‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው።’—ኢያሱ 1:9 NW

1, 2. (ሀ) መከራዎችን ለመቋቋም የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? (ለ) እምነትን እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ? በምሳሌ አስረዳ።

ይሖዋን ማገልገል ደስታ ያስገኝልናል። ያም ሆኖ ማንኛውም ሰው እንደሚያጋጥመው ችግር ይደርስብናል፤ እንዲሁም ‘ለጽድቅ ስንል መከራ ልንቀበል’ እንችላለን። (1 ጴጥ. 3:14፤ 5:8, 9፤ 1 ቆሮ. 10:13) በመሆኑም እንዲህ ያሉ መከራዎችን ለመቋቋም እምነትና ድፍረት ያስፈልገናል።

2 ለመሆኑ እምነት ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ሲሆን እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” (ዕብ. 11:1) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮች እንደሚገኙ ዋስትና የሚሰጥ የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ነው። እምነት የማናያቸው ነገሮች እውን መሆናቸውን እርግጠኛ የምንሆንበት ነው” ይላል። (ዘ ሲምፕል ኢንግሊሽ ባይብል) አንድ ንብረት የእኛ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ከተሰጠን ንብረቱ በእጃችን እንደሚገባ የምንጠራጠርበት ምክንያት የለም። አምላክ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚፈጽም እምነት ስላለን የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ የያዝን ያህል ነው። በይሖዋ ላይ ያለን እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ እንደምንመለከት እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል፤ በተጨማሪም የማናያቸውን ነገሮች ጨምሮ በቃሉ አማካኝነት የነገረን ነገሮች በሙሉ እውነት እንደሆኑ አንጠራጠርም።

3, 4. (ሀ) ድፍረት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) እምነታችንን ለማጠናከርና ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ከሚረዱን መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

3 ድፍረት “አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ያለ ምንም ፍርሃት ለመናገርና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። (ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል) ደፋር ሰው ብርቱና ቆራጥ ሌላው ቀርቶ ምንም የማይፈራ ነው።—ማር. 6:49, 50፤ 2 ጢሞ. 1:7

4 እምነትና ድፍረት አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ናቸው። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ እምነታችንን መገንባትና ይበልጥ ደፋሮች መሆን  እንዳለብን ይሰማን ይሆናል። እነዚህን ባሕርያት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው የተመዘገበ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በመሆኑም እምነታችንን ለማጠናከርና ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ከሚረዱን መንገዶች አንዱ የእነዚህን ሰዎች ምሳሌ መመርመር ነው።

ይሖዋ ከኢያሱ ጋር ነበር

5. ኢያሱ ኃላፊነቱን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ምን ያስፈልገው ነበር?

5 እስቲ 3,500 ዓመታት ወደ ኋላ እንመለስ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በይሖዋ ብርቱ እጅ አማካኝነት ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ አርባ ዓመታት አልፈዋል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሕዝቡን ሲመራ የቆየው ነቢዩ ሙሴ ነበር። የ120 ዓመት ሰው የሆነው ሙሴ ተስፋይቱን ምድር ከርቀት ከተመለከተ በኋላ በናባው ተራራ ጫፍ ላይ ሕይወቱ አለፈ። ከዚያም ‘የጥበብ መንፈስ የተሞላው’ ኢያሱ እሱን ተካው። (ዘዳ. 34:1-9) በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ለመውረስ ተቃርበው ነበር። ኢያሱ ሕዝቡን የመምራት ኃላፊነቱን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት አምላካዊ ጥበብ ያስፈልገዋል። በተጨማሪም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ማሳየት ብሎም ደፋርና ጠንካራ መሆን ይኖርበታል።—ዘዳ. 31:22, 23

6. (ሀ) ኢያሱ 23:6 እንደሚጠቁመው ድፍረት ማሳየት የሚኖርብን መቼ ነው? (ለ) ከሐዋርያት ሥራ 4:18-20 እና ሥራ 5:29 ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 እስራኤላውያን ከነዓናውያንን ድል ለማድረግ በርካታ ዓመታት የፈጀ ውጊያ ባካሄዱበት ወቅት ኢያሱ ያሳየው ጥበብ፣ ድፍረትና እምነት ሕዝቡን አበረታቷቸው መሆን አለበት። እስራኤላውያን በጦርነቱ ለመካፈል ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ለመታዘዝም ድፍረት ያስፈልጋቸው ነበር። ኢያሱ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ እንዲህ የሚል የስንብት ቃል ተናግሮ ነበር፦ “ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ [“ደፋሮችና ቆራጦች መሆን አለባችሁ፣” NW]።” (ኢያሱ 23:6) እኛም ብንሆን ምንጊዜም ይሖዋን ለመታዘዝ ድፍረት ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ ሰዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጻረር ነገር እንድናደርግ በሚጠይቁን ጊዜም ድፍረት ማሳየትን ይጨምራል። (የሐዋርያት ሥራ 4:18-20ን እና ሥራ 5:29ን አንብብ።) ወደ ይሖዋ በመጸለይ በእሱ እንደምንታመን የምናሳይ ከሆነ እንዲህ ያለውን የድፍረት እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል።

መንገዳችን የተቃና እንዲሆን ማድረግ

7. ኢያሱ ደፋር እንዲሆንና መንገዱ እንዲቃናለት ምን ማድረግ አስፈልጎታል?

7 የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት እንዲኖረን ከፈለግን ቃሉን ማጥናትና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ኢያሱ ሙሴን በተካበት ወቅት እንዲህ እንዲያደርግ ተነግሮት ነበር፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አገልጋዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። . . . ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት እያነበብክ አሰላስል፤ እንዲህ ካደረክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።” (ኢያሱ 1:7, 8 NW) ኢያሱ ይህን ምክር ስለተከተለ ‘መንገዱ የተቃና’ ሆኖለታል። እኛም እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይበልጥ ደፋሮች ስለምንሆን በአምላክ አገልግሎት መንገዳችን የተቃና ይሆናል።

የ2013 የዓመት ጥቅሳችን፦ ‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው።’—ኢያሱ 1:9 NW

8. የ2013 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ አንተን ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

8 ኢያሱ ይሖዋ ቀጥሎ የነገረውን ሲሰማ በጣም ተበረታቶ መሆን አለበት፤ ‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ’ ብሎታል። (ኢያሱ 1:9 NW) ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው። በመሆኑም ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብን ‘መሸበር ወይም መፍራት’ አይገባንም። በተለይ ‘ደፋርና  ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው’ የሚለው አገላለጽ ትኩረት የሚስብ ነው። በኢያሱ 1:9 ላይ የሚገኘው ይህ ሐሳብ የ2013 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን ተመርጧል። የእምነትና የድፍረት ምሳሌ የሚሆኑን ሰዎች ከተናገሩትና ካደረጉት ነገር በተጨማሪ ይህ ጥቅስ በቀጣዮቹ ወራት እንደሚያበረታን ምንም ጥርጥር የለውም።

በድፍረት አቋም ወስደዋል

9. ረዓብ እምነትና ድፍረት ያሳየችው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

9 ጋለሞታይቱ ረዓብ፣ ኢያሱ ወደ ከነዓን የላካቸውን ሁለት ሰላዮች በመደበቅ ጠላቶቻቸውን በሌላ አቅጣጫ መራቻቸው። ረዓብ እምነትና ድፍረት በማሳየቷ እስራኤላውያን ኢያሪኮን ሲያጠፉ እሷና ቤተሰቧ ሊተርፉ ችለዋል። (ዕብ. 11:30, 31፤ ያዕ. 2:25) ረዓብ ይሖዋን ለማስደስት ስትል መጥፎ አኗኗሯን እንደተወች ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንዲህ ያለ ለውጥ በማድረግ አምላክን ለማስደሰት እምነት፣ ድፍረትና የሥነ ምግባር ጥንካሬ ማሳየት ጠይቆባቸዋል።

10. ሩት ከእውነተኛው አምልኮ ጎን የቆመችው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና ነው? ይህስ ምን በረከት አስገኝቶላታል?

10 ድፍረት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የምትሆነን ሌላዋ ሴት ኢያሱ ከሞተ በኋላ የኖረችው ሞዓባዊቷ ሩት ናት፤ ሩት የይሖዋን አምልኮ በድፍረት ደግፋለች። ባሏ እስራኤላዊ ስለነበር ስለ ይሖዋ የተወሰነ እውቀት እንደነበራት ግልጽ ነው። ይሁንና በሞዓብ ትኖር የነበረችው አማቿ ኑኃሚን ባሏንና ልጆቿን በሞት በማጣቷ የእስራኤል ከተማ ወደሆነችው ወደ ቤተልሔም ለመመለስ ተነሳች። ኑኃሚን በመንገድ ላይ ሳለች ወደ ወገኖቿ እንድትመለስ ሩትን ለመነቻት፤ ይሁንና ሞዓባዊቷ ሩት “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ . . . ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል” በማለት መለሰችላት። (ሩት 1:16) ሩት ይህን የተናገረችው ከልቧ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሩት የኑኃሚን የባል ዘመድ የሆነውን ቦዔዝን አገባች፤ ከዚያም ልጅ ወልዳ የዳዊትና የኢየሱስ ቅድመ አያት ለመሆን በቃች። በእርግጥም ይሖዋ እምነትና ድፍረት የሚያሳዩ ሰዎችን ይባርካል።—ሩት 2:12፤ 4:17-22፤ ማቴ. 1:1-6

ብዙዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል!

11. ዮዳሄና ዮሳቤት ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋቸውስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

11 አምላክ፣ ከራሳቸው ይልቅ የእሱን ፍላጎትና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ደኅንነት የሚያስቀድሙ ሰዎችን እንደሚደግፍ ማወቃችን እምነታችንን የሚገነባልን ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ደፋሮች እንድንሆን ያደርገናል። ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄንና ሚስቱ ዮሳቤትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ንጉሥ አካዝያስ ሲሞት እናቱ ጎቶልያ ከኢዮአስ በስተቀር የንጉሡን ልጆች በሙሉ በማጥፋት ዙፋኑን ወረሰች። ዮዳሄና ዮሳቤት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ለስድስት ዓመታት ሸሸጉት። በሰባተኛው ዓመት ላይ ዮዳሄ፣ ኢዮአስ መንገሡን አወጀ፤ እንዲሁም ጎቶልያን አስገደላት። (2 ነገ. 11:1-16) ከጊዜ በኋላም ዮዳሄ ቤተ መቅደሱን ለማደስ ከንጉሥ ኢዮአስ ጋር ተባብሯል። ዮዳሄ፣ ‘በእስራኤል ውስጥ ለአምላክና ለቤተ መቅደሱ መልካም ስለሠራ’ በ130 ዓመቱ ሲሞት የተቀበረው ከነገሥታቱ ጋር ነበር። (2 ዜና 24:15, 16) በተጨማሪም ዮዳሄና ሚስቱ የወሰዱት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ከዳዊት ወደ መሲሑ የሚሄደው የነገሥታት መስመር እንዲጠበቅ አድርጓል።

12. አቤሜሌክ ምን ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ወስዷል?

12 በንጉሥ ሴዴቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባለሥልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ለኤርምያስ ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ነበር። በአንድ ወቅት የይሁዳ መኳንንት ሕዝብን አሳምጿል በሚል ኤርምያስን በሐሰት ከስሰውት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ኤርምያስን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም እንዲሞት ጭቃ በተሞላ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። (ኤር. 38:4-6) በዚህ ጊዜ አቤሜሌክ ኤርምያስን ለመታደግ ንጉሡን ለመነ፤ ኤርምያስ በመኳንንቱ ዘንድ በጣም የተጠላ ከመሆኑ አንጻር አቤሜሌክ ይህን ማድረጉ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነበር። ሴዴቅያስም አቤሜሌክ የጠየቀውን ነገር የፈቀደለት ከመሆኑም በላይ ኤርምያስን ለማዳን 30 ሰዎች ይዞ እንዲሄድ ነገረው። በመሆኑም ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ሲያጠፉ እሱ በሕይወት እንደሚተርፍ ይሖዋ በነቢዩ  ኤርምያስ አማካኝነት ቃል ገባለት። (ኤር. 39:15-18) በእርግጥም አምላካዊ ድፍረት ማሳየት የሚክስ ነው።

13. ሦስቱ ዕብራውያን ምን ዓይነት የድፍረት እርምጃ ወስደዋል? ከእነሱ ታሪክስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖሩትና የአምላክ አገልጋይ የሆኑት የሦስቱ ዕብራውያን ታሪክ ይሖዋ እምነትና ድፍረት የሚያሳዩ ሰዎችን እንደሚክስ በግልጽ ያሳያል። ንጉሥ ናቡከደነፆር የባቢሎንን ባለሥልጣናት በሙሉ በመሰብሰብ እሱ ላቆመው የወርቅ ምስል እንዲሰግዱ አዘዛቸው። በወቅቱ፣ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ወደ እቶን እሳት እንደሚጣል ተናግሮ ነበር። ሦስቱ ዕብራውያን ለናቡከደነፆር በአክብሮት እንዲህ አሉት፦ “በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” (ዳን. 3:16-18) ዳንኤል 3:19-30 እነዚህ ሦስት ዕብራውያን እንዴት አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደዳኑ ይገልጻል። እርግጥ ነው፣ በእቶን እሳት ውስጥ አንጣል ይሆናል። ይሁንና ንጹሕ አቋማችንን የሚፈትን ነገር ያጋጥመናል፤ በዚህ ጊዜ እምነትና ድፍረት የምናሳይ ከሆነ አምላክ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

14. ዳንኤል ምዕራፍ 6 ላይ እንደምናነበው ዳንኤል ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?

14 ዳንኤልም ቢሆን እምነትና ድፍረት አሳይቷል። ጠላቶቹ፣ ዳርዮስ ‘ወደ እሱ ካልሆነ በቀር ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ የሚጸልይ ማንም ሰው በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንዲጣል’ የሚያዝዝ አዋጅ እንዲያወጣ አግባቡት። ዳንኤል “ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ።” (ዳን. 6:6-10) ደፋር የሆነው ዳንኤል በዚህ ምክንያት ወደ አንበሶች ጉድጓድ ቢጣልም ይሖዋ አድኖታል።—ዳን. 6:16-23

15. (ሀ) አቂላና ጵርስቅላ እምነትና ድፍረት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትተዋል? (ለ) ዮሐንስ 13:34 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ትእዛዝ ምን ትርጉም አለው? በርካታ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ፍቅር ያሳዩትስ እንዴት ነው?

15 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁኔታው በዝርዝር ባይገለጽም አቂላና ጵርስቅላ ለጳውሎስ ‘ነፍስ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል።’ (ሥራ 18:2፤ ሮም 16:3, 4) የሚከተለውን የኢየሱስን ትእዛዝ በድፍረት ተግባራዊ አድርገዋል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።” (ዮሐ. 13:34) የሙሴ ሕግ አንድ ሰው ባልንጀራውን እንደ ራሱ እንዲወድድ ያዝዝ ነበር። (ዘሌ. 19:18) ኢየሱስ የሰጠው ትእዛዝ ግን እሱ እንዳደረገው ለሌላ ሰው ሲሉ ሕይወትን እስከመስጠት የሚያደርስ ፍቅር ማሳየትን ስለሚያካትት  “አዲስ” ነው ሊባል ይችላል። በርካታ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸው በጠላቶቻቸው እጅ አደጋ እንዳይደርስባቸው ወይም እንዳይገደሉ ሲሉ በድፍረት ‘ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ’ ፍቅር አሳይተዋል።—1 ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ አልነበሩም

16, 17. አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ምን የእምነት ፈተና አጋጥሟቸዋል? በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችስ ምን ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟቸዋል?

16 እንደ ኢየሱስ ሁሉ የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ለይሖዋ ብቻ አምልኮ በማቅረብ ድፍረት አሳይተዋል። (ማቴ. 4:8-10) ለሮም ንጉሠ ነገሥት ክብር ሲባል በሚደረገው የዕጣን ማጠን ሥርዓት ላይ ለመካፈል ፈቃደኞች አልነበሩም። (ሥዕሉን ተመልከት።) ዳንኤል ማኒክስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “እሳት የሚነድበት መሠዊያ፣ በትርዒት ማሳያው ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ለክርስቲያኖቹ በሚያመች ቦታ ላይ ቢደረግም አቋማቸውን ያላሉት ክርስቲያኖች በጣም ጥቂት ነበሩ። አንድ እስረኛ የሚጠበቅበት ጥቂት ዕጣን በእጁ ቆንጥሮ በእሳቱ ላይ መበተን ብቻ ነበር፤ ይህን ካደረገ መሥዋዕት ስለማቅረቡ የምሥክር ወረቀት ይሰጠውና ነፃ ይለቀቅ ነበር። በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱን ማምለኩ እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ ንጉሠ ነገሥቱ የሮም ብሔር መሪ እንደመሆኑ መጠን መለኮታዊነቱን መቀበሉን ለማመልከት ብቻ እንደሆነ ሊያሳምኑት ይሞክሩ ነበር። ያም ቢሆን በዚህ መንገድ ነፃ ለመውጣት የሞከረ ክርስቲያን አልነበረም ለማለት ይቻላል።”—ዞስ አባውት ቱ ዳይ

17 በዘመናችንም ቢሆን የሞት ቅጣት ተደቅኖባቸው የነበሩ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የታሰሩ በርካታ ክርስቲያኖች ይሖዋን መካዳቸውን በሚገልጸው ሰነድ ላይ ከፈረሙ ነፃ እንደሚለቀቁ በተደጋጋሚ ተገልጾላቸው ነበር። በዚህ ወቅት እንዲህ ያደረጉት በጣም ጥቂት ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በሩዋንዳ በተደረገው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ወቅት ቱትሲና ሁቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል አንዳቸው ሌላውን ጠብቀዋል። በእርግጥም እንዲህ ያሉ መከራዎችን በጽናት መወጣት እምነትና ድፍረት ይጠይቃል።

ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነ አስታውሱ!

18, 19. በስብከቱ ሥራችን ለመቀጠል የሚያስችለንን እምነትና ድፍረት እንድናገኝ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

18 በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ታላቅ ሥራ ይኸውም የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ኢየሱስ በዚህ ረገድ ወደር የማይገኝለት ምሳሌያችን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር።” (ሉቃስ 8:1) እኛም እንደ እሱ የመንግሥቱን መልእክት ለመስበክ እምነትና ድፍረት ያስፈልገናል። ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በተደቀነበትና “ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም” ውስጥ ደፋር “የጽድቅ ሰባኪ” እንደነበረው እንደ ኖኅ ሁሉ እኛም በአምላክ እርዳታ ደፋሮች መሆን እንችላለን።—2 ጴጥ. 2:4, 5

19 ጸሎት በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል ይረዳናል። በስደት ላይ ያሉ አንዳንድ የክርስቶስ ተከታዮች “የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር” እንዲችሉ ያቀረቡት ጸሎት ምላሽ አግኝቷል። (የሐዋርያት ሥራ 4:29-31ን አንብብ።) ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የሚያስፈራህ ከሆነ ይሖዋ እምነትና ድፍረት እንዲሰጥህ ጠይቀው፤ እሱም ጸሎትህን ይሰማል።—መዝሙር 66:19, 20ን አንብብ። *

20. የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ምን እርዳታ አለልን?

20 በዚህ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ችግሮች ሲጋረጡብን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ተፈታታኝ ነው። ያም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም። አምላክ ከእኛ ጋር ነው። የጉባኤው ራስ የሆነው ልጁ ኢየሱስም ከእኛ ጋር ነው። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ከ7,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉልን። ከእነሱ ጋር በመሆን እምነት ማሳየታችንንና ምሥራቹን ማወጃችንን እንቀጥል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው’ የሚለውን የ2013ን የዓመት ጥቅስ ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ኢያሱ 1:9 NW

^ စာပိုဒ်၊ 19 ተጨማሪ የድፍረት ምሳሌዎችን ለማግኘት በየካቲት 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ደፋርና ብርቱ ሁን” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።