በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ ማገልገል

ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ ማገልገል

“ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ።”—ፊልጵ. 3:13

1-3. (ሀ) ጸጸት ሲባል ምን ማለት ነው? በእኛ ላይስ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆነን አምላክን በማገልገል ረገድ ከጳውሎስ ምን እንማራለን?

“በአንደበት ወይም በብዕር ሲገለጹ ከሚሰሙት አሳዛኝ አነጋገሮች ሁሉ በጣም የከፋው ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ!’ የሚለው ነው” በማለት ጆን ግሪንሊፍ ዊተር የተባሉ ገጣሚ ጽፈዋል። እኚህ ገጣሚ የምንጸጸትባቸው ይኸውም ወደ ኋላ መመለስ ቢቻል ኖሮ በተለየ መንገድ እናደርጋቸው እንደነበረ የሚሰሙንን ነገሮች መጥቀሳቸው ነው። “መጸጸት” የሚለው ቃል ከዚህ በፊት የተፈጸመን ወይም ሳይደረግ የቀረን ነገር እያሰቡ ማዘንን ወይም በዚህ ሳቢያ የሚመጣን የአእምሮ ሥቃይ ያመለክታል፤ “እንደገና ማልቀስ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ሁላችንም ብንሆን የምንጸጸትባቸውና ወደ ኋላ መመለስ ቢቻል ኖሮ ማስተካከል የምንፈልጋቸው ነገሮች አይጠፉም። አንተስ የምትጸጸትበት ነገር አለ?

2 አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ስህተት አልፎ ተርፎም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙበት ጊዜ አለ። ሌሎች ደግሞ መጥፎ ነገር ባይሠሩም በሕይወታቸው ውስጥ ያደረጓቸውን አንዳንድ ውሳኔዎች በማሰብ የተሻለ ምርጫ ማድረግ ይችሉ እንደነበረ ይሰማቸዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ፣ ያሳለፉት ነገር የሚያሳድርባቸውን ተጽዕኖ ተቋቁመው የሚኖሩ አሉ። ሌሎቹ ግን “ምናለ እንዲህ ቢሆን ኖሮ” በማለት ሲቆጩ ይኖራሉ። (መዝ. 51:3) አንተ ከየትኛው ወገን ነህ? ቢያንስ ከዚህ በኋላ ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆነህ አምላክን ማገልገል ትፈልጋለህ? ይሁንና በዚህ ረገድ ምሳሌ ሊሆነን የሚችል ሰው አለ? አዎ አለ፤ እሱም ሐዋርያው ጳውሎስ ነው።

3 ጳውሎስ በሕይወት ዘመኑ ከባድ ስህተቶችን የሠራባቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎችን ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። ከዚህ በፊት በሠራው ነገር ከልቡ ቢጸጸትም አምላክን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለማገልገል ምን ማድረግ እንዳለበትም ተምሯል። እንግዲያው ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆነን አምላክን ለማገልገል የእሱ ምሳሌ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

የጳውሎስ መጥፎ ትዝታ

4. ጳውሎስ በኋላ ላይ የተጸጸተበት ምን ድርጊት ፈጽሟል?

4 ጳውሎስ በወጣትነቱ ፈሪሳዊ ነበር፤ በዚህ ወቅት በኋላ ላይ የተጸጸተበትን ነገር አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለማሳደድ ዘመቻ አካሂዷል። እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ምን እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ እንዲህ  ይላል፦ “[ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ የተባለው] ሳኦል . . . በጉባኤው ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ ጀመረ። በየቤቱ እየገባ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ጎትቶ በማውጣት ለወህኒ ቤት አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር።” (ሥራ 8:3) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልበርት ባርነስ እንዳሉት ከሆነ “ከፍተኛ ጥቃት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሳኦል “ስደት በሚያደርስበት ወቅት የነበረውን የቅንዓትና የቁጣ ስሜት የሚያሳይ ጠንከር ያለ አገላለጽ ነው።” ባርነስ አክለው “ሳኦል ልክ እንደ አውሬ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ በቁጣ ተነስቶ ነበር” ብለዋል። ሳኦል ቀናተኛ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን አምላክ የክርስትናን እምነት እንዲያጠፋ ኃላፊነት እንደሰጠው ያምን ነበር። በመሆኑም ሳኦል “ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ላይ በመዛትና እነሱን ለመግደል ቆርጦ” በመነሳት ክርስቲያኖችን ማሳደዱን ተያያዘው።—ሥራ 9:1, 2፤ 22:4 *

5. የኢየሱስን ተከታዮች ያሳድድ የነበረው ሳኦል ስለ ክርስቶስ መስበክ የጀመረው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

5 ሳኦል ወደ ደማስቆ በመሄድ በዚያ ያሉትን የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ከየቤታቸው ጎትቶ እያወጣ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ለማቅረብ ስላሰበ ወደዚያ አቀና። ይሁንና ከክርስቲያን ጉባኤ ራስ ጋር እየተጋጨ ስለነበር ዓላማው ከሸፈ። (ኤፌ. 5:23) ሳኦል ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ ሳለ ኢየሱስ የተገለጠለት ከመሆኑም ሌላ ከሰማይ የመጣ ብርሃን ዓይኑን አሳወረው። ከዚያም ኢየሱስ፣ ወደ ደማስቆ እንዲሄድና የሚያናግረው ሰው እስኪልክለት ድረስ እንዲጠብቅ ለሳኦል ነገረው። ከዚህ በኋላ የሆነውን ነገር ሁላችንም እናውቀዋለን።—ሥራ 9:3-22

6, 7. ጳውሎስ ከባድ ስህተት መፈጸሙን እንደተረዳ በምን እናውቃለን?

6 ጳውሎስ ወደ ክርስትና ሲለወጥ ከፍተኛ ግምት ይሰጠው የነበረው ነገርም ተቀየረ። የክርስቲያኖች ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ትቶ ክርስትናን በቅንዓት ማስፋፋት ጀመረ። ያም ሆኖ በኋላ ላይ ስለ ራሱ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት ሳለሁ ምን ዓይነት ሰው እንደነበርኩ ሰምታችኋል፤ የአምላክን ጉባኤ ከልክ በላይ አሳድድና አጠፋ ነበር።” (ገላ. 1:13) ከጊዜ በኋላም በቆሮንቶስና በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲሁም ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀደም ሲል የሠራውን የሚጸጽት ድርጊት በድጋሚ ጠቅሶታል። (1 ቆሮንቶስ 15:9ን አንብብ፤ ፊልጵ. 3:6፤ 1 ጢሞ. 1:13) ጳውሎስ ይህን ጉዳይ የጻፈው በኩራት ስሜት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ነገር እንዳልፈጸመ ሆኖ ለመቅረብ አልሞከረም። ከባድ ስህተቶችን እንደሠራ አምኖ ተቀብሏል።—ሥራ 26:9-11

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ፍሬድሪክ ፋራር፣ ሳኦል “አስከፊ በሆነው የስደት” ወቅት ስለነበረው ሚና ገልጸዋል። ፋራር እንደተናገሩት “ጳውሎስ ይሰማው የነበረውን ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት እና ክፉ ጠላት ከሆኑበት ሰዎች የሚደርስበት ማንጓጠጥ የሚፈጥርበትን ጫና መረዳት የምንችለው” ጳውሎስ በቀድሞ ሕይወቱ የፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከተገነዘብን ብቻ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ የተለያዩ ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ወቅት አንዳንድ ወንድሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኙት ‘ጳውሎስ ማለት አንተ ነህ? ለካ እንደዛ መከራችንን ስታሳየን የነበርከው አንተ ነህ!’ ብለውት ሊሆን ይችላል።—ሥራ 9:21

8. ጳውሎስ ይሖዋና ኢየሱስ ስላሳዩት ምሕረትና ፍቅር ምን ተሰማው? ይህስ ለእኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

8 ጳውሎስ የአምላክን ጸጋ ባያገኝ ኖሮ አገልግሎቱን መፈጸም እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስ በጻፋቸው 14 ደብዳቤዎች ውስጥ የአምላክ ምሕረት መገለጫ የሆነውን ይህን ባሕርይ 90 ጊዜ ያህል የጠቀሰ ሲሆን የእሱን ያህል ይህን ባሕርይ የጠቀሰ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የለም። (1 ቆሮንቶስ 15:10ን አንብብ።) ጳውሎስ ለተደረገለት ምሕረት ከፍተኛ አድናቆት ያሳየ ከመሆኑም በላይ የአምላክ ጸጋ ከንቱ ሆኖ እንዲቀር አልፈለገም። በመሆኑም ከሁሉም ሐዋርያት ‘በላይ በትጋት ሠርቷል።’ እኛም ኃጢአታችንን ከተናዘዝንና ከመጥፎ ድርጊታችን ከተመለስን፣ የሠራነው ከባድ ኃጢአት ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ሊለን ፈቃደኛ እንደሆነ የጳውሎስ ምሳሌ በግልጽ ያሳያል። የክርስቶስ መሥዋዕት በግለሰብ ደረጃ እንደሚጠቅመው ለመቀበል የሚከብደው ሰው ካለ ከዚህ ምሳሌ ጥሩ ትምህርት ማግኘት ይችላል! (1 ጢሞቴዎስ 1:15, 16ን  አንብብ።) ጳውሎስ የክርስቶስ ቀንደኛ አሳዳጅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ‘የወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠው የአምላክ ልጅ’ በማለት ስለ ኢየሱስ ጽፏል። (ገላ. 2:20፤ ሥራ 9:5) አዎን፣ ጳውሎስ በጸጸት ስሜት ከመዋጥ ይልቅ አምላክን ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። አንተስ እንደ ጳውሎስ ይህን ተምረሃል?

ጳውሎስ ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ ይሖዋን ማገልገል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምሯል

የሚጸጽትህ ነገር አለ?

9, 10. (ሀ) አንዳንድ የይሖዋ ሕዝቦች የጸጸት ስሜት የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ከዚህ በፊት የፈጸምነውን ነገር በማሰብ ያለማቋረጥ መጨነቅ ምን ጉዳት አለው?

9 በአሁኑ ጊዜ የሚጸጽትህ ከዚህ በፊት የፈጸምከው ድርጊት አለ? ጉልበትህንና ጊዜህን አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማሳደድ አባክነሃል? ሌሎችን የሚጎዳ ነገርስ አድርገሃል? ወይም ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የጸጸት ስሜት ይኖርህ ይሆናል። ዋናው ነገር ‘ይህን ስሜት ለማሸነፍ ምን ማድረግ ትችላለህ?’ የሚለው ነው።

10 ብዙ ሰዎች ከዚህ በፊት የፈጸሙትን ነገር በማሰብ ይጨነቃሉ! ያለማቋረጥ መጨነቅ ማለት በራስ ላይ መከራ ማምጣት፣ በራስ ላይ ስደት ማምጣት እንዲሁም ብስጭት ማትረፍ ማለት ነው። ስለ ጉዳዩ ባሰብን ቁጥር እንሠቃይ ይሆናል። ታዲያ መጨነቅ መፍትሔ ያስገኛል? በፍጹም! መጨነቅ፣ በሚወዛወዝ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ወደ ፊት ለመሄድ ከመሞከር ተለይቶ አይታይም፤ ለሰዓታት ጉልበትህን ብታጠፋም ከቦታው ፈቀቅ አትልም! ከመጨነቅ ይልቅ አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድህ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝልህ ይችላል። ለምሳሌ የበደልከው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅ ትችላለህ፤ ይህ ደግሞ የቀድሞ ወዳጅነታችሁ እንዲመለስ ያደርግ ይሆናል። እንዲሁም መጥፎ ድርጊት ወደ መፈጸም ከመራህ ነገር በመራቅ ዳግም ችግር ውስጥ ከመግባት መጠበቅ ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ የፈጸምከው ስህተት ያስከተለብህን መከራ ችለህ መኖር ግድ ሊሆንብህ ይችላል። መጨነቅ ግን አምላክን በተሟላ ሁኔታ እንዳታገለግል አንተን ሽባ አድርጎ ከማስቀመጥ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። በመሆኑም በመጨነቅ የሚገኝ ነገር የለም!

11. (ሀ) የይሖዋን ምሕረትና ፍቅራዊ ደግነት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በፊት በፈጸምናቸው ስህተቶች የተነሳ የሚሰማንን የጸጸት ስሜት ለማስወገድ ልንወስደው የሚገባንን እርምጃ ሲጠቁም ምን ይላል?

11 አንዳንዶች ከዚህ በፊት የፈጸሙት ስህተት ያሳደረባቸው ጭንቀት እንዲቆጣጠራቸው በመፍቀዳቸው  ምክንያት በአምላክ ፊት ዋጋ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። ከትክክለኛው ጎዳና ርቀው በመሄዳቸው አሊያም በተደጋጋሚ በመውጣታቸው ሳቢያ አምላክ ይቅር እንደማይላቸው ሊሰማቸው ይችላል። እውነታው ግን እነሱ እንደሚያስቡት አይደለም፤ ከዚህ በፊት የሠሩት ስህተት ምንም ይሁን ምን ንስሐ መግባት፣ መለወጥና አምላክ ይቅር እንዲላቸው መጠየቅ ይችላሉ። (ሥራ 3:19) ይሖዋ ለሌሎች እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም ምሕረቱንና ፍቅራዊ ደግነቱን ሊያሳያቸው ይችላል። አንድ ሰው ትሑትና ሐቀኛ በመሆን ከልቡ ንስሐ የሚገባ ከሆነ ይሖዋ በደግነት ይቅር ይለዋል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ደግነት ለኢዮብ አሳይቶታል፤ ኢዮብ “በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ [“እጸጸታለሁ፣” የ1954 ትርጉም]” ብሏል። (ኢዮብ 42:6) መጽሐፍ ቅዱስ የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ልንወስደው የሚገባንን እርምጃ ሲጠቁም እንዲህ ይላል፦ “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።” (ምሳሌ 28:13፤ ያዕ. 5:14-16) በመሆኑም ለአምላክ መናዘዝ፣ ይቅር እንዲለን መጸለይ እንዲሁም የሠራነውን ስህተት ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 7:10, 11) እንዲህ ካደረግን “ይቅርታው ብዙ” የሆነው አምላክ ምሕረት ያደርግልናል።—ኢሳ. 55:7

12. (ሀ) በጥፋተኝነት ስሜት የምንሠቃይ ከሆነ የዳዊት ምሳሌ ትምህርት የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ይጸጸታል ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ማወቃችን የሚረዳንስ እንዴት ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።)

12 ጸሎት ከፍተኛ ኃይል አለው፤ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ትልቅ ሚና ይጫወታል። ዳዊት፣ ጸሎት ባለው ኃይል ላይ እምነት እንዳለው በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ግሩም በሆነ መንገድ ገልጿል። (መዝሙር 32:1-5ን አንብብ።) ዳዊት የጥፋተኝነት ስሜቱን ደብቆ ለመያዝ መሞከሩ አጥንቱን እንዳበላሸው ማለትም አቅም እንዳሳጣው ሳይሸሽግ ተናግሯል። ኃጢአቱን ሳይናዘዝ መቅረቱ የአእምሮና የአካል ሥቃይ እንዳስከተለበት ብሎም ደስታውን እንዳሳጣው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ታዲያ ዳዊት የኃጢአት ይቅርታና እፎይታ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ብቸኛው መፍትሔ በደሉን ለአምላክ መናዘዙ ነበር። ይሖዋ የዳዊትን ጸሎት ሰምቷል፤ እንዲሁም የአእምሮ ሰላም አግኝቶ ሕይወቱን እንዲመራ ብሎም መልካም ነገሮችን ማከናወኑን እንዲቀጥል አበረታቶታል። አንተም በተመሳሳይ የውስጥህን አውጥተህ የምትጸልይ ከሆነ ይሖዋ ልመናህን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ከዚህ በፊት የሠራሃቸው ስህተቶች የሚረብሹህ ከሆነ በቅድሚያ ይሖዋ ይቅር እንዲልህ መጸለይና ነገሮችን ለማስተካከል የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል፤ ከዚያም ይሖዋ ጸሎትህን ሰምቶ ይቅር እንዳለህ እምነት ይኑርህ!—መዝ. 86:5

ከፊታችሁ ባለው ነገር ላይ ትኩረት አድርጉ

13, 14. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ምንድን ነው? (ለ) አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለመመርመር የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?

13 ስላለፈው ጊዜ በማሰብ ትምህርት ማግኘት ይቻላል፤ ሕይወትህን ለመምራት ግን የተሻለው ነገር ስለወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ነው። በመሆኑም ስላለፈው ጊዜ ከመጨነቅ ይልቅ አሁን ባለንበትና በወደፊቱ ሕይወታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። አሁን እያደረግን ያለነው ወይም ሳናደርገው  የቀረነው ነገር አለ? ይህ ሁኔታ ከዓመታት በኋላ ሊጸጽተን ስለሚችል ከወዲሁ ብናስብበት የተሻለ አይሆንም? ወደፊት የሚጸጽተን ነገር እንዳይኖር አሁን አምላክን በታማኝነት እያገለገልን ነው?

14 ታላቁ መከራ ሲቀርብ እንደሚከተለው እያልን እንዳንቆጭ ከወዲሁ ብናስብበት ይሻላል፦ ‘አምላክን በተሻለ መንገድ ማገልገል እችል ነበር? አጋጣሚው እያለኝ አቅኚ ያልሆንኩት ለምንድን ነው? የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን ያልተጣጣርኩት ለምንድን ነው? አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ከልቤ ጥረት አድርጌ ነበር? ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚፈቅድለት ዓይነት ሰው ነኝ?’ በዚያን ጊዜ እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ መጨነቅ ምንም ፋይዳ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ አሁን ራሳችንን መመርመርና በይሖዋ አገልግሎት ምርጣችንን ለመስጠት የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በመሆኑም ምንም ማድረግ በማንችልበት ጊዜ እንዳንቆጭ አሁኑኑ ለጸጸት የማይዳርገውን የሕይወት ጎዳና እንምረጥ።—2 ጢሞ. 2:15

ለቅዱስ አገልግሎት በከፈልከው መሥዋዕትነት ፈጽሞ አትቆጭ

15, 16. (ሀ) ብዙዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት ቅድሚያ ለመስጠት ሲሉ ምን መሥዋዕትነት ከፍለዋል? (ለ) ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ስንል በከፈልነው መሥዋዕትነት መቆጨት የሌለብን ለምንድን ነው?

15 ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል ስትል መሥዋዕትነት ከፍለህ ከሆነስ? ምናልባትም አኗኗርህን ቀላል በማድረግ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ስትል ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ሙያ ወይም ንግድ ትተህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ቤቴል እንደማገልገል፣ ዓለም አቀፍ የግንባታ ሠራተኛ እንደመሆን፣ በወረዳ ሥራ እንደመካፈልና ሚስዮናዊ እንደመሆን ባሉ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስኮች ውስጥ ለመግባት ስትል በነጠላነት ለመኖር፣ ባለትዳር ከሆንክ ደግሞ ልጅ ላለመውለድ ወስነህ ይሆናል። በይሖዋ አገልግሎት ዓመታት እያስቆጠርክ ስትሄድ በውሳኔህ ልትቆጭ ይገባሃል? የከፈልከው መሥዋዕትነት አላስፈላጊ እንደሆነ ወይም ጊዜህን እንዳባከንክ ሆኖ ሊሰማህ ይገባል? በፍጹም!

16 እነዚህን ውሳኔዎች ያደረግከው ለይሖዋ ባለህ ጥልቅ ፍቅርና የእሱን አገልጋዮች ለመርዳት ባለህ ልባዊ ፍላጎት ተነሳስተህ ነው። ሕይወትህን በተለየ መንገድ ብትመራ ኖሮ የተሻለ ይሆን እንደነበር ሊሰማህ አይገባም። ትክክል እንደሆነ የምታውቀውን ነገር በማድረግህ እውነተኛ እርካታ ሊሰማህ ይገባል። እንዲሁም ለይሖዋ አገልግሎት ምርጥህን በመስጠትህ ልትደሰት ይገባል። ይሖዋ የራስህን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳለፍከውን ሕይወት በፍጹም አይረሳም። እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ስታገኝ፣ ዛሬ ልታስበው ከምትችለው በላይ በረከቶችን አትረፍርፎ ይሰጥሃል!—መዝ. 145:16፤ 1 ጢሞ. 6:19

ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ ማገልገል

17, 18. (ሀ) ጳውሎስ ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ አምላክን እንዲያገለግል የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን ከማገልገል ጋር በተያያዘ ስላለፈው፣ ስለ አሁኑና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

17 ጳውሎስ ከጸጸት ስሜት ነፃ ሆኖ አምላክን ለማገልገል የረዳው ምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ . . . ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።” (ፊልጵስዩስ 3:13, 14ን አንብብ።) ጳውሎስ በአይሁድ እምነት ሳለ በፈጸማቸው የተሳሳቱ ድርጊቶች ላይ አላሰላሰለም። ከዚህ ይልቅ ወደፊት ለተዘጋጀለት የዘላለም ሕይወት ሽልማት ብቁ ለመሆን የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ አተኩሯል።

18 ሁላችንም የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ከዚህ በፊት በፈጸምናቸውና ልንቀይራቸው በማንችላቸው ነገሮች ከመብሰልሰል ይልቅ ከፊታችን ያሉትን ነገሮች ለማግኘት መንጠራራት ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ቀደም ሲል የሠራነውን ስህተት ሙሉ በሙሉ መርሳት እንችላለን ማለት አይደለም፤ ያም ሆኖ ነጋ ጠባ በዚያ ነገር ላይ ማሰላሰል አይኖርብንም። ከኋላችን ያሉትን ነገሮች ለመተው ጥረት ማድረግ እንዲሁም አሁን ባለን ሕይወት ለአምላክ አገልግሎት ምርጣችንን መስጠት ብሎም አስደሳች የሆነውን የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠበቅ ይኖርብናል።

^ စာပိုဒ်၊ 4 ሳኦል ከሚያሳድዳቸው መካከል ሴቶችም እንደሚገኙበት በተደጋጋሚ መጠቀሱ ልክ እንደ ዛሬው ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ክርስትናን በማስፋፋት ረገድ ሴቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ እንደነበር ያሳያል።—መዝ. 68:11 የ1980 ትርጉም