“በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።”—መዝ. 73:24

1, 2. (ሀ) ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) አንዳንዶች ለአምላክ ተግሣጽ ምላሽ ስለሰጡበት መንገድ የሚገልጹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎችን መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

“ለእኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይሻለኛል፤ ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ።” (መዝ. 73:28 NW) መዝሙራዊው እዚህ ጥቅስ ላይ ያሰፈረው ሐሳብ በአምላክ እንደሚተማመን ያሳያል። እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት እንዲገነባ የረዳው ምንድን ነው? መዝሙራዊው፣ ክፉዎች የተሳካ ሕይወት እንደሚመሩ ሲመለከት መጀመሪያ ላይ በሕይወቱ ተማርሮ ነበር። “ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!” በማለት በምሬት ተናግሮ ተናግሯል። (መዝ. 73:2, 3, 13, 21) “ወደ አምላክ መቅደስ” ሲገባ ግን አስተሳሰቡን ለማስተካከልና ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ዝምድና ጠብቆ ለመኖር የሚያስችል እርዳታ አገኘ። (መዝ. 73:16-18) አምላክን የሚፈራው ይህ ሰው ከዚህ ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ቀስሟል፤ ይኸውም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ይዞ ለመቀጠል ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መሆን፣ ምክርን መቀበል እንዲሁም ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተምሯል።—መዝ. 73:24

2 እኛም እውነተኛና ሕያው ከሆነው አምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ይሖዋ የሚሰጠን ምክር ወይም ተግሣጽ እንዲቀርጸን መፍቀዳችን አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ካደረግን እሱን የምናስደስት ዓይነት ሰዎች እንሆናለን! አምላክ መሐሪ በመሆኑ በጥንት ዘመናት ለአንዳንድ ግለሰቦችና ብሔራት ተግሣጽ በመስጠት አካሄዳቸውን እንዲለውጡ አጋጣሚ የሰጠባቸው ወቅቶች ነበሩ። እነዚህ ግለሰቦችና ብሔራት አምላክ ለሰጣቸው ተግሣጽ የሰጡት ምላሽ “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” እንዲሁም “የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ” ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦልናል። (ሮም 15:4፤ 1 ቆሮ. 10:11) እነዚህን ዘገባዎች በጥልቀት መመርመራችን ስለ ይሖዋ ባሕርያት ለማወቅ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እሱ ሲቀርጸን ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ያስተምረናል።

 ሸክላ ሠሪው ሥልጣኑን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

3. ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ያለው ሥልጣን በኢሳይያስ 64:8 እና ኤርምያስ 18:1-6 ላይ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተገለጸው እንዴት ነው? (በገጽ 24 ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

3 ይሖዋ በግለሰቦች ወይም በብሔራት ላይ ያለው ሥልጣን በኢሳይያስ 64:8 ላይ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደሚከተለው ተገልጿል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች፣ አንተም ሸክላ ሠሪ ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።” አንድ ሸክላ ሠሪ በጭቃው የፈለገውን ዓይነት ዕቃ የመሥራት ሙሉ መብት አለው። ሸክላው በዚህ ረገድ የራሱ ምርጫ ሊኖረው አይችልም። ከአምላክ እና ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የፈለገውን ቅርጽ ሊሰጠው በሚችለው ሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ ሁሉ የሰው ልጆችም የሚቀረጹበትን መንገድ በተመለከተ ከአምላክ ጋር መሟገት አይችሉም።—ኤርምያስ 18:1-6ን አንብብ።

4. አምላክ ሰዎችን ወይም ብሔራትን የሚቀርጸው እሱ እንዳሻው ነው? አብራራ።

4 ይሖዋ የጥንቱን የእስራኤል ብሔር የቀረጸው አንድ ሸክላ ሠሪ ሸክላውን በሚቀርጽበት መንገድ እንደሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገልጿል። ይሁንና ሸክላ ሠሪውና ይሖዋ በሚቀርጹበት መንገድ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ሸክላ ሠሪው ደስ ያለውን ዓይነት የሸክላ ዕቃ በጭቃው መሥራት ይችላል። ታዲያ ይሖዋስ ሰዎችን ወይም ብሔራትን እሱ እንዳሻው በመቅረጽ አንዳንዶችን ጥሩ ሌሎችን ደግሞ መጥፎ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እንዳልሆነ ይገልጻል። ይሖዋ ለሰው ልጆች በዋጋ የማይተመን ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ሥልጣኑን ከዚህ ስጦታው ጋር በሚጋጭ መንገድ አይጠቀምበትም። ፈጣሪያችን ይሖዋ የሰው ልጆችን የሚቀርጸው እነሱ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ከሆኑ ብቻ ነው።—ኤርምያስ 18:7-10ን አንብብ።

5. የሰው ልጆች በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ካልሆኑ ይሖዋ በእነሱ ላይ ያለውን ሥልጣን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

5 የሰው ልጆች ልባቸውን ቢያደነድኑና በታላቁ ሸክላ ሠሪ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ባይሆኑስ? በዚህ ጊዜ ይሖዋ መለኮታዊ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? አንድ ሸክላ ሠሪ የያዘው ጭቃ ላሰበው ዓላማ ተስማሚ ባይሆን ምን ያደርጋል? በዚሁ ጭቃ ሌላ ዓይነት ዕቃ ይሠራበታል ካልሆነም ጭቃውን ይጥለዋል! ይሁንና ጭቃው ጥቅም ላይ ካልዋለ አብዛኛውን ጊዜ ጥፋቱ የሸክላ ሠሪው ነው። ከታላቁ ሸክላ ሠሪ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ፈጽሞ የተለየ ነው። (ዘዳ. 32:4) አንድ ሰው በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ካልሆነ ጥፋቱ ምንጊዜም የራሱ የግለሰቡ ነው። ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመቅረጽ ያለውን ሥልጣን የሚጠቀምበት ሊቀርጻቸው ሲሞክር የሚሰጡትን ምላሽ መሠረት በማድረግ ነው፤ የሚሰጡትን ምላሽ በመመልከት እነሱን የሚይዝበትን መንገድ ይቀያይራል። ይሖዋ ሲቀርጻቸው ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ በሚችሉበት መንገድ ይቀረጻሉ። ለምሳሌ ያህል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ክቡር ለሆነ አገልግሎት የሚሆኑ ዕቃዎች’ ሆነው የተቀረጹ “የምሕረት ዕቃዎች” ናቸው። በሌላ በኩል ግን ልበ ደንዳና በመሆን አምላክን የሚቃወሙ ሰዎች ‘ለጥፋት የተዘጋጁ የቁጣ ዕቃዎች’ ይሆናሉ።—ሮም 9:19-23

6, 7. ንጉሥ ዳዊትና ንጉሥ ሳኦል ይሖዋ ለሰጣቸው ምክር የሰጡት ምላሽ የሚለያየው እንዴት ነው?

 6 ይሖዋ ሰዎችን የሚቀርጽበት አንዱ መንገድ ምክር ወይም ጠንከር ያለ ተግሣጽ በመስጠት ነው። ይሖዋ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሰዎችን የሚቀርጸው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት የመጀመሪያዎቹን የእስራኤል ነገሥታት ይኸውም ሳኦልንና ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በፈጸመበት ወቅት ድርጊቱ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት አስከትሎ ነበር። ዳዊት፣ ንጉሥ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ለእሱ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ከመስጠት ወደኋላ አላለም። በነቢዩ ናታን አማካኝነት ከበድ ያለ መልእክት ላከበት። (2 ሳሙ. 12:1-12) ታዲያ ዳዊት ምን ምላሽ ሰጠ? ልቡ የተሰበረ ሲሆን በድርጊቱ ተጸጽቶ ንስሐ ገባ። በመሆኑም የአምላክን ምሕረት ማግኘት ቻለ።—2 ሳሙኤል 12:13ን አንብብ።

 7 ከዚህ በተቃራኒ ከዳዊት በፊት ንጉሥ የነበረው ሳኦል ለተሰጠው ምክር ጥሩ ምላሽ ሳይሰጥ  ቀርቷል። ይሖዋ፣ አማሌቃውያንን እና እንስሶቻቸውን በሙሉ ፈጽሞ እንዲያጠፋ በነቢዩ ሳሙኤል በኩል ለሳኦል ግልጽ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። ሳኦል ግን ይህን መለኮታዊ መመሪያ አልታዘዘም። የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግንና ምርጥ ምርጡን እንስሳ በሕይወት አስቀረ። ይህን ያደረገው ለምን ነበር? አንዱ ምክንያት ለራሱ ክብር ማግኘት ስለፈለገ ነው። (1 ሳሙ. 15:1-3, 7-9, 12) ሳኦል ምክር ሲሰጠው ልቡን ከማደንደን ይልቅ ታላቁ ሸክላ ሠሪ እንዲቀርጸው ፈቃደኛ መሆን ነበረበት። እሱ ግን በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲያውም ለድርጊቱ ሰበብ ለማቅረብ ሞከረ። እንስሳቱ ለአምላክ መሥዋዕት ሆነው ሊቀርቡ እንደሚችሉ በመናገር ያደረገው ነገር ስህተት እንዳልሆነ ለማሳመን ሞከረ፤ እንዲሁም የሳሙኤልን ምክር አቃለለ። በመሆኑም ይሖዋ ሳኦልን ንጉሥ እንዳይሆን ናቀው፤ ከዚያ በኋላም ሳኦል ከእውነተኛው አምላክ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና መልሶ ማግኘት አልቻለም።—1 ሳሙኤል 15:13-15, 20-23ን አንብብ።

ሳኦል የተሰጠውን ምክር አቃልሏል። በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኛ አልነበረም! (ተመልከት አንቀጽ 7ን)

ዳዊት ምክር ሲሰጠው ልቡ የተሰበረ ሲሆን ምክሩን ተቀብሏል። በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነበር። አንተስ? (ተመልከት አንቀጽ 6ን)

አምላክ አያዳላም

8. የእስራኤል ሕዝብ ይሖዋ ሲቀርጸው ከሰጠው ምላሽ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

8 ይሖዋ፣ የሚቀርጸው ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ብሔራትንም ጭምር ነው። ከ ግብፅ ባርነት ነፃ የወጡት እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። እስራኤላውያን የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ሲሆኑ በታላቁ ሸክላ ሠሪ እጅ የመቀረጽ መብት ተዘርግቶላቸው ነበር። ሕዝቡ ግን በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በዙሪያቸው የነበሩትን ብሔራት አማልክት እስከ ማምለክ ደርሰው ነበር። ይሖዋ ነቢያቱን በተደጋጋሚ በመላክ እስራኤላውያን ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ለመርዳት ቢሞክርም ሕዝቡ ግን አሻፈረን አሉ። (ኤር. 35:12-15) እስራኤላውያን ልባቸውን በማደንደናቸው ከባድ ተግሣጽ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። ለጥፋት እንደተዘጋጁ ዕቃዎች በመሆናቸው አሥሩን ነገድ ያቀፈው የሰሜኑ መንግሥት በአሦራውያን እጅ የወደቀ ሲሆን ሁለቱን ነገድ ያቀፈው በስተ  ደቡብ የሚገኘው መንግሥት ደግሞ በባቢሎናውያን እጅ ተመሳሳይ ዕጣ አጋጥሞታል። ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! ይሖዋ ሲቀርጸን ጥቅም ማግኘታችን የተመካው በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው።

9, 10. የነነዌ ሰዎች መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ምን አደረጉ?

9 ይሖዋ፣ የአሦር ዋና ከተማ ለሆነችው ለነነዌ ነዋሪዎችም ማስጠንቀቂያ በመስጠት አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አጋጣሚ ከፍቶላቸው ነበር። ዮናስን “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቶአልና” ብሎት ነበር። ነነዌ ለጥፋት እንደተዘጋጀ ዕቃ ሆና ነበር።—ዮናስ 1:1, 2፤ 3:1-4

10 ይሁንና ዮናስ የፍርድ መልእክቱን ሲነግራቸው የነነዌ ሰዎች “እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።” ንጉሡም ጭምር “ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሱንም አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ።” የነነዌ ሰዎች ይሖዋ እነሱን ለመቅረጽ ላደረገው ጥረት ጥሩ ምላሽ በመስጠት ንስሐ ገብተዋል። በመሆኑም ይሖዋ በእነሱ ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላመጣባቸውም።—ዮናስ 3:5-10

11. ይሖዋ ከእስራኤል ብሔርና ከነነዌ ሰዎች ጋር በተያያዘ ካደረገው ነገር የትኛውን ባሕርይውን በግልጽ መመልከት እንችላለን?

11 እስራኤላውያን የተመረጠ ብሔር መሆናቸው ተግሣጽ እንዳይሰጣቸው አላደረገም። በሌላ በኩል ግን የነነዌ ሰዎች ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን ላይ የተመሠረተ ዝምድና ባይኖራቸውም ይሖዋ የፍርድ መልእክት እንዲታወጅላቸው አድርጓል። እነሱም በቀላሉ እንደሚቀረጽ የሸክላ ጭቃ በመሆናቸው ይሖዋ ምሕረት አሳይቷቸዋል። እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ይሖዋ “አድልዎ የማያደርግ” አምላክ እንደሆነ የሚያሳዩ ግሩም ማስረጃዎች ናቸው!—ዘዳ. 10:17

ይሖዋ ምክንያታዊና ሐሳቡን ለመቀየር ፈቃደኛ ነው

12, 13. (ሀ) አምላክ፣ ሰዎችን ሲቀርጽ መልካም ምላሽ ከሰጡ ሐሳቡን የሚቀይረው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከሳኦል ጋር በተያያዘ ‘ተጸጸተ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ከነነዌ ሰዎች ጋር በተያያዘስ?

12 አምላክ እኛን የሚቀርጽበት መንገድ ምክንያታዊና ሐሳቡን ለመቀየር ፈቃደኛ እንደሆነ ያሳያል። ይሖዋ በሰዎች ላይ ትክክለኛ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ ከወሰነ በኋላ ሰዎቹ የሰጡትን ምላሽ ሲያይ ሐሳቡን የለወጠባቸው ጊዜያት መኖራቸው ይህን ይጠቁማል። ይሖዋ፣ የመጀመሪያውን የእስራኤል ንጉሥ በተመለከተ “ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ” እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጿል። (1 ሳሙ. 15:11) የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው ከመጥፎ ጎዳናቸው በተመለሱ ጊዜ ደግሞ አምላክ ምን እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “እግዚአብሔርም . . . ራራላቸው [‘ተጸጸተ፣’ የ1954 ትርጉም]፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም” ይላል።—ዮናስ 3:10

13 ‘ተጸጸተ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የአመለካከት ወይም የዓላማ ለውጥ ማድረግን ያመለከታል። ይሖዋ ሳኦልን ንጉሥ አድርጎ በመረጠው ወቅት ለእሱ የነበረው አመለካከት ከጊዜ በኋላ ተቀየረ፤ በመሆኑም ሳኦል ለንግሥና እንደማይበቃ ተናግሯል። ይሖዋ አመለካከቱን የለወጠው ያደረገው ምርጫ ስህተት ስለነበረ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሳኦል ከጊዜ በኋላ እምነት የለሽና ዓመፀኛ በመሆኑ ነው። እውነተኛው አምላክ ከነነዌ ሰዎች ጋር በተያያዘ ‘ተጸጸተ’ የተባለውም በእነሱ ላይ ለመውሰድ ያሰበውን እርምጃ በመቀየሩ ነው። ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ምክንያታዊና ሐሳቡን ለመቀየር ፈቃደኛ፣ መሐሪና ቸር እንዲሁም ኃጢአተኞች አካሄዳቸውን ሲያስተካክሉ ውሳኔውን ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ አምላክ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!

የይሖዋን ተግሣጽ አትናቁ

14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚቀርጸን እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ሲቀርጸን ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?

14 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በዋነኝነት የሚቀርጸን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በድርጅቱ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ታዲያ በእነዚህ መንገዶች የሚሰጠንን ማንኛውንም ምክር ወይም ጠንከር ያለ ተግሣጽ መቀበል አይኖርብንም? ከተጠመቅን ምንም ያህል ብንቆይ ወይም በርካታ የአገልግሎት መብቶች ቢኖሩንም ይሖዋ የሚሰጠንን ምክር መቀበላችንን በመቀጠል ክቡር ለሆነ አገልግሎት የሚውል ዕቃ ሆነን ለመቀረጽ ፈቃደኞች መሆን አለብን።

15, 16. (ሀ) ተግሣጽ ተሰጥቶን የአገልግሎት መብቶቻችንን ስናጣ ምን ዓይነት አሉታዊ ስሜት ሊያድርብን ይችላል? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ተግሣጽ ሲሰጠን የሚሰማንን አሉታዊ ስሜት ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

 15 ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጠን በተለያየ መንገድ ነው፤ የሚጠበቅብን ምን እንደሆነ ያስተምረናል፤ ወይም ደግሞ አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል እርማት ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ ግን የተሳሳተ አካሄድ በመከተላችን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስፈልገን ይሆናል። እንዲህ ያለው ተግሣጽ ሲሰጠን ያሉንን መብቶች ልናጣ እንችላለን። ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ዴኒስን * እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከሥራው ጋር በተያያዘ ጥበብ የጎደለው ድርጊት በመፈጸሙ ሽማግሌዎች በግል ተግሣጽ ሰጡት። ዴኒስ፣ ከዚያ በኋላ ሽማግሌ እንዳልሆነ ለጉባኤው ማስታወቂያ ሲነገር ምን ተሰማው? “የማልረባ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ብዙ መብቶች አግኝቼ ነበር። የዘወትር አቅኚ ነበርኩ፤ ቤቴላዊ የነበርኩበት ጊዜም አለ። እንዲሁም የጉባኤ አገልጋይ ከዚያም ሽማግሌ ሆኜ አገልግያለሁ። በአውራጃ ስብሰባ ላይ የመጀመሪያ ንግግሬን ካቀረብኩም ብዙ አልቆየሁም። በድንገት እነዚህን ሁሉ መብቶች አጣሁ። በኀፍረትና በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጥኩ ሲሆን ከእንግዲህ በድርጅቱ ውስጥ ምንም ቦታ እንደማይኖረኝ ተሰማኝ።”

16 ዴኒስ፣ ሽማግሌዎቹ እርማት እንዲሰጡት ምክንያት የሆነውን የተሳሳተ አካሄድ ማስተካከል ነበረበት። ይሁንና ይሰማው የነበረውን አፍራሽ የሆነ ስሜት ለመቋቋም ምን ረዳው? እንዲህ ብሏል፦ “መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አዘውትሬ ማከናወኔን ላለመተው ቆርጬ ነበር። ከክርስቲያን ወንድሞቼ ያገኘሁት ድጋፍና ከጽሑፎቻችን ያገኘሁት ማበረታቻም በጣም ጠቅሞኛል። ነሐሴ 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው ‘ከዚህ ቀደም ታገለግል ነበር? አሁንስ ማገልገል ትችላለህ?’ የሚለው ርዕስ ለእኔ የተጻፈ ደብዳቤና የጸሎቴ መልስ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። ከጽሑፉ ላይ በጣም የወደድኩት ሐሳብ ‘በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ስለሌሉህ አጋጣሚውን መንፈሳዊነትህን ለማጠናከር ተጠቀምበት’ የሚለው ነበር።” ዴኒስ ከተሰጠው ተግሣጽ ጥቅም ያገኘው እንዴት ነው? ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ “ይሖዋ እንደገና የጉባኤ አገልጋይ የመሆን መብት በመስጠት ባርኮኛል” በማለት ተናግሯል።

17. የውገዳ ዝግጅት አንድ ኃጢአተኛ በመንፈሳዊ እንዲያገግም ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ጥቀስ።

17 ውገዳ ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ነው። እንዲህ ያለው እርምጃ ጉባኤውን ከመጥፎ ተጽዕኖ የሚጠብቅ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአት የሠራው ግለሰብ በመንፈሳዊ እንዲያገግም ሊረዳው ይችላል። (1 ቆሮ. 5:6, 7, 11) ሮበርት ለ16 ዓመታት ገደማ ተወግዶ ቆይቷል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ወላጆቹና ወንድሞቹ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ከኃጢአተኞች ጋር እንዳንሆንና ሰላም እንኳ እንዳንላቸው የሚያዝዘውን መመሪያ በጥብቅ በመከተል ታማኝ ሆነው ቆይተዋል። አሁን ሮበርት ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ከተመለሰ የተወሰኑ ዓመታት ያለፉ ሲሆን በመንፈሳዊም ጥሩ እድገት እያደረገ ነው። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ወደ ይሖዋና ወደ ሕዝቦቹ ለመመለስ ያነሳሳው ምን እንደሆነ ሲጠየቅ ቤተሰቡ የወሰዱት አቋም በጣም እንደረዳው ይናገራል። “ቤተሰቤ ከእኔ ጋር በተወሰነ መጠን እንኳ ቢቀራረቡ ለምሳሌ ስለ ደኅንነቴ ለማወቅ ያህል ብቻ ቢያነጋግሩኝ ኖሮ ምንም እንደጎደለኝ አይሰማኝም ነበር፤ እንደ ድሮው ከእነሱ ጋር ለመቀራረብ የነበረኝ ፍላጎት ወደ አምላክ እንድመለስ አነሳሳኝ” ብሏል።

18. ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ተግሣጽ በመስጠት ሲቀርጸን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?

18 እርግጥ ነው፣ አንተ እንዲህ ዓይነት ጠንከር ያለ ተግሣጽ አያስፈልግህ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ተግሣጽ በመስጠት ሲቀርጸን እያንዳንዳችን ምን ምላሽ እንደምንሰጥ ማሰብ ይኖርብናል። እንደ ዳዊት ዓይነት ምላሽ እንሰጣለን? ወይስ እንደ ሳኦል እንሆናለን? ታላቁ ሸክላ ሠሪ አባታችን ነው። “አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል” የሚለውን ጥቅስ ምንጊዜም መርሳት አይኖርብንም። እንግዲያው “የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር” የሚለውን ምክር እንከተል።—ምሳሌ 3:11, 12

^ አን.15 ስሙ ተቀይሯል።