“አቅኚ መሆን ለአንቺ ቀላል ነው። ሁለቱም ወላጆችሽ እውነት ውስጥ ስለሆኑ ሊረዱሽ ይችላሉ።” ይህን ያልነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርታ ታገለግል ለነበረች አንዲት ጓደኛችን ነው። እሷ ግን “የሁላችንም አባት እኮ አንድ ነው” በማለት መለሰችልን። የሰጠችን መልስ ትልቅ ትምህርት ያዘለ ነው፦ በሰማይ ያለው አባታችን አገልጋዮቹን ይንከባከባል እንዲሁም ያበረታቸዋል። በእርግጥም ያሳለፍነው ሕይወት ይህን ሐቅ አረጋግጦልናል።

 የተወለድነው በሰሜናዊ ኦስትሮቦትንያ፣ ፊንላንድ ውስጥ ሲሆን በግብርና ይተዳደሩ የነበሩት ወላጆቻችን አሥር ልጆች ነበሯቸው። በልጅነት ዕድሜያችን የተካሄደው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጥፎ ትዝታ ጥሎብን አልፏል። እንኖር የነበረው ከጦርነቱ አውድማ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ቢሆንም የጦርነቱ አሰቃቂነት ከአእምሯችን አልጠፋም። ኦሉ እና ካላጆኪ የሚባሉት አጎራባች ከተሞች በቦምብ ሲደበደቡ በምሽት ሰማዩ ቀልቶ ይታይ ነበር። ወላጆቻችን የጦር አውሮፕላኖች በአካባቢያችን ሲበሩ ካየን ቶሎ ብለን እንድንሸሸግ አጥብቀው ይመክሩን ነበር። ስለዚህ ታላቅ ወንድማችን ታኡኖ ምድር ገነት እንደምትሆንና የፍትሕ መዛባት እንደሚወገድ ሲነግረን ልባችን ተነካ።

ታኡኖ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በማንበብ ሲሆን በወቅቱ የ14 ዓመት ልጅ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው የተነሳ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ታሰረ። እዚያም ብዙ ግፍ ደረሰበት። ይህ ሁኔታ ግን ይሖዋን ለማገልገል ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ አጠናከረለት፤ በመሆኑም ከእስር ከተፈታ በኋላ ከበፊቱ ይበልጥ አገልግሎቱን በቅንዓት ማከናወን ቀጠለ። ወንድማችን የተወልን ጥሩ ምሳሌ የይሖዋ ምሥክሮች በአቅራቢያው ባለው መንደር ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች እንድንሄድ አነሳሳን። በተጨማሪም ለጉዞ የሚሆን በቂ ገንዘብ ለማጠራቀም ከፍተኛ ጥረት ቢጠይቅብንም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ እንገኝ ነበር። ለጎረቤቶቻችን ልብስ በመስፋት፣ ሽንኩርት በመትከልና እንጆሪ በመልቀም ገንዘብ እናጠራቅማለን። የግብርና ሥራችን ብዙ ነገር ማከናወን ይጠይቅብን ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ በስብሰባዎቹ ላይ አንድ ላይ መገኘት አንችልም፤ በመሆኑም የምንሄደው በየተራ ነበር።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ማቲ (አባታችን)፣ ታኡኖ፣ ሳይሚ፣ ማሪያ ኤሚሊያ (እናታችን)፣ ቫይኖ (ሕፃን)፣ አይሊ እና አኒኪ በ1935

ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የተማርናቸው እውነቶች ለእሱ ያለንን ፍቅር ስላጠነከሩልን ሕይወታችንን ለእሱ ወሰንን። በ1947 ሁለታችንም ሕይወታችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት በውኃ ተጠመቅን። (አኒኪ የ15 አይሊ ደግሞ የ17 ዓመት ልጆች ነበሩ።) እህታችን ሳይሚ የተጠመቀችው በዚያው ዓመት ነበር። በተጨማሪም ባለትዳር የነበረችውን እህታችንን ሊኒያን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናናት። እሷና ቤተሰቧም የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ከተጠመቅን በኋላ የአቅኚነት ግብ በማውጣት አልፎ አልፎ በእረፍት ጊዜ (በረዳት) አቅኚነት እናገለግል ነበር።

ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ኤቫ ካሊዮ፣ ሳይሚ ማቲላ ሲይርጃላ፣ አይሊ፣ አኒኪ እና ሣራ ኖፖነን በ1949

በ1955 በስተ ሰሜን ርቃ ወደምትገኝ ኬሚ የምትባል ከተማ ተዛወርን። ሁለታችንም የሙሉ ቀን ሠራተኞች ብንሆንም አቅኚ የመሆን ፍላጎታችን አልጠፋም ነበር፤ ይሁንና ራሳችንን ችለን ለመኖር እንቸገራለን የሚል ስጋት አደረብን። በመጀመሪያ የተወሰነ ገንዘብ ማጠራቀም እንዳለብን ተሰማን። መግቢያው ላይ ከተጠቀሰችው አቅኚ እህት ጋር የተወያየነው በዚህ ጊዜ ነበር። ከእሷ ጋር ያደረግነው ውይይት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ማገልገል፣ ባለን ገንዘብ ወይም ከወላጆቻችን በምናገኘው ድጋፍ ላይ ብቻ የተመካ እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ረዳን። ዋናው ነገር በሰማዩ አባታችን ላይ መታመናችን ነው።

በ1952 በክዎፕዮ ወደተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ስንጓዝ። ከግራ ወደ ቀኝ፦ አኒኪ፣ አይሊ እና ኤቫ ካሊዮ

በወቅቱ የሁለት ወር ወጪያችንን ለመሸፈን የሚበቃ ገንዘብ አጠራቅመን ነበር። ስለዚህ ግንቦት 1957 ፈራ ተባ እያልን ለሁለት ወራት ከአርክቲክ የሐሳብ መስመር በላይ በላፕላንድ በምትገኝ ፔሎ የምትባል ከተማ በአቅኚነት ለማገልገል አመለከትን።  ከሁለት ወር በኋላም ያጠራቀምነው ገንዘብ ምንም አልተነካም፤ ስለዚህ ለተጨማሪ ሁለት ወራት በአቅኚነት ለመቀጠል አመለከትን። እንደገና ሁለት ወር ካለፈ በኋላም ገንዘባችን እንዳለ ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እንደሚንከባከበን እርግጠኞች ሆንን። በአቅኚነት ለ50 ዓመታት ካገለገልን በኋላም ገንዘቡ እስካሁን አልተነካም! ወደኋላ መለስ ብለን ስናስብ ይሖዋ እጃችንን ይዞ ‘አትፍሩ፤ እረዳችኋለሁ’ ያለን ያህል እንደነበረ እናምናለን።—ኢሳ. 41:13

የዛሬ 50 ዓመት አቅኚነት ከመጀመራችን በፊት ያጠራቀምነው ገንዘብ አሁንም አለ!

ካይሱ ሬይኮ እና አይሊ በመስክ አገልግሎት ላይ

በ1958 የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን በላፕላንድ ወደምትገኘው የሶዳንኪላ ከተማ ተዛውረን በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ሐሳብ አቀረበልን። በዚያን ጊዜ በዚያ አካባቢ የነበረችው አንዲት እህት ብቻ ነበረች። ይህች እህት እውነትን የሰማችው በሚገርም መንገድ ነው። ልጇ ከክፍሉ ተማሪዎች ጋር የፊንላንድ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ሄልሲንኪ ለጉብኝት ሄዶ ነበር። ተማሪዎቹ ከተማዋን እየጎበኙ ሳለ አንዲት አረጋዊት እህት ከኋላ ለነበረው ለዚህ ልጅ አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም ሰጡትና ለእናቱ እንዲሰጣት ነገሩት። ልጁ እንደተባለው ያደረገ ሲሆን እናቱም ወዲያውኑ እውነትን እንዳገኘች ተገነዘበች።

ከአንድ እንጨት መሰንጠቂያ ድርጅት በላይ የሚገኝ አንድ ክፍል ቤት ተከራየን። ስብሰባችንን የምናደርገው እዚያው ነበር። መጀመሪያ ላይ ስብሰባ የምናደርገው ሁለታችን እንዲሁም በዚያ የምትኖረው እህትና ሴት ልጇ ብቻ ነበርን። የሚጠናውን ጽሑፍ አብረን እናነብ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና አንድ ሰው በእንጨት መሰንጠቂያው ድርጅት ለመሥራት መጣ። እሱና ቤተሰቡ ከእኛ ጋር መሰብሰብ ጀመሩ። ውሎ አድሮ እሱና ሚስቱ ተጠመቁ። ይህ ወንድም ስብሰባዎቻችንን ይመራልን ጀመር። በተጨማሪም በእንጨት መሰንጠቂያው የሚሠሩ አንዳንድ ሰዎች በስብሰባ ላይ መገኘት የጀመሩ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበሉ። ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ቡድናችን አድጎ ጉባኤ ተቋቋመ።

ተፈታታኝ ሁኔታዎች

ረጅም ርቀት የምንጓዝ መሆኑ የስብከቱ ሥራችንን ተፈታታኝ አድርጎብን ነበር። በበጋ በእግር ወይም በብስክሌት እንጓዛለን፤ አልፎ ተርፎም በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማግኘት በጀልባ እንሄዳለን። በተለይ ብስክሌቶቻችን በእጅጉ ጠቅመውናል። በተጨማሪም ብስክሌቶቹን ወደ አውራጃ ስብሰባዎችና ብዙ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ ወላጆቻችንን ለመጠየቅ ስንሄድ እንጠቀምባቸው ነበር። በክረምት ወራት በማለዳ አውቶቡስ ተሳፍረን ወደ አንድ መንደር ከተጓዝን በኋላ ከቤት ወደ ቤት በእግራችን እየሄድን እናገለግል ነበር። አንዱን መንደር ካዳረስን በኋላ ወደሚቀጥለው መንደር በእግር እንሄዳለን። በረዶው ጥልቀት ያለው ከመሆኑም ሌላ ከመንገድ ላይ ሳይጠረግ የሚቀርባቸው ጊዜያት ነበሩ። ብዙውን ጊዜ በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎች በበረዶው ላይ ያለፉበትን መንገድ ተከትለን እንጓዝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ የሚዘንበው በረዶ ሰዎች ቀደም ብለው የተጓዙበትን መንገድ ይሸፍነዋል፤ በጸደይ ወቅት መጀመሪያ  ላይ ደግሞ በረዶው መሟሟት ስለሚጀምር የምንራመደው በብዙ ትግል ነው።

ክረምት ላይ ብርዳማ በሆነ ቀን አብረን ስናገለግል

ኃይለኛ ቅዝቃዜ ስላለና በረዶ ስለሚዘንብ የሚያሞቅ ልብስ መልበስ ለምደናል። ከሱፍ የተሠሩ ስቶኪንጎችንና ሁለት ወይም ሦስት ካልሲዎችን እንዲሁም ረጅም ቡትስ ጫማ እናደርግ ነበር። ያም ሆኖ ብዙውን ጊዜ ቡትስ ጫማችን ውስጥ በረዶ ይገባል። አንድ ቤት ለማንኳኳት ደረጃው ላይ ልንወጣ ስንል ቡትሳችንን አውልቀን በረዶውን እናራግፋለን። በተጨማሪም በበረዶው ውስጥ እየዳከርን ስንሄድ ረጃጅም የክረምት ጃኬቶቻችን ጠርዛቸው ይበሰብሳል። ከዚያም ብርዱ ሲጨምር የጃኬታችን ጠርዝ በቅዝቃዜው ቆርፍዶ እንደ ብረት ይደርቃል። አንዲት የቤት እመቤት “ማንም ሳያስገድዳችሁ እንዲህ ዓይነቱን ከባድ የአየር ሁኔታ ተቋቁማችሁ የምትመጡት እውነተኛ እምነት ስላላችሁ መሆን አለበት” ብላናለች። እሷ ቤት ለመድረስ ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዘናል።

የምንሄድባቸው ቦታዎች ከመራቃቸው የተነሳ ብዙውን ጊዜ በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እናድር ነበር። እየመሸ ሲሄድ ማደሪያ ቦታ መጠየቅ እንጀምራለን። ቤቶቹ አነስተኛ ቢሆኑም ሰዎቹ ሰው ወዳዶችና እንግዳ ተቀባዮች ስለነበሩ የምንተኛበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን የምንበላው ምግብም ይሰጡናል። ብዙውን ጊዜ የምንተኛው በርኤም፣ በአጋዘን ወይም በድብ ቆዳ ላይ ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ ምቾት ያለው ማረፊያ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ትልቅ ቤት የምትኖር አንዲት ሴት ፎቅ ላይ ወዳለ የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ያስገባችን ሲሆን ክፍሉ ውስጥ ነጭ የአልጋ ልብስ የተነጠፈበት የሚያምር አልጋ ይገኝ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በምናድርበት ቤት ከቤተሰቡ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እየተወያየን በጣም እናመሻለን። አንድ ባልና ሚስት በቤታቸው እንድናድር ፈቅደውልን እነሱ በአንዱ ጥግ ሲተኙ እኛ ደግሞ በዚያው ክፍል ውስጥ በሌላው ጥግ ተኛን። ከእነሱ ጋር ሌሊቱን ሙሉ፣ ጎሕ እስኪቀድ ድረስ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት አደረግን። ባልና ሚስቱ በየተራ ጥያቄዎችን እያከታተሉ ይጠይቁን ነበር።

ፍሬያማ አገልግሎት

ላፕላንድ ያልለማ ቢሆንም ውብ አገር ሲሆን ውበቱ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ይለዋወጣል። ለእኛ ግን ለይሖዋ አድናቆት ያላቸው ሰዎች ከዚያ ይበልጥ ውብ ሆነው ይታዩን ነበር። ከመሠከርንላቸው ቅን ሰዎች መካከል በላፕላንድ፣ ዛፍ ቆራጮች በሠፈሩባቸው ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይገኙበታል። አንዳንድ ጊዜ ወደ አንድ ጎጆ ስንገባ በደርዘን የሚቆጠሩ ወንዶች አንድ ላይ ሆነው እናገኛለን፤ እኛ በአንጻራዊ ሁኔታ ስንታይ ደቃቃዎች ነበርን። እነዚህ ጠብደል ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በደስታ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን ጽሑፎችንም ይወስዳሉ።

ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች አጋጥመውናል። አንድ ቀን በአውቶቡስ ማቆሚያው ውስጥ የነበረው ሰዓት አምስት ደቂቃ ቀድሞ ስለነበር አውቶቡሱ አመለጠን። ስለዚህ ወደ ሌላ መንደር የሚሄድ አውቶቡስ ተሳፍረን ለመሄድ ወሰንን። ከዚህ በፊት በዚያ አካባቢ አገልግለን አናውቅም። በመጀመሪያው ቤት ያገኘናት አንዲት ወጣት ሴት “ትመጣላችሁ ብዬ ስጠብቃችሁ ነበር” አለችን። የዚህች ወጣት ሴት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ነበረች። በመሆኑም በዚህ ቀን መጥተን እንድናነጋግራት በእህቷ በኩል መልእክት ልካብን ነበር። እኛ ግን መልእክቷ አልደረሰንም። እሷና ጎረቤቶቿ የሆኑት ዘመዶቿ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እነዚህን ጥናቶች ቀላቅለን አሥራ ሁለት የሚሆኑ ሰዎችን አንድ ላይ ማስጠናት  ጀመርን። ከጊዜ በኋላም አብዛኞቹ የዚህ ቤተሰብ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።

በ1965 ከአርክቲክ ክልል ትንሽ ዝቅ ብሎ ኩሳሞ ውስጥ በሚገኝ አሁን ባለንበት ጉባኤ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያን ጊዜ የጉባኤው አስፋፊዎች ጥቂት ነበሩ። መጀመሪያ ላይ አዲሱ ክልላችን ትንሽ አስቸጋሪ ይመስል ነበር። የክልሉ ነዋሪዎች በጣም ሃይማኖተኛ ስለነበሩ ለእኛ ጭፍን ጥላቻ ነበራቸው። ያም ሆኖ ብዙዎቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የነበራቸው ሲሆን ይህም ከእነሱ ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሩ መሠረት ሆኖልናል። ስለዚህ ቀስ በቀስ ሰዎቹን እያወቅናቸው በመሄዳችን ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቀላል ሆነልን።

አሁንም በአገልግሎት በንቃት እየተሳተፍን ነው

መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው መካከል አንዳንዶቹ

በዛሬው ጊዜ ቀኑን ሙሉ በአገልግሎት ለማሳለፍ የሚያስችል አቅም ባይኖረንም አሁንም በየዕለቱ ማለት ይቻላል በአገልግሎት እንካፈላለን። አይሊ የወንድማችን ልጅ በሰጣት ማበረታቻ በ1987 በ56 ዓመቷ መኪና መንዳት ተምራ መንጃ ፈቃድ በያዘች ጊዜ ምሥራቹን ሰፊ በሆነው ክልላችን ላሉ ሰዎች ማዳረስ ቀላል ሆነልን። በተጨማሪም አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ከተሠራ በኋላ ከአዳራሹ ጋር ተያይዞ ወደተገነባው ፎቅ የተዛወርን ሲሆን ይህም ሁኔታዎችን አቅልሎልናል።

ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የታየው እድገት ታላቅ ደስታ አስገኝቶልናል። በሰሜናዊ ፊንላንድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስንጀምር በዚያ ሰፊ ክልል ውስጥ ተበታትነው የሚገኙት አስፋፊዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። አሁን በዚህ ክልል ውስጥ በርከት ያሉ ጉባኤዎችን ያቀፈ አንድ ወረዳ አለ። ብዙውን ጊዜ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ አንድ ሰው መጥቶ ከተዋወቀን በኋላ እናስታውሰው እንደሆነ ይጠይቀናል። አንዳንድ ጊዜ መጥቶ የሚተዋወቀን ሰው በቤታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንመራ በነበርንበት ጊዜ ሕፃን ልጅ የነበረ ሊሆን ይችላል። ይህም ከዓመታት፣ አልፎ ተርፎም ከአሥርተ ዓመታት በፊት የተዘራው የእውነት ዘር አድጎ ለፍሬ እንደበቃ ያሳያል!—1 ቆሮ. 3:6

ዝናብ ባለበት ቀንም እንኳ አገልግሎት መውጣት ያስደስተናል

በ2008 የልዩ አቅኚነት አገልግሎታችንን ከጀመርን 50 ዓመት ሞላን። እርስ በርስ እየተበረታታን ይሖዋ በሰጠን ውድ ሥራ መጽናት በመቻላችን አምላካችንን እናመሰግነዋለን። ኑሯችን ቀላል የነበረ ቢሆንም ያጣነው አንዳች ነገር የለም። (መዝ. 23:1) የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ፈራ ተባ ማለታችን ምንም ትርጉም አልነበረውም! ደስ የሚለው ነገር፣ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ይሖዋ በኢሳይያስ 41:10 ላይ “አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” በማለት ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ አበርትቶናል።