የሶርያ ንጉሥ የአምላክ ነቢይ የሆነውን ኤልሳዕን አድኖ ለመያዝ እየተከታተለው ነበር፤ ንጉሡ፣ ይህ ነቢይ በኮረብቶች መሃል በምትገኘውና በቅጥር በተከበበችው በዶታይን ከተማ እንደሚገኝ ሰማ። የሶርያው ንጉሥ በሌሊት ፈረሶችን፣ የጦር ሠረገሎችንና እግረኛ ወታደሮችን ወደ ዶታይን ላከ። ጎህ ሲቀድ ሠራዊቱ ከተማዋን ከብቧት ነበር።—2 ነገ. 6:13, 14

የኤልሳዕ አገልጋይ ማለዳ ላይ ተነስቶ ወደ ውጭ ሲወጣ ነቢዩን ለመያዝ የመጣውን ሠራዊት ተመለከተ። በዚህ ጊዜ “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ብሎ ጮኸ። ኤልሳዕም “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው። ከዚያም ነቢዩ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።” (2 ነገ. 6:15-17) ታዲያ ከዚህ ክስተትና ኤልሳዕ በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት ሌሎች ነገሮች ምን ትምህርት እናገኛለን?

ኤልሳዕ በይሖዋ ስለሚተማመንና አምላክ ለእሱ ጥበቃ እያደረገለት እንደሆነ ስለተመለከተ የሶርያ ሠራዊት ቢከብበውም አልተደናገጠም። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለ ተአምር አንጠብቅም፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ እንደሚጠብቅ እናውቃለን። እኛም የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በዙሪያችን ያሉ ያህል ነው። እነዚህን የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በእምነት ዓይን ‘የምናይ’ እንዲሁም ምንጊዜም በአምላክ የምንተማመን ከሆነ ‘ያለ ሥጋት እናድራለን’፤ የይሖዋን በረከትም እናገኛለን። (መዝ. 4:8) እስቲ ኤልሳዕ በሕይወቱ ያጋጠሙትን ሌሎች ክስተቶችም በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።

ኤልሳዕ ነቢዩ ኤልያስን ማገልገል ጀመረ

በአንድ ወቅት፣ ኤልሳዕ በእርሻው ላይ ሳለ ነቢዩ ኤልያስ ወደ እሱ ቀረበና መጐናጸፊያውን ጣለበት። ኤልሳዕ፣ ኤልያስ ያደረገው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ተረድቶ ነበር። ስለዚህ ድግስ አዘጋጅቶ አባትና እናቱን ተሰናበተና ኤልያስን ለማገልገል ሄደ። (1 ነገ. 19:16, 19, 21) ኤልሳዕ አምላክን በሙሉ ነፍሱ ለማገልገል ምንም ሳያመነታ ራሱን ስላቀረበ ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች የተጠቀመበት ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ በኤልያስ ምትክ በነቢይነት አገልግሏል።

ኤልሳዕ፣ ኤልያስን ለስድስት ዓመታት ያህል ሳያገለግለው አልቀረም። በዚህ ወቅት “የኤልያስን እጅ ያስታጥብ የነበረው”  ኤልሳዕ ነው። (2 ነገ. 3:11) በዛሬው ጊዜ እንደሚደረገው ሹካ፣ ማንኪያ ወይም የመሳሰሉትን ነገሮች የመጠቀም ልማድ ባለመኖሩ ሰዎች የሚመገቡት በእጃቸው ነበር። በመሆኑም ከምግብ በኋላ አገልጋዮች የጌቶቻቸውን እጅ ማስታጠባቸው የተለመደ ነበር። ኤልሳዕ ከሚያከናውናቸው እንደነዚህ ያሉ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ዝቅ ተደርገው ይታዩ ይሆናል። ኤልሳዕ ግን የኤልያስ አገልጋይ መሆንን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥረው ነበር።

በዛሬው ጊዜም ብዙ ክርስቲያኖች በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ይሰማራሉ። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው እምነትና ይሖዋን በሙሉ ኃይላቸው ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት ነው። አንዳንዶቹ በቤቴል፣ በግንባታ ፕሮጀክቶች እና በመሳሰሉት የአገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል ከቤተሰባቸው መለየትና ብዙዎች እንደ ዝቅተኛ አድርገው የሚቆጥሯቸውን ሥራዎች መሥራት ጠይቆባቸዋል። ይሖዋ በእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች የሚከናወኑትን ሁሉንም ሥራዎች ከፍ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ማንም ክርስቲያን ዝቅተኛ እንደሆኑ ወይም እንደሚያዋርዱ አድርጎ ሊመለከታቸው አይገባም።—ዕብ. 6:10

ኤልሳዕ አገልግሎቱን በጽናት ቀጥሏል

አምላክ ‘ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ከመውሰዱ’ በፊት ከጌልገላ ወደ ቤቴል ልኮት ነበር። ኤልያስ፣ ተከትሎት እንዳይሄድ ለኤልሳዕ ሐሳብ ቢያቀርብለትም እሱ ግን “ካንተ አልለይም” አለው። በጉዞ ላይ እያሉም ኤልያስ ሁለት ጊዜ ኤልሳዕን ከእሱ ጋር እንዳይሄድ አጥብቆ ቢጠይቀውም ኤልሳዕ ፈቃደኛ አልሆነም። (2 ነገ. 2:1-6) ሩት ኑኃሚንን የሙጥኝ እንዳለች ሁሉ ኤልሳዕም ከኤልያስ ጋር ተጣበቀ። (ሩት 1:8, 16, 17) ለምን? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኤልሳዕ፣ ኤልያስን እንዲያገለግል አምላክ የሰጠውን መብቱን ከፍ አድርጎ ስለተመለከተው ነው።

ኤልሳዕ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በአምላክ ድርጅት ውስጥ አንድ የአገልግሎት መብት ሲሰጠን ይሖዋን እያገለገልን መሆኑን የምናስብ ከሆነ መብቱን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። በእርግጥም ይሖዋን ከማገልገል የሚበልጥ ክብር የለም!—መዝ. 65:4፤ 84:10

“ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ”

ሁለቱ ሰዎች እየተጓዙ ሳሉ ኤልያስ ለኤልሳዕ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ሰለሞን ከዓመታት በፊት እንዳደረገው ሁሉ ኤልሳዕም የጠየቀው ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል የሚረዳው ነገር እንዲሰጠው ነው። ኤልሳዕ ‘የኤልያስ መንፈስ በእጥፍ እንዲያድርበት’ ለመነ። (1 ነገ. 3:5, 9፤ 2 ነገ. 2:9) በእስራኤል ውስጥ የበኩር ልጆች ሁለት እጅ ውርሻ ይሰጣቸው ነበር። (ዘዳ. 21:15-17) ከዚህ አንጻር ኤልሳዕ የኤልያስ መንፈሳዊ ወራሽ እንዲሆን በሌላ አባባል በእሱ ምትክ የይሖዋ ነቢይ ለመሆን እየጠየቀ ነበር። ከዚህም በላይ ኤልሳዕ፣ ‘ለይሖዋ እጅግ እንደቀናው’ እንደ ኤልያስ ያለ ድፍረት እንዲኖረው የፈለገ ይመስላል።—1 ነገ. 19:13, 14

ኤልያስ ለአገልጋዩ ልመና ምን ምላሽ ሰጠ? “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ ያለበለዚያ ግን አይሆንም” አለው። (2 ነገ. 2:10) ኤልያስ ይህን ሲል ሁለት ነገሮችን መጠቆም የፈለገ ይመስላል። አንደኛ፣ ኤልሳዕ የለመነውን ነገር ማግኘት ይችል እንደሆነ መወሰን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ ኤልሳዕ የለመነውን ነገር እንዲያገኝ ከፈለገ የመጣው ቢመጣ ከኤልያስ ጋር ለመቆየት ባደረገው ቁርጥ ውሳኔ መጽናት ነበረበት።

ኤልሳዕ ያየው ነገር

ኤልሳዕ የኤልያስን መንፈስ በእጥፍ ለማግኘት ላቀረበው ልመና አምላክ ምን ምላሽ ሰጠ? ዘገባው እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ። ኤልሳዕም ይህን [አየ]።” * ኤልሳዕ ላቀረበው ልመና ይሖዋ የሰጠው መልስ ይህ ነበር። ኤልሳዕ፣ ኤልያስ ከእሱ ሲወሰድ ስላየው የኤልያስን መንፈስ በእጥፍ ተቀበለ፤ እንዲሁም የነቢዩ መንፈሳዊ ወራሽ ሆነ።—2 ነገ. 2:11-14

ኤልሳዕ፣ ከኤልያስ ላይ የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሳና ለበሰው። ይህን መጐናጸፊያ መልበሱ የአምላክ ነቢይ መሆኑን ያሳውቃል። ኤልሳዕ ቆየት ብሎ የዮርዳኖስን ወንዝ በመክፈል የፈጸመው ተአምርም ነቢይ ሆኖ መሾሙን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ኤልያስ በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት ኤልሳዕ የተመለከተውን ነገር ፈጽሞ እንደማይረሳው ጥርጥር የለውም። ደግሞም እኮ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ማየት የተለመደ ነገር አይደለም! እነዚህ ነገሮች ይሖዋ፣ ለኤልሳዕ የጠየቀውን ነገር እንደሰጠው የሚያሳዩ ናቸው። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ አምላክ ለጸሎታችን ምላሽ ሲሰጠን የእሳት ሠረገሎችና ፈረሶችን በራእይ አናይም። ያም ቢሆን  አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም ታላቅ ኃይሉን እንደሚጠቀም ማስተዋላችን አይቀርም። ደግሞም ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል እየባረከው መሆኑን እየተመለከትን ነው፤ ይህም የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት ሲሄድ ‘የምናየው’ ያህል ነው።—ሕዝ. 10:9-13

ኤልሳዕ፣ ይሖዋ እጅግ ታላቅ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ብዙ ነገሮችን በሕይወቱ ተመልክቷል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነቢዩ 16 ተአምራት እንዲፈጽም አስችሎታል፤ ይህም ኤልያስ እንደፈጸማቸው ከተገለጹት ተአምራት እጥፍ መሆኑ ነው። * ኤልሳዕ የእሳት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ለሁለተኛ ጊዜ የተመለከተው በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው በዶታይን አስጊ ሁኔታ ገጥሞት በነበረበት ወቅት ነው።

ኤልሳዕ በይሖዋ ተማምኗል

ኤልሳዕ በዶታይን በጠላት ቢከበብም አልተደናገጠም። ለምን? በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ነው። እኛም ይህን የመሰለ እምነት ያስፈልገናል። እንግዲያው እምነትን ጨምሮ ሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማሳየት እንድንችል አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን እንጸልይ።—ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23

በዶታይን የተከሰተው ነገር ደግሞ ኤልሳዕ፣ በይሖዋ እንዲሁም በዓይን የማይታየው የእሱ ሠራዊት በሚያደርግለት ጥበቃ ይበልጥ ለመተማመን የሚያበቃ ጠንካራ ምክንያት ሆኖታል። ነቢዩ፣ አምላክ በመላእክት አማካኝነት ከተማዋንና ወራሪውን ሠራዊት እንደከበበ ተገንዝቦ ነበር። አምላክ የጠላት ሠራዊት እንዲታወር በማድረግ ኤልሳዕንና አገልጋዩን በተአምር አድኗቸዋል። (2 ነገ. 6:17-23) ኤልሳዕ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ፣ አደጋ በተደቀነበት በዚያ ወቅትም ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ተማምኖ ነበር።

እኛም እንደ ኤልሳዕ በይሖዋ አምላክ እንተማመን። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲህ ካደረግን አምላክ ‘ይባርከናል፤ ፊቱንም በላያችን ያበራል።’ (መዝ. 67:1) እውነት ነው፣ ቃል በቃል በዙሪያችን የእሳት ሠረገሎችና ፈረሶች የሉም። ይሁን እንጂ በመጪው “ታላቅ መከራ” ወቅት ይሖዋ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ጥበቃ ያደርጋል። (ማቴ. 24:21፤ ራእይ 7:9, 14) እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ “መጠጊያችን” እንደሆነ ምንጊዜም እናስታውስ።—መዝ. 62:8

^ አን.16 ኤልያስ ያረገው መንፈሳዊ አካል የሆኑት ይሖዋና መላእክቱ ወደሚኖሩበት ሰማይ አይደለም። የመስከረም 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15ን ተመልከት።

^ አን.19 የነሐሴ 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10ን ተመልከት።