በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሰኔ 2013

ስለ ይሖዋ ታማኝነትና ይቅር ባይነት ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ

ስለ ይሖዋ ታማኝነትና ይቅር ባይነት ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ

“ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤ ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም።”—መዝ. 86:5

1, 2. (ሀ) ታማኝ እና ይቅር ባይ የሆኑ ወዳጆችን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

እውነተኛ ጓደኛ የምትለው ምን ዓይነት ሰው ነው? አሽሊ የተባለች አንዲት ክርስቲያን “እውነተኛ ጓደኛ የምለው በክፉውም ሆነ በደጉ ወቅት ከጎኔ የሚቆምና ስሳሳት ይቅር የሚለኝን ሰው ነው” ብላለች። ማንኛችንም ብንሆን ታማኝ እና ይቅር ባይ የሆኑ ወዳጆችን ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እንዲህ ያሉ ጓደኞች ምንጊዜም እንደማይለዩንና እንደሚወዱን ይሰማናል።—ምሳሌ 17:17

2 ይሖዋ ከማንም በላይ ታማኝ እና ይቅር ባይ የሆነ ወዳጃችን ነው። መዝሙራዊው “ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤ ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ [ወይም “ታማኝ ፍቅርህ፣”] ወሰን የለውም” ማለቱ ተገቢ ነው። (መዝ. 86:5) ታማኝ እና ይቅር ባይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ እነዚህን ግሩም ባሕርያት የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን ከማንም የበለጠ ለምንቀርበው ወዳጃችን ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል። ከዚህም ሌላ ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናክርልናል።—1 ዮሐ. 4:7, 8

ይሖዋ ታማኝ ነው

3. ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

3 ታማኝነት ከአንድ አካል ጋር መጣበቅን፣ እምነት የሚጣልበት መሆንን እንዲሁም የማይቋረጥ ድጋፍ መስጠትን የሚያጠቃልል አስደሳች ባሕርይ ነው። ታማኝ ሰው ወረተኛ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታማኝ ለሆነለት አካል (ወይም ነገር) ጥልቅ ፍቅር ስላለው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ከዚያ አካል (ወይም ነገር) ጋር ይቆራኛል። “ታማኝ” በመሆን ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው።—ራእይ 16:5

4, 5. (ሀ) ይሖዋ ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ታማኝነቱን ስላሳየባቸው ሁኔታዎች በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን ሊያበረታታን የሚችለው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም። ከእነዚህ አንዱ የሆነው ንጉሥ ዳዊት  ስለ ይሖዋ ታማኝነት መሥክሯል። (2 ሳሙኤል 22:26ን አንብብ።) ዳዊት መከራ ባጋጠመው ወቅት ይሖዋ እሱን በመምራት፣ በመጠበቅ እንዲሁም በመታደግ ታማኝነቱን አሳይቷል። (2 ሳሙ. 22:1) ዳዊት የይሖዋ ታማኝነት በቃላት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ለዳዊት ታማኝነት ያሳየው ለምንድን ነው? ዳዊት ራሱ “ታማኝ ሰው” ስለነበረ ነው። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያሳዩትን ታማኝነት ከፍ አድርጎ የሚመለከት ሲሆን ለእነሱ ታማኝ በመሆን ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል።—ምሳሌ 2:6-8

5 ይሖዋ ታማኝነቱን ስላሳየባቸው ሁኔታዎች በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን ሊያበረታታን ይችላል። ሪድ የተባለ አንድ ታማኝ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ዳዊት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ስላደረገለት ነገር የሚገልጹ ታሪኮችን ማንበቤ በጣም ያበረታታኛል። ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ በየዋሻው እየተደበቀ ይኖር በነበረበት ወቅትም ይሖዋ የሚያስፈልገውን አሟልቶለታል። ይህን ማወቄ በእጅጉ ያጽናናኛል! ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመኝ እንዲሁም ሁሉ ነገር ጭልምልም ከማለቱ የተነሳ ሰማይ የተደፋብኝ ያህል ቢሰማኝ እንኳ እኔ ለይሖዋ ታማኝ እስከሆንኩ ድረስ እሱ ከጎኔ እንደማይለይ እንዳስታውስ ይረዳኛል።” አንተም እንደዚህ እንደሚሰማህ ጥያቄ የለውም።—ሮም 8:38, 39

6. ይሖዋ ታማኝነት የሚያሳይባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህስ ለአገልጋዮቹ ምን ጥቅም ያስገኛል?

6 ይሖዋ ታማኝነት የሚያሳይባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው? አንደኛው መንገድ፣ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በማክበር ነው። ይሖዋ “እስከ ሽምግልናችሁ . . . እኔው ነኝ” በማለት እንደማይለወጥ አረጋግጧል። (ኢሳ. 46:4) አምላክ ምንጊዜም ውሳኔ የሚያደርገው ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን በተመለከተ ባወጣቸው መሥፈርቶች ላይ ተመሥርቶ ነው፤ እነዚህ መሥፈርቶች ደግሞ የሚለዋወጡ አይደሉም። (ሚል. 3:6) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የገባውን ቃል በመፈጸም ታማኝ መሆኑን ያሳያል። (ኢሳ. 55:11) በመሆኑም የይሖዋ ታማኝነት ለሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ ጥቅም ያስገኛል። እንዴት? የእሱን መሥፈርቶች ለመጠበቅ የተቻለንን ያህል ጥረት እስካደረግን ድረስ እሱም የገባውን ቃል በመጠበቅ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳ. 48:17, 18

ታማኝ በመሆን ረገድ ይሖዋን ምሰሉ

7. ታማኝ በመሆን ረገድ አምላክን መምሰል የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

 7 እኛስ ታማኝ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በመርዳት ነው። (ምሳሌ 3:27) ለምሳሌ ያህል፣ በጤና ማጣት፣ ቤተሰቡ በሚያደርስበት ተቃውሞ ወይም በግል ድክመቶቹ ምክንያት ተስፋ የቆረጠ ክርስቲያን ታውቃለህ? ጊዜ ወስደህ ይህንን ሰው “ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል” ለማነጋገር ለምን አትሞክርም? (ዘካ. 1:13) * ይህን ስታደርግ “ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ” ታማኝና እውነተኛ ጓደኛ እንደሆንክ ታሳያለህ።—ምሳሌ 18:24

8. በትዳር ውስጥ ታማኝ በመሆን የይሖዋን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8 ታማኝ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ለምንወዳቸው ሰዎች ምንጊዜም ታማኞች ሆነን በመገኘት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ባለትዳር ከሆንን ምንጊዜም ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆን እንዳለብን እናውቃለን። (ምሳሌ 5:15-18) በመሆኑም ምንዝር መፈጸም ይቅርና ወደዚህ ድርጊት ሊመራን የሚችል ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም እንቆጠባለን። (ማቴ. 5:28) በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችንን ከማማት ወይም ስማቸውን ከማጥፋት በመራቅ እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ጎጂ ወሬዎችን ማሰራጨት ይቅርና ለመስማት እንኳ ፈቃደኞች ባለመሆን ለእነሱ ታማኝ መሆናችንን እናሳያለን።—ምሳሌ 12:18

9, 10. (ሀ) ከሁሉም በላይ ታማኝ መሆን የምንፈልገው ለማን ነው? (ለ) የይሖዋን ትእዛዛት ማክበር ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ የምንለው ለምንድን ነው?

9 ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንፈልጋለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ነገሮችን ከእሱ አመለካከት አንጻር በማየት  ማለትም እሱ የሚወደውን በመውደድና የሚጠላውን በመጥላት እንዲሁም ሕይወታችንን ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ በመምራት ነው። (መዝሙር 97:10ን አንብብ።) አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ከይሖዋ አስተሳሰብና ስሜት ጋር ለማጣጣም ጥረት ባደረግን መጠን ትእዛዛቱን ማክበር ይበልጥ ቀላል እየሆነልን ይሄዳል።—መዝ. 119:104

10 እርግጥ ነው፣ የይሖዋን ትእዛዛት ማክበር ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ታማኝ ሆነን ለመኖር ትግል ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ አንዳንድ ያላገቡ ክርስቲያኖች ማግባት ቢፈልጉም ከይሖዋ አገልጋዮች መካከል ተስማሚ የትዳር ጓደኛ አላገኙ ይሆናል። (1 ቆሮ. 7:39) የማያምኑ የሥራ ባልደረቦቿ ሁልጊዜ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ሊያገናኟት የሚጥሩ አንዲት ያላገባች እህትን እንውሰድ። ይህች እህት ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገለች ይሆናል። ያም ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ ሆና ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ታማኝነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን የእምነት ባልንጀሮቻችን አድናቆት ሊቸራቸው አይገባም? ይሖዋ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ለእሱ ታማኝ ሆነው ለመኖር ለሚጥሩ አገልጋዮቹ በሙሉ ወሮታ እንደሚከፍላቸው ጥርጥር የለውም።—ዕብ. 11:6

“ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።”—ምሳሌ 18:24 (ተመልከት አንቀጽ 7ን)

“እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌ. 4:32 (ተመልከት አንቀጽ 16ን)

ይሖዋ ይቅር ባይ ነው

11. ይቅር ባይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ተወዳጅ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ሌላው ደግሞ ይቅር ባይነት ነው። ይቅር ባይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ይቅር ለማለት የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት እስካለ ድረስ የበደለን ግለሰብ የፈጸመውን ስህተት ማለፍ ማለት ነው። ይህ ሲባል ይቅር የሚለው ግለሰብ የተፈጸመበትን በደል እንዲሁ ችላ ብሎ ያልፈዋል ወይም ምንም እንዳልተከሰተ አድርጎ ይቆጥረዋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በበደለው ግለሰብ ላይ ቂም አይዝም ማለት ነው። ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች “ይቅር ባይ” እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ።—መዝ. 86:5

12. (ሀ) ይሖዋ ይቅር ባይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ‘ኃጢአት ይደመሰሳል’ ሲባል ምን ማለት ነው?

12 ይሖዋ ይቅር ባይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ “ይቅርታው ብዙ ነው”፤ ይህም ሲባል አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ ይቅር ይለዋል እንዲሁም ኃጢአቱን መልሶ አያነሳውም ማለት ነው። (ኢሳ. 55:7) ይሖዋ ይቅር የሚለው ሙሉ በሙሉ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን? በሐዋርያት ሥራ 3:19 ላይ የሚገኘውን ማረጋገጫ ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አድማጮቹን “ንስሐ ግቡ፣  ተመለሱም” በማለት አሳስቧቸዋል። አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ ከገባ በመጥፎ አካሄዱ ተጸጽቷል ማለት ነው። እንዲሁም ኃጢአቱን መልሶ ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። (2 ቆሮ. 7:10, 11) ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአተኛው ንስሐ የገባው ከልቡ ከሆነ መጥፎ አካሄዱን እርግፍ አድርጎ በመተው ‘ይመለሳል’ እንዲሁም አምላክን በሚያስደስት መንገድ መመላለስ ይጀምራል። ጴጥሮስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች እንዲህ በማድረግ ከልባቸው ንስሐ መግባታቸውን ካሳዩ ምን ጥቅም ያገኛሉ? ጴጥሮስ ‘ኃጢአታቸው እንደሚደመሰስ’ ነግሯቸዋል። “እንዲደመሰስ” የሚለው አገላለጽ “ሙልጭ አድርጎ መጥረግ፣ ማጽዳት” የሚል ፍቺ ካለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው። ይሖዋ አንድን ሰሌዳ ሙልጭ አድርጎ የማጽዳት ያህል ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር ይለናል።—ዕብ. 10:22፤ 1 ዮሐ. 1:7

13. “ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም” የሚለው ጥቅስ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

13 ይሖዋ አንድ ጊዜ ይቅር ካለ በኋላ የግለሰቡን ኃጢአት መልሶ እንደማያነሳው እንዴት እናውቃለን? እስቲ ኤርምያስ የተናገረውን ትንቢት እንመልከት፤ ኤርምያስ በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ለሚያሳዩ ሁሉ እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ስለሚያስገኘውና ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ስለተደረገው ቃል ኪዳን ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 31:34ን አንብብ።) ይሖዋ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም” ብሏል። ስለዚህ ይሖዋ አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በኋላ ወደፊት በዚያ ኃጢአት መልሶ አይጠይቀንም። የሠራነውን ጥፋት እንደ አዲስ እያነሳ አይወቅሰንም ወይም አይቀጣንም። ከዚህ ይልቅ ያንን ኃጢአት ይቅር ካለን ከዚያ በኋላ ጨርሶ አያነሳውም።—ሮም 4:7, 8

14. ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ማሰላሰላችን የሚያጽናናን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

14 ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ማሰላሰላችን ያጽናናናል። አንድ ምሳሌ እንውሰድ። ኢሌን * የተባለች አንዲት እህት ከበርካታ ዓመታት በፊት ተወግዳ ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ግን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተመለሰች። ኢሌን እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ይቅር እንዳለኝ ራሴን ለማሳመን የምሞክር ከመሆኑም ሌላ ለሌሎችም ይህንኑ እናገር ነበር። ያም ቢሆን ግን አምላክ ከእኔ እንደራቀ ወይም ሌሎች ሰዎች ከእኔ ይበልጥ እንደሚቀርቡትና እውን እንደሚሆንላቸው ይሰማኝ ነበር።” ኢሌን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱትን የይሖዋን ይቅር ባይነት የሚያሳዩ ምሳሌያዊ አገላለጾች ማንበቧና በዚያ ላይ ማሰላሰሏ አጽናንቷታል። “ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደኝና እንደሚንከባከበኝ መረዳት የቻልኩት በዚህ ጊዜ ነው” በማለት አክላ ተናግራለች። ኢሌን ከሁሉ የበለጠ የነካት “ይሖዋ ኃጢአታችንን አንዴ ይቅር ካለን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ኃጢአታችን ያስከተለብንን ኃፍረት ተሸክመን እንደምንኖር ሆኖ ሊሰማን አይገባም” * የሚለው ሐሳብ ነው። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይሖዋ ኃጢአቴን ሙሉ በሙሉ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል እንዲሁም የሠራሁት በደል ያስከተለብኝን የጥፋተኝነት ስሜት ዕድሜ ልኬን ተሸክሜ መኖር እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን ጊዜ ቢወስድም እንኳ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንደምችል ይሰማኛል፤ እንዲሁም ከባድ ሸክም ከራሴ ላይ የወረደልኝ ያህል ቅልል ብሎኛል።” እንዲህ ያለውን አፍቃሪና ይቅር ባይ አምላክ ማገልገል ምንኛ መታደል ነው!—መዝ. 103:9

ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋን ምሰሉ

15. ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

15 እኛም ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ እርስ በርስ ይቅር በመባባል የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ሉቃስ 17:3, 4ን አንብብ።) ይሖዋ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን እንደሚረሳው ማለትም ከዚያ በኋላ ፈጽሞ እንደማያነሳው አስታውስ። እኛም ሌሎችን ይቅር ስንል ጉዳዩን መርሳትና ወደፊትም እንደገና ከማንሳት መቆጠብ ይኖርብናል።

16. (ሀ) ይቅር ባይ እንሆናለን ሲባል የተፈጸመብንን በደል እንዲሁ ችላ ብለን እናልፈዋለን ወይም ደግሞ ሌሎች መጠቀሚያ ሲያደርጉን ዝም ብለን እንመለከታለን ማለት ነው? አብራራ። (ለ) አምላክ ይቅር እንዲለን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

 16 ይቅር ባይ እንሆናለን ሲባል የተፈጸመብንን በደል እንዲሁ ችላ ብለን እናልፈዋለን ወይም ደግሞ ሌሎች መጠቀሚያ ሲያደርጉን ዝም ብለን እንመለከታለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በበደለን  ሰው ላይ ቂም አንይዝም ማለት ነው። አምላክ ይቅር እንዲለን ከፈለግን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እንደ ይሖዋ ይቅር ባይ መሆን እንደሚኖርብን ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 6:14, 15) ይሖዋ የሌሎችን ሁኔታ የሚረዳ በመሆኑ “ትቢያ መሆናችንን” ያስባል። (መዝ. 103:14) እኛም የእሱን ምሳሌ በመከተል የሌሎችን ጉድለት ችለን ለማለፍ ፈቃደኛ ልንሆን እንዲሁም በነፃ ከልባችን ይቅር ልንላቸው አይገባንም?—ኤፌ. 4:32፤ ቆላ. 3:13

ስለበደለን ሰው ከልባችን መጸለይ ይኖርብናል (ተመልከት አንቀጽ 17ን)

17. አንድ የእምነት ባልንጀራችን ጎድቶን ከሆነ ይቅር ባይ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

 17 እርግጥ ነው፣ ይቅር ባይ መሆን ከባድ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንኳ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ከብዷቸው የነበረ ይመስላል። (ፊልጵ. 4:2) እኛም አንድ የእምነት ባልንጀራችን ጎድቶን ከሆነ ይቅር ባይ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? እስቲ የኢዮብን ምሳሌ እንመልከት። ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉት ወዳጅ ተብዬዎች በኢዮብ ላይ መሠረት የሌለው ክስ በሰነዘሩበት ጊዜ ስሜቱ በጥልቅ ተጎድቶ ነበር። (ኢዮብ 10:1፤ 19:2) በኋላ ላይ፣ የሐሰት ክስ የሰነዘሩትን እነዚህን ሰዎች ይሖዋ የገሠጻቸው ከመሆኑም በላይ ወደ ኢዮብ ሄደው ለኃጢአታቸው መሥዋዕት እንዲያቀርቡ አዟቸዋል። (ኢዮብ 42:7-9) ይሁን እንጂ ኢዮብም ቢሆን ማድረግ ያለበት ነገር እንዳለ ይሖዋ ነግሮታል። አምላክ፣ ኢዮብን ስለ ከሳሾቹ እንዲጸልይ አዞት ነበር። ኢዮብ እንደታዘዘው ያደረገ ሲሆን የይቅር ባይነት መንፈስ በማሳየቱም ይሖዋ ባርኮታል። (ኢዮብ 42:10, 12, 16, 17ን አንብብ።) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ቅር ስላሰኘን ሰው ልባዊ ጸሎት ማቅረባችን ቂም እንዳንይዝ ይረዳናል።

ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያላችሁን ግንዛቤ ማሳደጋችሁን ቀጥሉ

18, 19. ተወዳጅ ባሕርያት ስላሉት አምላካችን ያለንን ግንዛቤ ማሳደጋችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

18 አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን ስለ ይሖዋ ባሕርያት መመርመራችን መንፈስን የሚያድስ አይደለም? ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ፣ የማያዳላ፣ ለጋስ፣ ምክንያታዊ፣ ታማኝና ይቅር ባይ አምላክ መሆኑን ተምረናል። እርግጥ ነው፣ ስለ ይሖዋ ባሕርያት እስካሁን ያገኘነው ግንዛቤ ባሕርን በጭልፋ የመጨለፍ ያህል ነው። ወደፊት ስለ ይሖዋ ለዘላለም በመማር የሚገኘውን ደስታ የማጣጣም አጋጣሚ ተዘርግቶልናል። (መክ. 3:11) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!” የአምላክን ፍቅርና እስካሁን ያየናቸውን ስድስት ባሕርያት በተመለከተም እንዲህ ብለን መናገር እንችላለን።—ሮም 11:33

19 ሁላችንም ተወዳጅ ባሕርያት ስላሉት አምላካችን ያለንን ግንዛቤ ማሳደጋችንን እንቀጥል። ስለ ባሕርያቱ በሚገባ ማወቃችን፣ በእነሱ ላይ ማሰላሰላችንና እነዚህን ባሕርያት በሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቃችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል። (ኤፌ. 5:1) ይህን ስናደርግ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ እንደሚሰማን ጥርጥር የለውም።—መዝ. 73:28

^ አን.7 በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማግኘት በጥር 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በቅርቡ ያበረታታኸው ሰው አለን?” የሚለውን ርዕስና በሚያዝያ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ማነቃቃት ያለባችሁ እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.14 ስሟ ተቀይሯል።