በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2012

እምነት የሚጣልባችሁ መጋቢዎች ናችሁ!

እምነት የሚጣልባችሁ መጋቢዎች ናችሁ!

“እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም።”—1 ቆሮ. 6:19

1. ሰዎች ስለ ባርነት ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ምንድን ነው?

ከዛሬ 2,500 ዓመታት ገደማ በፊት የኖረ አንድ ግሪካዊ ጸሐፌ ተውኔት “የባርነትን ቀንበር በፈቃደኝነት የሚሸከም አንድም ሰው የለም” ሲል ጽፏል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በዚህ አባባል ይስማማሉ። ባርነት የሚለውን ቃል ስንሰማ የተጨቆኑና የታሰሩ ሰዎች ወደ አእምሯችን ይመጣሉ፤ እነዚህ ሰዎች በሚያከናውኑት ሥራና በሚከፍሏቸው መሥዋዕቶች የሚጠቀሙት እነሱ ራሳቸው ሳይሆኑ የሚገዟቸውና የሚጨቁኗቸው ሰዎች ናቸው።

2, 3. (ሀ) በፈቃደኝነት የክርስቶስ ባሪያ ወይም አገልጋይ የሆኑ ሰዎች ምን ዓይነት ቦታ አላቸው? (ለ) ከመጋቢነት ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ያም ሆኖ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ትሑት አገልጋዮች ወይም ባሪያዎች እንደሚሆኑ ተናግሯል። ይሁንና እውነተኛ ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት የተቀበሉት ይህ ባርነት እነሱን ዝቅ የሚያደርግ ወይም ለጭቆና የሚዳርግ አይደለም። እነዚህ ባሪያዎች የተከበረና ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ እምነት ይጣልባቸዋል። ለምሳሌ ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለ አንድ “ባሪያ” የተናገረውን ሐሳብ ተመልከት። ክርስቶስ የተለያዩ ኃላፊነቶችን የሚሰጠው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚኖር ተናግሮ ነበር።—ማቴ. 24:45-47

3 በሌላ ቦታ በተጻፈ ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ይህ ባሪያ “መጋቢ” ተብሎ መጠራቱ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 12:42-44ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ በሕይወት ያሉ አብዛኞቹ ታማኝ ክርስቲያኖች የዚህ ታማኝ መጋቢ ክፍል አይደሉም። ይሁንና ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች በሙሉ የመጋቢነት ኃላፊነት እንዳላቸው ይገልጻሉ። እነዚህ ሰዎች ያሉባቸው ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ መታየት ይኖርባቸዋል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በጥንት ዘመን መጋቢዎች ምን ኃላፊነት እንደነበራቸው እንመርምር።

የመጋቢዎች ኃላፊነት

4, 5. በጥንት ጊዜ የነበሩ መጋቢዎች ምን ኃላፊነቶች ነበሯቸው? ምሳሌዎች ጥቀስ።

4 በጥንት ዘመን አንድ መጋቢ የጌታውን ቤት ወይም ንግድ  በበላይነት እንዲቆጣጠር የሚሾም እምነት የሚጣልበት ባሪያ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ መጋቢዎች ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሲሆን የቤተሰቡን ንብረት፣ ገንዘብና ሌሎች አገልጋዮችን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይሰጣቸው ነበር። ኤሊዔዘርን እንደ ምሳሌ ብንወስድ አብርሃም ያፈራውን ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት የመቆጣጠር ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር። አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት ወደ መስጴጦምያ የላከው ኤሊዔዘርን ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥም ኤሊዔዘር ወሳኝ የሆነና ብዙ ነገሮች የሚያካትት ኃላፊነት ነበረው!—ዘፍ. 13:2፤ 15:2፤ 24:2-4

5 የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ዮሴፍ የጲጥፋራን ቤት ያስተዳድር ነበር። (ዘፍ. 39:1, 2) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ የራሱን መጋቢ ለመሾም በቅቷል፤ መጋቢው ‘በዮሴፍ ቤት ላይ’ ተሹሞ ነበር። በመሆኑም መጋቢው የዮሴፍ አሥር ወንድሞች በአግባቡ እንዲስተናገዱ ዝግጅት አድርጓል። በተጨማሪም ዮሴፍ በሰጠው መመሪያ መሠረት “ከተሰረቀው” የብር ዋንጫ ጋር በተያያዘ ሁኔታዎችን አቀነባብሯል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጋቢዎች ታማኝነት የሚጠይቅ የኃላፊነት ቦታ ነበራቸው።—ዘፍ. 43:19-25፤ 44:1-12

6. የተለያዩ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን የመጋቢነት ኃላፊነት አለባቸው?

6 ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ‘በአምላክ የተሾሙ መጋቢዎች’ እንደሆኑ ጽፏል። (ቲቶ 1:7) ‘የአምላክን መንጋ’ እንዲጠብቁ የተሾሙት የበላይ ተመልካቾች በጉባኤ ውስጥ መመሪያ ይሰጣሉ፤ እንዲሁም ግንባር ቀደም ሆነው ይሠራሉ። (1 ጴጥ. 5:1, 2) እርግጥ ሁሉም ተመሳሳይ ኃላፊነቶች የሏቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚያገለግሉት አንድን ጉባኤ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ደግሞ በርካታ ጉባኤዎችን ያገለግላሉ። በሌላ በኩል የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በአንድ አገር ውስጥ ያሉትን ጉባኤዎች በሙሉ በኃላፊነት ይከታተላሉ። ያም ሆነ ይህ ሁሉም ኃላፊነታቸውን በታማኝነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፤ ደግሞም ሁሉም ለአምላክ ‘ስሌት ማቅረብ’ ይኖርባቸዋል።—ዕብ. 13:17

7. ሁሉም ክርስቲያኖች መጋቢዎች ናቸው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

7 ይሁንና የበላይ ተመልካች ያልሆኑ በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው ስጦታ መሠረት በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች በመሆን፣ የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።” (1 ጴጥ. 1:1፤ 4:10) አምላክ በጸጋው አማካኝነት የእምነት አጋሮቻችንን ለማገልገል ልንጠቀምበት የምንችል ልዩ ልዩ ስጦታ፣ ጥሪት፣ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ለሁላችንም ሰጥቶናል። በመሆኑም አምላክን የሚያገለግሉ በሙሉ መጋቢዎች ናቸው። አምላክ የመጋቢነት ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ ይፈልጋል፤ ደግሞም እምነት የሚጥልብን ከመሆኑም ሌላ በአክብሮት ይመለከተናል።

የአምላክ ንብረት ነን

8. ልናስታውሰው የሚገባ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት የትኛው ነው?

8 መጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት። አንደኛ፦ ሁላችንም የአምላክ ንብረት ነን፤ እንዲሁም በእሱ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን። ጳውሎስ “እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤ ምክንያቱም በዋጋ [መሥዋዕት ሆኖ በፈሰሰው በክርስቶስ ደም] ተገዝታችኋል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 6:19, 20) የይሖዋ ንብረት በመሆናችን ትእዛዛቱን የመጠበቅ ግዴታ አለብን፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም። (ሮም 14:8፤ 1 ዮሐ. 5:3) በተጨማሪም የክርስቶስ ባሪያዎች ሆነናል። በጥንት ዘመን እንደነበሩት መጋቢዎች ሰፊ ነፃነት አለን፤ ሆኖም የተሰጠን ነፃነት ገደብ አለው። የተጣሉብንን ኃላፊነቶች በተሰጠን መመሪያ መሠረት መወጣት ይኖርብናል። ያለን የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን ሁላችንም የአምላክና የክርስቶስ አገልጋዮች ነን።

9. ኢየሱስ በጌታና በባሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት በምሳሌ የገለጸው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በጌታና በባሪያ መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽ እንዲሆንልን አድርጓል። በአንድ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ፣ ቀኑን ሙሉ ሲሠራ ውሎ ወደ ቤት  ስለተመለሰ አንድ ባሪያ ነግሯቸው ነበር። ጌታው ባሪያውን “ቶሎ ናና ወደ ማዕድ ቅረብ” ይለዋል? በጭራሽ። ከዚህ ይልቅ “ራቴን አዘጋጅልኝ፤ በልቼና ጠጥቼ እስክጨርስም ድረስ አሸርጠህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ መብላትና መጠጣት ትችላለህ” ይለዋል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረበት ዓላማ ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚህ እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።”—ሉቃስ 17:7-10

10. ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት በምን እናውቃለን?

10 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በማለት ያረጋግጥልናል። (ዕብ. 6:10) ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ ፈጽሞ አይጠይቀንም። በተጨማሪም እንድናደርገው የሚያዘን ነገር ሁሉ መልሶ እኛኑ ይጠቅመናል፤ ደግሞም ትእዛዙ ከባድ ሸክም አይደለም። ያም ቢሆን፣ ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ጋር በሚስማማ መልኩ አንድ ባሪያ የራሱን ፍላጎት በማስቀደም ራሱን አያስደስትም። ዋናው ቁም ነገር ራሳችንን ለአምላክ በወሰንበት ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የእሱን ፍላጎት ለማስቀደም የመረጥን መሆኑ ነው። በዚህ አትስማማም?

ይሖዋ ከሁላችንም የሚጠብቀው ነገር

11, 12. መጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን የትኛውን ባሕርይ ማንጸባረቅ ይኖርብናል? ልናስወግደው የሚገባው ባሕርይስ የትኛው ነው?

11 ሁለተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ይህ ነው፦ መጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም መሠረታዊ የሆኑ ተመሳሳይ መሥፈርቶችን እንከተላለን። እውነት ነው፣ አንዳንድ ኃላፊነቶች የሚሰጡት በጉባኤ ውስጥ ላሉ ጥቂት ግለሰቦች ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ኃላፊነቶች ሁሉም ክርስቲያኖች ሊወጧቸው የሚገቡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትና የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ትእዛዝ ተሰጥቶናል። ኢየሱስ፣ ፍቅር የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:35) ይሁንና ክርስቲያን ወንድሞቻችንን በመውደድ ብቻ መወሰን አይኖርብንም። በእምነት ለማይዛመዱን ሰዎችም ፍቅር ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። ይህ ሁላችንም ማድረግ የምንችለው ነገር ነው፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይጠበቅብናል።

12 ከሁላችንም የሚጠበቀው ሌላው ነገር ደግሞ መልካም ባሕርይ ማሳየት ነው። የአምላክ ቃል ከሚያወግዛቸው ባሕርያትና የአኗኗር ዘይቤዎች መራቅ እንፈልጋለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮ. 6:9, 10) ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ጥረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችን በርካታ ጥቅሞች ስለሚያስገኝልን ይክሳል፤ ከጥቅሞቹ መካከል የተሻለ ጤንነትና በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ማግኘት እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይገኙበታል።—ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።

13, 14. ለሁሉም ክርስቲያኖች ምን ኃላፊነት ተሰጥቷል? እንዴትስ ልንመለከተው ይገባል?

13 አንድ መጋቢ የሚያከናውነው ሥራ እንዳለውም አስታውሱ። እኛም የምናከናውነው ሥራ አለን። በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ይኸውም የእውነት እውቀት ተሰጥቶናል። አምላክ ይህን እውቀት ለሌሎች እንድናካፍል ይጠብቅብናል። (ማቴ. 28:19, 20) ጳውሎስ “እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን የክርስቶስ የበታቾችና የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር መጋቢዎች እንደሆን አድርጎ ይቁጠረን” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 4:1) ጳውሎስ ይህ የመጋቢነት ሥራ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ‘ቅዱሱን ሚስጥር’ በአግባቡ የመያዝና ለሌሎች በታማኝነት የማስተማር ኃላፊነት እንደሚያስከትልበት ተገንዝቧል።—1 ቆሮ. 9:16

14 ደግሞም እውነትን ለሌሎች ማካፈል የሚያስደስት ሥራ ነው። እርግጥ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ሁኔታ የተለያየ ነው። ሁሉም ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ማከናወን አይችሉም። ይሖዋ  ይህንን በሚገባ ያውቃል። ዋናው ቁም ነገር በግለሰብ ደረጃ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን ነው። በመሆኑም ለአምላክና ለሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እናሳያለን።

እንድናከናውነው የተሰጠንን ሥራ በታማኝነት እንፈጽም

ታማኝ የመሆን አስፈላጊነት

15-17. (ሀ) አንድ መጋቢ ታማኝ መሆኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ታማኝነት ማጓደል የሚያስከትለውን መዘዝ በምሳሌ የገለጸው እንዴት ነው?

15 ሦስተኛው መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ከላይ ካየናቸው ሁለት ነጥቦች ጋር በጣም የተያያዘ ነው፤ ታማኝና እምነት የሚጣልብን መሆን አለብን። አንድ መጋቢ በርካታ ግሩም ባሕርያትና ችሎታዎች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ሆኖም ኃላፊነት የማይሰማው ከሆነ ወይም ለጌታው ታማኝ ካልሆነ ሁሉም ዋጋ አይኖራቸውም። አንድ መጋቢ በሥራው ውጤታማና የተሳካለት እንዲሆን ታማኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ “መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል” ብሎ መጻፉን አስታውስ።—1 ቆሮ. 4:2

16 በታማኝነት ጎዳና መመላለሳችን ወሮታ እንደሚያስገኝልን ምንም ጥርጥር የለውም። ታማኞች ካልሆን ደግሞ ለኪሳራ እንዳረጋለን። የዚህን እውነተኝነት ኢየሱስ ስለ ታላንት ከተናገረው ምሳሌ ማየት እንችላለን። ጌታቸው በሰጣቸው ገንዘብ በታማኝነት ‘የነገዱት’ ባሪያዎች የተመሰገኑ ከመሆኑም ሌላ ተጨማሪ መብት አግኝተዋል። ጌታው በአደራ የሰጠውን ታላንት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የያዘው ባሪያ “ክፉ፣” “ሰነፍ” እና “የማይረባ” ተብሎ ተኮንኗል። ይህ ባሪያ የተሰጠው ታላንት የተወሰደበት ከመሆኑም ሌላ ወደ ውጭ ተጥሏል።—ማቴዎስ 25:14-18, 23, 26, 28-30ን አንብብ።

17 በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ታማኝ አለመሆን የሚያስከትለውን መዘዝ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ የቤት አስተዳዳሪ ነበረው፤ ይህ ሀብታም ሰው፣ አስተዳዳሪው ንብረቱን እያባከነበት እንዳለ የሚገልጽ ክስ ደረሰው። ስለዚህ አስተዳዳሪውን ጠራውና ‘ይህ ስለ አንተ የምሰማው ነገር ምንድን ነው? ከዚህ በኋላ ቤቱን ማስተዳደር ስለማትችል በአስተዳዳሪነት ስትሠራበት የነበረውን የሒሳብ መዝገብ አስረክብ’ አለው።” (ሉቃስ 16:1, 2) መጋቢው የጌታውን ንብረት በማባከኑ  ጌታው ከኃላፊነት ቦታው አባሮታል። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ይዟል! ከተሰጠን ኃላፊነት ጋር በተያያዘ ታማኝነት የምናጓድል ሰዎች ሆነን መገኘት አንፈልግም።

ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ጥበብ ነው?

18. ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር የሌለብን ለምንድን ነው?

18 እያንዳንዳችን ‘የመጋቢነት ኃላፊነቴን የምመለከተው እንዴት ነው?’ ብለን መጠየቅ እንችላለን። ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድር ከሆነ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያነጻጽር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ የሚመካበት ነገር ያገኛል።” (ገላ. 6:4) የምናደርገውን ነገር ከሌሎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ እኛ ራሳችን ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ማተኮር አለብን። ይህ ደግሞ በኩራት ከመወጠር ወይም ተስፋ ከመቁረጥ ይጠብቀናል። ራሳችንን በምንገመግምበት ጊዜ ሁኔታዎች እንደሚለወጡ መገንዘብ ይኖርብናል። ምናልባት በሕመም፣ በዕድሜ መግፋት ወይም የተለያዩ ኃላፊነቶች ያሉብን በመሆኑ የተነሳ በፊት የምናከናውነውን ያህል መሥራት ሊያቅተን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ከምናደርገው የበለጠ መሥራት እንደምንችል እንገነዘብ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ የምናደርገውን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ለምን ጥረት አናደርግም?

19. አንድ መብት ሳናገኝ ብንቀር ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

19 ትኩረት ልናደርግበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ካሉን ወይም ከምንመኛቸው የኃላፊነት ቦታዎች ጋር የተያያዘ ነው። ለምሳሌ አንድ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የማገልገል ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ንግግር የማቅረብ ፍላጎት ይኖረው ይሆናል። እነዚህን መብቶች ለማግኘት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ተግተን መሥራታችን ጥሩ ቢሆንም መብቱን አገኛለሁ ብለን ተስፋ ባደረግንበት ጊዜ ሳናገኝ ብንቀር ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ለእኛ ግልጽ ባልሆኑልን ምክንያቶች የተነሳ አንዳንድ መብቶችን የምናገኘው ከጠበቅነው ጊዜ በላይ ዘግይቶ ሊሆን ይችላል። ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ ለማውጣት ብቁ እንደሆነ ተሰምቶት የነበረ ቢሆንም እንዲህ ለማድረግ 40 ዓመት መጠበቅ እንዳስፈለገው አስታውስ። ይህን ያህል ጊዜ መጠበቁ ዓመፀኛና አንገተ ደንዳና የሆነውን ሕዝብ ለመምራት የሚያስፈልጉትን ባሕርያት ለማዳበር በቂ ጊዜ እንዲያገኝ አስችሎታል።—ሥራ 7:22-25, 30-34

20. ዮናታን ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

20 አንድን መብት ጨርሶ የማናገኝበት ጊዜም ሊኖር ይችላል። ዮናታን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞታል። የሳኦል ልጅ የነበረው ዮናታን በመላው እስራኤል ላይ የመንገሥ አጋጣሚ ነበረው። ይሁን እንጂ አምላክ ለንግሥና የመረጠው ከዮናታን በዕድሜ በጣም የሚያንሰውን ዳዊትን ነበር። ዮናታን ሁኔታውን እንዴት ተቀበለው? ጉዳዩን በጸጋ የተቀበለ ከመሆኑም ሌላ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥልበት ቢሆንም እንኳ ዳዊትን ከመደገፍ ወደኋላ አላለም። ዳዊትን “በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ” ብሎታል። (1 ሳሙ. 23:17) ነጥቡ ግልጽ ሆኖልሃል? ዮናታን ሁኔታውን አሜን ብሎ የተቀበለ ሲሆን እንደ አባቱ በዳዊት ላይ ቅናት አላደረበትም። እኛም ሌሎች ባገኙት መብት ከመቅናት ይልቅ የተሰጡንን ኃላፊነቶች በመወጣት ላይ ትኩረት ማድረጋችን ተገቢ ነው። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ የሁሉንም አገልጋዮቹን ተገቢ ፍላጎቶች እንደሚያሟላ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

21. ለመጋቢነት ኃላፊነታችን ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

21 እምነት የሚጣልብን መጋቢዎች እንደመሆናችን መጠን ለጭቆናና ለሐዘን የሚዳርግ የከፋ ባርነት አይደርስብንም። ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ፈጽሞ በማይደገመው ምሥራቹን በማወጁ ሥራ የመካፈል መብት ማግኘታችን ታላቅ ክብር ነው። በዚህ ሥራ ስንካፈል ኃላፊነቶቻችንን ከምንወጣበት መንገድ ጋር በተያያዘ ሰፊ ነፃነት አለን። እንግዲያው ታማኝ መጋቢዎች እንሁን። በተጨማሪም በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ ያለውን አምላክ የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመልከት።