“[“ይሖዋ፣” NW] ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።”—መዝ. 145:9

1, 2. የይሖዋ ወዳጆች ምን አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል?

ሞኒካ የተባለች አንዲት ክርስቲያን “ከባለቤቴ ጋር በትዳር 35 ዓመታት ያህል ስላሳለፍን ልብ ለልብ እንተዋወቃለን” በማለት ተናግራለች። አክላም “የሚገርመው፣ ይህን ሁሉ ዓመት በትዳር ካሳለፍን በኋላም አንዳችን ስለ ሌላው ከዚህ በፊት የማናውቀውን ነገር ማግኘታችንም አልቀረም!” ብላለች። በርካታ ባለትዳሮችና ጓደኛሞችም በዚህ ሐሳብ እንደሚስማሙ ጥርጥር የለውም።

2 ስለ ወዳጆቻችን ይበልጥ እያወቅን መሄዳችን ያስደስተናል። ከማንኛውም ሰው ጋር ከምንመሠርተው ወዳጅነት ይበልጥ ከፍ አድርገን የምንመለከተው ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንደሆነ ግልጽ ነው። በእርግጥ መቼም ቢሆን ስለ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም። (ሮም 11:33) ደስ የሚለው ግን ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያለንን ግንዛቤ እያሳደግንና ይህን ማድረግ የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶልናል።—መክ. 3:11

3. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 የመጀመሪያው የጥናት ርዕስ ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብና የማያዳላ አምላክ ስለመሆኑ ያለንን ግንዛቤ አሳድጎልናል። አሁን ደግሞ ተወዳጅ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ስለ ሁለቱ ይኸውም ስለ ልግስናውና ስለ ምክንያታዊነቱ እንመረምራለን። ይህን ማድረጋችን “እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት ሙሉ በሙሉ ለመገንዘብ ይረዳናል።—መዝ. 145:9

ይሖዋ ለጋስ ነው

4. እውነተኛ ልግስና የሚገለጸው በምንድን ነው?

4 ለጋስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? በሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ የሚገኘው “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። ኢየሱስ በዚህ ቅልብጭ ያለ ሐሳብ አማካኝነት እውነተኛ ልግስና ምን እንደሆነ ገልጿል። ለጋስ የሆነ ሰው ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ጥሪቱን ምንም ሳይሰስት ለሌሎች የሚሰጥ ሲሆን ይህን የሚያደርገውም በደስታ ነው። አንድን ሰው ለጋስ የሚያስብለው የስጦታው ትልቅነት ሳይሆን ለመስጠት  የተነሳሳበት ዝንባሌ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ “ደስተኛ ከሆነው አምላክ” ከይሖዋ የበለጠ ለጋስ የለም።—1 ጢሞ. 1:11

5. ይሖዋ ለጋስ መሆኑን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ይሖዋ ለጋስ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ አምላኪዎቹ ያልሆኑትን ጨምሮ ለሁሉም የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይሰጣቸዋል። በእርግጥም “እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው።” ይሖዋ “በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:45) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋን ለማያመልኩ ሰዎች እንደሚከተለው ብሎ መናገር የቻለው ለዚህ ነው፦ “[አምላክ] መልካም ነገሮች [ያደርጋል]፤ . . . ከሰማይ ዝናብ በማዝነብ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት የተትረፈረፈ ምግብ ያቀርብላችኋል፣ ልባችሁንም በደስታ ይሞላዋል።” (ሥራ 14:17) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ልግስና የሚያሳየው ለሰው ልጆች በሙሉ ነው።—ሉቃስ 6:35

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደስተው የእነማንን ፍላጎት ማሟላት ነው? (ለ) አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን የሚያሟላላቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

6 ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ከሁሉ የበለጠ ያስደስተዋል። ንጉሥ ዳዊት “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 37:25) በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች ይሖዋ እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ እንደሚያደርግ በራሳቸው ሕይወት ተመልክተዋል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

7 ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማራች ናንሲ የተባለች አንዲት እህት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። ናንሲ “የቤት ኪራይ ለመክፈል 66 የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገኝ የነበረ ሲሆን ኪራዩን በቀጣዩ ቀን መክፈል ነበረብኝ” በማለት ታስታውሳለች። “ገንዘቡን እንዴት ማግኘት እንደምችል ግራ ገብቶኝ ነበር። ስለ ጉዳዩ ከጸለይኩ በኋላ ወደ ሥራዬ ሄድኩ፤ የምሠራው በአስተናጋጅነት ሲሆን ያን ቀን ብዙም ደንበኛ ስለማይኖር ያን ያህል ጉርሻ (ቲፕ) አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም። የሚገርመው ያን ዕለት ወደ ምግብ ቤቱ ብዙ ሰዎች መጡ። ሥራዬን ከጨረስኩ በኋላ ያገኘሁትን ጉርሻ ስቆጥረው 66 ዶላር ሆነ።” ናንሲ፣ ይሖዋ ልክ የሚያስፈልጋትን ያህል በልግስና እንደሰጣት እርግጠኛ ነች።—ማቴ. 6:33

8. ይሖዋ ከሁሉ በላይ ልግስናውን ያሳየበት ስጦታ ምንድን ነው?

8 ይሖዋ ከሁሉ በላይ ልግስናውን ያሳየበትን ስጦታ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው ይችላል። ይህ ስጦታ ምንድን ነው? ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱ ነው። “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:16) እዚህ ጥቅስ ላይ “ዓለም” የሚለው ቃል የሰው ዘሮችን በሙሉ ያመለክታል። ይሖዋ ከሁሉ በላይ ልግስናውን ያሳየበትን ይህን ስጦታ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ ሊያገኘው ይችላል። በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩ ሁሉ ሕይወት ይትረፈረፍላቸዋል፤ በሌላ አባባል የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዮሐ. 10:10) ይሖዋ ለጋስ መሆኑን የሚያሳይ ከዚህ የበለጠ ምን ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል?

 ልግስና በማሳየት ረገድ ይሖዋን ምሰሉ

እስራኤላውያን ልግስና በማሳየት ረገድ ይሖዋን እንዲመስሉ ተበረታትተዋል (ተመልከት አንቀጽ 9ን)

9. ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

 9 እኛስ ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ “ለእኛ ደስታ ሲል ሁሉን ነገር አትረፍርፎ [ይሰጠናል]”፤ በመሆኑም እኛም ለሌሎች “ለማካፈል ፈቃደኞች” መሆን ይኖርብናል፤ ይህን ስናደርግ እነሱም ደስታ ያገኛሉ። (1 ጢሞ. 6:17-19) ለምንወዳቸው ሰዎች እንዲሁም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስጦታ መስጠት ያስደስተናል። (ዘዳግም 15:7ን አንብብ።) ይሁንና ልግስና ማሳየትን እንዳንዘነጋ ምን ሊረዳን ይችላል? አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ስጦታ በተሰጣቸው ቁጥር እነሱም በበኩላቸው ለሌላ ሰው ስጦታ ይሰጣሉ። በእርግጥም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የልግስና መንፈስ የሚያሳዩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች መኖራቸው በረከት ነው።

10. ለጋስ መሆናችንን ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

10 ለጋስ መሆናችንን ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ሌሎችን ለመርዳትና ለማበረታታት ጊዜያችንን እንዲሁም ጉልበታችንን መጠቀም ነው። (ገላ. 6:10) በዚህ ረገድ ራሳችንን ለመገምገም እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በሌሎች ዘንድ የምታወቀው እንዴት ነው? ሰዎችን ለመርዳት ራሴን በፈቃደኝነት እንደማቀርብ እንዲሁም የሚያሳስባቸውን ነገር ሲነግሩኝ በትኩረት ለማዳመጥ ፈቃደኛ እንደሆንኩ አድርገው ይመለከቱኛል? አንድ ሰው የሆነ ሥራ በማከናወን እንዳግዘው ቢጠይቀኝ ወይም አንድ ቦታ ሊልከኝ ቢፈልግ ሁኔታዎች የሚፈቅዱልኝ እስከሆነ ድረስ እሺ እላለሁ? ለአንድ የቤተሰቤ አባል ወይም የእምነት ባልንጀራዬ ከልቤ እንደማደንቀው በቅርብ ጊዜ ነግሬው አውቃለሁ?’ ‘ሰጪዎች መሆናችን’ ከይሖዋም ሆነ ከወዳጆቻችን ጋር ይበልጥ እንደሚያቀራርበን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 6:38፤ ምሳሌ 19:17

11. ለይሖዋ በልግስና መስጠት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

 11 ለይሖዋም በልግስና መስጠት እንችላለን። ቅዱሳን መጻሕፍት “እግዚአብሔርን በሀብትህ . . . አክብረው” የሚል ምክር ይሰጡናል። (ምሳሌ 3:9) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘ሀብት’ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን  እንዲሁም ጥሪታችንን የሚያካትት ሲሆን እነዚህን ነገሮች በአምላክ አገልግሎት ምንም ሳንሰስት ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ትናንሽ ልጆችም እንኳ ለይሖዋ በልግስና መስጠትን ሊማሩ ይችላሉ። ጄሰን የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “መዋጮ ለማድረግ ስናስብ ልጆቻችን ገንዘቡን በመንግሥት አዳራሹ በሚገኘው የመዋጮ ሳጥን ውስጥ እንዲከትቱ እናደርጋለን። ልጆቻችን ይህን ሲያደርጉ ‘ለይሖዋ አንድ ነገር እንደሰጡ’ ስለሚሰማቸው ይደሰታሉ።” ለይሖዋ በለጋስነት መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ በትንሽነታቸው የቀመሱ ልጆች አዋቂ ከሆኑም በኋላ ይህን ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።—ምሳሌ 22:6

ይሖዋ ምክንያታዊ ነው

12. ምክንያታዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

12 ተወዳጅ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ሌላው ምክንያታዊነት ነው። ምክንያታዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ አብዛኛውን ጊዜ “ምክንያታዊ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እሺ ባይ” የሚል ፍቺ አለው። (ቲቶ 3:1, 2) ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሕጉ ላይ የሰፈረውን ብቻ ይዞ ሙጭጭ አይልም፤ ከልክ በላይ ጥብቅ፣ ግትር ወይም ደግሞ ኃይለኛ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት፣ ሁኔታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በገርነት ይይዛቸዋል። ሌሎችን ለመስማት እንዲሁም የሚቻል ከሆነ የእነሱን ፍላጎት ለማሟላትና ከእነሱ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ነው።

13, 14. (ሀ) ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ከሎጥ ጋር በተያያዘ ካደረገው ነገር ስለ ምክንያታዊነት ምን እንማራለን?

13 ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ የአገልጋዮቹን ስሜት በደግነት ግምት ውስጥ ያስገባል፤ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከጻድቁ ሎጥ ጋር በተያያዘ ያደረገውን እንመልከት። ይሖዋ፣ ሰዶምና ገሞራን ለማጥፋት በወሰነበት ጊዜ ለሎጥ ወደ ተራሮቹ ሸሽቶ እንዲያመልጥ ግልጽ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። ሎጥ ግን ወደ ሌላ ቦታ ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ተማጸነ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! ሎጥ፣ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ እንዲለውጥ እየጠየቀ ነበር።ዘፍጥረት 19:17-20ን አንብብ።

14 ሎጥ እንዲህ በማለቱ ፈሪ እንደሆነ ወይም ለመታዘዝ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ልናስብ እንችል ይሆናል። ይሖዋ፣ ሎጥ የትም ቢሆን እሱን ማዳን እንደማይከብደው የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ሎጥ የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረውም። ያም ቢሆን ግን ሁኔታው ሎጥን አስፈርቶታል፤ ይሖዋም ጥያቄውን በመቀበል እሺ ባይ መሆኑን አሳይቷል። ይሖዋ፣ ሎጥ ሸሽቶ ሊሄድባት የፈለገውን ከተማ ሊያጠፋት አስቦ የነበረ ቢሆንም ሐሳቡን በመለወጥ ወደዚያ እንዲሄድ ፈቅዶለታል። (ዘፍጥረት 19:21, 22ን አንብብ።) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ከሚገባው በላይ ጥብቅ ወይም ግትር አይደለም። ከዚህ ይልቅ እሺ ባይ እና ምክንያታዊ አምላክ ነው።

15, 16. የሙሴ ሕግ ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? (በገጽ 12 ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት)

15 ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳይ በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኝ ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። አንድ እስራኤላዊ በጣም ድሃ ከመሆኑ የተነሳ በግ ወይም ፍየል ማቅረብ ባይችል በዚያ ፋንታ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት ርግቦች ማቅረብ ይችል ነበር። ይሁንና አንድ እስራኤላዊ ሁለት ርግቦች እንኳ ለማቅረብ አቅሙ ባይፈቅድለትስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ እስራኤላዊ አነስተኛ መጠን ያለው ዱቄት እንዲያቀርብ ይሖዋ ፈቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሰጠውን መመሪያ ልብ በል፦ ችግረኛው እስራኤላዊ የሚያቀርበው ማንኛውንም ዱቄት ሳይሆን ለተከበሩ እንግዶች ምግብ ለማዘጋጀት የሚውለውን የላመ ወይም “ስልቅ ዱቄት” ነበር። (ዘፍ. 18:6) ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?—ዘሌዋውያን 5:7, 11ን አንብብ።

16 ምንም የሌለህ ድሃ እስራኤላዊ ነህ እንበል። አነስተኛ መጠን ያለው ዱቄት መሥዋዕት አድርገህ ለማቅረብ ወደ ማደሪያው ድንኳን ስትሄድ ከአንተ የተሻለ ሀብት ያላቸው እስራኤላውያን መሥዋዕት የሚያደርጓቸውን እንስሳት ይዘው ሲመጡ ታያለህ። ይዘህ የመጣኸው የዱቄት መሥዋዕት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ስለሚሰማህ ትሸማቀቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ በይሖዋ ፊት የአንተም መሥዋዕት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ታውቃለህ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ለመሥዋዕት የሚቀርበው ዱቄት ምርጥ እንዲሆን አዝዟል። በሌላ አባባል ይሖዋ ድሃ  ለሆኑት እስራኤላውያን ‘ባለጸጋ የሆኑትን እስራኤላውያን ያህል ማቅረብ ባትችሉም እንኳ ካላችሁ ነገር ምርጡን እንዳቀረባችሁ አውቃለሁ’ ያላቸው ያህል ነው። በእርግጥም ይሖዋ የአገልጋዮቹን የአቅም ገደብና ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል።—መዝ. 103:14

17. ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

 17 ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ ስለሆነ በሙሉ ነፍሳችን የምናቀርበውን አገልግሎት እንደሚቀበለን ማወቃችን ያጽናናናል። (ቆላ. 3:23) ኮንስታንስ የተባሉ አንዲት በዕድሜ የገፉ ጣሊያናዊት እህት እንዲህ ብለዋል፦ “በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር ስለ ፈጣሪዬ ለሰዎች መናገር ነው። መስበኬንም ሆነ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናቴን የቀጠልኩት ለዚህ ነው። በጤና ማጣት የተነሳ ብዙ መሥራት ስለማልችል የማዝንበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ይሖዋ የአቅም ገደቤን እንደሚያውቅልኝ፣ የቻልኩትን ያህል በማድረጌ እንደሚደሰትብኝና እንደሚወደኝ ይገባኛል።”

ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ይሖዋን ምሰሉ

18. ወላጆች የይሖዋን ምሳሌ መከተል የሚችሉበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

18 እኛስ ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ ይሖዋ ከሎጥ ጋር በተያያዘ ያደረገውን እንደገና መለስ ብለን እንመልከት። ይሖዋ ከሎጥ የበለጠ ሥልጣን ቢኖረውም ሎጥ ያሳሰበውን ነገር ሲናገር በደግነት አዳምጦታል። እንዲሁም የፈለገውን እንዲያደርግ ፈቅዶለታል። አንተም ወላጅ ከሆንክ የይሖዋን ምሳሌ መከተል ትችላለህ? የልጆችህን ሐሳብ ለማዳመጥና የሚቻል ከሆነም ፍላጎታቸውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ነህ? የመስከረም 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ አንዳንድ ወላጆች ለቤተሰባቸው መመሪያዎችን ሲያወጡ ከልጆቻቸው ጋር እንደሚወያዩ ገልጿል። ለአብነት ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸው በስንት ሰዓት ቤት መግባት እንዳለባቸው በሚወስኑበት ጊዜ ሰዓቱን ራሳቸው የመምረጥ መብት እንዳላቸው የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ግን ክርስቲያን ወላጆች፣ ቤት መግቢያ ሰዓትን በተመለከተ ልጆቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ሊፈቅዱላቸው ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች በወሰኑት ሰዓት ረገድ ማስተካከያ ለማድረግ ይስማሙ ይሆናል። ወላጆች በቤታቸው ውስጥ የሚያወጡትን መመሪያዎች በተመለከተ የልጆቻቸውን ሐሳብ ግምት ውስጥ ሲያስገቡ ልጆቹ መመሪያዎቹን ማክበርና ወላጆቻቸውን መታዘዝ ቀላል ይሆንላቸዋል።

19. ሽማግሌዎች ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

19 የጉባኤ ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። ይሖዋ ድሃ የሆኑ እስራኤላውያን ያቀረቧቸውን መሥዋዕቶች ጭምር ከፍ አድርጎ እንደተመለከታቸው አስታውስ። በተመሳሳይም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በጤና ማጣት ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ በአገልግሎት የሚያደርጉት ተሳትፎ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች ባሉባቸው የአቅም ገደቦች ምክንያት ተስፋ ቢቆርጡ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ምርጣቸውን እስከሰጡት ድረስ ይሖዋ እንደሚወዳቸው ሽማግሌዎች በደግነት ሊያረጋግጡላቸው ይገባል።—ማር. 12:41-44

20. ምክንያታዊ እንሆናለን ሲባል በአምላክ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ከማድረግ ወደኋላ እንላለን ማለት ነው? አብራራ።

20 እርግጥ ነው፣ ምክንያታዊ እንሆናለን ሲባል ‘በራሳችን ላይ መጨከን የለብንም’ በሚል ሰበብ በአምላክ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ከማድረግ ወደኋላ እንላለን ማለት አይደለም። (ማቴ. 16:22) ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ‘ምክንያታዊ ነን’ በሚል ሰበብ ቸልተኞች መሆን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ሁላችንም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ “ከፍተኛ ተጋድሎ [ማድረግ]” ይኖርብናል። (ሉቃስ 13:24) በእርግጥም በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ይገባናል። በአንድ በኩል ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ራሳችንን ሳንቆጥብ በመሳተፍ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ አለብን። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ምንጊዜም ከአቅማችን በላይ እንደማይጠብቅብን ማስታወስ ይኖርብናል። ለይሖዋ ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በስጦታችን እንደሚደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱን አድናቂና ምክንያታዊ አምላክ ማገልገል የሚያስደስት አይደለም? በሚቀጥለው ርዕስ ደግሞ ተወዳጅ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት መካከል ሁለቱን እንመለከታለን።—መዝ. 73:28

‘ይሖዋን በሀብትህ አክብረው።’—ምሳሌ 3:9 (ተመልከት አንቀጽ 11ን)

“የምታደርጉትን ሁሉ . . . በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት።”—ቆላ. 3:23 (ተመልከት አንቀጽ 17ን)