በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ፈጽሞ ‘በይሖዋ ላይ አትቆጡ’

ፈጽሞ ‘በይሖዋ ላይ አትቆጡ’

‘የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፣ ልቡም በይሖዋ ላይ ይቈጣል።’—ምሳሌ 19:3 የ1954 ትርጉም

1, 2. በዓለም ላይ ለሚታዩት ችግሮች ተጠያቂው ይሖዋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ አስደሳች የትዳር ሕይወት አለህ እንበል። አንድ ቀን ወደ ቤትህ ስትመለስ ግን ሁሉ ነገር ምስቅልቅሉ ወጥቶ አገኘኸው። የቤት ዕቃዎችህ ተሰባብረዋል፤ ምንጣፍህም እንዳልነበረ ሆኗል። የሚያምረው ቤትህ የጦርነት ቀጠና መስሏል። ይህን ስታይ በቁጣ ገንፍለህ “እንዴ! ሚስቴ ምን ሆና ነው ቤቱን እንዲህ ያደረገችው?” ትላለህ? ወይስ “ቤቱን እንዲህ ያመሰቃቀለው ማን ነው?” ብለህ ትጠይቃለህ? ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ሁለተኛው ጥያቄ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምን? ምክንያቱም የምትወዳት ባለቤትህ ቤቱን እንዲህ እንደማታደርገው ታውቃለህ።

2 የሰው ዘር መኖሪያ የሆነችው ምድር በዛሬው ጊዜ በአካባቢ ብክለት፣ በዓመፅ እና በሥነ ምግባር ብልግና ተበላሽታለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ያመጣው ይሖዋ እንዳልሆነ እናውቃለን። አምላክ፣ ፕላኔታችንን የፈጠራት ውብ ገነት እንድትሆን አድርጎ ነው። (ዘፍ. 2:8, 15) ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታችን፣ በዓለማችን ላይ ለሚታዩት ለአብዛኞቹ ችግሮች ተጠያቂው “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ማወቅ ችለናል።—ዮሐ. 14:30፤ 2 ቆሮ. 4:4

3. አስተሳሰባችን ሊዛባ የሚችለው እንዴት ነው?

3 ይሁን እንጂ፣ ለሚደርሱብን ችግሮች ሁሉ ተጠያቂው ሰይጣን ነው ማለት አይቻልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንዳንዶቹ ችግሮች የሚፈጠሩት እኛው ራሳችን በሠራናቸው ስህተቶች የተነሳ ነው። (ዘዳግም 32:4-6ን አንብብ።) ይህን እውነታ ብንገነዘብም እንኳ ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን አስተሳሰባችን ሊዛባና ለጉዳት የሚዳርግ አካሄድ ልንከተል እንችላለን። (ምሳሌ 14:12) እንዲህ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? ለደረሰብን ችግር ራሳችንን ወይም ሰይጣንን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ይሖዋን ማማረር ልንጀምር እንችላለን። አልፎ ተርፎም ‘በይሖዋ ላይ እንቆጣ’ ይሆናል።—ምሳሌ 19:3 የ1954 ትርጉም

4, 5. አንድ ክርስቲያን ‘በይሖዋ ላይ ሊቆጣ’ የሚችለው እንዴት ነው?

4 አንድ ሰው በእርግጥ በይሖዋ ላይ ሊቆጣ ይችላል? አዎን፣  ይህን ማድረግ ግን ከንቱ እንደሆነ የታወቀ ነው። (ኢሳ. 41:11) ደግሞስ እንዲህ ማድረግ ምን የሚያስገኘው ጥቅም ይኖራል? አንድ ገጣሚ “ክንድህ ስለማይደርስ አምላክን ለመምታት እጅህን አትሰንዝር” ብሎ ነበር። እርግጥ ነው፣ በይሖዋ ላይ ቅር እንደተሰኘን አፍ አውጥተን አንናገር ይሆናል። ያም ቢሆን ምሳሌ 19:3 (የ1954 ትርጉም) እንዲህ ይላል፦ “የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፣ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል።” ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ አንድ ሰው በልቡ በአምላክ ላይ ሊቆጣ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ የሚታይባቸው አንዳንድ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ግለሰቡ ይሖዋን እንዳኮረፈ የሚያስቆጥር ነገር ያደርግ ይሆናል። በዚህም የተነሳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ሊያቆም ወይም ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን በሙሉ ልቡ መደገፉን ሊተው ይችላል።

5 ‘በይሖዋ ላይ እንድንቆጣ’ ሊያደርጉን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲህ ካለው ወጥመድ መራቅ የምንችለውስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ይህን ማወቃችን ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ረገድ ለውጥ ያመጣል።

‘በይሖዋ ላይ እንድንቆጣ’ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

6, 7. በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ያጉረመረሙት ለምን ነበር?

6 አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ፣ አምላኩን በልቡ ማማረር እንዲጀምር ሊያደርጉት የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ አምስት ነጥቦችን እስቲ እንመልከት፤ እንዲሁም በጥንት ዘመን አንዳንዶች በዚህ ወጥመድ የወደቁት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመርምር።—1 ቆሮ. 10:11, 12

ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7 ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። (ዘዳግም 1:26-28ን አንብብ።) እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ ብዙም አልቆዩም። ይሖዋ በዚህች ጨቋኝ አገር ላይ አሥር ተአምራዊ መቅሰፍቶችን ያመጣ ከመሆኑም በላይ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ውስጥ እንዲሰጥሙ አደረጋቸው። (ዘፀ. 12:29-32, 51፤ 14:29-31፤ መዝ. 136:15) የአምላክ ሕዝቦች ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ደፍ ላይ ደርሰዋል። ይሁንና ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። ሕዝቡ፣ እምነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረጉት ለምንድን ነው? ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት መካከል አንዳንዶቹ በነዙት አሉታዊ ወሬ የተነሳ ልባቸው በመራዱ ነው። (ዘኍ. 14:1-4) ውጤቱስ ምን ሆነ? ትውልዱ በአጠቃላይ ‘ወደ መልካሚቱ ምድር’ እንዳይገባ ተከለከለ። (ዘዳ. 1:34, 35) እኛስ ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር እምነታችንን እንዲያዳክመውና በይሖዋ ላይ እንድናጉረመርም እንዲያደርገን እንፈቅዳለን?

8. በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ለደረሰባቸው ችግር ይሖዋን ተጠያቂ ያደረጉት ለምንድን ነው?

8 መከራና ችግር ተስፋ ያስቆርጠን ይሆናል። (ኢሳይያስ 8:21, 22ን አንብብ።) በኢሳይያስ ዘመን፣ የይሁዳ ብሔር በጣም አስጨናቂ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። አገሪቱ በጠላት ተከብባለች። የምግብ እጥረት ስላለ ብዙዎች ተርበዋል። ከዚህ የከፋው ግን በአገሪቱ የነበረው መንፈሳዊ ረሃብ ነው። (አሞጽ 8:11) ሕዝቡ፣ ችግሮቻቸውን ለመወጣት ይሖዋ እንዲረዳቸው ከመለመን ይልቅ ‘ንጉሣቸውንና አምላካቸውን መራገም’ ጀመሩ። ለእነዚህ ችግሮች ተጠያቂ ያደረጉት ይሖዋን ነው። እኛስ በሕይወታችን ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ወይም የሆነ ችግር ሲደርስብን ‘ይሖዋ በምፈልገው ጊዜ መች ደረሰልኝ?’ ብለን በልባችን እናማርር ይሆን?

9. በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን የተሳሳተ አመለካከት ያዳበሩት እንዴት ነው?

9 የማናውቃቸው ነገሮች አሉ። በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን የይሖዋ “መንገድ ቀና አይደለችም” ብለው ነበር፤ እንዲህ የተሰማቸው ግን የማያውቋቸው ነገሮች ስለነበሩ ነው። (ሕዝ. 18:29) ሕዝቡ፣ በይሖዋ ላይ ለመፍረድ ራሳቸውን ዳኛ ያደረጉ ያህል ነበር፤ የራሳቸው የፍትሕ መሥፈርት ከይሖዋ መሥፈርቶች የተሻለ እንደሆነ በማሰብ ውስን በሆነው እውቀታቸው ላይ ተመሥርተው በእሱ ላይ ለመፍረድ ሞከሩ። እኛም  በተመሳሳይ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በደንብ ላንረዳ ወይም በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን ነገሮች ግራ ልንጋባ እንችላለን፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ፣ ይሖዋ ፍትሐዊ እንዳልሆነ በሌላ አባባል ‘መንገዱ ቀና እንዳልሆነ’ ይሰማን ይሆን?—ኢዮብ 35:2

10. አንድ ሰው የአዳምን መጥፎ ምሳሌ ሊከተል የሚችለው እንዴት ነው?

10 የሠራነውን ኃጢአትና ስህተቶቻችንን በሌላ ማላከክ ይቀናናል። በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ አዳም፣ እሱ ለሠራው ኃጢአት አምላክን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። (ዘፍ. 3:12) አዳም የአምላክን ሕግ የጣሰው ድርጊቱ ምን መዘዝ እንደሚያስከትል እያወቀ ሆን ብሎ ቢሆንም ለስህተቱ ተጠያቂው ይሖዋ እንደሆነ ተሰማው። በሌላ አባባል አዳም፣ እንዲህ ዓይነት ስህተት የሠራው ይሖዋ መጥፎ ሚስት ስለሰጠው እንደሆነ እየገለጸ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሌሎችም ራሳቸው ለሠሩት ስህተት ይሖዋን ተጠያቂ በማድረግ የአዳምን ምሳሌ ተከትለዋል። እኛም ‘የሠራሁት ስህተት ያስከተለብኝ ብስጭትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት በይሖዋ መሥፈርቶች ቅር እንድሰኝ አድርጎኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።

11. ከዮናስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ስለ ራሳችን ብቻ እያሰብን ይሆናል። ነቢዩ ዮናስ፣ ይሖዋ ነነዌን በተመለከተ የወሰደው የምሕረት እርምጃ አላስደሰተውም። (ዮናስ 4:1-3) ለምን? ዮናስ ስለ ራሱ ክብር ከልክ በላይ ይጨነቅ የነበረ ይመስላል፤ በዚህም የተነሳ ያወጀው የፍርድ መልእክት ሳይፈጸም መቅረቱ አሳስቦታል። ዮናስ ስለ ስሙ ከልክ በላይ መጨነቁ ንስሐ ለገቡት የነነዌ ሰዎች ርኅራኄ እንዳያሳይ እንቅፋት ሆኖበታል። እኛስ ስለ ራሳችን ብቻ በማሰብ፣ ይሖዋ መጨረሻውን እስከ አሁን ባለማምጣቱ በእሱ ላይ ‘እንቆጣለን’? የይሖዋ ቀን እንደቀረበ ለአሥርተ ዓመታት ስንሰብክ ቆይተን ከሆነ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በማወጃችን ሲያሾፉብን ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ይከብደናል?—2 ጴጥ. 3:3, 4, 9

‘በይሖዋ ላይ እንዳንቆጣ’ ምን ሊረዳን ይችላል?

12, 13. ይሖዋ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ትክክለኛነት በልባችን መጠራጠር ከጀመርን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 ኃጢአተኞች በመሆናችን ይሖዋ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ትክክለኛነት በልባችን መጠራጠር ብንጀምርስ? እንዲህ ያለው አመለካከት ጥበብ የጎደለው እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ምሳሌ 19:3 “ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤  በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል” ይላል። ይህን ጥቅስ በአእምሯችን እንያዝና በሕይወት ውስጥ በሚያጋጥሙን ነገሮች የተነሳ ይሖዋን ማማረር እንዳንጀምር ሊረዱን የሚችሉ አምስት ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

13 ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና አቅልላችሁ አትመልከቱ። ፍጹማን ባለመሆናችን በአምላክ ላይ መቆጣት ይቀናናል፤ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ካለን ግን ይህን ዝንባሌ ማሸነፍ እንችላለን። (ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።) በይሖዋ ልንታመን ይገባል። በራሳችን አስተያየት ጠቢብ እንዳንሆን ወይም ስለ ራሳችን ብቻ እንዳናስብ መጠንቀቅም ይኖርብናል። (ምሳሌ 3:7፤ መክ. 7:16) እንዲህ ካደረግን መጥፎ ነገር ሲያጋጥመን ይሖዋን ተጠያቂ ከማድረግ እንቆጠባለን።

14, 15. ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ምን ሊረዳን ይችላል?

14 ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ተጽዕኖ እንዲያሳድርባችሁ አትፍቀዱ። በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚያስገባቸው ለማመን የሚያበቃ ምክንያት ነበራቸው። (መዝ. 78:43-53) ይሁን እንጂ፣ ታማኝ ያልሆኑት አሥር ሰላዮች የነዙትን አሉታዊ ወሬ ሲሰሙ የይሖዋን ‘ኃይል ማስታወስ’ አቃታቸው። (መዝ. 78:42) እኛ ግን ከእነሱ በተቃራኒ ይሖዋ እስከ አሁን ያደረገልንን መልካም ነገሮች ጨምሮ በእሱ ሥራዎች ላይ በማሰላሰል ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከር እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ሌሎች የሚናገሩት አሉታዊ ነገር ከይሖዋ ጋር እንድንቆራረጥ አያደርገንም።—መዝ. 77:11, 12

15 ስለ እምነት ባልንጀሮቻችን አሉታዊ አመለካከት ቢያድርብንስ? ይህ ሁኔታ ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (1 ዮሐ. 4:20) እስራኤላውያን አሮን በመሾሙ ምክንያት ባጉረመረሙበት ወቅት ይሖዋ በእሱ ላይ እንዳጉረመረሙ ተሰምቶት ነበር። (ዘኍ. 17:10) በተመሳሳይ እኛም ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል እንዲመሩ በሚጠቀምባቸው ሰዎች ላይ የምናጉረመርም ወይም የምናማርር ከሆነ ይህ በይሖዋ ላይ ከማጉረምረም ተለይቶ አይታይም።—ዕብ. 13:7, 17

16, 17. ችግሮች ሲያጋጥሙን ልናስታውሰው የሚገባ ነገር ምንድን ነው?

16 እየደረሱብን ላሉ ችግሮች ተጠያቂው ይሖዋ እንዳልሆነ አስታውሱ። በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ለይሖዋ ጀርባቸውን ቢሰጡትም እሱ ግን እነሱን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር። (ኢሳ. 1:16-19) በዛሬው ጊዜም ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ይሖዋ እንደሚያስብልንና ሊረዳን ፈቃደኛ እንደሆነ ማወቃችን ያጽናናል። (1 ጴጥ. 5:7) እንዲሁም ችግሮቻችንን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን ይሖዋ ቃል ገብቶልናል።—1 ቆሮ. 10:13

17 ታማኙ ኢዮብ እንዳጋጠመው ሁሉ እኛም ግፍ ከደረሰብን ለዚህ ተጠያቂው ይሖዋ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ይጠላል፤ ጽድቅን ደግሞ ይወዳል። (መዝ. 33:5) “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” ብሎ የተናገረው የኢዮብ ወዳጅ የኤሊሁ ዓይነት አመለካከት ይኑረን። (ኢዮብ 34:10) ይሖዋ ችግሮችን አያመጣብንም፤ እንዲያውም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ ነው።—ያዕ. 1:13, 17

18, 19. ይሖዋን ፈጽሞ መጠራጠር የሌለብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

18 ይሖዋን ፈጽሞ አትጠራጠሩት። አምላክ ፍጹም ነው፤ ሐሳቡም ከእኛ በጣም የላቀ ነው። (ኢሳ. 55:8, 9) በመሆኑም ትሕትና እና ልክን የማወቅ ባሕርይ ልናዳብር ይገባል፤ እነዚህ ባሕርያት ስለ ነገሮች ያለን ግንዛቤ ውስን መሆኑን አምነን እንድንቀበል ይረዱናል። (ሮም 9:20) ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ መረጃ የሚኖረን ሁልጊዜ አይደለም። “አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው” የሚለውን ምሳሌ እውነተኝነት በሕይወትህ ሳትመለከት አልቀረህም።—ምሳሌ 18:17

19 አንድ የምናምነው ወዳጃችን፣ ያደረገው ነገር መጀመሪያ ላይ ባይገባን ወይም ያልተለመደ ቢሆንብን ተሳስቷል ብለን ለመደምደም እንቸኩላለን? ወይስ እንዲህ ያደረገው የሆነ ምክንያት ቢኖረው ነው ብለን እናስባለን? በተለይ ወዳጃችንን ለረጅም ጊዜ የምናውቀው ከሆነ እንዲህ ብለን ማሰባችን  አይቀርም። ፍጹም ያልሆኑ ወዳጆቻችንን ይህን ያህል በፍቅር የምንይዛቸው ከሆነ ሐሳቡና መንገዱ ከእኛ እጅግ የላቀ የሆነውን የሰማዩ አባታችንን ይበልጥ ልናምነው እንደሚገባ ጥያቄ የለውም!

20, 21. ለችግራችን ተጠያቂው ማን መሆኑን ለይተን ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 ለችግራችሁ ተጠያቂው ማን መሆኑን ለይታችሁ እወቁ። እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ለአንዳንዶቹ ችግሮቻችን ተጠያቂው እኛው ራሳችን ልንሆን ስለምንችል ነው። ሁኔታው ይህ ከሆነ ጥፋታችንን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ገላ. 6:7) ይሖዋን ለችግሮቻችሁ ተጠያቂ ለማድረግ አትሞክሩ። ለምን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ መኪና በከፍተኛ ፍጥነት የመጓዝ አቅም ሊኖረው ይችላል። የመኪናው አሽከርካሪ ከተፈቀደው የፍጥነት መጠን በላይ መኪናውን እያበረረ ሄዶ ኩርባ ላይ ለመታጠፍ ሲሞክር አደጋ ደረሰበት እንበል። መኪናውን የሠራው ፋብሪካ ለዚህ አደጋ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? በፍጹም! በተመሳሳይም ይሖዋ ሲፈጥረን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ መመሪያዎችም ሰጥቶናል። ታዲያ የራሳችንን ስህተት ፈጣሪያችን ላይ የምናላክከው ለምንድን ነው?

21 እርግጥ ነው፣ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ መንስኤው ጥሩ ያልሆነ ውሳኔ ማድረጋችን ወይም የተሳሳተ አካሄድ መከተላችን ላይሆን ይችላል። “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ለአንዳንድ ችግሮቻችን መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። (መክ. 9:11 NW) ዞሮ ዞሮ ግን ለክፋት ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:9) ጠላታችን፣ ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አይደለም።—1 ጴጥ. 5:8

ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና እንደ ውድ ሀብት አድርጋችሁ ተመልከቱት

ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ በመታመናቸው ተባርከዋል (አንቀጽ 22ን ተመልከት)

22, 23. ያጋጠሙን ችግሮች ተስፋ አስቆርጠውን ከሆነ ልናስታውሰው የሚገባ ነገር ምንድን ነው?

22 መከራ እና ችግር ሲያጋጥማችሁ የኢያሱንና የካሌብን ምሳሌ አስታውሱ። እነዚህ ሁለት ታማኝ ሰዎች ከአሥሩ ሰላዮች በተቃራኒ መልካም ወሬ ይዘው ተመልሰዋል። (ዘኍ. 14:6-9) በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ያም ቢሆን ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ለ40 ዓመት በምድረ በዳ መንከራተት ነበረባቸው። ኢያሱና ካሌብ ይህ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው አጉረምርመው ወይም አማርረው ይሆን? በፍጹም! በይሖዋ ላይ እምነት ነበራቸው። ታዲያ በዚህ አካሄዳቸው ተባርከዋል? እንዴታ! በወቅቱ የነበረው ትውልድ በምድረ በዳ ሲያልቅ ሁለቱ ሰዎች ግን በመጨረሻ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገብተዋል። (ዘኍ. 14:30) እኛም በተመሳሳይ የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ረገድ “ካልታከትን” የእሱን በረከት እናገኛለን።—ገላ. 6:9፤ ዕብ. 6:10

23 ያጋጠሟችሁ ችግሮች እንዲሁም የሌሎች ወይም የራሳችሁ አለፍጽምና ተስፋ አስቆርጠዋችሁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? በይሖዋ ግሩም ባሕርያት ላይ ትኩረት አድርጉ። ይሖዋ የሰጣችሁን ተስፋ በዓይነ ሕሊናችሁ ለመመልከት ሞክሩ። ‘ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ባይኖረኝ ኖሮ ይሄኔ ሕይወቴ ምን ይመስል ነበር?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ምንጊዜም ከእሱ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም ልባችሁ ፈጽሞ በይሖዋ ላይ እንዲቆጣ አትፍቀዱ!