“ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ።”​—ዘዳ. 31:12

1, 2. ከትላልቅ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?

ላለፉት በርካታ ዓመታት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችና የአውራጃ ስብሰባዎች በዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ክንውኖች ሆነው ቆይተዋል። ብዙዎቻችን አስደሳች በሆኑት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተናል፤ ምናልባትም አንዳንዶች ለብዙ አሥርተ ዓመታት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተካፍለው ይሆናል።

2 በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊትም የአምላክ ሕዝቦች ቅዱስ ስብሰባዎችን ያደርጉ ነበር። በዘመናችን ለሚደረጉት ትላልቅ ስብሰባዎች ተምሳሌት የሆኑ በጥንት ጊዜ የተደረጉ አንዳንድ ስብሰባዎችን እስቲ እንመልከት፤ እንዲሁም በጥንት ጊዜና በዘመናችን በሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች መካከል ያለውን ተመሳሳይነትና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መካፈል የሚያስገኝልንን ጥቅም እንመለከታለን።​—መዝ. 44:1፤ ሮም 15:4

ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ስብሰባዎች​—ጥንትና ዛሬ

3. (ሀ) በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ካደረጓቸው ትላልቅ ስብሰባዎች የመጀመሪያው ተለይቶ የሚታወቀው በምንድን ነው? (ለ) እስራኤላውያን ለስብሰባ የሚጠሩት እንዴት ነበር?

3 በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች ካደረጓቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ሁሉ የመጀመሪያው በሲና ተራራ ግርጌ የተደረገው ነው። ይህ ስብሰባ በንጹሕ አምልኮ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን ነው። በቦታው የተገኙት ሁሉ ፈጽሞ ሊረሱት በማይችሉት በዚያ አስደሳች ወቅት ይሖዋ ለእስራኤላውያን ኃይሉን ያሳያቸው ከመሆኑም በላይ ሕጉን ሰጥቷቸዋል። (ዘፀ. 19:2-9, 16-19፤ ዘፀአት 20:18ን እና ዘዳግም 4:9, 10ን አንብብ።) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስራኤላውያን የተለዩ የአምላክ ሕዝብ ሆኑ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በሌሎች ጊዜያትም ሕዝቡን ለመሰብሰብ የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። “ማኀበረ ሰቡ በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ” እንዲሰበሰብ ለመጥራት የሚያገለግሉ ሁለት የብር መለከቶችን እንዲሠራ ሙሴን አዘዘው። (ዘኍ. 10:1-4) እንዲህ ባሉ ወቅቶች ምን ያህል ደስታ ሊኖር እንደሚችል መገመት አያዳግትም!

4, 5. በሙሴና በኢያሱ አማካኝነት የተደራጁት ትላልቅ ስብሰባዎች ወሳኝ ነበሩ የምንለው ለምንድን ነው?

 4 እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ያደረጉት ጉዞ ሊገባደድ ሲል ሙሴ ሕዝቡን ሰበሰበ። በአንጻራዊ ሁኔታ አዲስ ለሆነው ለዚህ ብሔር ይህ ወቅት ወሳኝ ነበር፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርቦ ነበር። በመሆኑም ሙሴ፣ ይሖዋ እስካሁን ያደረገላቸውንና ወደፊት የሚያደርግላቸውን ነገር ለወንድሞቹ መንገር የሚችልበት ትክክለኛው ወቅት ይህ ነበር።​—ዘዳ. 29:1-15፤ 30:15-20፤ 31:30

5 በየተወሰነ ጊዜ የሚካሄድ፣ ትምህርት የሚሰጥበት ስብሰባ እንደሚኖር ሙሴ ለሕዝቡ የተናገረው በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በእስራኤል ውስጥ የሚኖሩ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ልጆችና መጻተኞች ‘እንዲሰሙና አምላካቸውን መፍራት እንዲማሩ እንዲሁም የሕጉን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ’ በየሰባት ዓመቱ በዳስ በዓል ወቅት ይሖዋ በመረጠው ቦታ መሰብሰብ ነበረባቸው። (ዘዳግም 31:1, 10-12ን አንብብ።) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክ ሕዝቦች እንደ አንድ ብሔር በተደራጁበት ወቅት የይሖዋን ቃልና ዓላማ ለመመርመር በየተወሰነ ጊዜ ይሰበሰቡ ነበር። እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ከተቆጣጠሩ በኋላም ኢያሱ ሕዝቡን ሰበሰበ። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው አረማዊ ብሔራት ስለነበሩ እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ለመቀጠል ባደረጉት ቁርጥ ውሳኔ ለመጽናት ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ኢያሱ ተረድቶ ነበር። ሕዝቡም አምላክን ለማገልገል ቃል ገባ።​—ኢያሱ 23:1, 2፤ 24:1, 15, 21-24

6, 7. በዘመናዊ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ትላልቅ ስብሰባዎች የትኞቹ ናቸው?

6 በዘመናዊ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክም ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ይኸውም ከቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ወይም ቅዱሳን መጻሕፍትን ከመረዳት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ለውጦች የተደረጉባቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። (ምሳሌ 4:18) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ ያደረጉት በ1919 ነበር፤ ይህ ስብሰባ የተከናወነው በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። በስብሰባው ላይ 7,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ መካሄድ እንዳለበት ይፋ የሆነውም በዚህ ወቅት ነው። በ1922 በዚያው ቦታ በተደረገ የዘጠኝ ቀን ስብሰባ ላይ ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ንግግር አቅርቦ ነበር፤ አድማጮቹ ለስብከቱ ሥራ ትኩረት እንዲሰጡ እንዲህ በማለት አበረታቷቸው ነበር፦ “ለጌታ ታማኝና እውነተኛ ምሥክር ሁኑ። የባቢሎን ርዝራዦች በሙሉ እስኪወገዱ ድረስ በውጊያው ወደፊት ግፉ። መልእክቱን በስፋት ብሎም ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመሄድ አውጁ። ይሖዋ፣ አምላክ እንደሆነና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደሆነ የዓለም ሕዝብ ማወቅ ይኖርበታል። ይህ የቀኖች ሁሉ ቀን ነው። እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” በዚያ የነበሩትን ተሰብሳቢዎች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ይህን ማበረታቻ በታላቅ ደስታ ተቀብለውታል።

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ የሚለውን ስም በማግኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር። ከዚያም በ1935 በዋሽንግተን ዲ. ሲ. በተደረገው ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “በዙፋኑና በበጉ ፊት” እንደቆሙ ተደርገው የተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እነማን እንደሆኑ አብራራ። (ራእይ 7:9-17) በ1942 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ሳለ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድም ናታን ኖር “ሰላም​—ዘላቂ ሊሆን ይችላል?” በሚል ጭብጥ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር ሰጥቶ ነበር፤ ንግግሩን ሲሰጥ በራእይ 17 ላይ የተገለጸውን “ደማቅ ቀይ አውሬ” ማንነት ግልጽ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ከጦርነቱ በኋላ ከፍተኛ የስብከት ሥራ እንደሚካሄድ አመልክቷል።

በ1950 በኒው ዮርክ ሲቲ የተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ

8, 9. አንዳንድ ስብሰባዎች ልዩ ስሜት የሚፈጥሩ የሆኑት ለምንድን ነው?

8 በ1946 በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ በተደረገ “ደስተኛ ሕዝቦች” በተባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ “በመልሶ ግንባታውና በማስፋፋቱ ሥራ ወቅት የነበሩ ችግሮች” በሚል ጭብጥ ወንድም ኖር ያቀረበው ንግግር ፈጽሞ የማይረሳ ነው። ንግግሩ በአድማጮች ላይ የፈጠረውን ስሜት አስመልክቶ አንድ ወንድም እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ “በዚያ ምሽት መድረክ ላይ ከእሱ ጀርባ የመቆም መብት አግኝቼ ነበር፤ ስለ ሥራውና  በብሩክሊን የሚገኘውን የቤቴል ቤትና ፋብሪካ ለማስፋፋት ስለተያዘው ዕቅድ ሲናገር በዚያ የነበሩት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች ከደስታቸው የተነሳ በተደጋጋሚ ያጨበጭቡ ነበር። ከመድረክ ሆኖ የሰዎቹን ፊት ማየት ባይቻልም ደስታቸውን ማንበብ ግን ይቻል ነበር።” በ1950፣ በኒው ዮርክ ሲቲ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በማግኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም በተገቢው ቦታ ላይ እንዲመለስ ያደረገ በዘመናዊ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ትርጉም መሆን ችሏል።​—ኤር. 16:21

9 ስደትና እገዳ በነበሩባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ታማኝ የይሖዋ ሕዝቦች ከዚያ ወቅት በኋላ ያደረጓቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ልዩ ስሜት የሚፈጥሩ ነበሩ። ለምሳሌ አዶልፍ ሂትለር የይሖዋ ምሥክሮችን ከጀርመን ለማጥፋት ዝቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በ1955 የአውራጃ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት፣ ሂትለር ይፎክርበት የነበረውን ቦታ 107,000 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አጥለቅልቀውት ነበር። በዚህ ወቅት ብዙዎቹ የደስታ እንባ ያነቡ ነበር! “ለአምላክ ማደር” በሚል ጭብጥ በ1989 በፖላንድ በተካሄዱት ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ከተገኙት 166,518 ልዑካን መካከል ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትና ከቺኮዝላቫኪያ እንዲሁም ከሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የመጡ ብዙ ወንድሞች ነበሩ። አንዳንዶች 15 እና 20 ሆነው ይሰበሰቡ ስለነበር እንዲህ ባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ነው። ኪየቭ፣ ዩክሬን ውስጥ በተደረገው “መለኮታዊ ትምህርት” በተሰኘው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ደግሞ 7,402 ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ይህም በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት አኃዞች ከፍተኛው ነው፤ በዚያ የነበሩት ተሰብሳቢዎች ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ!​—ኢሳ. 60:22፤ ሐጌ 2:7

10. ለአንተ ልዩ ትዝታ የጣሉብህ የአውራጃ ስብሰባዎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?

10 ምናልባት በአንተም ላይ ልዩ ትዝታ የጣሉ የአውራጃ ስብሰባዎች ወይም ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይኖሩ ይሆናል። መጀመሪያ የተካፈልክበትን አሊያም የተጠመቅክበትን የአውራጃ ስብሰባ ታስታውሳለህ? እነዚህ ስብሰባዎች በሕይወትህ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የምትሰጣቸው መንፈሳዊ ክንውኖች እንደሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህን ወቅቶች ከልብህ ፈጽሞ ልታወጣቸው አይገባም!​—መዝ. 42:4

በቋሚነት የሚያሳልፏቸው አስደሳች ወቅቶች

11. አምላክ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በቋሚነት የሚያከብሯቸውን የትኞቹን በዓላት አዘጋጅቶ ነበር?

11 እስራኤላውያን በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ሦስት በዓላትን እንዲያከብሩ ይሖዋ ይጠብቅባቸው ነበር፤ እነዚህም የቂጣ በዓል፣ የመከር በዓልና (ከጊዜ በኋላ ጴንጤቆስጤ ተብሏል) የዳስ በዓል ናቸው። አምላክ እነዚህን በዓላት አስመልክቶ ሲናገር “በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረብ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀ. 23:14-17፤ ዘዳ. 16:16) በርካታ የቤተሰብ ራሶች፣ እነዚህ በዓላት ያላቸውን መንፈሳዊ ጥቅም ስለተገነዘቡ ቤተሰባቸውን በሙሉ ይዘው በቦታው ይገኙ ነበር።​—1 ሳሙ. 1:1-7፤ ሉቃስ 2:41, 42

12, 13. እስራኤላውያን በዓመታዊ በዓላት ላይ ለመገኘት የሚያደርጉት ጉዞ ምን ይመስል ነበር?

12 አንድ እስራኤላዊ ቤተሰብ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገው ጉዞ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ዮሴፍና ማርያም ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ትናንሽ ልጆችን ይዘህ  በእግር እንዲህ ያለውን ጉዞ ማድረግ ቢኖርብህ ምን ያህል ጊዜ የሚወስድብህ ይመስልሃል? ኢየሱስ በልጅነቱ ወደ ኢየሩሳሌም ስላደረገው ጉዞ ከሚተርከው ዘገባ መረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ባሉ ወቅቶች ከወዳጅ ዘመድ ጋር በቡድን ሆኖ መጓዝ የተለመደ ነገር ነበር። ቤተሰቡ ከዘመዶቻቸው ጋር በሚያደርጉት ጉዞ ላይ አብረው ያድሩና ምግባቸውን ያዘጋጁ ስለነበር የሚያሳልፉት ጊዜ የማይረሳ ትዝታ እንደሚጥልባቸው ጥርጥር የለውም። በጉዟቸው ወቅት በማያውቁት አካባቢ ማደሪያ ማመቻቸት ቢኖርባቸውም ለደኅንነታቸው የሚያሰጋ ሁኔታ የነበረ አይመስልም፤ ምክንያቱም የ12 ዓመት ልጅ የነበረው ኢየሱስ በራሱ መንቀሳቀስ እንዲችል ነፃነት ተሰጥቶት ነበር። ይህ ጊዜ፣ በተለይ ለታዳጊዎች ከአእምሮ የማይጠፋ ትዝታ እንደሚጥልባቸው መገመት አያዳግትም!​—ሉቃስ 2:44-46

13 እስራኤላውያን ከትውልድ አገራቸው ውጭ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው መኖር ሲጀምሩ ደግሞ በዓላት ላይ ለመገኘት ከተለያዩ አገሮች መምጣት ይጠበቅባቸው ነበር። ለምሳሌ በ33 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የተገኙ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች የመጡት እንደ ጣሊያን፣ ሊቢያ፣ ቀርጤስ፣ ትንሿ እስያና ሜሶጶጣሚያ ካሉ አካባቢዎች ነበር፤ ይህም እንዲህ ላሉ በዓላት አድናቆት እንዳላቸው ያሳያል።​—ሥራ 2:5-11፤ 20:16

14. እስራኤላውያን በዓመታዊ በዓላት ላይ መካፈላቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸው ነበር?

14 እነዚህ ጉዞዎች ለታማኝ እስራኤላውያን ልዩ ስሜት የሚፈጥሩበት ዋነኛ ምክንያት አምላክን ከሚወዱ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻቸው ጋር ይሖዋን ማምለክ መቻላቸው ነው። በዓላቱ በታዳሚዎቹ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥሩ ነበር? የዚህን ጥያቄ መልስ፣ ይሖዋ የዳስ በዓልን አስመልክቶ ለሕዝቡ በሰጠው ትእዛዝ ላይ ማግኘት እንችላለን፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ። እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእህል ምርትህና በጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል።”​—ዘዳ. 16:14, 15፤ ማቴዎስ 5:3ን አንብብ።

ለአውራጃ ስብሰባዎች አድናቆት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

15, 16. በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ምን ዓይነት መሥዋዕትነቶችን መክፈል ጠይቆብሃል? እንዲህ ያለው መሥዋዕትነት አያስቆጭም የምትለው ለምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በጥንት ዘመን ከሚደረጉ ስብሰባዎች ግሩም ትምህርት ማግኘት ይችላሉ! ምንም እንኳ ከትላልቅ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ ባለፉት መቶ ዘመናት ብዙ ለውጦች ቢደረጉም በዘመናችን የሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ጥንት የአምላክ ሕዝቦች ያደርጓቸው ከነበሩት ስብሰባዎች ጋር የሚመሳሰሉባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቅባቸው ነበር። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ያም ሆኖ የምንከፍለው መሥዋዕትነት የሚያስቆጭ አይደለም። ጥንትም ሆነ ዛሬ እንዲህ ያሉ ወቅቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ክንውኖች ናቸው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ፣ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ጠንካራ ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት የሚረዱ ትምህርቶች እናገኛለን። በተጨማሪም የአውራጃ ስብሰባዎች የተማርነውን ነገር ሥራ ላይ እንድናውል ያነሳሱናል፤ ችግር ውስጥ እንዳንገባ ይጠብቁናል፤ እንዲሁም ሸክም የሚሆኑብንን ነገሮች አስወግደን ደስታ ሊሰጡን በሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ ያበረታቱናል።​—መዝ. 122:1-4

ደቡብ ኮሪያ

16 ምንጊዜም ቢሆን በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አስደሳች ነው። በ1946 ስለተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ የቀረበ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ደስተኛ የሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ ተሰባስበው ማየት ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፤ ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ በስብሰባው የተገኙት ሁሉ በኦርኬስትራ ታጅበው ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጡትን የመንግሥቱን መዝሙሮች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲዘምሩ መስማት ነው።” ሪፖርቱ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍሉ፣ ከልዑካኑ መካከል በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞችን መዝግቦ ነበር፤ እነዚህ ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገል ያላቸው ልባዊ ፍላጎት ይህን በደስታ ለማከናወን አነሳስቷቸዋል።” አንተስ በአውራጃ ስብሰባዎች ወይም በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ  ስትገኝ እንዲህ ያለ ደስታ ይሰማሃል?​—መዝ. 110:3፤ ኢሳ. 42:10-12

17. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአውራጃ ስብሰባዎች በሚደራጁበት መንገድ ላይ ምን ዓይነት ለውጦች ተደርገዋል?

17 የአውራጃ ስብሰባዎች በሚደራጁበት መንገድ ላይ የተወሰኑ ለውጦች ተደርገዋል። ለምሳሌ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአውራጃ ስብሰባዎች እስከ ስምንት ቀን ይፈጁ እንደነበረ ያስታውሳሉ። የጠዋቱንና የከሰዓት በኋላውን ጨምሮ ስብሰባው እስከ ምሽት ድረስ ይቀጥል ነበር። በተጨማሪም መስክ አገልግሎት የስብሰባው ክፍል ነበር። አንዳንድ ጊዜ ስብሰባው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ይጀምርና እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ይዘልቅ ነበር። ፈቃደኛ ሠራተኞች ለተሰብሳቢዎቹ ቁርስ፣ ምሳና እራት ለማቅረብ ቀኑን ሙሉ በትጋት ይሠሩ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የአውራጃ ስብሰባዎች የሚካሄዱባቸው ቀናት አጥረዋል። እንዲሁም የምግብ ዝግጅት ስለቀረ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች የራሳቸውን ምግብ ይዘው ይመጣሉ፤ ይህ ደግሞ ትኩረታቸው ሳይከፋፈል ከመንፈሳዊው ገበታ ለመመገብ ያስችላቸዋል።

ሞዛምቢክ

18, 19. ከአውራጃ ስብሰባ ገጽታዎች አንተን የሚያጓጓህ የትኛው ነው? ለምንስ?

18 ከቀድሞ ጀምሮ የነበሩ አንዳንድ የአውራጃ ስብሰባ ገጽታዎች፣ ዛሬም ቢሆን በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው። “በተገቢው ጊዜ” የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ የምናገኘው በንግግሮች ብቻ ሳይሆን በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በሚወጡ አዳዲስ ጽሑፎች ጭምር ነው፤ እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ምግብ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና ትምህርቶች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል። (ማቴ. 24:45) አብዛኛውን ጊዜ በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚወጡ ጽሑፎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በሚገባ እንዲረዱ ያስችላሉ። ቀልብ የሚስቡት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ድራማዎች፣ ወጣት አዋቂ ሳይል ሁላችንም ልባችንን እንድንመረምር ብሎም ከአምላክ የራቀው ዓለም ከሚያሳድርብን ተጽዕኖ እንድንጠበቅ ይረዱናል። በተመሳሳይም የጥምቀት ንግግሩ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች እንድንመረምር አጋጣሚ ይከፍትልናል፤ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት በውኃ ሲጠመቁ መመልከትም ቢሆን አስደሳች ነው።

19 የንጹሕ አምልኮ ክፍል በመሆን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩት ትላልቅ ስብሰባዎች፣ የይሖዋ ሕዝቦች ደስተኛ እንዲሆኑ ብሎም ተፈታታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም ጭምር እሱን በተገቢው መንገድ እንዲያገለግሉት ረድተዋቸዋል። እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች በመንፈሳዊ እንድንነቃቃ፣ አዳዲስ ወዳጆችን እንድናፈራ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ኅብረት ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ የሚረዱን ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ሕዝቡን ለመባረክና ለመንከባከብ የሚጠቀምባቸው ወሳኝ መንገዶች ናቸው። በእርግጥም ሁላችንም በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከሚቀርቡት ክፍሎች አንዱም እንኳ እንዳያመልጠን የምንፈልግ ከሆነ ሁኔታችንን ማመቻቸት እንዳለብን ግልጽ ነው።​—ምሳሌ 10:22