“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”ፊልጵ. 1:10

1, 2. የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ትኩረት የሳበው ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የተነገረው የትኛው ትንቢት ነው? ለምንስ?

ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ በመጨረሻ ከኢየሱስ ጋር ለብቻቸው የመሆን አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ኢየሱስ ቀደም ሲል ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ የተናገረው ሐሳብ አእምሯቸው ውስጥ እየተጉላላ ነው። (ማር. 13:1-4) በመሆኑም “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” በማለት ጠየቁት። (ማቴ. 24:1-3) ኢየሱስ በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጦች የሚያስከትሉ እንዲሁም የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ለይተው የሚያሳውቁ ክስተቶችን ወይም ሁኔታዎችን ይነግራቸው ጀመር። ከእነዚህ ክስተቶች መካከል አንዱ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ትኩረት ይበልጥ ሳይስብ አልቀረም። ኢየሱስ ጦርነትን፣ የምግብ እጥረትንና የክፋት መባባስን ጨምሮ የተለያዩ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ከዘረዘረ በኋላ የመጨረሻዎቹን ቀኖች ለይቶ የሚያሳውቅ አንድ መልካም ነገር መኖሩን የሚገልጽ ትንቢት ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴ. 24:7-14

2 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከክርስቶስ ጋር ሆነው ምሥራቹን በመስበክ ደስታ አግኝተው ነበር። (ሉቃስ 8:1፤ 9:1, 2) ኢየሱስ “በእርግጥም አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ ሥራ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሎ የተናገረውን ሐሳብ አስታውሰው ይሆናል። (ሉቃስ 10:2) ይሁንና “በመላው ምድር” መስበክና “ለሕዝቦች ሁሉ” መመሥከር የሚችሉት እንዴት ነው? ሠራተኞቹስ የሚመጡት ከየት ነው? ከኢየሱስ ጋር ተቀምጠው በነበረበት በዚያን ቀን የወደፊቱን ጊዜ አሻግረው መመልከት ቢችሉ መልሱን ባወቁ ነበር! በማቴዎስ 24:14 ላይ ያሉትን ቃላት ፍጻሜ ቢመለከቱ በጣም እንደሚገረሙ ምንም ጥርጥር የለውም።

3. ሉቃስ 21:34 በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው? ራሳችንንስ ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

 3 ዛሬ የምንኖረው ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት ጊዜ ውስጥ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተባብረው በምድር ዙሪያ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ላይ ይገኛሉ። (ኢሳ. 60:22) ይሁንና ኢየሱስ አንዳንዶች በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ትኩረታቸውን መሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች ትኩረታቸው የሚከፋፈል ከመሆኑም ሌላ ‘ሸክም ይበዛባቸዋል።’ (ሉቃስ 21:34ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ የእነዚህንም ቃላት ፍጻሜ እየተመለከትን ነው። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተዘናግተዋል። ከሰብዓዊ ሥራ፣ ከከፍተኛ ትምህርትና ቁሳዊ ሀብት ከማካበት እንዲሁም በስፖርትና በመዝናኛ ከሚያሳልፉት ጊዜ ጋር በተያያዘ የሚያደርጉት ውሳኔ ይህን ያሳያል። ሌሎች ደግሞ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ጫናዎችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች የተነሳ ዝለዋል። አንተም ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅህ ተገቢ ነው፦ ‘እኔስ በዚህ ረገድ እንዴት ነኝ? የማደርጋቸው ውሳኔዎች በሕይወቴ ውስጥ ለምን ነገር ቅድሚያ እንደምሰጥ ያሳያሉ?’

4. (ሀ) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበሩትን ክርስቲያኖች በተመለከተ ምን ጸሎት አቅርቧል? ለምንስ? (ለ) በዚህና በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን? ግባችንስ ምንድን ነው?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ምንጊዜም መንፈሳዊ ነገሮችን ለማስቀደም ጥረት ማድረግ ጠይቆባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖች ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተው እንዲያውቁ’ ለእነሱ መጸለይ እንደሚያስፈልገው ተሰምቶት ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:9-11ን አንብብ።) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ በዚያን ጊዜ የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች “የአምላክን ቃል ያለ ፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት” አሳይተዋል። (ፊልጵ. 1:12-14) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የምንገኘው አብዛኞቻችን የአምላክን ቃል በድፍረት እንሰብካለን። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ነገር መመርመራችን፣ በጣም አስፈላጊ በሆነው የስብከት ሥራ ላይ ይበልጥ እንድናተኩር ሊረዳን ይችላል? አዎ፣ ይችላል! በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ይሖዋ በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገውን ዝግጅት እንመረምራለን። የይሖዋ ድርጅት ትኩረቱን ያደረገው በምን ላይ ነው? ይህን ማወቃችን እኛንም ሆነ ቤተሰባችንን ለተግባር ሊያነሳሳን የሚችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ደግሞ በአምላክ አገልግሎት መጽናትና ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ እንድንችል የሚረዳን ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል እየገሰገሰ ነው

5, 6. (ሀ) ይሖዋ የድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል በራእይ እንዲታይ ያደረገው ለምንድን ነው? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ነገር ምንድን ነው?

5 ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ውስጥ ያላካተታቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ አንጎል ወይም ስለ አጽናፈ ዓለም ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት አስደሳች ሊሆን ቢችልም ይሖዋ እንዲህ ያለ ማብራሪያ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ዓላማውን መረዳትና ሕይወታችንን ከዓላማው ጋር አስማምተን መኖር እንድንችል አስፈላጊውን መረጃ ሰጥቶናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በተመለከተ አንዳንድ ፍንጮች የሚሰጠን መሆኑ በጣም ያስደስታል! በኢሳይያስ፣ በሕዝቅኤልና በዳንኤል መጻሕፍት እንዲሁም በዮሐንስ ራእይ ዘገባ ላይ ይሖዋ በሰማይ ያቋቋመውን ሥርዓት በተመለከተ የሰፈረውን መግለጫ ስናነብ በአድናቆት ስሜት እንዋጣለን። (ኢሳ. 6:1-4፤ ሕዝ. 1:4-14, 22-24፤ ዳን. 7:9-14፤ ራእይ 4:1-11) ይሖዋ በሰማይ ያለውን ሁኔታ መመልከት እንድንችል መጋረጃውን የገለጠልን ያህል ነው! አምላክ ይህን መረጃ የሰጠን ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ የአጽናፈ ዓለማዊው ድርጅት ክፍል መሆናችንን ፈጽሞ እንድንዘነጋ አይፈልግም። በዓይናችን ከምናየው ውጭ የይሖዋን ዓላማ በመደገፍ የሚከናወን ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ሕዝቅኤል በአንድ ግዙፍ ሰማያዊ ሠረገላ የተመሰለውን የማይታየውን የይሖዋ ድርጅት ክፍል ተመልክቷል።  ይህ ሠረገላ በከፍተኛ ፍጥነት መጓዝ የሚችል ከመሆኑም በላይ በቅጽበት አቅጣጫውን መቀየር ይችላል። (ሕዝ. 1:15-21) መንኮራኩሮቹ በዞሩ ቁጥር ሠረገላው ረጅም ርቀት መጓዝ ይችላል። ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ የሠረገላውን ነጂ በተወሰነ መጠን መመልከት ችሎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ ‘እንደ ጋለ ብረት ያለ እሳት የሚመስል ነገር አየሁ፤ ይህም የእግዚአብሔር ክብር መልክ አምሳያ ነበረ።’ (ሕዝ. 1:25-28) ሕዝቅኤል ይህን ራእይ ማየቱ በታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲዋጥ ሳያደርገው አልቀረም! ይሖዋ የድርጅቱን እንቅስቃሴ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እየመራ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ተመልክቷል። እየገሰገሰ ያለውን የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የሚወክል እንዴት ያለ አስደናቂ መግለጫ ነው!

7. ዳንኤል ያየው ራእይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው እንዴት ነው?

7 ዳንኤል የተመለከተው ራእይም የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርገናል። “ጥንታዌ ጥንቱ” ተብሎ የተገለጸው ይሖዋ የእሳት ነበልባል ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል። ዙፋኑ መንኮራኩሮች ነበሩት። (ዳን. 7:9) ይሖዋ ድርጅቱ የእሱን ዓላማ ዳር ለማድረስ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ዳንኤል እንዲያውቅ ፈልጎ ነበር። በተጨማሪም ዳንኤል ‘የሰውን ልጅ የሚመስለው’ ኢየሱስ የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል እንዲያስተዳድር ሥልጣን ሲሰጠው ተመልክቷል። ፍጹም የሆነው የክርስቶስ አገዛዝ ለአጭር ዓመታት ብቻ የሚቆይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።” (ዳን. 7:13, 14) ይህ በይሖዋ እንድንታመን እንዲሁም እሱ እያከናወነ ያለውን ነገር እንድንገነዘብ ያስችለናል። ተፈትኖ ማንነቱን ላስመሠከረው ለልጁ ለኢየሱስ “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ሰጥቶታል። (የ1954 ትርጉም) ይሖዋ በልጁ ላይ እምነት አለው። በመሆኑም እኛም በኢየሱስ አመራር ላይ እምነት መጣል እንችላለን።

8. ሕዝቅኤልና ኢሳይያስ ይሖዋ ያሳያቸው ራእይ ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል? በእኛስ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር ይገባል?

 8 የማይታየውን የይሖዋ ድርጅት ክፍል በተመለከተ ያገኘነው ግንዛቤ ምን ስሜት ሊያሳድርብን ይገባል? እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እኛም ይሖዋ እያከናወነ ያለው ነገር ታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃትና የትሕትና ስሜት እንደሚያሳድርብን የተረጋገጠ ነው። (ሕዝ. 1:28) በይሖዋ ድርጅት ላይ ማሰላሰላችን ልክ እንደ ኢሳይያስ ለተግባር ሊያነሳሳን ይችላል። ኢሳይያስ ይሖዋ ምን እያደረገ እንዳለ ለሌሎች ሰዎች መናገር የሚያስችል አጋጣሚ ሲያገኝ አጋጣሚውን ያለምንም ማመንታት ተጠቅሞበታል። (ኢሳይያስ 6:5, 8ን አንብብ።) ኢሳይያስ በይሖዋ ድጋፍ የሚያጋጥመውን ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንደሚችል እምነት ነበረው። እኛም በተመሳሳይ ስለማይታየው የይሖዋ ድርጅት ክፍል ያገኘነው ፍንጭ አክብሮታዊ ፍርሃት ሊያሳድርብንና ለተግባር ሊያነሳሳን ይገባል። ምንጊዜም እየገሰገሰ ባለውና የይሖዋን ዓላማ ለመፈጸም በትጋት እየሠራ በሚገኘው በዚህ ድርጅት ላይ ማሰላሰላችን እንዴት የሚያበረታታ ነው!

የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል

9, 10. የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ከማይታየው የድርጅቱ ክፍል ጋር ተባብሮ የሚሠራ መዋቅር በምድር ላይ ዘርግቷል። በማቴዎስ 24:14 ላይ የተገለጸውን ሥራ ከፍጻሜው ለማድረስ የሚታይ መዋቅር ያስፈለገው ለምንድን ነው? እስቲ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።

10 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንደሚሰብኩ ተናግሯል። (ሥራ 1:8) በሁለተኛ ደረጃ፣ በዚህ ሥራ ለሚካፈሉ ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብና እነሱን ለመንከባከብ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። (ዮሐ. 21:15-17) በሦስተኛ ደረጃ፣ ምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ይሖዋን እንዲያመልኩና ሥራውን ማከናወን የሚችሉበትን መንገድ እንዲማሩ አንዳንድ ነገሮችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። (ዕብ. 10:24, 25) እነዚህን ግቦች እንዲሁ ዳር ማድረስ አይቻልም። የክርስቶስ ተከታዮች ስኬታማ መሆን እንዲችሉ ሥራው በሚገባ መደራጀት ይኖርበታል።

11. የይሖዋ ድርጅት ለሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ድጋፍ እንደምንሰጥ በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

11 የይሖዋ ድርጅት ለሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ድጋፍ እንደምንሰጥ በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ ዋነኛ መንገድ በስብከቱ ሥራችን አመራር በሚሰጡን ወንድሞች ላይ እምነት መጣል ነው፤ ይሖዋና ኢየሱስ እምነት እንደጣሉባቸው ሁሉ እኛም ምንጊዜም ልንተማመንባቸው ይገባል። በዛሬው ጊዜ በመካከላችን ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የሚሰጡንን ሰዎች ትኩረት ሊሻሙ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ይሁንና የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ምንጊዜም ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው?

‘ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች’ ላይ ትኩረት አድርገዋል

12, 13. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት እንዴት ነው? ይህስ አንተን የሚያበረታታህ እንዴት ነው?

12 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተሞክሮ ያካበቱ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሚያገለግሉበት አገር የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በፍጥነት ይስፋፋ ዘንድ በበላይነት አመራር እንዲሰጡ ተሹመዋል። እነዚህ ወንድሞች ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ የአምላክን ቃል ‘ለእግራቸው መብራት፣ ለመንገዳቸው ብርሃን’ አድርገው በመጠቀም መመሪያ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ደግሞም ይሖዋ እንዲመራቸው አጥብቀው ይጸልያሉ።—መዝ. 119:105፤ ማቴ. 7:7, 8

13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ይሰጡ እንደነበሩት ወንድሞች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የስብከቱን ሥራ በበላይነት የሚከታተሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎችም “ቃሉን በማስተማሩ ሥራ” ይተጋሉ። (ሥራ 6:4) ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ እነሱ ባሉበት አገርም ሆነ በመላው ምድር እያደገ መሄዱን ሲመለከቱ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል። (ሥራ 21:19, 20) እነዚህ ወንድሞች ስፍር ቁጥር የሌላቸው መመሪያዎችና  ደንቦች አያወጡም። ከዚህ ይልቅ የስብከቱ ሥራ መስፋፋቱን እንዲቀጥል የሚያግዙ ዝግጅቶችን በሚያደርጉበት ጊዜ የቅዱሳን መጻሕፍትንና የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር ይከተላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 15:28ን አንብብ።) እነዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች እንዲህ በማድረግ በአካባቢያቸው ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች በሙሉ ሊከተሉት የሚገባ መልካም ምሳሌ ይተዋሉ።—ኤፌ. 4:11, 12

14, 15. (ሀ) በምድር ዙሪያ የስብከቱን ሥራ ለመደገፍ ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል? (ለ) የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በመደገፍ ረገድ ስለምታደርገው ተሳትፎ ምን ይሰማሃል?

14 በጽሑፎቻችንም ሆነ በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን መንፈሳዊ ምግቦች በቀጣይነት ለማዘጋጀት የሚከናወነው አድካሚ ሥራ ከብዙዎች እይታ የተሰወረ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጽሑፎቻችንን 600 በሚያህሉ ቋንቋዎች ለመተርጎም ያለማሰለስ ይሠራሉ፤ ይህም ብዙ ሰዎች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” በራሳቸው ቋንቋ መማር እንዲችሉ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ሥራ 2:7-11) በርካታ ወጣት ወንድሞችና እህቶች ፈጣን በሆኑ የማተሚያና የመጠረዣ መሣሪያዎች አማካኝነት ጽሑፎችን ያዘጋጃሉ። ከዚያም እነዚህ ጽሑፎች ሩቅ በሆኑ የዓለማችን ክፍሎች እንኳ ሳይቀር በየጉባኤው ይሰራጫሉ።

15 ምሥራቹን ለመስበኩ ሥራ ትኩረት ሰጥተን ከጉባኤያችን ጋር ማገልገል እንድንችል በርካታ ዝግጅቶች ተደርገዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በመንግሥት አዳራሽና በትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ግንባታ ለመሳተፍ፣ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን ወይም ከጤና ጋር የተያያዘ ድንገተኛ ችግር የገጠማቸውን ለመርዳት፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማደራጀትና በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ላይ ለማስተማር ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ፤ ለአብነት ያህል ብቻ ከላይ ከተጠቀሱት ጥቂት ሥራዎች ጋር በተያያዘ ብዙዎች ምን እንደተከናወነ እንኳ ላያውቁ ይችላሉ። ይህ ሁሉ ሥራ የሚከናወንበት ዓላማ ምንድን ነው? ምሥራቹን ለመስበኩ ሥራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በሥራው የሚሳተፉት ሰዎች መንፈሳዊነት እንዲጠናከር ማድረግ እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ ማስፋፋት ነው። የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ቀጥሏል? እንዴታ!

የይሖዋን ድርጅት ምሳሌ ተከተሉ

16. በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ በየትኞቹ ነገሮች ላይ ምርምር ማድረግ እንችላለን?

16 አልፎ አልፎ፣ የይሖዋ ድርጅት እያከናወነ ባለው ሥራ ላይ ጊዜ ወስደን እናሰላስላለን? አንዳንዶች በቤተሰብ አምልኳቸው ወይም በግል ጥናታቸው ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ምርምር ለማድረግና ለማሰላሰል ጊዜ ይመድባሉ። ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤልና ዮሐንስ የተመለከቷቸውን ራእዮች ማጥናት በጣም አስደሳች ሊሆን ይችላል። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍና ሌሎች ጽሑፎች ወይም ዲቪዲዎች ስለ አምላክ ድርጅት ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፉ፣ ትኩረት የሚስቡ መረጃዎች ይዘዋል።

17, 18. (ሀ) ከዚህ የጥናት ርዕስ ምን ጥቅም አግኝተሃል? (ለ) ልናስብባቸው የሚገቡት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

17 ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት እያከናወነ ባለው ሥራ ላይ ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። ከዚህ አስደናቂ ድርጅት ጎን በመሰለፍ ምንጊዜም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን ጳውሎስ የነበረው ዓይነት ቁርጥ አቋም እንድንይዝ ያስችለናል፤ ሐዋርያው “በተደረገልን ምሕረት የተነሳ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 4:1) በተጨማሪም የእምነት ባልደረቦቹን “ካልታከትን ወቅቱ ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው” በማለት አበረታቷቸዋል።—ገላ. 6:9

18 በግለሰብ ወይም በቤተሰብ ደረጃ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማስቀደም አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልገን ይሆን? ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው የስብከት ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንድንችል ሕይወታችንን ቀላል ማድረግ ወይም ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን መቀነስ እንችላለን? በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መጓዝ እንድንችል የሚረዱንን አምስት ነገሮች እንመለከታለን።