“አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ።”—መዝ. 143:10

1, 2. የአምላክን ፈቃድ ግምት ውስጥ ማስገባት የሚጠቅመን እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ከንጉሥ ዳዊት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

በተራራማ አካባቢ እየተጓዝክ ሳለ የምትጓዝበት መንገድ አንድ መንታ መንገድ ላይ አደረሰህ እንበል። የትኛውን መንገድ ተከትለህ ትሄዳለህ? ይህን ለመወሰን በአቅራቢያህ ባለ ቋጥኝ ላይ ወጥተህ ሁለቱ መንገዶች ወዴት እንደሚያመሩ መመልከት ያስፈልግሃል። ከባድ ውሳኔዎችን በምንወስንበት ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማድረጋችን ሊጠቅመን ይችላል። ነገሮችን ፈጣሪ ካለው ከፍ ያለ እይታ አንጻር መመልከት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ባለው ‘መንገድ እንድንሄድ’ ያስችለናል።—ኢሳ. 30:21

2 የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በአብዛኛው የሕይወት ዘመኑ የአምላክን ፈቃድ ግምት ውስጥ በማስገባት ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ልቡ በይሖዋ አምላክ ዘንድ ፍጹም እንደሆነ ያስመሠከረው ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ካጋጠሙት አንዳንድ ሁኔታዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት።—1 ነገ. 11:4

ዳዊት ለይሖዋ ስም ከፍ ያለ ግምት ነበረው

3, 4. (ሀ) ዳዊት ጎልያድን እንዲጋፈጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ዳዊት ለይሖዋ ስም ምን አመለካከት ነበረው?

3 ዳዊት ፍልስጤማዊውን ጀግና ጎልያድን ለመግጠም በወጣ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ወጣቱ ዳዊት ሙሉ የጦር ትጥቅ የታጠቀውንና 2.9 ሜትር ቁመት የነበረውን ግዙፍ ሰው ለመገዳደር ያነሳሳው ምንድን ነው? (1 ሳሙ. 17:4) ዳዊት ይህን ያደረገው ደፋር ስለነበር ነው? ወይስ በአምላክ ላይ እምነት ስለነበረው? እነዚህ ሁለት ባሕርያት ላሳየው ጀግንነት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ጥርጥር የለውም። ይሁንና አስፈሪ የሆነውን ይህን ግዙፍ ሰው እንዲጋፈጥ በዋነኝነት ያነሳሳው ለይሖዋና ለታላቅ ስሙ የነበረው አክብሮት ነው። ዳዊት በቁጣ ስሜት ተሞልቶ “የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” በማለት ጠይቋል።—1 ሳሙ. 17:26

4 ወጣቱ ዳዊት ከጎልያድ ጋር በተጋጠመ ጊዜ እንዲህ ብሏል፦  “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።” (1 ሳሙ. 17:45) ዳዊት በእውነተኛው አምላክ በመታመኑ በወንጭፍ አንዲት ጠጠር ወርውሮ ፍልስጤማዊውን ጀግና ዘርሮታል። ዳዊት በዚህ ወቅት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በይሖዋ እንደሚታመንና ለመለኮታዊው ስም ከፍ ያለ ግምት እንዳለው አሳይቷል። በእርግጥም ዳዊት ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን በይሖዋ ‘ቅዱስ ስም እንዲጓደዱ’ ወይም እንዲኩራሩ ማሳሰቡ ተገቢ ነው።—1 ዜና መዋዕል 16:8-10ን አንብብ።

5. ጎልያድ ከሰነዘረው ዘለፋ ጋር የሚመሳሰል ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል?

5 ይሖዋ አምላክህ በመሆኑ ኩራት ይሰማሃል? (ኤር. 9:24) ጎረቤቶችህ፣ የሥራ ባልደረቦችህ፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ወይም ዘመዶችህ ስለ ይሖዋ መጥፎ ነገር ሲናገሩና በእሱ ምሥክሮች ላይ ሲቀልዱ ስትሰማ ምን ታደርጋለህ? የይሖዋ ስም ሲነቀፍ እሱ እንደሚረዳህ በመተማመን ለስሙ ጥብቅና ትቆማለህ? እውነት ነው “ለዝምታ ጊዜ አለው”፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ተከታዮች በመሆናችን ማፈር አይኖርብንም። (መክ. 3:1, 7፤ ማር. 8:38) ቀና አመለካከት የሌላቸው ሰዎች ሲያጋጥሙን ዘዴኛ መሆንና አክብሮት ማሳየት ያለብን ቢሆንም የጎልያድን ዘለፋ ሰምተው ‘እጅግ እንደፈሩትና እንደደነገጡት’ እስራኤላውያን መሆን የለብንም። (1 ሳሙ. 17:11) ከዚህ ይልቅ የይሖዋ አምላክን ስም ለማስቀደስ የሚያስችል ቆራጥ እርምጃ እንውሰድ። ፍላጎታችን ይሖዋ በእርግጥ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ሰዎች እንዲያውቁ መርዳት ነው። በመሆኑም ወደ አምላክ መቅረብ ያለውን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ ለመርዳት በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን እንጠቀማለን።—ያዕ. 4:8

6. ዳዊት ከጎልያድ ጋር የተጋጠመበት ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር? እኛስ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ምንድን ነው?

6 ዳዊት ከጎልያድ ጋር እንደተጋጠመ ከሚናገረው ታሪክ የምናገኘው ሌላም አስፈላጊ ትምህርት አለ። ዳዊት ወደ ጦር ግንባሩ እየሮጠ መጥቶ “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል?” ሲል ጠየቀ። በምላሹም ሕዝቡ “ይህን ሰው [ጎልያድን] ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል” በማለት አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። (1 ሳሙ. 17:25-27) ሆኖም ዳዊትን በዋነኝነት ያሳሰበው ቁሳዊ ነገሮችን የማግኘት ጉዳይ አልነበረም። ከዚህ ይበልጥ የሚያሳስበው ነገር ነበር። ዳዊት እውነተኛውን አምላክ የማስከበር ፍላጎት ነበረው። (1 ሳሙኤል 17:46, 47ን አንብብ።) የእኛስ ፍላጎት ምንድን ነው? በዋነኝነት የሚያሳስበን ሀብት በማጋበስና በዚህ ዓለም ትልቅ ቦታ በማግኘት ስማችን እንዲገን ማድረግ ነው? ከዚህ ይልቅ “ኑና ከእኔ ጋር እግዚአብሔርን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ” ብሎ እንደዘመረው እንደ ዳዊት መሆን እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 34:3) እንግዲያው ከእኛ ስም ይልቅ የእሱን ስም በማስቀደም በአምላክ እንደምንታመን እናሳይ።—ማቴ. 6:9

7. ቀና አመለካከት የሌላቸው ሰዎች ሲያጋጥሙን እንዳንፈራ ጠንካራ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

7 ዳዊት ጎልያድን በድፍረት ለመግጠም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን አስፈልጎታል። ወጣቱ ዳዊት ጠንካራ እምነት ነበረው። እንዲህ ዓይነቱን እምነት እንዲገነባ ከረዱት ነገሮች አንዱ የእረኝነት ሥራውን ሲያከናውን በአምላክ ይታመን የነበረ መሆኑ ነው። (1 ሳሙ. 17:34-37) እኛም በአገልግሎት መካፈላችንን ለመቀጠል ጠንካራ እምነት ያስፈልገናል፤ በተለይ ቀና አመለካከት የሌላቸው ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ማዳበራችን ይጠቅመናል። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን በአምላክ በመታመን እንዲህ ያለ እምነት ማዳበር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በሕዝብ ማጓጓዣ ስንጠቀም ከአጠገባችን ከተቀመጡ ሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ውይይት መጀመር እንችላለን። ደግሞስ ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ መንገድ ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ለምን ዝም ብለን እናልፋቸዋለን?—ሥራ 20:20, 21

 ዳዊት ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቋል

ዳዊት ሳኦልን የመግደል አጋጣሚ ቢያገኝም ይህን ከማድረግ እንዲቆጠብ የረዳው ምንድን ነው?

8, 9. ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ጋር በነበረው ግንኙነት የይሖዋን ፈቃድ ግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ያሳየው እንዴት ነው?

8 ዳዊት የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ከሆነው ከሳኦል ጋር የነበረው ግንኙነት በይሖዋ እንደሚታመን የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። ቅናት ያንገበገበው ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን በጦር ከግድግዳ ጋር ለማጣበቅ ከአንዴም ሦስቴ ሞክሮ ነበር፤ ዳዊት ግን ሦስቱንም ጊዜ ያመለጠ ሲሆን አጸፋ ለመመለስም አልሞከረም። በመጨረሻም ሳኦል እንዳያገኘው ሸሽቶ ሄደ። (1 ሳሙ. 18:7-11፤ 19:10) ከዚያም ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን ይዞ በምድረ በዳ ዳዊትን ማደን ጀመረ። (1 ሳሙ. 24:2) በዚህ መሃል ሳኦል፣ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ያሉበት ዋሻ ውስጥ ሳያውቅ ገባ። ዳዊት እሱን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳውን ንጉሥ ለመግደል ይህን አጋጣሚ መጠቀም ይችል ነበር። ደግሞም የአምላክ ፈቃድ ዳዊት ሳኦልን ተክቶ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ነው። (1 ሳሙ. 16:1, 13) ዳዊት አብረዉት የነበሩት ሰዎች የሰጡትን ምክር ቢሰማ ኖሮ ንጉሡ አብቅቶለት ነበር። ይሁንና ዳዊት “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግ . . . እግዚአብሔር ይጠብቀኝ” አላቸው። (1 ሳሙኤል 24:4-7ን አንብብ።) ሳኦል አሁንም በአምላክ የተቀባ ንጉሥ ነበር። ይሖዋ ሳኦልን ገና ከንግሥናው ስላልሻረው ዳዊት የሳኦልን ንግሥና መቀማት አልፈለገም። በመሆኑም ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ ከመቁረጥ ያለፈ ነገር ባለማድረግ ሳኦልን የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው አሳይቷል።—1 ሳሙ. 24:11

9 ዳዊት ከሳኦል ጋር ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኘበት ወቅትም አምላክ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። በዚያን ጊዜ ዳዊትና አቢሳ ሳኦል ወደሰፈረበት የጦር ሰፈር ሲመጡ ንጉሡ ተኝቶ አገኙት። አቢሳ የዳዊትን ጠላት አምላክ እጁ ላይ እንደጣለለት በመግለጽ ሳኦልን በጦር ወግቶ ከመሬት ጋር ለማጣበቅ ሐሳብ ቢያቀርብም ዳዊት በሐሳቡ አልተስማማም። (1 ሳሙ. 26:8-11) ዳዊት ምንጊዜም የአምላክን መመሪያ ለመከተል ይጥር ስለነበር አቢሳ ቢጎተጉተውም ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ የነበረውን ቁርጥ ውሳኔ ለማላላት ፈቃደኛ አልነበረም።

10. በግለሰብ ደረጃ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል? በአቋማችን ለመጽናት የሚረዳንስ ምንድን ነው?

10 በተመሳሳይም የምንቀራረባቸው ሰዎች የይሖዋን ፈቃድ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸውን ሰብዓዊ አመለካከት እንድንከተል ጫና ሊያሳድሩብን ይሞክራሉ። አልፎ ተርፎም አንዳንድ ሰዎች ልክ እንደ አቢሳ፣ አምላክ አንድን ጉዳይ አስመልክቶ ያለውን ፈቃድ ሳናመዛዝን እርምጃ እንድንወስድ ሊገፋፉን ይችላሉ። በአቋማችን ለመጽናት ይሖዋ ለጉዳዩ ያለው አመለካከት ግልጽ ሊሆንልንና ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።

11. የአምላክ ፈቃድ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ ማድረግን በተመለከተ ከዳዊት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 ዳዊት “ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ”  በማለት ለይሖዋ አምላክ ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 143:5, 8, 10ን አንብብ።) ዳዊት በራሱ አስተሳሰብ ከመታመን ወይም ለሌሎች ውትወታ ከመሸነፍ ይልቅ ከአምላክ የመማር ጉጉት ነበረው። በይሖዋ ‘ሥራዎች ላይ ያሰላስልና የአምላክን እጅ ሥራ ያውጠነጥን’ ነበር። እኛም ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት በማጥናትና አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት በሚገልጹ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ በማሰላሰል የአምላክን ፈቃድ መረዳት እንችላለን።

ዳዊት ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተገንዝቧል

12, 13. ዳዊት ሦስቱ ሰዎች ያመጡለትን ውኃ መሬት ላይ ያፈሰሰው ለምንድን ነው?

12 ዳዊት በሕጉ ውስጥ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በመረዳትና ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በመመላለስ ረገድ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ዳዊት ‘ከቤተልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጕድጓድ የሚጠጣ ውኃ’ ማግኘት እንደሚፈልግ በተናገረ ወቅት የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ከዳዊት ሰዎች መካከል ሦስቱ በፍልስጤማውያን ሠራዊት ወደተያዘችው ከተማ ሰንጥቀው በመግባት ውኃውን ቀድተው ተመለሱ። “እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው።” ለምን? ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?”—1 ዜና 11:15-19

ዳዊት ሦስቱ ሰዎች ያመጡለትን ውኃ ለመጠጣት ፈቃደኛ አለመሆኑ ምን ያስተምረናል?

13 ዳዊት ደም በይሖዋ ፊት መፍሰስ እንጂ መበላት እንደሌለበት ከሕጉ ተረድቶ ነበር። ይህ የሚደረገውም ለምን እንደሆነ እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። ዳዊት “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ” መሆኑን ያውቃል። ይሁንና ያመጡለት ውኃ እንጂ ደም አይደለም። ታዲያ ዳዊት ለመጠጣት ያልፈለገው ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረገው ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተረድቶ ስለነበር ነው። ዳዊት ውኃውን የተመለከተው ክቡር እንደሆነው እንደ ሦስቱ ሰዎች ደም አድርጎ ነው። በመሆኑም ዳዊት ውኃውን መጠጣት ፈጽሞ የማያስበው ነገር ነበር። ውኃውን ከመጠጣት ይልቅ መሬት ላይ ማፍሰስ እንዳለበት ተሰምቶታል።—ዘሌ. 17:11፤ ዘዳ. 12:23, 24

14. ዳዊት የይሖዋን አመለካከት እንዲይዝ የረዳው ምንድን ነው?

14 ዳዊት ለአምላክ ሕግ ከፍተኛ ትኩረት ለመስጠት ጥረት ያደርግ ነበር። “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ”  ሲል ዘምሯል። (መዝ. 40:8) ዳዊት የአምላክን ሕግ ያጠና የነበረ ከመሆኑም ሌላ ባጠናው ነገር ላይ በጥልቅ ያሰላስል ነበር። የይሖዋ ትእዛዛት ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ እምነት ነበረው። በመሆኑም ዳዊት በሙሴ ሕግ ላይ የሰፈረውን ቃል ብቻ ሳይሆን የሕጉንም መንፈስ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ያነበብነውን ነገር ማሰላሰላችንና በልባችን መያዛችን ጥበብ ነው፤ እንዲህ ካደረግን አንድን ጉዳይ አስመልክቶ ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ለማወቅ እንችላለን።

15. ሰለሞን ለአምላክ ሕግ አክብሮት ሳያሳይ የቀረው በምን መንገድ ነው?

15 ይሖዋ አምላክ፣ የዳዊትን ልጅ ሰለሞንን በእጅጉ ባርኮት ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ሰለሞን ለአምላክ ሕግ የነበረው አክብሮት እየጠፋ ሄደ። ሰለሞን፣ አንድ እስራኤላዊ ንጉሥ “ብዙ ሚስቶችን አያግባ” የሚለውን የይሖዋን ትእዛዝ ሳያከብር ቀርቷል። (ዘዳ. 17:17) እንዲያውም በርካታ የባዕድ አገር ሴቶችን አግብቷል። ዕድሜው በገፋበት ወቅት “ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት።” ሰለሞን ለዚህ ድርጊት ምንም ዓይነት ሰበብ አቅርቦ ሊሆን ቢችልም “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት [ፈጽሟል]፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።” (1 ነገ. 11:1-6) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! በተለይ ትዳር ለመመሥረት ስናስብ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

16. “በጌታ ብቻ” ስለማግባት ከተሰጠው ትእዛዝ በስተጀርባ ያለውን መንፈስ መረዳት ለማግባት የሚያስቡ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል?

16 አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ከእኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር እንደከጀሉ ስናውቅ የምንሰጠው ምላሽ እንደ ዳዊት ዓይነት ነው ወይስ እንደ ሰለሞን? እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮ. 7:39) አንድ ክርስቲያን ለማግባት ቢፈልግ ማግባት ያለበት የእምነት ባልንጀራውን ብቻ ነው። በተጨማሪም ከዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ በስተጀርባ ያለውን መንፈስ መረዳታችን የማያምን ሰው ከማግባት እንድንርቅ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ወደ መመሥረት የሚያመሩ የፍቅር መግለጫዎችን ከመቀበል እንድንቆጠብ ያደርገናል።

17. የብልግና ምስሎችን መመልከት ወጥመድ እንዳይሆንብን ምን ሊረዳን ይችላል?

17 እስቲ አሁን ደግሞ ዳዊት የአምላክን መመሪያ ከልብ በመፈለግ ረገድ የተወው ምሳሌ የብልግና ምስሎችን እንድንመለከት የሚደርስብንን ፈተና ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብና የያዙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር፤ እንዲሁም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርግ። (መዝሙር 119:37ንማቴዎስ 5:28, 29ን እና ቆላስይስ 3:5ን አንብብ።) ከፍ ወይም ላቅ ባሉት የአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰላችን የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ወጥመድ እንድንርቅ ይረዳናል።

ምንጊዜም የአምላክ አመለካከት ይኑራችሁ

18, 19. (ሀ) ዳዊት ፍጽምና የሚጎድለው ቢሆንም የአምላክን ሞገስ ሳያጣ እንዲኖር የረዳው ምንድን ነው? (ለ) አንተስ ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

18 ዳዊት በብዙ መንገዶች ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው፤ ሆኖም ከባድ ኃጢአቶች የፈጸመባቸው ጊዜያት ነበሩ። (2 ሳሙ. 11:2-4, 14, 15, 22-27፤ 1 ዜና 21:1, 7) ይሁንና ዳዊት ኃጢአት በሠራ ጊዜ ሁሉ እውነተኛ ንስሐ ይገባ ነበር። በአምላክ ፊት “በልበ ቅንነት” ተመላልሷል። (1 ነገ. 9:4) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ዳዊት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መልኩ ለመመላለስ ጥረት ያደርግ ነበር።

19 እኛም ፍጽምና የሚጎድለን ቢሆንም የይሖዋን ሞገስ ሳናጣ መኖር እንችላለን። ይህን በአእምሯችን በመያዝ የአምላክን ቃል በትጋት እናጥና፣ በተማርነው ነገር ላይ በጥልቀት እናሰላስል እንዲሁም በልባችን የያዝነውን እውቀት በሥራ ለማዋል ፈጣን እንሁን። እንዲህ ካደረግን “ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ” በማለት በትሕትና የጠየቀውን የመዝሙራዊውን ስሜት እንጋራለን።