“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።” (ዕብ. 4:12) ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ቃል ያለውን ልብ የመንካትና ሕይወት የመለወጥ ኃይል ጎላ አድርጎ የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር።

ይሁን እንጂ በትንቢት የተነገረው ክህደት ከሐዋርያት ሞት በኋላ ሥር እየሰደደ ሲሄድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ስላለው ኃይል የተሳሳተ አመለካከት እያዳበሩ መጡ። (2 ጴጥ. 2:1-3) ከጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአምላክ ቃል አስማታዊ ኃይል እንዳለው ማስተማር ጀመሩ። ፕሮፌሰር ሃሪ ጋምበል “ክርስቲያናዊ ጽሑፎች አስማታዊ ጥቅም” እንዳላቸው ተደርጎ ይታሰብ እንደነበር ጽፈዋል። ጋምበል፣ በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበረው ኦሪጀን የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት “ቅዱስ የሆኑ ቃላትን በጆሮ መስማት በራሱ የተወሰነ ጠቀሜታ አለው፤ አረማውያን አስማት ሲፈጽሙ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ኃይል ከኖራቸው በትክክል መለኮታዊ ምንጭ ያላቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ቃላትማ ምን ያህል የበለጠ ኃይል ይኖራቸው!” ማለቱን ጽፈዋል። በአራተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የኖረው ጆን ክሪሶስተም “ዲያብሎስ ወንጌል ወደተቀመጠበት ቤት ዝር አይልም” ሲል ጽፏል። ከዚህም በላይ አንዳንዶች ከወንጌል ውስጥ የተወሰዱ ቃላትን በአንገታቸው ላይ እንደ ክታብ እንደሚያስሩ ተናግሯል። በተጨማሪም ፕሮፌሰር ጋምበል፣ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆነው ኦገስቲን “አንድ ሰው ራስ ምታት ከያዘው የዮሐንስን ወንጌል ትራሱ ሥር አድርጎ መተኛቱ ምንም ችግር የለውም” ብሎ ያስብ እንደነበር ገልጸዋል። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለአስማታዊ ዓላማ ያገለግሉ ነበር። አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን የምትመለከተው ከክፉ ነገር እንደሚጠብቅ ክታብ ወይም ገድ አድርገህ ነው?

ከሁሉ በላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው አጉል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ቢብልዮማንሲ የሚባለው ልማድ ሳይሆን አይቀርም። ቢብልዮማንሲ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን የሆነ ቦታ ላይ እንዳመጣለት ከፍቶ መጀመሪያ ላይ ዓይን ውስጥ የገባውን ጥቅስ ማንበቡ አስፈላጊውን መመሪያ ያስገኛል የሚል እምነት ነው። ለምሳሌ፣ ፕሮፌሰር ጋምበል በአንድ ወቅት ኦገስቲን ጎረቤቱ የሚገኝ አንድ ሕፃን “ገልጠህ አንብብ፣ ገልጠህ አንብብ” ሲል በሰማ ጊዜ ይህን ድምፅ እንደ መለኮታዊ ትእዛዝ ቆጥሮ መጽሐፍ ቅዱስን እንደገለጠና ዓይኑ ያረፈበትን የመጀመሪያውን ጥቅስ እንዳነበበ ተናግረዋል።

አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ወደ አምላክ ከጸለዩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ያገኙበት ቦታ ላይ ሲገልጡ የሚያዩት የመጀመሪያው ጥቅስ ለችግራቸው መፍትሔ እንደሚሆን ስለሚያምኑ ሰዎች ሰምተህ ታውቃለህ? እነዚህ ሰዎች ይህን ያደረጉት በመልካም ዓላማ ተነሳስተው ሊሆን ቢችልም ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አይኖርባቸውም።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ” እንደሚልክላቸው አረጋግጦላቸው ነበር። አክሎም “ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:26) በአንጻሩ ግን ቢብልዮማንሲ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንዲኖረን አይጠይቅም።

ቢብልዮማንሲም ሆነ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀሞች በጣም የተለመዱ ናቸው። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ጥንቆላን ያወግዛል። (ዘሌ. 19:26፤ ዘዳ. 18:9-12፤ ሥራ 19:19) “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ” ቢሆንም በአጠቃቀሙ ረገድ ጥሩ ችሎታ ማዳበር ያስፈልገናል። የሰዎችን ሕይወት የሚያሻሽለው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንጂ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም አይደለም። ብዙዎች እንዲህ ያለውን እውቀት ማግኘታቸው ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው፣ መጥፎ የሆነ አኗኗራቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ፣ የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲያጠናክሩና ከመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ጋር ያላቸውን የግል ዝምድና እንዲያሳድጉ ረድቷቸዋል።