“ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል።”—1 ቆሮ. 6:11

1. ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታዎችን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ተደናግጠዋል። የይሖዋ ተቃዋሚ በመሆኑ የታወቀ አንድ የባዕድ አገር ሰው በቤተ መቅደሱ በሚገኝ ክፍል ውስጥ እየኖረ ነው። ሌዋውያኑ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ትተዋል። ሽማግሌዎቹም ሕዝቡን በአምልኮ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው መምራት ሲገባቸው በሰንበት ቀን መነገድ ጀምረዋል። በርካታ እስራኤላውያን፣ አይሁዳዊ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ተጋብተዋል። ነህምያ በ443 ዓ.ዓ. አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ እንደዚህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ተመለከተ።—ነህ. 13:6

2. እስራኤላውያን የተቀደሰ ሕዝብ የተባሉት ለምንድን ነው?

2 እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ነበር። በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከልባቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር። “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” በማለት ተናግረዋል። (ዘፀ. 24:3) በመሆኑም አምላክ ቀደሳቸው፤ በሌላ አባባል የተመረጡ ሕዝቦቹ እንዲሆኑ ለያቸው። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነበር! ከአርባ ዓመት በኋላ ሙሴ እንደሚከተለው በማለት ይህን መብታቸውን አስታውሷቸዋል፦ “አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።”—ዘዳ. 7:6

3. ነህምያ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ አይሁዳውያን ያሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

3 የሚያሳዝነው ነገር፣ እስራኤላውያን ቅዱስ ሕዝብ ሆነው ሲመረጡ የነበራቸው ስሜት አልዘለቀም። ከሕዝቡ መካከል አምላክን የሚያገለግሉ አንዳንድ ግለሰቦች ባይጠፉም በጥቅሉ ሲታይ ግን አይሁዳውያኑን ይበልጥ የሚያሳስባቸው የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ሳይሆን ቅዱስ ወይም ለአምላክ ያደሩ መስለው መታየታቸው ነበር። ነህምያ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ታማኝ አይሁዳውያን ንጹሑን አምልኮ መልሰው ለማቋቋም ከባቢሎን ከተመለሱ መቶ ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል። የሚያሳዝነው ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበራቸው ቅንዓት እንደገና ቀዝቅዞ ነበር።

4. ቅዱስ የሆነው ሕዝብ አባላት ሆነን ለመቀጠል የሚረዱንን የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

4 አምላክ፣ እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮችም በቡድን ደረጃ ቀድሷቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት፣ ቅዱሳን ማለትም  ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የተለዩ ሕዝብ ናቸው። (ራእይ 7:9, 14, 15፤ 1 ቆሮ. 6:11) እስራኤላውያን በአምላክ ፊት ቅዱስ ሆነው መታየታቸው ከጊዜ በኋላ ቀርቷል፤ ማናችንም ብንሆን ይህ ዓይነት ሁኔታ እንዲደርስብን አንፈልግም። እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይደርስብን ለማድረግ እንዲሁም ቅዱስ ሆነን ለመቀጠልና ምንጊዜም በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ ድርሻ ለማበርከት ምን ሊረዳን ይችላል? በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ በነህምያ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሱ አራት ነገሮችን እንመረምራለን፤ እነሱም (1) ከመጥፎ ጓደኝነት መራቅ፣ (2) ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን መደገፍ፣ (3) መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም፣ (4) ክርስቲያናዊ መለያችሁ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ናቸው። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር።

ከመጥፎ ጓደኝነት መራቅ

ነህምያ ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (አንቀጽ 5, 6ን ተመልከት)

5, 6. ኤልያሴብ እና ጦብያ እነማን ናቸው? ኤልያሴብ ከጦብያ ጋር የተቀራረበው ለምን ሊሆን ይችላል?

5 ነህምያ 13:4-9ን አንብብ። ርኩስ በሆኑ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ነገሮች ስለተከበብን ቅድስናችንን ጠብቀን መቀጠል ቀላል አይደለም። የኤልያሴብን እና የጦብያን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤልያሴብ ሊቀ ካህን ነበር፤ ጦብያ ደግሞ አሞናዊ ሲሆን በይሁዳ ባለው የፋርስ አስተዳደር ውስጥ ያገለግል የነበረ ይመስላል። ጦብያና አጋሮቹ፣ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ይቃወሙ ነበር። (ነህ. 2:10) የአምላክ ሕግ አሞናውያን ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ ይከለክላል። (ዘዳ. 23:3) ታዲያ ሊቀ ካህኑ፣ እንደ ጦብያ ዓይነት ሰው በቤተ መቅደሱ ዕቃ ቤት ውስጥ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

6 ጦብያ የኤልያሴብ የቅርብ ወዳጅ ነበር። ጦብያ እና ልጁ የሆሐናን አይሁዳውያን ሴቶችን ያገቡ ሲሆን በርካታ አይሁዳውያን ስለ ጦብያ መልካምነት ያወሩ ነበር። (ነህ. 6:17-19) ከኤልያሴብ የልጅ ልጆች አንዱ፣ የሰማርያ ገዥና የጦብያ የቅርብ ጓደኛ የሆነውን የሰንባላጥን ልጅ አግብቶ ነበር። (ነህ. 13:28) ኤልያሴብ፣ ይሖዋን የማያመልክ እንዲያውም ተቃዋሚ የሆነ ሰው ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት የፈቀደው ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር ባለው ቅርርብ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ነህምያ ግን የጦብያን የቤት ዕቃዎች በሙሉ ከቤተ መቅደሱ አውጥቶ በመጣል ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል።

7. ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች በይሖዋ ፊት ቅድስናቸውን ጠብቀው ለመመላለስ ምን ማድረግ አለባቸው?

7 ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብን ለይሖዋ ነው። የጽድቅ መሥፈርቶቹን ካላከበርን በእሱ ፊት ቅዱስ ሆነን መቀጠል አንችልም። ለቤተሰባችን ታማኝ ለመሆን ስንል የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መጣስ የለብንም። ክርስቲያን ሽማግሌዎች በራሳቸው አመለካከትና ስሜት ከመመራት ይልቅ በይሖዋ ለመመራት ይጥራሉ። (1 ጢሞ. 5:21) እነዚህ ሽማግሌዎች በይሖዋ ፊት ያላቸውን አቋም የሚያበላሽ ነገር ላለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።—1 ጢሞ. 2:8

8. ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ከጓደኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

8 “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” የሚለውን ምክር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (1 ቆሮ. 15:33) ከዘመዶቻችን መካከል አንዳንዶቹ በጎ ተጽዕኖ ላያሳድሩብን ይችላሉ። ኤልያሴብ፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደገና በሚገነባበት ወቅት ነህምያን ከልቡ በመደገፍ ለሕዝቡ ግሩም ምሳሌ ትቷል። (ነህ. 3:1) ውሎ አድሮ ግን ጦብያና ሌሎች ሰዎች ያሳደሩበት መጥፎ ተጽዕኖ ኤልያሴብ በይሖዋ ፊት ቅድስናውን እንዲያጣ የሚያደርጉ ነገሮችን ወደ መፈጸም ሳይመራው አልቀረም። ጥሩ ጓደኞች፣ ጠቃሚ በሆኑ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች እንድንካፈል ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት እንድንካፈል ያበረታቱናል። ትክክለኛውን ነገር እንድናደርግ የሚያበረታቱንን የቤተሰባችንን አባላት ይበልጥ እንወዳቸዋለን እንዲሁም እናደንቃቸዋለን።

ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን መደገፍ

9. ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ የነበረው ዝግጅት የተስተጓጎለው ለምንድን ነው? ነህምያ ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂ ያደረገው ማንን ነው?

9 ነህምያ 13:10-13ን አንብብ። ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰበት ወቅት ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባው ስጦታ በጣም ቀንሶ ነበር። ሌዋውያን፣ ከሕዝቡ የሚያገኙት ድጋፍ ስለቀረ በቤተ መቅደሱ  የሚያከናውኑትን አገልግሎት ትተው በእርሻቸው ላይ መሥራት ጀመሩ። ነህምያ ለዚህ ሁኔታ ተጠያቂ ያደረገው ሹማምንቱን ነው። እነዚህ ሹማምንት ኃላፊነታቸውን ቸል ብለው የነበረ ይመስላል። ሹማምንቱ፣ ወይ ሕዝቡ የሚሰጠውን አሥራት አልሰበሰቡም አሊያም ደግሞ የሰበሰቡትን ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። (ነህ. 12:44) በመሆኑም ነህምያ አሥራቱ እንዲሰበሰብ ዝግጅት አደረገ። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ ዕቃ ቤት ኃላፊ የሚሆኑና የሕዝቡን መዋጮ ለሌዋውያኑ የሚያከፋፍሉ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን ሾመ።

10, 11. የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ የሚያስችል ምን መብት አግኝተዋል?

10 ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለ? አዎን፣ ይህ ታሪክ ይሖዋን በሀብታችን የማክበር መብት እንደተሰጠን ያስታውሰናል። (ምሳሌ 3:9) የእሱን ሥራ ለመደገፍ አስተዋጽኦ ስናደርግ ከይሖዋ የተቀበልነውን መልሰን እየሰጠነው ነው። (1 ዜና 29:14-16) ለይሖዋ የምንሰጠው ብዙ ነገር እንደሌለን ይሰማን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ፍላጎቱ ካለን ሁላችንም ብንሆን መስጠት እንችላለን።—2 ቆሮ. 8:12

11 ብዙ ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት በዕድሜ የገፉ ልዩ አቅኚ ባልና ሚስትን ለበርካታ ዓመታት በሳምንት አንድ ቀን ቤታቸው ይጋብዟቸው ነበር። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ስምንት ልጆች ስላሉ ቤተሰቡ ትልቅ ነው፤ ያም ቢሆን እናትየው “ለአሥር ሰው የሚሆን ምግብ ማዘጋጀቴ ስለማይቀር ሁለት ሰው ቢጨመር ምን ይጎዳል?” ትል ነበር። አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ከዚህ ቤተሰብ ጋር በየሳምንቱ መመገባቸው ያን ያህል ትልቅ ነገር አይመስል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አቅኚዎቹ የተደረገላቸውን መስተንግዶ ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር! ቤተሰቡም ቢሆን ይህን በማድረጉ በረከት አግኝቷል። ልጆቹ፣ አቅኚ የሆኑትን ባልና ሚስት ተሞክሮ መስማታቸውና የእነሱን ማበረታቻ ማግኘታቸው በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ፣ ሁሉም ልጆች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገቡ።

12. በጉባኤ ውስጥ የተሾሙ ወንዶች ምን በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ?

12 ከነህምያ ታሪክ የምናገኘው ሌላው ትምህርት ደግሞ ይህ ነው፦ በዛሬው ጊዜ ያሉ የተሾሙ ወንዶች ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን በመደገፍ ረገድ ልክ እንደ ነህምያ ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው። የእነሱ ምሳሌነት ሌሎቹን የጉባኤው አባላት ይጠቅማል። የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲህ ሲያደርጉ የሐዋርያው ጳውሎስንም ምሳሌ ይከተላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛውን አምልኮ የደገፈ ከመሆኑም ሌላ ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ መዋጮ ማድረግን በተመለከተ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለጉባኤዎች አካፍሏል።—1 ቆሮ. 16:1-3፤ 2 ቆሮ. 9:5-7

መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም

13. አንዳንድ አይሁዳውያን ሰንበትን ያቃለሉት እንዴት ነው?

13 ነህምያ 13:15-21ን አንብብ። በሕይወታችን ውስጥ ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ከተጠመድን ቀስ በቀስ መንፈሳዊነታችንን ልናጣ እንችላለን። ዘፀአት 31:13 እንደሚናገረው እስራኤላውያን በየሳምንቱ  ሰንበትን እንዲያከብሩ የታዘዙት የተቀደሰ ሕዝብ መሆናቸውን እንዲያስታውሱ ነው። የሰንበት ቀን፣ እስራኤላውያን በቤተሰብ ሆነው አምልኳቸውን ለማከናወን፣ ለመጸለይ እና በአምላክ ሕግ ላይ ለማሰላሰል እንዲያውሉት የተለየ ዕለት ነበር። በነህምያ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ግን በሌሎች ቀናት እንደሚያደርጉት ሁሉ በሰንበት ቀንም የወትሮ ሥራቸውን ያከናውኑ ነበር። በመሆኑም ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ ችላ ተባለ። ነህምያ ይህን ሁኔታ ሲመለከት ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ነጋዴዎችን፣ ሰንበት ከመጀመሩ በፊት ከከተማይቱ ካስወጣ በኋላ ልክ ፀሐይ ስትጠልቅ የከተማይቱ በሮች እንዲዘጉ አደረገ።

14, 15. (ሀ) ከሰብዓዊ ሥራ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ገደብ የማናበጅ ከሆነ ምን ሊከሰት ይችላል? (ለ) ወደ አምላክ እረፍት መግባት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ነህምያ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? የምናገኘው አንዱ ትምህርት ከሰብዓዊ ሥራ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ገደብ ልናበጅ እንደሚገባ ነው። አለዚያ ትኩረታችንን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማድረግ ሊያስቸግረን ይችላል፤ በተለይ ደግሞ ሰብዓዊ ሥራችንን የምንወደው ከሆነ ልባችን ሊከፈል ይችላል። ኢየሱስ፣ ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ ስለ መገዛት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 6:24ን አንብብ።) ነህምያ ቁሳዊ ሀብት ለማከማቸት የሚያስችል አጋጣሚ ነበረው፤ ይሁንና በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ጊዜውን የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ነህ. 5:14-18) ከጢሮስ እና ከሌላ አገር ሰዎች ጋር ንግድ ከመጀመር ይልቅ ወንድሞቹን በመርዳትና የይሖዋን ስም ለማስቀደስ የሚያስችሉ ነገሮችን በማከናወን ተጠምዶ ነበር። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ጉባኤውን በሚጠቅም ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፤ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ማሳየታቸውም በእምነት ባልንጀሮቻቸው ዘንድ እንዲወደዱ ያደርጋቸዋል። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ ሰላምና የደኅንነት ስሜት ሊኖር የቻለው በዚህ የተነሳ ነው።—ሕዝ. 34:25, 28

15 ክርስቲያኖች በየሳምንቱ ሰንበትን እንዲያከብሩ ባይጠበቅባቸውም ጳውሎስ “የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ይጠብቀዋል” በማለት ጽፏል። አክሎም “ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏል” ብሏል። (ዕብ. 4:9, 10) ክርስቲያኖች፣ ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ እንዲሁም ታዛዦች በመሆን ወደ አምላክ እረፍት መግባት ይችላሉ። ታዲያ አንተም ሆንክ የቤተሰብህ አባላት በቤተሰብ ሆናችሁ ለምታከናውኑት አምልኮ፣ ለስብሰባዎችና ለአገልግሎት በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያውን እየሰጣችሁ ነው? አሠሪያችን ወይም የሥራ ባልደረቦቻችን ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ለመስጠት የምናደርገውን ጥረት የማያከብሩልን ከሆነ ቁርጥ አቋም መውሰድ ይኖርብናል። በሌላ አባባል ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ተገቢውን ትኩረት እና ቅድሚያውን ለመስጠት ልክ እንደ ነህምያ ‘የከተማይቱን በሮች መዝጋትና የጢሮስን ሰዎች ማባረር’ ሊያስፈልገን ይችላል። የተቀደስን ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ‘አኗኗሬ ለይሖዋ አገልግሎት የተለየሁ ሰው መሆኔን ያሳያል?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።—ማቴ. 6:33

ክርስቲያናዊ መለያችሁ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ

16. በነህምያ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን የአምላክ ቅዱስ ሕዝብ እንደሆኑ የሚያሳውቃቸውን መለያ ለማጣት ተቃርበው የነበረው እንዴት ነው?

16 ነህምያ 13:23-27ን አንብብ። በነህምያ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሴቶችን ያገቡ ነበር። ነህምያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣበት ወቅት፣ ሽማግሌዎቹ በሙሉ እስራኤላውያን ወንዶች የሌላ አገር ሴቶችን እንደማያገቡ በሚገልጽ የውል ስምምነት ላይ እንዲፈርሙ አድርጎ ነበር። (ነህ. 9:38፤ 10:30) ነህምያ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ግን አይሁዳውያን የባዕድ አገር ሴቶችን እንዳገቡና በዚህም የተነሳ የአምላክ ቅዱስ ሕዝብ እንደሆኑ የሚያሳውቃቸውን መለያ ለማጣት እንደተቃረቡ ተገነዘበ። ከእነዚህ የባዕድ አገር ሴቶች የተወለዱት ልጆች ዕብራይስጥ ማንበብም ሆነ መናገር አይችሉም ነበር። እነዚህ ልጆች ሲያድጉ ራሳቸውን እንደ እስራኤላዊ ይቆጥራሉ? ወይስ የአሽዶድ፣ የአሞን ወይም የሞዓብ ሰው እንደሆኑ ይሰማቸዋል? ደግሞስ ዕብራይስጥ የማያውቁ ከሆነ የአምላክን ሕግ እንዴት መረዳት ይችላሉ? የእናቶቻቸውን የሐሰት አማልክት ሳይሆን ይሖዋን ማወቅና እሱን ማገልገል የሚችሉትስ እንዴት ነው? ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ሳይውል ሳያድር ቆራጥ እርምጃ  መውሰድ ያስፈልግ ነበር፤ ነህምያም ይህን እርምጃ ወስዷል።—ነህ. 13:28

ልጆቻችሁ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሠርቱ እርዷቸው (አንቀጽ 17, 18ን ተመልከት)

17. ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜም ልጆቻችን ክርስቲያናዊ መለያ እንዲኖራቸው ለመርዳት ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። ወላጆች እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ልጆቼ “ንጹሑን ልሳን” ምን ያህል አጥርተው ይናገራሉ? በሌላ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ምን ያህል ጠንቅቀው ያውቃሉ እንዲሁም ይናገራሉ? (ሶፎ. 3:9 የ1954 ትርጉም) ልጆቼ የሚያወሩት ነገር የአምላክ መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንዳለ ያሳያል? ወይስ ንግግራቸው የዓለምን መንፈስ ያንጸባርቃል?’ ልጆቻችሁ ማሻሻል ያለባቸው ነገር እንዳለ ካስተዋላችሁ ቶሎ ተስፋ አትቁረጡ። አንድን ቋንቋ መማር በተለይ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ካሉ ጊዜ ይወስዳል። ልጆቻችሁ አቋማቸውን እንዲያላሉ ከባድ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። በመሆኑም የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁንና ሌሎች አጋጣሚዎችን በመጠቀም ልጆቻችሁ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው በትዕግሥት እርዷቸው። (ዘዳ. 6:6-9) ከሰይጣን ዓለም የተለዩ መሆን ምን ጥቅም እንዳለው በደንብ አስረዷቸው። (ዮሐ. 17:15-17) እንዲሁም ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርጉ።

18. ልጆች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ በመርዳት ረገድ ከወላጆቻቸው የተሻለ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ሰው የለም የምንለው ለምንድን ነው?

18 እርግጥ ነው፣ ይሖዋን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል ውሳኔ የሚያደርገው ልጁ ነው። ያም ቢሆን ወላጆች በዚህ ረገድ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ መሆንን፣ ልጁ ማድረግ የሌለበትን ነገር በግልጽ መንገርንና የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ማስረዳትን ይጨምራል። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ በመርዳት ረገድ ከእናንተ የተሻለ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ሰው የለም። ልጆቻችሁ ክርስቲያናዊ መለያ እንዲኖራቸውና ይህንንም እንዳያጡት የእናንተ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ሁላችንም ምሳሌያዊ ‘መደረቢያችንን’ ላለማጣት መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው፤ በሌላ አባባል የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳውቁት ባሕርያትና መሥፈርቶች በሕይወታችን ሊንጸባረቁ ይገባል።—ራእይ 3:4, 5፤ 16:15

ይሖዋ “በመልካም” ያስበናል

19, 20. ይሖዋ “በመልካም” እንዲያስበን ምን ማድረግ አለብን?

19 በነህምያ ዘመን የኖረው ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ስሙን ለሚያከብሩ . . . የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ” ብሏል። (ሚል. 3:16, 17) አምላክ ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸውና ስሙን የሚወዱ ሰዎችን መቼም አይረሳቸውም።—ዕብ. 6:10

20 ነህምያ “አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ” በማለት ጸልዮአል። (ነህ. 13:31 የ1954 ትርጉም) እኛም ከመጥፎ ጓደኞች የምንርቅ፣ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን የምንደግፍ፣ መንፈሳዊ ነገሮችን የምናስቀድም እንዲሁም ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ የምንጠነቀቅ ከሆነ እንደ ነህምያ ስማችን በአምላክ የመታሰቢያ መጽሐፍ ላይ ይጻፋል። እንግዲያው ‘በእምነት ውስጥ እየተመላለስን መሆናችንን ለማወቅ ዘወትር ራሳችንን እንመርምር።’ (2 ቆሮ. 13:5) ለይሖዋ የተለየው ቅዱስ ሕዝብ አባል ሆነን ለመኖር የምንችለውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋ “በመልካም” ያስበናል።