በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2013

ልባችሁ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ሐሴት ያድርግ

ልባችሁ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ሐሴት ያድርግ

‘ማሳሰቢያህ የዘላለም ውርሴ ነው።’—መዝ. 119:111 NW

1. (ሀ) ሰዎች ማሳሰቢያ ሲሰጣቸው ምን ምላሽ ይሰጣሉ? ለምንስ? (ለ) ኩራት አንድ ሰው ለምክር የሚኖረውን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?

ሰዎች ለሚሰጣቸው መመሪያ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ነው። ማሳሰቢያው የመጣው ሥልጣን ካለው ሰው ከሆነ በአክብሮት ይቀበሉታል፤ ምክሩን የሰጣቸው እኩያቸው ወይም ከእነሱ የበታች የሆነ ሰው ከሆነ ግን ከቁብም ላይቆጥሩት ይችላሉ። ሰዎች ተግሣጽ ወይም ምክር ሲሰጣቸው የሚሰማቸው ስሜትም ቢሆን በእጅጉ ይለያያል። አንዳንዶች ሲያዝኑ፣ ሲከፋቸው ወይም ሲያፍሩ ሌሎች ደግሞ ተግሣጹ ወይም ምክሩ ለተግባር እንዲነሳሱ፣ በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንዲጨምርና የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ልዩነት ሊፈጠር የቻለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ኩራት ነው። በእርግጥም የእብሪት መንፈስ አንድ ሰው ያለውን የማመዛዘን ችሎታ ስለሚያጨልምበት የሚሰጠውን ምክር ችላ እንዲል ሊያደርገው አልፎ ተርፎም ሊያገኝ የሚችለውን ጠቃሚ መመሪያ ሊያሳጣው ይችላል።—ምሳሌ 16:18

2. እውነተኛ ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጣቸው በአድናቆት የሚቀበሉት ለምንድን ነው?

2 በሌላ በኩል ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሆነ በተለይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጣቸው በደስታ ይቀበላሉ። የይሖዋ ማሳሰቢያዎች አስተዋይ እንድንሆን ስለሚያደርጉን ከፍቅረ ንዋይና ከፆታ ብልግና እንዲሁም ዕፆችን ወይም የአልኮል መጠጦችን አላግባብ ከመጠቀም ወጥመድ ይጠብቁናል። (ምሳሌ 20:1፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ 1 ተሰ. 4:3-5፤ 1 ጢሞ. 6:6-11) በተጨማሪም የአምላክን ማሳሰቢያዎች መታዘዛችን ‘ከልብ የመነጨ ደስታ’ ያስገኝልናል።—ኢሳ. 65:14

3. መዝሙራዊው የነበረውን የትኛውን አመለካከት ማዳበራችን ተገቢ ነው?

3 ከሰማዩ አባታችን ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ከፈለግን ይሖዋ የሚሰጠንን ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። አመለካከታችን እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን የመዝሙራዊውን ስሜት የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት፦ “ማሳሰቢያዎችህ ልቤን ደስ ስለሚያሰኙ  የዘላለም ውርሴ ናቸው።” (መዝ. 119:111 NW) እኛስ በተመሳሳይ በይሖዋ ትእዛዛት እንደሰታለን ወይስ እንደ ሸክም እንቆጥራቸዋለን? የሚሰጠን ምክር አንዳንድ ጊዜ ቅር ቢያሰኘንም እንኳ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። እጅግ ታላቅ በሆነው የይሖዋ ጥበብ ላይ የማይናወጥ እምነት ማዳበር እንችላለን! እስቲ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።

በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ ያላችሁን እምነት ገንቡ

4. በዳዊት ሕይወት ውስጥ ያልተለወጠው ነገር ምንድን ነው?

4 ንጉሥ ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ክፉም ሆነ ደግ ነገሮችን ያሳለፈ ቢሆንም ምንጊዜም የማይለወጥ አንድ ባሕርይ ነበረው፤ ይህም በፈጣሪው ላይ ያለው የማይናወጥ እምነት ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ፤ አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።” (መዝ. 25:1, 2) ዳዊት በሰማይ በሚገኘው አባቱ ላይ እንዲህ ያለ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብር የረዳው ምንድን ነው?

5, 6. ዳዊት ከይሖዋ ጋር ስለነበረው ዝምድና የአምላክ ቃል ምን ይነግረናል?

5 ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ የሚጸልዩት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ብቻ ነው። አንድ ጓደኛህ ወይም ዘመድህ አንተ ጋ የሚመጣው ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር ሲፈልግ ብቻ ቢሆንስ? ውሎ አድሮ ወደ አንተ የሚመጣበትን ምክንያት መጠራጠርህ አይቀርም። ዳዊት ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አልነበረም። ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማለትም በደጉም ሆነ በክፉው ጊዜ ያቀረባቸው ጸሎቶች ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው ብሎም በእሱ እንደሚታመን ያሳያሉ።—መዝ. 40:8

6 ዳዊት ለይሖዋ ምን ብሎ ውዳሴና ምስጋና እንዳቀረበ ልብ በል፦ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው! ክብርህ ከሰማያት በላይ፣ ከፍ ከፍ ብሎአል።” (መዝ. 8:1) ዳዊት በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር ምን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበረው አስተዋልክ? ዳዊት የአምላክን ግርማና ክብር ማድነቁ “ቀኑን ሙሉ” እሱን እንዲያወድሰው አነሳስቶታል።—መዝ. 35:28

7. ወደ አምላክ በጸሎት መቅረባችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

7 እኛም እንደ ዳዊት በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማዳበር አዘውትረን ከእሱ ጋር መነጋገር ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕ. 4:8) በተጨማሪም በጸሎት አማካኝነት ወደ እሱ መቅረብ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ከምናገኝባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ነው።—1 ዮሐንስ 3:22ን አንብብ።

8. በምንጸልይበት ጊዜ ተመሳሳይ አገላለጾችን ከመጠቀም መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?

8 በምትጸልይበት ወቅት ተመሳሳይ አገላለጾችን ደጋግመህ ትጠቀማለህ? ከሆነ ከመጸለይህ በፊት ጥቂት ጊዜ ወስደህ ስለምትጸልየው ነገር አስብ። ከአንድ ወዳጃችን ወይም ዘመዳችን ጋር በተገናኘን ቁጥር አንድ ዓይነት አነጋገር የምንጠቀም ቢሆን ይህ ነገር የሚያስደስተው ይመስልሃል? ትንሽ ቆይቶ ለምንናገረው ነገር ጆሮ መስጠቱን እንደሚያቆም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በቅንነት የሚያቀርቡለትን ጸሎት አልሰማም አይልም። ሆኖም የምንናገረው ነገር አሰልቺ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን።

9, 10. (ሀ) በጸሎታችን ውስጥ ምን ነገሮችን ማካተት እንችላለን? (ለ) ልባዊ ጸሎት ለማቅረብ ምን ሊረዳን ይችላል?

9 ወደ አምላክ የመቅረብ ልባዊ ፍላጎት ካለን ጸሎታችን ጥልቀት ያለው እንደሚሆን የታወቀ ነው። ለይሖዋ የልባችንን አውጥተን በነገርነው መጠን ይበልጥ ወደ እሱ እየቀረብን እንሄዳለን፤ እንዲሁም ይበልጥ በእሱ እንታመናለን። ይሁንና ጸሎታችን ምን ነገር ማካተት ይኖርበታል? የአምላክ ቃል መልሱን ሲሰጥ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” (ፊልጵ. 4:6) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ወይም ሕይወታችንን የሚነካ ማንኛውም ነገር ሲያጋጥመን ጉዳዩን በጸሎታችን ውስጥ ማካተታችን ተገቢ ነው።

10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ያቀረቡትን ጸሎት በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (1 ሳሙ. 1:10, 11፤ ሥራ 4:24-31) የመዝሙር መጽሐፍ ለይሖዋ የቀረቡ ልብ የሚነኩ ጸሎቶችንና  መዝሙሮችን ይዟል። ሐዘንና ደስታን ጨምሮ ሰዎች የሚሰሟቸው ስሜቶች በሙሉ በእነዚህ ጸሎቶችና መዝሙሮች ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የተናገሯቸውን አባባሎች መመርመራችን ለይሖዋ ትርጉም ያለው ጸሎት ለማቅረብ ይረዳናል።

በአምላክ ማሳሰቢያዎች ላይ አሰላስሉ

11. አምላክ በሚሰጠን ምክሮች ላይ ማሰላሰል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

11 ዳዊት “የይሖዋ ማሳሰቢያ እምነት የሚጣልበት ነው፤ ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል” ብሏል። (መዝ. 19:7 NW) አዎ፣ ተሞክሮ የሌለን ብንሆንም እንኳ የአምላክን መመሪያዎች በመታዘዝ ጥበበኞች መሆን እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ምክሮች የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ግን በምክሮቹ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ የሚደርስብንን ተጽዕኖ ተቋቁመን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ፣ አምላክ ደምን አስመልክቶ ያወጣውን መመሪያ መታዘዝ፣ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችንን መጠበቅና በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ከፈለግን በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። እንዲህ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የአምላክን አስተሳሰብ ማዳበራችን ችግሮቹ ከመምጣታቸው በፊት አስቀድመን እንድንዘጋጅ ይረዳናል። ይህን ካደረግን ደግሞ ችግሩ ሲፈጠር ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ አንጋባም። በዚህ መልኩ አርቀን ማሰባችንና አስቀድመን ዝግጅት ማድረጋችን ከብዙ ጣጣ ይጠብቀናል።—ምሳሌ 15:28

12. የአምላክን ማሳሰቢያዎች ለመጠበቅ የሚረዳን በምን ጉዳዮች ላይ ማሰላሰላችን ነው?

12 አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ሊፈጸሙ የተቃረቡ ከመሆናቸው አንጻር አኗኗራችን ምን ይመስላል? በመንፈሳዊ ንቁዎች እንደሆንን የሚያሳይ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ታላቂቱ ባቢሎን በቅርቡ እንደምትጠፋ በእርግጥ እናምናለን? ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖርን ጨምሮ ወደፊት የምናገኛቸው በረከቶች መጀመሪያ ስንሰማቸው የነበረውን ያህል እውን ሆነው ይታዩናል? በሕይወታችን ውስጥ ለግል ጉዳዮቻችን ትልቅ ቦታ ከመስጠት ይልቅ አገልግሎታችንን በቅንዓት እያከናወንን ነው? ስለ ትንሣኤ ተስፋ፣ ስለ ይሖዋ ስም መቀደስና ስለ ሉዓላዊነቱስ ምን ይሰማናል? እነዚህ ነገሮች አሁንም ለእኛ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው? እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን መዝሙራዊው እንደተናገረው የአምላክን ማሳሰቢያዎች ‘የዘላለም ውርሳችን’ ለማድረግ ያነሳሳናል።—መዝ. 119:111

13. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንዳንድ ነገሮችን መረዳት የከበዳቸው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ላንረዳቸው እንችላለን፤ ይህ የሆነው ይሖዋ ጉዳዩን ግልጽ የሚያደርግበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ መሠቃየቱና መገደሉ ግድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜያት ለሐዋርያቱ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 12:40ን እና 16:21ን አንብብ።) ይሁንና ሐዋርያቱ ኢየሱስ የነገራቸውን ነገር አልተረዱም ነበር። ይህ ጉዳይ ግልጽ የሆነላቸው ኢየሱስ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ሲሆን በዚህ ወቅት ሥጋዊ አካል በመልበስ ለበርካታ ደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:44-46፤ ሥራ 1:3) በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት የሚቋቋመው በሰማይ እንደሆነ የገባቸው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ ነበር።—ሥራ 1:6-8

14. በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በርካታ ወንድሞች የመጨረሻዎቹን ቀኖች አስመልክቶ የተሳሳተ አመለካከት ቢኖራቸውም ምን ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል?

14 በተመሳሳይም በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የመጨረሻዎቹን ቀኖች’ አስመልክቶ ይጠብቋቸው የነበሩ አንዳንድ ነገሮች የተሳሳቱ ነበሩ። (2 ጢሞ. 3:1) ለአብነት ያህል፣ በ1914 አንዳንዶች ወደ ሰማይ የሚሄዱበት ጊዜ እንደደረሰ ተሰምቷቸው ነበር። የጠበቁት ነገር ባሰቡት ጊዜ እንዳልመጣ ሲገነዘቡ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት መመርመር ጀመሩ፤ በዚህም የተነሳ ታላቅ የስብከት ዘመቻ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው አስተዋሉ። (ማር. 13:10) በመሆኑም በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው  ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ እንደሚከተለው በማለት ተናግሮ ነበር፦ “እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ መስበክ በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች መለያ ምልክት ሆኗል።—ማቴ. 4:23፤ 24:14

15. አምላክ ሕዝቡን የተንከባከበበትን መንገድ እያሰብን ማሰላሰላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

15 ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሕዝቡን የተንከባከበባቸውን አስደናቂ መንገዶች እያሰብን ማሰላሰላችን ወደፊት ፈቃዱንና ዓላማውን ከግብ እንደሚያደርስ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። በተመሳሳይም አምላክ ቃል በገባቸው ወደፊት በሚፈጸሙ ተስፋዎች ላይ ማሰላሰላችን እነዚህ ተስፋዎች በልባችንና በአእምሯችን ላይ ምንጊዜም ሕያው ሆነው እንዲሳሉ ያደርጋል። ይህም አምላክ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር እንደሚረዳን የተረጋገጠ ነው።

በመንፈሳዊ ሥራዎች አማካኝነት በይሖዋ ላይ ያላችሁን እምነት ገንቡ

16. አገልግሎታችንን ምንጊዜም በቅንዓት ማከናወናችን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?

16 አምላካችን ይሖዋ ምንጊዜም በሥራ ላይ ነው። መዝሙራዊው ይሖዋን አስመልክቶ “እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” በማለት ከጠየቀ በኋላ “እጅህ ኀያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 89:8, 13) ይሖዋ ምንጊዜም በሥራ ላይ ያለ በመሆኑ እኛም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል፤ እንዲሁም ጥረታችንን ይባርከዋል። ወንድ ሴት፣ ልጅ አዋቂ ሳይል አገልጋዮቹ በሙሉ ቁጭ ብለው “የስንፍና እንጀራ” የማይበሉ እንደሆኑ ሲመለከት በጣም ይደሰታል። (ምሳሌ 31:27) በመሆኑም የፈጣሪያችንን ምሳሌ በመከተል በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን እናስጠምዳለን። አምላክን በሙሉ ልባችን ማገልገላችን ውስጣዊ እርካታ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ይሖዋን በእጅጉ ስለሚያስደስተው አገልግሎታችንን ይባርክልናል።—መዝሙር 62:12ን አንብብ።

17, 18. መንፈሳዊ ሥራዎች ይሖዋ በሚሰጠን ምክር ላይ እምነት እንድንጥል ይረዱናል የምንለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

 17 ታዲያ መንፈሳዊ ሥራዎችን ማከናወን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለመገንባት የሚረዳን እንዴት ነው? እስቲ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ የሆነውን ነገር ለማየት እንሞክር። ይሖዋ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲያቋርጡ መመሪያ ሰጣቸው። ይሁንና ወደ ወንዙ ሲደርሱ በጸደይ ወቅት በጣለው ዝናብ ምክንያት ወንዙ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ታዲያ እስራኤላውያን ምን ያደርጉ ይሆን? ወንዙ አጠገብ በመስፈር ውኃው እስኪጎድል ለሳምንታት አሊያም ከዚያ በላይ ይጠብቁ ይሆን? በጭራሽ፤ ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን መመሪያውን ተከተሉ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ . . . የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናትም፣ ሕዝቡ ሁሉ ማለት እስራኤል በሙሉ ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቁ ምድር ላይ ቀጥ ብለው ቆመው ነበር።” (ኢያሱ 3:12-17) እየተንደረደረ ሲመጣ የነበረው ውኃ ቀጥ ሲል እስራኤላውያኑ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ገምት! እስራኤላውያን ይሖዋ በሰጣቸው መመሪያ በመታመናቸው በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ተጠናክሮ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው።

በኢያሱ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን እንዳደረጉት በይሖዋ ላይ ትታመናለህ? (አንቀጽ 17ን እና 18ን ተመልከት)

18 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ሕዝቦቹ እንዲህ ዓይነት ተአምር አይሠራም፤ ይሁንና ሕዝቦቹ የሚያከናውኗቸውን መንፈሳዊ ሥራዎች ይባርካል። በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል የመንግሥቱን መልእክት በዓለም ዙሪያ ማዳረስ እንዲችሉ ኃይል ይሰጣቸዋል። ከሁሉ የላቀ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ምንጊዜም ከጎናቸው እንደሚሆን ማረጋገጫ ሲሰጣቸው እንዲህ ብሏል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ . . . እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) የማፈር ወይም የመፍራት ባሕርይ የነበራቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት ለሚያገኟቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲናገሩ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድፍረት እንደሰጣቸው ተሰምቷቸዋል።—መዝሙር 119:46ን እና 2 ቆሮንቶስ 4:7ን አንብብ።

19. አቅማችን ውስን ቢሆንም እንኳ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል?

19 አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በሕመም ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት እንደ ልብ መንቀሳቀስ አይችሉ ይሆናል። ያም ቢሆን እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ያሉበትን ሁኔታ እንደሚረዳ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (2 ቆሮ. 1:3) ይሖዋ፣ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ስንል የምናደርገውን ጥረት ሁሉ በአድናቆት ይመለከታል። አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችን እንዳለ ሆኖ በዋነኝነት ነፍሳችንን ሕያው አድርገን ማኖር የምንችለው በክርስቶስ ቤዛ ላይ ባለን እምነት መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል።—ዕብ. 10:39

20, 21. በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

20 ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ያሉንን ቁሳዊ ነገሮች ምንም ሳንቆጥብ መሥዋዕት ማድረግን ይጨምራል። አዎ፣ በሙሉ ልባችን ‘የወንጌላዊነትን ሥራ ማከናወን’ እንፈልጋለን። (2 ጢሞ. 4:5) ደግሞም እንዲህ ማድረግ ያስደስተናል፤ ምክንያቱም ሌሎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እየረዳን ነው። (1 ጢሞ. 2:4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋን ማክበራችንና ማወደሳችን በመንፈሳዊ ያበለጽገናል። (ምሳሌ 10:22) እንዲሁም ከፈጣሪያችን ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ያስችለናል።—ሮም 8:35-39

21 እስካሁን እንደተመለከተነው ‘ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ ከይሖዋ አገኛለሁ’ የሚለው እምነት የሚመጣው በአንድ ጀምበር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ መታመንህ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ይሖዋ በጥንት ጊዜ ፈቃዱን እንዴት እንዳከናወነ እንዲሁም ወደፊት ቃሉን እንዴት እንደሚፈጽም አሰላስል። በተጨማሪም መንፈሳዊ ሥራዎችን በማከናወን በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት ገንባ። አዎ፣ የይሖዋ ማሳሰቢያዎች በእርግጥም ዘላለማዊ ናቸው። አንተም እነዚህን ማሳሰቢያዎች እስከታዘዝክ ድረስ ለዘላለም ትኖራለህ!