በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን

ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን

“ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፣ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”—ማቴ. 5:37

1. ኢየሱስ መማልን በተመለከተ ምን ብሏል? እንዲህ ያለውስ ለምንድን ነው?

በጥቅሉ ሲታይ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሐላ መፈጸም አያስፈልጋቸውም። ይህ የሆነው ኢየሱስ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን” በማለት የተናገረውን ቃል ስለሚታዘዙ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል አንድ ሰው የገባውን ቃል መፈጸም አለበት ማለቱ ነው። ይህን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት “ፈጽሞ አትማሉ” ሲል ተናግሮ ነበር። ይህን የተናገረው ብዙ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው እርስ በርስ ሲነጋገሩ ቃላቸውን የመፈጸም ዓላማ ሳይኖራቸው ለትንሹም ለትልቁም ደጋግመው የመማል አላስፈላጊ ልማድ ማዳበራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ ፈልጎ ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ሲናገሩ በቀላሉ “አዎ” ወይም “አይደለም” ማለት ሲችሉ “ከዚህ ውጭ” አልፈው መሄዳቸው እምነት የማይጣልባቸው እንደሆኑና ‘በክፉው’ ተጽዕኖ ሥር እንደወደቁ ያሳያል።—ማቴዎስ 5:33-37ን አንብብ።

2. መማል ሁልጊዜ ስህተት ያልሆነው ለምን እንደሆነ አብራራ።

2 ኢየሱስ ይህን ሲል ማንኛውም ዓይነት መሐላ ስህተት ነው ማለቱ ነበር? እንዲህ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በመጀመሪያው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተማርነው ይሖዋ አምላክና ጻድቅ አገልጋዩ የሆነው አብርሃም ከባድ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሐላ ገብተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ሕግ በሰዎች መካከል አንዳንድ አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ጉዳዩ በመሐላ እንዲቋጭ ያዝ ነበር። (ዘፀ. 22:10, 11፤ ዘኍ. 5:21, 22) በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ፍርድ ቤት ቀርቦ የምሥክርነት ቃል ሲሰጥ የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑን በመሐላ ማረጋገጥ ሊያስፈልገው ይችላል። ወይም አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን፣ ሰዎች ውስጣዊ ዓላማውን በተመለከተ ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው ወይም አንድ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ሲል መማል ግድ ሊሆንበት ይችላል። ኢየሱስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሲያስምለው ይህን ማድረግን ከመቃወም ይልቅ በአይሁድ የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት እውነቱን ተናግሯል። (ማቴ. 26:63, 64) ይሁንና ኢየሱስ ለማንም መማል አያስፈልገውም ነበር። ያም ሆኖ የመልእክቱን ተአማኒነት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ሲል ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ከመናገሩ በፊት “እውነት እውነት እላችኋለሁ” የሚለውን ለየት ያለ  አባባል ይጠቀም ነበር። (ዮሐ. 1:51፤ 13:16, 20, 21, 38) ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ቃላቸውን የጠበቁ ሌሎች ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ምን ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ—ከሁሉ የላቀው ምሳሌ

ኢየሱስ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለአባቱ የገባውን ቃል አክብሯል

3. ኢየሱስ በጸሎት ለአምላክ ምን ቃል ገብቷል? በሰማይ ያለው አባቱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

3 “እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ . . . ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።” (ዕብ. 10:7) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ቃላት ስለ ተስፋው ዘር የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ ለመፈጸም ቃል በመግባት ራሱን ለአምላክ እንዳቀረበ ያሳያሉ፤ ይህም ሰይጣን ‘ተረከዙን እንደሚቀጠቅጠው’ የተነገረውን ትንቢት ይጨምራል። (ዘፍ. 3:15) ከኢየሱስ ሌላ እንዲህ ዓይነት ከባድ ኃላፊነት ለመሸከም በፈቃደኝነት ራሱን ያቀረበ አንድም ሰው የለም። ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ የሚያረጋግጥ መሐላ እንዲገባ ኢየሱስን ባይጠይቀውም እንኳ ከሰማይ የተናገረው ቃል በልጁ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን ያሳያል።—ሉቃስ 3:21, 22

4. ኢየሱስ የገባውን ቃል ምን ያህል አክብዶ ይመለከት ነበር?

4 ኢየሱስ ቃሉን በመጠበቅ ምንጊዜም ያስተማረውን ትምህርት በተግባር ያውል ነበር። የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብክና አምላክ ወደ ኢየሱስ የሳባቸውን ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲያደርግ አባቱ የሰጠውን ተልእኮ ከመፈጸም ምንም ነገር እንዲያዘናጋው አልፈቀደም። (ዮሐ. 6:44) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ አማካኝነት አዎ ሆነዋል” በማለት ኢየሱስ ምን ያህል ቃሉን ይጠብቅ እንደነበር ያረጋግጣል። (2 ቆሮ. 1:20) በእርግጥም ኢየሱስ ለአባቱ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ በመፈጸም ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ቀጥሎ ደግሞ አቅሙ በፈቀደው መጠን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ስላደረገ ሰው እንመለከታለን።

ጳውሎስ—እንደ ቃሉ የኖረ ሰው

5. ሐዋርያው ጳውሎስ ልንከተለው የሚገባ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

5 “ጌታ ሆይ፣ ምን ባደርግ ይሻላል?” (ሥራ 22:10) ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ ክብር የተጎናጸፈው ጌታ ኢየሱስ በራእይ በተገለጠለት ጊዜ እነዚህን ከልብ የመነጩ ቃላት በመናገር ጌታ ለሰጠው አመራር ምላሽ ሰጥቷል፤ በወቅቱ ኢየሱስ የተገለጠለት ደቀ መዛሙርቱን ከማሳደድ እንዲታቀብ ለማድረግ ነበር። ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ከተገለጠለት በኋላ ሳኦል ቀደም ሲል ለፈጸማቸው ድርጊቶች በትሕትና ንስሐ በመግባት ተጠመቀ፤ እንዲሁም ለአሕዛብ ስለ ኢየሱስ ምሥክርነት እንዲሰጥ የተሰጠውን ልዩ ተልእኮ ተቀበለ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጳውሎስ ኢየሱስን “ጌታዬ” ብሎ ይጠራው የነበረ ሲሆን ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ለኢየሱስ እንደሚገዛ በሚያሳይ መንገድ ኖሯል። (ሥራ 22:6-16፤ 2 ቆሮ. 4:5፤ 2 ጢሞ. 4:8) ጳውሎስ “‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የምትሉኝ፣ የምለውን ግን የማታደርጉት ለምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስ እንደነቀፋቸው ዓይነት ሰዎች አልነበረም። (ሉቃስ 6:46) አዎ፣ ኢየሱስ ጌታዬ ብለው የሚጠሩት  ሰዎች ሁሉ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ቃላቸውን እንዲጠብቁ ይፈልጋል።

6, 7. (ሀ) ጳውሎስ ቆሮንቶስን በድጋሚ ለመጎብኘት የነበረውን ዕቅድ የለወጠው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እምነት የሚጣልበት ሰው እንዳልሆነ አድርገው የከሰሱት ሰዎች ክሳቸው መሠረተ ቢስ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡን የተሾሙ ወንድሞች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

6 ጳውሎስ ብዙ ጉባኤዎችን በማቋቋምና ዳግመኛ ሄዶ በመጎብኘት የመንግሥቱን መልእክት በትንሹ እስያና በአውሮፓ በቅንዓት አዳርሷል። አንዳንድ ጊዜ፣ የጻፈውን ነገር እውነተኝነት ለማረጋገጥ መማል አስፈልጎት ነበር። (ገላ. 1:20) በቆሮንቶስ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ጳውሎስ እምነት የሚጣልበት ሰው እንዳልሆነ አድርገው በከሰሱት ጊዜ “አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ሁሉ እኛ ለእናንተ የምንናገረው ቃልም አዎ ከሆነ አይ ማለት ሊሆን አይችልም” ሲል ተሟግቷል። (2 ቆሮ. 1:18) ይህን በጻፈበት ወቅት ኤፌሶንን ለቆ በመቄዶንያ በኩል ወደ ቆሮንቶስ እየተጓዘ ነበር። በመጀመሪያ ወደ መቄዶንያ ከመሄዱ በፊት ቆሮንቶስን ዳግመኛ ለመጎብኘት አቅዶ ነበር። (2 ቆሮ. 1:15, 16) ሆኖም በዛሬው ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንደሚያጋጥማቸው አንዳንድ ጊዜ የጉብኝት ፕሮግራም መቀየር ግድ ይሆናል። እንዲህ ያለ ማስተካከያ የሚደረገው እንዲሁ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ወይም ለራስ ጥቅም ተብሎ ሳይሆን አንዳንድ ያልታሰቡ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ነው። ጳውሎስ ቆሮንቶስን ለመጎብኘት የነበረውን ዕቅድ ያዘገየው ለጉባኤው ጥቅም ሲል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

7 ጳውሎስ፣ መጀመሪያ ላይ ወደ ቆሮንቶስ ለመሄድ ዕቅድ ካወጣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በቆሮንቶስ ጉባኤ ክፍፍል እንደተፈጠረና የሥነ ምግባር ብልግና ቸል እንደተባለ የሚገልጽ አሳሳቢ የሆነ ሪፖርት ደረሰው። (1 ቆሮ. 1:11፤ 5:1) ሁኔታውን ለማስተካከል ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ ላይ ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቷቸዋል። ከዚያም ጳውሎስ ከኤፌሶን በቀጥታ ወደ ቆሮንቶስ ከመጓዝ ይልቅ ወንድሞቹ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ጊዜ ለመስጠት ወሰነ፤ ይህን ማድረጉ ከጊዜ በኋላ ሲሄድ ጉብኝቱ ይበልጥ አበረታች እንዲሆን የተሻለ አጋጣሚ የሚከፍት ነበር። ጳውሎስ ዕቅዱን የለወጠበት ምክንያት ይህ መሆኑን ለማረጋገጥ በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወደ ቆሮንቶስ እስካሁን ያልመጣሁት ለባሰ ሐዘን እንዳልዳርጋችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ አምላክ በገዛ ነፍሴ ላይ ይመሥክርብኝ።” (2 ቆሮ. 1:23) እኛም ጳውሎስን እንደተቹት ዓይነት ሰዎች እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል! ከዚህ ይልቅ በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡን የተሾሙ ወንድሞች ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። ጳውሎስ ክርስቶስን እንደመሰለ ሁሉ እኛም ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ መከተላችን የተገባ ነው።—1 ቆሮ. 11:1፤ ዕብ. 13:7

ሌሎች ግሩም ምሳሌዎች

8. ርብቃ ልንከተለው የሚገባ ምን ምሳሌ ትታለች?

8 “አዎን፤ እሄዳለሁ።” (ዘፍ. 24:58) ርብቃ ለእናቷና ለወንድሟ እንዲህ ስትል በአጭሩ መልስ በመስጠት የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ሚስት ለመሆን በዚያው ቀን ከቤተሰቧ ተለይታ ከማታውቀው ሰው ጋር ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች። (ዘፍ. 24:50-58) ርብቃ ቃሏን በመጠበቅ አምላክን የምትፈራ ታማኝ ሚስት ሆናለች። በቀሪው የሕይወት ዘመኗ በተስፋዪቱ ምድር መጻተኛ ሆና በድንኳን ኖራለች። ታማኝ ሆና በመገኘቷ አስቀድሞ የተነገረለት ዘር ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት በመሆን ተባርካለች።—ዕብ. 11:9, 13

9. ሩት ቃሏን አክብራ የተገኘችው እንዴት ነው?

9 “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን።” (ሩት 1:10) ይህን ቃል ደጋግመው ለኑኃሚን የተናገሩት ባሎቻቸውን በሞት ያጡት ሞዓባውያኑ ሩትና ዖርፋ ሲሆኑ ይህን ያሉት መበለት የሆነችው አማታቸው ከሞዓብ ወደ ቤተልሔም መመለስ በጀመረች ጊዜ ነበር። በመጨረሻ በኑኃሚን ውትወታ ዖርፋ ወደ አገሯ ተመለሰች። ሩት ግን በቃሏ ጸንታለች። (ሩት 1:16, 17ን አንብብ።) ቤተሰቧንና የሞዓብን የሐሰት ሃይማኖት እርግፍ አድርጋ ትታ ከኑኃሚን ጋር በታማኝነት ተጣብቃለች። ይሖዋን በታማኝነት በማምለክ የጸናች ሲሆን ማቴዎስ የክርስቶስን የዘር ሐረግ ሲዘረዝር ከጠቀሳቸው አምስት ሴቶች መካከል አንዷ በመሆን ወሮታ አግኝታለች።—ማቴ. 1:1, 3, 5, 6, 16

10. ኢሳይያስ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

 10 “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ።” (ኢሳ. 6:8) ኢሳይያስ ይህን ከመናገሩ በፊት አንድ አስደናቂ ራእይ የተመለከተ ሲሆን በራእዩ ላይ ይሖዋ ከእስራኤል ቤተ መቅደስ በላይ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር። ኢሳይያስ ይህን አስደናቂ ራእይ እየተመለከተ ሳለ ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” ሲል ሰማ። ይህ ጥያቄ የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ የአምላክን መልእክት ዓመፀኛ ለሆኑት ሕዝቦቹ የሚያደርስ ሰው ለማግኘት የቀረበ ጥሪ ነበር። ኢሳይያስ ከሰጠው ምላሽ ጋር በሚስማማ መንገድ ቃሉን አክብሮ ኖሯል። ኃይለኛ የውግዘት መልእክቶችን እንዲሁም እውነተኛው አምልኮ ዳግመኛ እንደሚቋቋም የሚገልጹ ግሩም ተስፋዎችን በማወጅ ከ46 ዓመታት በላይ በታማኝነት ነቢይ ሆኖ አገልግሏል።

11. (ሀ) የገባነውን ቃል መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቃላቸውን ሳይጠብቁ በመቅረታቸው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ የሚሆኑን አንዳንድ ሰዎች እነማን ናቸው?

11 ይሖዋ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች በቃሉ ላይ እንዲሰፍሩ ያደረገው ለምንድን ነው? የገባነውን ቃል አክብረን መኖራችንስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ቃላቸውን የማይጠብቁ” ሰዎች “ሞት ይገባቸዋል” ተብለው ከሚፈረጁት መካከል እንደሆኑ በማመልከት በግልጽ ያስጠነቅቃል። (ሮም 1:31, 32) መጽሐፍ ቅዱስ ከሚዘረዝራቸው ቃላቸውን ሳያከብሩ የቀሩ መጥፎ ምሳሌዎች መካከል የግብፁ ፈርዖን፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲሁም ሐናንያና ሰጲራ ይገኙበታል። ሁሉም ውድቀት የደረሰባቸው ሲሆን ለእኛ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆኑናል።—ዘፀ. 9:27, 28, 34, 35፤ ሕዝ. 17:13-15, 19, 20፤ ሥራ 5:1-10

12. ቃላችንን ጠብቀን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

12 “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” የምንኖር እንደመሆናችን መጠን ‘ታማኝ ባልሆኑ’ ሰዎች ተከበናል፤ እነዚህ ሰዎች “ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፣ ኃይሉን ግን ይክዳሉ።” (2 ጢሞ. 3:1-5) በተቻለን መጠን ከእንዲህ ዓይነት ክፉ ባልንጀርነት መራቅ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ቃላቸውን ለማክበር ከሚጥሩ ሰዎች ጋር አዘውትረን መሰብሰብ አለብን።—ዕብ. 10:24, 25

“አዎ” ብላችሁ የገባችሁት የላቀ ክብደት የሚሰጠው ቃል

13. አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ “አዎ” ሲል የሚገባው የላቀ ክብደት የሚሰጠው ቃል የትኛው ነው?

13 አንድ ሰው ከሚገባው ቃል ሁሉ የላቀ ክብደት የሚሰጠው ራሱን ለአምላክ ሲወስን የሚገባው ቃል ነው። ራሳቸውን በመካድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን የሚፈልጉ ሰዎች በሦስት የተለያዩ ወቅቶች ውሳኔያቸውን በተመለከተ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች “አዎ” የሚል መልስ መስጠት የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ማቴ. 16:24) ሁለት ሽማግሌዎች ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ያሰበን ሰው ሲያነጋግሩ ግለሰቡ “በእርግጥ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ልባዊ ፍላጎት አለህ?” የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል። ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ለመጠመቅ ሲፈልግ ሽማግሌዎቹ “በጸሎት አማካኝነት ራስህን ለይሖዋ ወስነሃል?” ብለው ይጠይቁታል። በመጨረሻም በጥምቀት ቀን እጩ ተጠማቂዎቹ “በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት በማመን ከኃጢአታችሁ ንስሐ ገብታችሁ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ  ራሳችሁን ወስናችኋል?” የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። በዚህ ጊዜ ተጠማቂዎቹ አምላክን ለዘላለም ለማገልገል የገቡትን ቃል በተመለከተ በምሥክሮች ፊት “አዎ” የሚል መልስ ይሰጣሉ።

“አዎ” ብለህ የገባኸውን የላቀ ክብደት የሚሰጠው ቃል አክብረህ እየኖርክ ነው?

14. አልፎ አልፎ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

14 በቅርብ ጊዜ የተጠመቅክም ሆንክ አምላክን ለአሥርተ ዓመታት ስታገለግል የቆየህ አልፎ አልፎ ራስህን መመርመርና እንዲህ እያልክ ራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል፦ ‘የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል፣ “አዎ” ስል የገባሁትን የላቀ ክብደት የሚሰጠው ቃል አሁንም አክብሬ እየኖርኩ ነው? ሕይወቴ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ኢየሱስን አሁንም እየታዘዝኩ ነው?’—2 ቆሮንቶስ 13:5ን አንብብ።

15. ቃላችንን ማክበራችን አስፈላጊ የሆነው በየትኞቹ የሕይወታችን ዘርፎች ነው?

15 ራሳችንን ስንወስን የፈጸምነውን መሐላ ጠብቆ መኖር፣ አስፈላጊ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮችም ታማኞች መሆን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል ባለትዳር ነህ? ከሆንክ የትዳር ጓደኛህን ለመውደድና ለመንከባከብ የገባኸውን ክቡር ቃለ መሐላ አክብረህ መኖርህን ቀጥል። አንድ ዓይነት የሥራ ውል ተፈራርመሃል? ወይም ደግሞ ቲኦክራሲያዊ መብቶችን ለማግኘት የሞላኸው ቅጽ አለ? እንግዲያው የገባኸውን ውል ወይም ቃል ፈጽም። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ግብዣ አቅርቦልህ ግብዣው ላይ ለመገኘት ተስማምተሃል? ከሆነ የተሻለ እንደሆነ የሚሰማህ ሌላ ግብዣ ስለቀረበልህ ብቻ አስቀድመህ የያዝከውን ቀጠሮ አታፍርስ። ወይም ደግሞ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ላገኘኸው ሰው ተመልሰህ ሄደህ እንደምታወያየው ቃል ገብተህለታል? ከሆነ በተቻለ መጠን ቃልህን ለመጠበቅ ጥረት አድርግ፤ እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ አገልግሎትህን ይባርክልሃል።—ሉቃስ 16:10ን አንብብ።

ሊቀ ካህናችንና ንጉሣችን ሊረዳን ይችላል

16. ቃላችንን ሳናከብር ብንቀር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በተለይ በአንደበት አጠቃቀማችን ረገድ ‘ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንደምንሰናከል’ ይገልጻል። (ያዕ. 3:2) ቃላችንን ሳናከብር እንደቀረን በምንገነዘብበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ አንድ ሰው ‘ሳያስብ በግዴለሽነት በመማል’ በደል ቢፈጽም ምሕረት የሚያገኝበት ዝግጅት ተደርጎ ነበር። (ዘሌ. 5:4-7, 11) እንዲህ ያለ ኃጢአት ለፈጸሙ ክርስቲያኖችም የሚያገለግል ፍቅራዊ ዝግጅት አለ። የሠራነውን ኃጢአት ለይሖዋ ከተናዘዝን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያከናውነው አገልግሎት አማካኝነት ምሕረት ያደርግልናል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) ይሁንና የአምላክን ሞገስ ላለማጣት እንዲህ ያሉ ኃጢአቶችን ልማድ ባለማድረግና ሳናስብ የተናገርነው ነገር ያስከተለውን ጉዳት ለማካካስ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ ማሳየት ይኖርብናል። (ምሳሌ 6:2, 3) እርግጥ ነው፣ መፈጸም የማንችለውን ቃል ከመግባታችን በፊት በጉዳዩ ላይ በጥሞና ማሰባችን እጅግ የተሻለ ነው።—መክብብ 5:2ን አንብብ።

17, 18. ቃላቸውን ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ ምን ግሩም ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

17 የገቡትን ቃል ለማክበር ጥረት የሚያደርጉ የይሖዋ አምላኪዎች በሙሉ እጅግ አስደሳች የሆነ ጊዜ ይጠብቃቸዋል! በመንፈስ የተቀቡት 144,000 ክርስቲያኖች በሰማይ የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ፤ እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ “ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛሉ።” (ራእይ 20:6) በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ምድር ገነት ሆና በክርስቶስ መንግሥት በምትተዳደርበት ጊዜ ከሚገኘው ጥቅም ይቋደሳሉ። በዚያን ጊዜ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ፍጽምና ላይ እንዲደርሱ የሚያስችል እርዳታ ያገኛሉ።—ራእይ 21:3-5

18 በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ የመጨረሻውን ፈተና በታማኝነት ካለፍን ከዚያ በኋላ የማንንም ቃል የምንጠራጠርበት ምክንያት አይኖርም። (ራእይ 20:7-10) ያን ጊዜ ቃላችን “አዎ” ከሆነ አዎ ይሆናል፣ “አይደለም” ከሆነ ደግሞ አይደለም ይሆናል። በዚያን ወቅት በሕይወት የሚኖር ሰው ሁሉ “የእውነት አምላክ” የሆነውን በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን ይሖዋን ፍጹም በሆነ መንገድ መምሰል ይችላል።—መዝ. 31:5