በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2013

በእርግጥ ጆሴፈስ ጽፎታል?

በእርግጥ ጆሴፈስ ጽፎታል?

ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የአንደኛው መቶ ዘመን ታሪክ ፀሐፊ ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ በተባለው መጽሐፉ ላይ ስለ ያዕቆብ መገደል የጻፈ ሲሆን ያዕቆብ “ክርስቶስ እየተባለ የሚጠራው የኢየሱስ ወንድም ነው” ሲል ገልጿል። በርካታ ምሁራን ይህ መግለጫ ትክክለኛ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ምሁራን ኢየሱስን በተመለከተ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ሌላ ሐሳብ እውነት መሆኑን ይጠራጠራሉ። ቴስቲሞንየም ፍላቭያነም በመባል የሚታወቀው ይህ ምንባብ እንዲህ ይላል፦

“በዚህ ወቅት፣ አስደናቂ የሆኑ ተአምራት ያደርግ የነበረ በመሆኑ፣ ሰው ብሎ ለመጥራት የሚከብድ ቢሆንም ኢየሱስ የተባለ እውነትን በደስታ የሚቀበሉ ሰዎችን የሚያስተምር ጠቢብ ሰው ነበር። በርካታ አይሁዳውያንንም ሆነ በርካታ አሕዛብን ወደ ራሱ መሳብ ችሏል። እሱ ክርስቶስ ነበር፤ ጲላጦስ በመካከላችን ያሉ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሰዎች ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት መስቀል ላይ እንዲገደል በፈረደበት ጊዜም ቀድሞውንም ይወዱት የነበሩት ሰዎች አልከዱትም፤ ምክንያቱም በአምላክ የተላኩ ነቢያት [ከሞት እንደሚነሳም] ሆነ እሱን በተመለከተ ሌሎች በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ድንቅ ነገሮችን በተነበዩት መሠረት በሦስተኛው ቀን ሕያው ሆኖ ተገልጦላቸዋል፤ ስለሆነም በእሱ ስም የተሰየሙት ክርስቲያኖች የሚባሉ ሰዎች ዛሬም አልጠፉም።”—ጆሴፈስ—ዘ ኮምፕሊት ወርክስ፣ በዊልያም ዊስተን የተተረጎመ

ከ16ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አንስቶ ይህ ምንባብ በትክክል ጆሴፈስ የጻፈው ነው በሚሉና ጆሴፈስ መጻፉን በሚጠራጠሩ ሰዎች መካከል የጦፈ ክርክር ሲካሄድ ቆይቷል። ፈረንሳዊ ታሪክ ፀሐፊና የጥንታዊ ሥነ ጽሑፎች ሊቅ የሆኑት ሰርዥ ባርዴ፣ ባለፉት አራት መቶ ዓመታት እጅግ ተወሳስቦ የቆየውን የክርክር ቋጠሮ ለመፍታት ጥረት አድርገዋል። የምርምራቸውን ውጤት ለ ቴስቲሞንየም ፍላቭያነም—ኤክሳመ ኢስቶሪክ ኮንሲዴራስዮ ኢስቶሪዮግራፊክ (ቴስቲሞንየም ፍላቭያነም —ታሪካዊ ጭብጦችን በማገናዘብ የተደረገ ታሪካዊ ጥናት) በተባለ መጽሐፍ አውጥተዋል።

ጆሴፈስ የክርስትናን እምነት የሚከተል ፀሐፊ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አይሁዳዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው፤ ስለሆነም አብዛኛው ውዝግብ ያተኮረው ኢየሱስ “ክርስቶስ” ተብሎ በመጠራቱ ላይ ነው። ባርዴ በትንታኔያቸው ላይ ይህ የማዕረግ ስም “ግሪካውያን በሰዎች ስም ላይ [ጠቃሽ] አመልካች ከመጨመራቸው ጋር” ይመሳሰላል በማለት አረጋግጠዋል። በማከልም በአይሁድና በክርስትና አመለካከት መሠረት “ጆሴፈስ ክሪስቶስ በሚለው ቃል መጠቀሙ ሊሆን የማይችል ነገር አለመሆን ብቻ” ሳይሆን “ተቺዎች በጥቅሉ ሳያስተውሉት በመቅረታቸው ከባድ ስህተት የሠሩበት” ትልቅ ትርጉም ያለው ፍንጭ ነው ብለዋል።

ይህ ምንባብ በኋለኞቹ ዓመታት የተነሳ አስመሳይ ፀሐፊ የጆሴፈስን የአጻጻፍ ስልት አስመስሎ የጻፈው ሊሆን ይችላል? ባርዴ የታሪክና የጽሑፍ መረጃዎችን ካገናዘቡ በኋላ አንድ ሰው ይህን ያህል አስመስሎ መጻፍ ከቻለ እንደ ተአምር ይቆጠራል ብለዋል። ይህ ሰው “በጥንታዊው ዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የማስመሰል ችሎታ” ያለው መሆን ይኖርበታል፤ በሌላ አባባል “ሌላ ጆሴፈስ መሆን አለበት” ማለት ነው።

ታዲያ ጉዳዩ ይህን ያህል ያወዛገበው ለምንድን ነው? ባርዴ የችግሩን ዋነኛ መንስኤ ሲያመለክቱ “ከአብዛኞቹ የጥንት ጽሑፎች ጋር ሲነጻጸር በቴስቲሞንየም ላይ ብዙ ጥርጣሬ ሊፈጠር የቻለው በቴስቲሞንየም ላይ ጥያቄ በመነሳቱ ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል። አክለውም ሲናገሩ ባለፉት መቶ ዘመናት የተወሰዱት አቋሞች የምንባቡን ትክክለኛነት በሚደግፉት የጽሑፉ ትንታኔዎች ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ “ስውር ፍላጎቶችን” መሠረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

የባርዴ ትንታኔ ምሁራን በቴስቲሞንየም ፍላቭያነም ላይ ያላቸውን አመለካከት ያስለውጥ እንደሆነ ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል። ሆኖም ይህ ትንታኔ በጥንት ዘመን የነበሩትን የአይሁድና የክርስትና እምነቶች ያጠኑትን ፒየር ዦልትሬ የተባሉ እውቅ የሆኑ ሊቅ አሳምኗቸዋል። ቀደም ሲል እኚህ ሰው ቴስቲሞንየም በጆሴፈስ ጽሑፍ ውስጥ የተጨመረ ሐሳብ እንደሆነ ሲናገሩ የነበሩ ከመሆናቸውም ሌላ በትክክለኛነቱ በሚያምኑ ሰዎች ያሾፉ ነበር። ሆኖም አመለካከታቸውን ለውጠዋል። ለዚህ ምክንያት የሆናቸው የባርዴ ትንታኔ እንደሆነ ተናግረዋል። ዦልትሬ እንዲህ ብለዋል፦ “ከአሁን በኋላ ማንም ሰው ‘አሳማኝ ያልሆነው የጆሴፈስ ምሥክርነት’ ብሎ ለመናገር መድፈር አይኖርበትም።”

እርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው ይበልጥ አሳማኝ የሆነ ምክንያት አላቸው፤ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃ ነው።—2 ጢሞ. 3:16