በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2013

ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?

ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?

“እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ . . . እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል።” —ኤር. 24:7

1, 2. አንዳንዶች ስለ በለስ ማወቅ የሚፈልጉት ለምን ሊሆን ይችላል?

በለስ መብላት ትወዳለህ? ብዙዎች ይወዳሉ፤ በመሆኑም በለስ በብዛት ይመረታል። በለስ በጥንት አይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅ ፍሬ ነበር። (ናሆም 3:12፤ ሉቃስ 13:6-9) አሰርና የተለያዩ ማዕድናት እንዲሁም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ስላሉት ለልብ ጥሩ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ።

2 ይሖዋ በለስን ከልብ ጋር አያይዞ የተናገረበት ጊዜ አለ። ይሁንና አምላክ በለስ መመገብ ለሰውነት ስለሚሰጠው ጥቅም መግለጹ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በምሳሌያዊ መንገድ እየተናገረ ነበር። በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ስለ ልብ የተናገረው ሐሳብ ለአንተም ሆነ ለወዳጆችህ የሚጠቅም ትምህርት ይዟል። የተናገረውን ሐሳብ በምንመረምርበት ጊዜ ምሳሌው ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም እንዳለው አስብ።

3. በኤርምያስ ምዕራፍ 24 ላይ የተገለጹት የበለስ ዓይነቶች ምን ያመለክታሉ?

3 በመጀመሪያ አምላክ በኤርምያስ ዘመን ስለ በለስ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። በ617 ዓ.ዓ. የይሁዳ ብሔር በአስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። አምላክ ወደፊት ምን እንደሚመጣ በራእይ ያሳወቀ ሲሆን ሁኔታውን በሁለት ዓይነት የበለስ ፍሬ ይኸውም “መልካም” በሆነና “እጅግ መጥፎ” በሆነ በለስ በምሳሌያዊ መንገድ ገልጾታል። (ኤርምያስ 24:1-3ን አንብብ።) መጥፎው በለስ፣ በንጉሥ ናቡከደነፆርና በወታደሮቹ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸው የነበሩትን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መሰሎቹን ያመለክታል። በወቅቱ በባቢሎን የነበሩትን ሕዝቅኤልን፣ ዳንኤልንና ሦስቱ ጓደኞቹን እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደዚያ የተወሰዱትን አንዳንድ አይሁዳውያን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች በመልካም በለስ ተመስለዋል። ከእነሱ መካከል የሚቀሩት ሰዎች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ዳግመኛ ለመገንባት ወደዚያ የመመለስ ተስፋ ነበራቸው። ይህም ጊዜውን ጠብቆ ተፈጽሟል።—ኤር. 24:8-10፤ 25:11, 12፤ 29:10

4. አምላክ ስለ መልካም በለስ ከተናገረው ሐሳብ ምን ማበረታቻ እናገኛለን?

4 ይሖዋ በመልካም በለስ የተመሰሉትን ሰዎች “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ . . . እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል” ብሏቸዋል። (ኤር. 24:7) ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተው በዚህ ጥቅስ ላይ ሲሆን ጥቅሱ እጅግ የሚያበረታታ ሐሳብ ይዟል! አምላክ እሱን “የሚያውቅ ልብ” ለሰዎች  ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። በዚህ አገባቡ “ልብ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ዝንባሌ ያመለክታል። አንተም እንዲህ ያለ ልብ እንዲኖርህ እንደምትፈልግና ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል ለመሆን እንደምትጓጓ የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ እንዲሳካልህ የምትፈልግ ከሆነ ልትወስዳቸው ከሚገቡ እርምጃዎች መካከል የአምላክን ቃል ማጥናትና በሥራ ማዋል፣ ንስሐ መግባትና መመለስ፣ ሕይወትህን ለአምላክ መወሰን እንዲሁም በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ይገኙበታል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 3:19) እነዚህን እርምጃዎች ወስደህ ይሆናል፤ አሊያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አዘውትረህ በመሰብሰብ እነዚህን እርምጃዎች እየወሰድክ ይሆናል።

5. ኤርምያስ በዋነኝነት የጻፈው የእነማንን ልብ በተመለከተ ነው?

5 ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ወይም ሁሉንም እርምጃዎች ወስደን ይሆናል፤ ይሁንና አሁንም ለአስተሳሰባችንና ለምግባራችን ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። ኤርምያስ ስለ ልብ ከጻፋቸው ሌሎች ሐሳቦች በመነሳት ይህ የሆነበትን ምክንያት መረዳት እንችላለን። በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ምዕራፎች በይሁዳ ዙሪያ ስለነበሩት ብሔራት የሚናገሩ ቢሆንም መጽሐፉ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው በአምስቱ የአይሁዳውያን ነገሥታት የግዛት ዘመን በነበረው የይሁዳ ብሔር ላይ ነው። (ኤር. 1:15, 16) አዎ፣ ኤርምያስ በዋነኝነት መልእክቱን የጻፈው ራሳቸውን ወስነው ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመሠረቱ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ነበር። አባቶቻቸው በብሔር ደረጃ በራሳቸው ፈቃድ ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና መሥርተው ነበር። (ዘፀ. 19:3-8) በኤርምያስ ዘመን ደግሞ ሕዝቡ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል። “አንተ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላካችን ነህና፤ አዎን፤ ወደ አንተ እንመጣለን” ብለዋል። (ኤር. 3:22) ይሁንና ልባቸው በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር?

ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋል?

6. አምላክ ስለ ልብ ለተናገረው ነገር ልዩ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

6 በዘመናችን ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ተጠቅመው የልብን ጤንነት መመርመር ችለዋል። ይሁንና ይሖዋ በኤርምያስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይችላል። በዚህ ረገድ አምላክ እጅግ የላቀ ችሎታ እንዳለው ከሚከተለው ሐሳብ መረዳት እንችላለን፦ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል? እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ።” (ኤር. 17:9, 10) ‘ልብን መመርመር’ የሚለው አነጋገር በ70 ወይም በ80 ዓመት ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ያህል ጊዜ የሚመታውን የሰውን ልብ በሕክምና ዘዴ መመርመር ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ስለ ምሳሌያዊ ልብ እየተናገረ ነበር። እዚህ ላይ የተገለጸው “ልብ” የአንድን ሰው ፍላጎት፣ ሐሳብ፣ ዝንባሌ፣ አመለካከትና ግብ ጨምሮ ውስጣዊ ማንነቱን በአጠቃላይ ያመለክታል። አንተም እንዲህ ዓይነት ልብ አለህ። አምላክ ልባችንን መመርመር ይችላል፤ አንተም በተወሰነ መጠን ልብህን መመርመር ትችላለህ።

7. ኤርምያስ በዘመኑ የነበሩትን የአብዛኞቹን አይሁዳውያን ልብ የገለጸው እንዴት ነው?

7 ይህን ምርመራ ለማድረግ ‘በኤርምያስ ዘመን፣ አብዛኞቹ አይሁዳውያን የነበራቸው ምሳሌያዊ ልብ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር?’ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ኤርምያስ “የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው አልተገረዘም” በማለት የተናገረውን ያልተለመደ አባባል እንመርመር። ኤርምያስ አይሁዳውያን ወንዶች ያከናውኑት የነበረውን የተለመደ ግርዘት ማመልከቱ አልነበረም። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሥጋቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል’” በማለት የተናገረው ሐሳብ ይህን በግልጽ ያሳያል። የተገረዙ አይሁዳውያን ወንዶችም እንኳ “ልባቸው አልተገረዘም” ነበር። (ኤር. 9:25, 26) ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው?

8, 9. አብዛኞቹ አይሁዳውያን ከልባቸው ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር?

8 አምላክ አይሁዳውያን ሊያደርጉት የሚገባውን ነገር በተመለከተ የሰጣቸው ማሳሰቢያ ‘ያልተገረዘ ልብ’ የሚለው አነጋገር ምን ማለት እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች . . . የልባችሁንም ሸለፈት  አስወግዱ፤ አለዚያ ስለ ሠራችሁት ክፋት፣ ቍጣዬ እንደ እሳት ይንበለበላል።” ይሁንና የሠሩት ክፋት ከየት የመነጨ ነበር? ከውስጥ ይኸውም ከልባቸው የመነጨ ነበር። (ማርቆስ 7:20-23ን አንብብ።) አዎ፣ አምላክ በኤርምያስ አማካኝነት አይሁዳውያኑ መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ በትክክል መርምሮ ደርሶበታል። ልባቸው እልኸኛና ዓመፀኛ ነበር። ውስጣዊ ፍላጎታቸውና አስተሳሰባቸው እሱን አላስደሰተውም። (ኤርምያስ 5:23, 24፤ 7:24-26ን አንብብ።) አምላክ “ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ” ብሏቸዋል።—ኤር. 4:4፤ 18:11, 12

9 በመሆኑም በሙሴ ጊዜ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ በኤርምያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኸውም ‘ልባቸውን መገረዝ’ አስፈልጓቸው ነበር። (ዘዳ. 10:16፤ 30:6) ‘የልባቸውን ሸለፈት መግረዝ’ ሲባል ልባቸው ደንዳና እንዲሆን ያደረገውን ነገር ይኸውም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረነውን አስተሳሰባቸውን፣ ፍላጎታቸውን ወይም ዝንባሌያቸውን ማስወገድ ማለት ነው።—ሥራ 7:51

ዛሬም እሱን “የሚያውቅ ልብ” ሊኖረን ይገባል

10. የዳዊትን አርዓያ በመከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 አምላክ ምሳሌያዊውን ልብ ጠንቅቀን ማወቅ እንድንችል ስለሚረዳን እጅግ አመስጋኞች ነን! ይሁንና አንዳንዶች ‘ይህ ጉዳይ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ለምን ያሳስባቸዋል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይህ የሆነው በየጉባኤው ያሉት በርካታ ክርስቲያኖች በጥንት ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን መጥፎ አካሄድ ስለተከተሉ ወይም “መጥፎ በለስ” ስለሆኑ አይደለም። ይልቁንም በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ለእሱ ያደሩ ንጹሕ ሕዝቦች ናቸው። ይሁንና ጻድቅ የነበረው ዳዊት እንኳ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ” ብሎ ይሖዋን እንደለመነ አትዘንጋ።—መዝ. 17:3፤ 139:23, 24

11, 12. (ሀ) እያንዳንዳችን ልባችንን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ምን ያደርጋል ብለን መጠበቅ አይኖርብንም?

11 ይሖዋ እያንዳንዳችን በእሱ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም እንድንይዝና ይህን አቋሟችንን ጠብቀን እንድንኖር ይፈልጋል። ኤርምያስ ጻድቁን ሰው በተመለከተ ሲናገር “ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ” ብሏል። (ኤር. 20:12) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የጻድቁን ሰው ልብ እንኳ የሚመረምር ከሆነ እኛም ልባችንን በሐቀኝነት መመርመር አይኖርብንም? (መዝሙር 11:5ን አንብብ።) እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ በቸልታ ልናልፈው የማይገባ አመለካከት ወይም ግብ እንዳለን አሊያም ደግሞ አንድ ዓይነት ስሜት እንደተጠናወተን እንገነዘብ ይሆናል። ልባችን በተወሰነ መጠን እንዲደነዝዝ ያደረገ ምሳሌያዊ ‘የልብ ሸለፈት’ እንዳለ ልናስተውልና ማስወገድ እንደሚኖርብን ልንገነዘብ እንችላለን። በዚህ መንገድ ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና እናደርጋለን። ምሳሌያዊ ልብህን መመርመርህ ጥሩ እንደሆነ ከተገነዘብክ ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልግህ ምን ላይ ነው? አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?—ኤር. 4:4

12 አንድ ሐቅ አለ፦ ይሖዋ ለውጥ እንድናደርግ ያስገድደናል ብለን መጠበቅ አይኖርብንም። “መልካም በለስ” ለሆኑት “[እኔን] የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ” ሲል ቃል ገብቷል። ይሁንና አስገድዶ ልባቸው እንዲለወጥ እንደሚያደርግ አልተናገረም። አምላክን እንደሚያውቁ የሚያሳይ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ልብ ለማግኘት መመኘታቸው አስፈላጊ ነው። ይህ የእኛም ፍላጎት ሊሆን አይገባም?

ልብን መመርመርና ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ማስወገድ በረከት ያስገኛል

13, 14. አንድ ክርስቲያን ልቡ ጉዳት ላይ ሊጥለው የሚችለው እንዴት ነው?

 13 ኢየሱስ “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመስከርና ስድብ ይወጣሉ” ብሏል። (ማቴ. 15:19) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደምንችለው አንድ ወንድም ልቡ ደንድኖ ምንዝር ወይም ዝሙት ቢፈጽምና ንስሐ ሳይገባ ቢቀር የአምላክን ሞገስ ለዘለቄታው ሊያጣ ይችላል። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ባይሠራም እንኳ በልቡ ክፉ ምኞት እንዲያቆጠቁጥ ሊፈቅድ ይችላል። (ማቴዎስ 5:27, 28ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ ግለሰቡ ልቡን መመርመሩ ይጠቅመዋል። ልብህን በሚገባ ስትመረምር ለተቃራኒ ፆታ ተገቢ ያልሆነ ስሜት ይኸውም አምላክ የማይቀበለውና መወገድ ያለበት ስውር ምኞት በውስጥህ መኖሩን ታስተውል ይሆን?

14 አሊያም ደግሞ አንድ ወንድም ቃል በቃል ሰው ‘ባይገድልም’ በክርስቲያን ባልንጀራው ላይ ያደረበት ቁጣ በልቡ ውስጥ ሥር ሰድዶ ወንድሙን እስከ መጥላት ሊደርስ ይችላል። (ዘሌ. 19:17) ልቡ እንዲደነድን ሊያደርጉ የሚችሉትን እንዲህ ያሉ ስሜቶች ለማስወገድ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርግ ይሆን?—ማቴ. 5:21, 22

15, 16. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ‘ያልተገረዘ ልብ’ ሊኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ይሖዋ ‘ያልተገረዘን ልብ’ ይጠላል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ደስ የሚለው ነገር አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ‘የልብ ችግር’ የለባቸውም። ይሁንና ኢየሱስ ‘ስለ ክፉ ሐሳብም’ ተናግሯል። እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት በብዙ የሕይወታችን ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ለዘመዶቹ አግባብ ያልሆነ ታማኝነት ያሳይ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ከሚኖሩት በርካታ ሰዎች በተለየ ሁኔታ ለዘመዶቻቸው “ተፈጥሯዊ ፍቅር” ማሳየት ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞ. 3:1, 3) ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ለዘመዶቻችን የምናሳየው ፍቅር ሚዛኑን የሳተ ሊሆን ይችላል። “ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ” እንደሚባለው ብዙዎች ለዘመዶቻቸው የማድላት ባሕርይ ይታይባቸዋል። በመሆኑም ዘመዳቸው በደል ከተፈጸመበት በእነሱ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አድርገው በመቁጠር ምንም ይምጣ ምን ለዘመዳቸው ሊሟገቱ ወይም ከእሱ ጎን ሊቆሙ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ከልክ ያለፈ ስሜት የዲናን ወንድሞች ምን እንዲፈጽሙ እንዳነሳሳቸው አስታውስ። (ዘፍ. 34:13, 25-30) በተጨማሪም አቤሴሎም በልቡ ውስጥ ያደረው መጥፎ ስሜት የአባቱን ልጅ አምኖንን እንዲገድል አነሳስቶታል። (2 ሳሙ. 13:1-30) አዎ፣ “ክፉ ሐሳብ” በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል።

16 እውነተኛ ክርስቲያኖች ነፍስ እንደማያጠፉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በዘመዳቸው ላይ በደል ሲፈጽሙ ወይም እንደፈጸሙ አድርገው ሲያስቡ ለእነሱ መጥፎ ስሜት ያድርባቸው ይሆን? ዘመዳቸውን እንደበደለ አድርገው ያሰቡት የእምነት ባልንጀራቸው  ግብዣ ሲያቀርብላቸው አይቀበሉም ወይም እነሱ አይጋብዙትም። (ዕብ. 13:1, 2) እንዲህ ያለ አሉታዊ ስሜት ማንጸባረቅ እንዲሁም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አለማሳየት ፍቅር እንደሚጎድለን የሚጠቁም ሲሆን በቸልታ ሊታለፍ አይገባውም። በዚህ ጊዜ፣ ልብን የሚመረምረው አምላክ ‘ልባችን እንዳልተገረዘ’ ሊያስተውል ይችላል። (ኤር. 9:25, 26) ይሖዋ “የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ” ሲል ማሳሰቢያ መስጠቱን አስታውስ።—ኤር. 4:4

አምላክን “የሚያውቅ ልብ” ማግኘትና ላለማጣት መጠንቀቅ

17. ይሖዋን መፍራታችን ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ልብ እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?

17 ምሳሌያዊ ልብህን ስትመረምር ልብህ ይሖዋ ለሚሰጠው ምክር የሚገባውን ያህል ፈጣን ምላሽ እንደማይሰጥና በበቂ ሁኔታ ‘እንዳልተገረዘ’ ታስተውል ይሆናል። ምናልባትም ሰውን እንደምትፈራ፣ ዝና ወይም የተንደላቀቀ ኑሮ እንደምትመኝ አልፎ ተርፎም በተወሰነ ደረጃ የእልኸኝነት ወይም በራስ የመመራት መንፈስ እንዳለህ ትገነዘብ ይሆናል። እንዲህ ያለ ችግር የነበረባቸው ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። (ኤር. 7:24፤ 11:8) ኤርምያስ በዘመኑ የነበሩት ታማኝ ያልሆኑ አይሁዳውያን “የሸፈተና እልከኛ ልብ” እንደነበራቸው ጽፏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በልባቸውም፣ ‘የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚያዘንበውን . . . አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ’ አላሉም።” (ኤር. 5:23, 24) ይህ ሐሳብ ይሖዋን እጅግ መፍራታችንና ለእሱ የአድናቆት ስሜት ማዳበራችን ‘የልባችንን ሸለፈት’ ለማስወገድ እንደሚረዳን አያሳይም? እያንዳንዳችን እንዲህ ያለ ጤናማ ፍርሃት ማዳበራችን አምላክ ለሚፈልግብን ነገር ልባችን ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ይረዳዋል።

18. ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ለታቀፉት ምን ቃል ገብቷል?

18 እንዲህ ያለ ጥረት ስናደርግ ይሖዋ እሱን “የሚያውቅ ልብ” ይሰጠናል። እንዲያውም በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለታቀፉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” በተጨማሪም እሱን በሚገባ ማወቅን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤ . . . በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።”—ኤር. 31:31-34 *

19. እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ግሩም ተስፋ አላቸው?

19 በሰማይ ወይም በምድር ከዚህ አዲስ ቃል ኪዳን ዘላለማዊ ጥቅም ለማግኘት በተስፋ የምትጠባበቅ ከሆነ ይሖዋን ለማወቅና ከሕዝቦቹ እንደ አንዱ ለመቆጠር ልባዊ ፍላጎት ሊያድርብህ ይገባል። እንዲህ ያለ ጥቅም ማግኘት የምትችለው በክርስቶስ ቤዛ መሠረት ኃጢአትህ ይቅር ከተባለ ብቻ ነው። ኃጢአትህ ይቅር ሊባልልህ እንደሚችል ማወቅህ በጣም ያበሳጩህን ሰዎች ጨምሮ ሌሎችን ይቅር እንድትል ሊያነሳሳህ ይገባል። ለሌሎች ሰዎች ያለህን ማንኛውም መጥፎ ስሜት ከውስጥህ ለማስወገድ ጥረት ማድረግህ ለልብህ ጤንነት ጠቃሚ ነው። ይህን ማድረግህ ይሖዋን ለማገልገል እንደምትፈልግ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እሱን እንዳወቅከው ያሳያል። ደግሞም ይሖዋ በኤርምያስ በኩል፣ “እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤ እኔም እገኝላችኋለሁ” በማለት እንደተናገረላቸው ዓይነት ሰዎች ትሆናለህ።—ኤር. 29:13, 14

^ စာပိုဒ်၊ 18 አዲሱን ቃል ኪዳን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የጥር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-30 ተመልከት።