋቂ ሳይል ሁሉንም ክርስቲያኖች በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታ ክርስቲያናዊ ምግባር ለማንጸባረቅ ያነሳሳቸዋል።

የንጽጽሩን ሁለተኛ ክፍል ማስታወስ ትችላላችሁ?

ንጽጽሮች ያላቸውን ጥቅም በተረዳህ መጠን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀላሉ ልትለያቸው ትችላለህ፤ ለክርስቲያናዊ አገልግሎትህም ጠቃሚ ሆነው እንደምታገኛቸው ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ አገልግሎት ላይ የቤቱን ባለቤት “ብዙ ሰዎች የማትሞት ነፍስ እንዳለችን ይሰማቸዋል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን እንደሚል ባሳይዎት ደስ ይለኛል” ልንለው እንችላለን። ወይም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ “ብዙ ሰዎች በአምላክና በኢየሱስ መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ ያምናሉ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አንተስ ምን ይሰማሃል?”

አዎ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ትምህርት ሰጪ የሆኑ በርካታ ንጽጽሮችን ይዘዋል፤ እነዚህ ንጽጽሮች ደግሞ አምላክ የሚፈልገውን ጎዳና ተከትለን እንድንጓዝ ይረዱናል። በሌላ በኩል ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለማስተማር ንጽጽሮችን መጠቀም እንችላለን።