በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የአምላክን ክብር እንዳታገኙ ምንም ነገር እንቅፋት አይሁንባችሁ

የአምላክን ክብር እንዳታገኙ ምንም ነገር እንቅፋት አይሁንባችሁ

“ትሑት መንፈስ ያለው . . . ክብርን ይጐናጸፋል።”—ምሳሌ 29:23

1, 2. (ሀ) “ክብር” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

“ክብር” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ክብር የተላበሱት የፍጥረት ሥራዎች? (መዝ. 19:1) ወይስ የላቀ ሀብት ላላቸው እንዲሁም በእውቀታቸውና ባከናወኑት ሥራ አንቱ ለተባሉ ሰዎች የሚሰጠው ክብር እና ውዳሴ? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ክብር” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት ክብደት የሚለውን ሐሳብ ያስተላልፋሉ። በጥንት ዘመን ገንዘብ የሚሠራው ውድ ከሆኑ ማዕድናት በመሆኑ አንድ ሳንቲም ክብደቱ በጨመረ መጠን የሚኖረው ዋጋም ያንኑ ያህል ከፍ ይል ነበር። ክብደት የሚለውን ሐሳብ የሚያስተላልፉ ቃላት እንደ ውድ ተደርገው የሚታዩ፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ወይም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን ለማመልከት የተሠራባቸው ለዚህ ነው።

2 ኃያል የሆኑ፣ ትልቅ ቦታ ያላቸው ወይም ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ከፍ ተደርገው ይታያሉ፤ ይሁንና አምላክ ሰዎችን ሲመለከት ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ ለሰው ልጆች ክብር የሚሰጠው ምንን በመመልከት እንደሆነ ይናገራሉ። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 22:4 “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” ይላል። እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በይሖዋ ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 4:10) ይሖዋ ለሰው ልጆች የሚሰጠው ክብር ምንድን ነው? ይህን ክብር እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ምንድን ነው? ደግሞስ ሌሎች ይህን ክብር እንዲያገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

3-5. ይሖዋ ክብር የሚያጎናጽፈን እንዴት ነው?

3 መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ቀኝ እጁን ይዞ እንደሚመራውና ወደ ክብር እንደሚያስገባው ያለውን እምነት ገልጿል። (መዝሙር 73:23, 24ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ወደ ክብር የሚያስገባቸው በተለያዩ መንገዶች ነው። ፈቃዱን እንዲገነዘቡ በማድረግ ይባርካቸዋል። (1 ቆሮ. 2:7) እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙና እሱን የሚታዘዙ ሰዎችን ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመፍቀድ ያከብራቸዋል።—ያዕ. 4:8

4 ከዚህም ሌላ ይሖዋ፣ እጅግ ውድ ሀብት የሆነውን ክርስቲያናዊ  አገልግሎት ለአገልጋዮቹ በአደራ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 4:1, 7) ይህ አገልግሎት ደግሞ ክብር እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ፣ በዚህ የአገልግሎት መብት ተጠቅመው እሱን ለሚያወድሱና ሌሎችን ለሚረዱ ሁሉ “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” የሚል ቃል ገብቷል። (1 ሳሙ. 2:30) እንዲህ ያሉ ሰዎች በይሖዋም ሆነ በሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ ጥሩ ስም ስለሚያተርፉ ክብር ያገኛሉ።—ምሳሌ 11:16፤ 22:1

5 ‘ይሖዋን ደጅ የሚጠኑና መንገዱን የሚጠብቁ’ ሰዎች ወደፊት ምን ያገኛሉ? እነዚህ ሰዎች “ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ [ይሖዋ] ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚል ቃል ተገብቶላቸዋል። (መዝ. 37:34) እነዚህ ሰዎች የዘላለም ሕይወት በማግኘት ወደር የሌለው ክብር የመጎናጸፍ ተስፋ አላቸው።—መዝ. 37:29

“ከሰው ክብር አልቀበልም”

6, 7. ብዙዎች በኢየሱስ ለማመን ፈቃደኞች ያልሆኑት ለምን ነበር?

6 ይሖዋ የሚሰጠንን ክብር እንዳንጎናጸፍ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ምንድን ነው? እንቅፋት ከሚሆኑብን ነገሮች አንዱ በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም የሌላቸው ሰዎች ላላቸው አመለካከት ከፍ ያለ ቦታ መስጠት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በኢየሱስ ዘመን ከፍተኛ ቦታ የነበራቸውን ሰዎች አስመልክቶ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት፦ “ከገዥዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች [በኢየሱስ] አመኑ፤ ነገር ግን ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያስወጧቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር፤ ይህም የሆነው ከሰው የሚገኘውን ክብር ከአምላክ ከሚገኘው ክብር እንኳ ሳይቀር አስበልጠው ስለወደዱ ነው።” (ዮሐ. 12:42, 43) እነዚህ ገዥዎች ለፈሪሳውያን አመለካከት ያን ያህል ትልቅ ቦታ ባይሰጡ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር!

7 ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ፣ ብዙዎች እሱን የማይቀበሉትና በእሱ የማያምኑት ለምን እንደሆነ በግልጽ ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 5:39-44ን አንብብ።) የእስራኤል ብሔር ለበርካታ መቶ ዓመታት የመሲሑን መምጣት ሲጠባበቅ ቆይቷል። ኢየሱስ ማስተማር በጀመረበት ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች፣ ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜ እንደደረሰ ከዳንኤል ትንቢት አስተውለው መሆን አለበት። ኢየሱስ ማስተማር ከመጀመሩ ከጥቂት ወራት በፊት ብዙዎች አጥማቂው ዮሐንስ ሲሰብክ ሲመለከቱ “ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን?” ብለው አስበው ነበር። (ሉቃስ 3:15) ብዙም ሳይቆይ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ በመካከላቸው መስበክ ጀመረ። ይሁንና ሕጉን እናውቃለን የሚሉት ሰዎች ሊቀበሉት ፈቃደኞች አልሆኑም። ኢየሱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲጠቁም “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡና ከአንዱ አምላክ የሚገኘውን ክብር የማትፈልጉ ሆናችሁ ሳላችሁ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” ብሏቸዋል።

8, 9. ብርሃንን እንደ ምሳሌ በመጠቀም፣ ከሰዎች ክብር ለማግኘት መፈለግ መለኮታዊ ክብር እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው እንዴት እንደሆነ አስረዳ።

8 ከሰዎች ለሚገኘው ክብር ትልቅ ቦታ መስጠት ለመለኮታዊው ክብር ትኩረት እንዳንሰጥ የሚያደርገን እንዴት እንደሆነ በምሳሌ ለማስረዳት ክብርን ከብርሃን ጋር እያነጻጸርን እንመልከት። አስደናቂ የሆነው አጽናፈ ዓለም በተለያዩ የብርሃን አካላት የተሞላ ነው። ደመና በሌለበት ምሽት በሺህዎች በሚቆጠሩ ከዋክብት ያሸበረቀውን ሰማይ ተመልክተህ ታውቃለህ? ከሆነ እጅግ በሚያስደንቀው “የከዋክብት ክብር” ተደምመህ መሆን አለበት። (1 ቆሮ. 15:40, 41) ይሁንና ደማቅ በሆኑ መብራቶች በተንቆጠቆጠች ከተማ ውስጥ ሆነህ ወደ ሰማይ አሻቅበህ ብትመለከት ተመሳሳይ ነገር ማየት የምትችል ይመስልሃል? በከተማዋ ውስጥ ያሉት መብራቶች ድምቀት በርቀት ያሉትን ከዋክብት ብርሃን ማየት አስቸጋሪ እንዲሆንብን ያደርጋል። ይህ የሆነው በመንገድ ላይ፣ በስታዲየሞች እንዲሁም በሕንፃዎች ውስጥ የሚበሩት መብራቶች ከዋክብት ከሚፈነጥቁት ብርሃን የበለጠ ኃይል ወይም ውበት ስላላቸው ነው? በፍጹም አይደለም! ከዚህ ይልቅ ከከዋክብቱ ብርሃን ይልቅ ከተማዋ ውስጥ ያሉት መብራቶች ለእኛ ቅርብ መሆናቸው እነዚህን የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ጥርት ባለ መንገድ እንዳንመለከት ስለሚያግደን ነው። በመሆኑም ምሽት ላይ ሰማዩ የሚኖረውን ግርማ ለመመልከት ሰው ሠራሽ ከሆኑ መብራቶች መራቅ ይኖርብናል።

9 በተመሳሳይም ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ከሰዎች ለምናገኘው ክብር ከሆነ ይሖዋ የሚሰጠንን ዘላለማዊ ክብር እንዳናደንቅና እንዳንፈልግ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ብዙዎች፣ ጓደኞቼ ወይም ዘመዶቼ ምን ይሉኛል ብለው ስለሚፈሩ የመንግሥቱን መልእክት  ለመቀበል ፈቃደኞች አይሆኑም። ይሁንና ከሰዎች ክብር ለማግኘት መፈለግ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖችንም ሊነካ ይችላል? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት ብዙ የሚያውቁት ሰዎች ባሉበት አካባቢ እንዲያገለግል ተመደበ እንበል፤ ይሁን እንጂ ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ አያውቁም። ፍርሃት በዚህ አካባቢ ከመስበክ ወደኋላ እንዲል ያደርገው ይሆን? ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፦ አንድ ወንድም መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ሌሎች ሰዎች ቢያሾፉበትስ? ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታ የሌላቸው ሰዎች በሕይወቱ ውስጥ በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርጉ ይፈቅድ ይሆን? ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ክርስቲያንን ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። በጉባኤ ውስጥ ያለውን ቦታ ላለማጣት ወይም የሚወዳቸው ሰዎች እንዳያዝኑበት በማሰብ ኃጢአቱን ይደብቅ ይሆን? ይህ ክርስቲያን በዋነኝነት የሚያሳስበው ከይሖዋ ጋር ያለውን ግንኙነት ማስተካከሉ ከሆነ “የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ [ጠርቶ]” እንዲረዱት ይጠይቃቸዋል።—ያዕቆብ 5:14-16ን አንብብ።

10. (ሀ) ሌሎች ስለ እኛ የሚኖራቸው አመለካከት ከመጠን በላይ የሚያሳስበን ከሆነ ምን ሊፈጠር ይችላል? (ለ) ትሑት ከሆንን ምን እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

10 በሌላ በኩል ደግሞ በመንፈሳዊ ጥሩ እድገት ለማድረግ ጠንክረን እየሠራን እንደሆነ ቢሰማንም አንድ የእምነት ባልንጀራችን ምክር ይሰጠን ይሆናል። ኩራትና ክብሬ ተነካ የሚል ስሜት ካለን አሊያም ለድርጊታችን ሰበብ መፍጠር የሚቃጣን ከሆነ ወንድማችን በሐቀኝነት ከሰጠን ምክር ጥቅም ማግኘት አንችልም። ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንውሰድ፦ ከእምነት ባልንጀራህ ጋር በጋራ አንድ ሥራ እንድታከናውን ተመደብክ እንበል። አንተ ባመነጨሃቸው ጥሩ ሐሳቦች ወይም በትጋት ባከናወንኸው ሥራ ሌላው መመስገኑ ስለሚያሳስብህ ከእሱ ጋር ተባብረህ ከመሥራት ወደኋላ ትላለህ? እንደዚህ ዓይነት አዝማሚያ እንዳለህ ካስተዋልክ “ትሑት መንፈስ ያለው . . . ክብርን ይጐናጸፋል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወስህ ይጠቅምሃል።—ምሳሌ 29:23

11. ሌሎች ሲያደንቁን ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

11 የበላይ ተመልካቾችና እዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለመድረስ ‘የሚጣጣሩ’ ወንዶችም ከሰዎች ክብር የመፈለግ ዝንባሌ እንዳያድርባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞ. 3:1፤ 1 ተሰ. 2:6) አንድ ወንድም ላከናወነው መልካም ሥራ ሌሎች ሲያመሰግኑት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርበታል? በእርግጥ እንደ ንጉሥ ሳኦል ለራሱ የመታሰቢያ ሐውልት አያቆም ይሆናል። (1 ሳሙ. 15:12) ያም ቢሆን ሥራውን በተሳካ መንገድ ማከናወን የቻለው ይሖዋ በጸጋው ስለባረከው እንደሆነ እንዲሁም ወደፊትም ቢሆን በሚያከናውናቸው ነገሮች ስኬታማ መሆን የሚችለው ጥረቱን አምላክ ከባረከለትና ከረዳው ብቻ እንደሆነ ይገነዘባል? (1 ጴጥ. 4:11) ሌሎች ሲያደንቁን የሚኖረን ስሜት የምንፈልገው የማንን ክብር እንደሆነ ያሳያል።—ምሳሌ 27:21

“የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ”

12. አንዳንድ አይሁዳውያን ኢየሱስን እንዳይሰሙ እንቅፋት የሆነባቸው ምንድን ነው?

12 የአምላክን ክብር እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ሌላው ነገር ደግሞ በውስጣችን ያለ የተሳሳተ ፍላጎት ነው። እንዲህ ያለው ፍላጎት እውነትን ጨርሶ እንዳንሰማ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (ዮሐንስ 8:43-47ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ አንዳንድ አይሁዳውያን የእሱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑት ‘የአባታቸውን [የዲያብሎስን] ፍላጎት ለመፈጸም ስለሚሹ’ እንደሆነ ተናግሯል።

13, 14. (ሀ) የተለያዩ ሰዎች በአንድ ጊዜ ሲያናግሩን አእምሯችን ስለሚሠራበት መንገድ ተመራማሪዎች ምን ይላሉ? (ለ) የምናዳምጠው ማንን እንደሆነ የሚወስነው ምንድን ነው?

13 አንዳንድ ጊዜ፣ የምንሰማው መስማት የምንፈልገውን ብቻ ነው። (2 ጴጥ. 3:5) ይሖዋ የፈጠረን አእምሯችን አንዳንድ የማይፈለጉ ድምፆችን አጣርቶ የማስቀረት አስደናቂ ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ነው። እስቲ ለአንድ አፍታ ሐሳብህን ሰብሰብ አድርገህ ምን ያህል የተለያዩ ድምፆችን መስማት እንደምትችል ለማስተዋል ሞክር። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እነዚህ ድምፆች መኖራቸውን አላስተዋልክ ይሆናል። እነዚያን ሁሉ ድምፆች መስማት ብንችልም አእምሯችን ድምፆቹን ልብ እንዳንላቸው በማድረግ አንድ ነገር ላይ ብቻ እንድናተኩር ይረዳናል። ይሁንና በአንድ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች የሚናገሩ ከሆነ እያንዳንዳቸውን እኩል ማዳመጥ ይበልጥ ከባድ እንደሚሆንብን ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ይህም ሲባል ሁለት ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ቢያናግሩህ ለየትኛው ትኩረት እንደምትሰጥ መወሰን ይኖርብሃል ማለት ነው።  ምርጫህ የተመካው ማንን መስማት ትፈልጋለህ በሚለው ላይ ነው። አይሁዳውያኑ ኢየሱስን ያልሰሙት የአባታቸውን ማለትም የዲያብሎስን ፍላጎት መፈጸም ይፈልጉ ስለነበር ነው።

14 መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ” እና “ጥበብ የለሽ ሴት” እንደሚያናግሩን የሚገልጽ ምሳሌያዊ ሐሳብ ይዟል። (ምሳሌ 9:1-5, 13-17) ጥበብም ሆነ ጥበብ የለሽ ሴት ግብዣ እያቀረቡልን በመሆኑ የማንኛቸውን ድምፅ እንደምንሰማ መምረጥ አለብን። ታዲያ ለመስማት የምንመርጠው የማንን ድምፅ ነው? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ የማንን ፈቃድ ለማድረግ እንደምንፈልግ ያሳያል። የኢየሱስ በጎች የእሱን ድምፅ በመስማት ይከተሉታል። (ዮሐ. 10:16, 27) በጎቹ ‘የቆሙት ከእውነት ጎን ነው።’ (ዮሐ. 18:37) እንዲሁም “የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።” (ዮሐ. 10:5) እንዲህ ያሉት ትሑት ሰዎች ክብር ያገኛሉ።—ምሳሌ 3:13, 16፤ 8:1, 18

“ይህ ለእናንተ ክብር ነው”

15. ጳውሎስ የደረሰበት መከራ ለሌሎች “ክብር” የሆነው በምን መንገድ ነው?

15 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ስንል ፈተናዎችን በጽናት መቋቋማችን ሌሎች አምላክ የሚሰጠውን ክብር እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ለእናንተ ስል እየደረሰብኝ ባለው መከራ የተነሳ ተስፋ እንዳትቆርጡ አደራ እላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ይህ ለእናንተ ክብር ነው።” (ኤፌ. 3:13) ጳውሎስ የደረሰበት መከራ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች “ክብር” የሆነው በምን መንገድ ነው? ጳውሎስ መከራዎች ቢደርሱበትም እነሱን ለማገልገል ሲል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑ የኤፌሶን ወንድሞች፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ያገኟቸው መብቶች ምን ያህል ውድና የላቁ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ጳውሎስ መከራ ሲደርስበት ወደኋላ ቢል ኖሮ በኤፌሶን የሚገኙት ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና፣ አገልግሎታቸው እንዲሁም ተስፋቸው ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችል ነበር። ጳውሎስ በጽናት ማገልገሉ ክርስትና እንዲከበር ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የትኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነገር እንደሆነ አሳይቷል።

16. ጳውሎስ በልስጥራ ምን መከራ አጋጠመው?

16 የጳውሎስ ቅንዓትና ጽናት በሌሎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማሰብ ሞክር። የሐዋርያት ሥራ 14:19, 20 እንዲህ ይላል፦ “አይሁዳውያን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጎትተው ከከተማዋ [ከልስጥራ] አወጡት። ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በከበቡት ጊዜ ግን ተነስቶ ወደ ከተማይቱ ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ።” ሞቷል ተብሎ ለታሰበ ሰው በማግስቱ 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ ያውም ዛሬ ያሉት ዘመናዊ መጓጓዣዎች በሌሉበት ወቅት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንበት አስበው!

17, 18. (ሀ) ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ በልስጥራ ስላጋጠመው መከራ ሊያውቅ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የጳውሎስ ጽናት በጢሞቴዎስ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?

17 ጳውሎስ በልስጥራ መከራ በደረሰበት ወቅት ከረዱት ‘ደቀ መዛሙርት’ መካከል ጢሞቴዎስ ይኖር ይሆን? በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ ይህን በግልጽ ባይናገርም ጢሞቴዎስ በቦታው  ኖሮ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት፦ “አንተ ግን ትምህርቴን፣ አኗኗሬን . . . በጥብቅ ተከትለሃል፤ በተጨማሪም የደረሰብኝን ስደትና መከራ፣ በአንጾኪያ [ከከተማው ተባርሯል]፣ በኢቆንዮንና [በድንጋይ ሊወግሩት ሞክረዋል] በልስጥራ [በድንጋይ ተወግሯል] ያጋጠሙኝን ነገሮች እንዲሁም ችዬ ያሳለፍኩትን መከራ ሁሉ ታውቃለህ፤ ይሁንና ጌታ ከእነዚህ ሁሉ አዳነኝ።”—2 ጢሞ. 3:10, 11፤ ሥራ 13:50፤ 14:5, 19

18 ጢሞቴዎስ ስለ እነዚህ ሁኔታዎች እንዲሁም ስለ ጳውሎስ ጽናት በደንብ ያውቅ ነበር። ጢሞቴዎስ የተመለከተው ነገር በጥልቅ ነክቶት መሆን አለበት። ጳውሎስ ልስጥራን ሲጎበኝ ጢሞቴዎስ “በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች ዘንድ በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን ሆኖ ነበር። (ሥራ 16:1, 2) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጢሞቴዎስ ከባድ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ ሆኗል።—ፊልጵ. 2:19, 20፤ 1 ጢሞ. 1:3

19. የእኛ መጽናት በሌሎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

19 የአምላክን ፈቃድ ስናደርግ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት መወጣታችን በሌሎች በተለይም በወጣቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፤ እነዚህ ወጣቶች ሲያድጉ በአምላክ አገልግሎት እጅግ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ወጣት ደቀ መዛሙርት፣ በአገልግሎት ሰዎችን ስናስተምር የምንጠቀምባቸውን ግሩም ዘዴዎች ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች የምንወጣበትን መንገድ በማየትም ከእኛ ይማራሉ። ጳውሎስ “ሁሉንም ነገር በጽናት [ተቋቁሞ]” የኖረው ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች “መዳን ከዘላለማዊ ክብር ጋር ያገኙ ዘንድ” እንደሆነ ተናግሯል።—2 ጢሞ. 2:10

ወጣቶች፣ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ከሚተዉት የጽናት ምሳሌ ብዙ ጥቅም ያገኛሉ

20. ከአምላክ የሚገኘውን ክብር መፈለጋችንን መቀጠል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

20 ታዲያ እስካሁን ካየነው አንጻር፣ “ከአንዱ አምላክ የሚገኘውን ክብር” መፈለጋችንን መቀጠል አይኖርብንም? (ዮሐ. 5:44፤ 7:18) በእርግጥም ይህን ለማድረግ የምንችለውን ያህል መጣር ይኖርብናል። (ሮም 2:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ “ክብርን፣ . . . ለሚፈልጉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።” በተጨማሪም “በመልካም ሥራ በመጽናት” ሌሎች በታማኝነት እንዲቀጥሉ የምናበረታታቸው ሲሆን ይህም ዘላለማዊ በረከት እንዲያጭዱ ያስችላቸዋል። እንግዲያው የአምላክን ክብር እንዳታገኙ ምንም ነገር እንቅፋት አይሁንባችሁ!