በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ጥቅምት 2015

 ለቤተሰብ | ወጣቶች

ወደ ቤተሰቦችህ መመለስ ሲኖርብህ

ወደ ቤተሰቦችህ መመለስ ሲኖርብህ

ተፈታታኙ ነገር

አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ለመኖር ከቤት ይወጣሉ፤ ከዚያም ኑሮ ሲከብዳቸው ወደ ቤት ለመመለስ ያስባሉ። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞሃል?

እናትህንና አባትህን የምትወዳቸው ቢሆንም እንኳ ተመልሰህ እነሱ ጋ መግባት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሣራ * የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ራሴን ችዬ ለብቻዬ መኖሬ በራሴ ይበልጥ እንድተማመን አድርጎኛል። ወደ ቤተሰቦቼ ተመልሼ መግባቴ ግን እንደገና ልጅ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ።” ሪቻርድ የተባለ አንድ ወጣትም እንደ ሣራ ተሰምቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ቤት መመለስ አልፈለግኩም ነበር፤ ራሴን ችዬ መኖር ስላልቻልኩ ግን ምርጫ አልነበረኝም። ምንም ነገር የማይሳካለት ሰው እንደሆንኩ ተሰማኝ።”

አንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች እንደገና ራስህን ችለህ እንድትኖር ሊረዱህ ይችላሉ።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

የገንዘብ ችግር። በርካታ ወጣቶች ኑሮ ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚገነዘቡት ከቤት ወጥተው በራሳቸው መኖር ሲጀምሩ ነው፤ ይህ ደግሞ ያስደነግጣቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሪቻርድ “ራሴን ለማስተዳደር ስፍጨረጨር ያጠራቀምኩት ገንዘብ ሁሉ ተሟጠጠ” ብሏል። በ24 ዓመቷ ከቤት ወጥታ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የተመለሰችው ሼነ የምትባል ወጣትም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች፦ “ገንዘቤን በአግባቡ መያዝ ነበረብኝ። ከቤት ስወጣ ምንም ገንዘብ አልነበረኝም፤ እንዲያውም ወደ ቤት ስመለስ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቄ ነበር።” *

ሥራ ማጣት። አንድ ሰው ራሱን ችሎ ለመኖር የሚያስችል የተሻለ የሚባለውን ዕቅድ ቢያወጣ እንኳ ከሥራ ሲፈናቀል ዕቅዱ ሁሉ ሊከሽፍበት እንደሚችል ሼነ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “የተመረቅኩት በሕክምናው መስክ ሲሆን አንድ ድርጅት ሥራ እንዳገኝ ረዳኝ። ይሁን እንጂ ከሥራ ስፈናቀል ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ። የምኖረው በገጠራማ አካባቢ በመሆኑ በተማርኩት መስክ ሥራ የማግኘት አጋጣሚ አልነበረኝም።”

ከእውነታው የራቀ ነገር መጠበቅ። አንዳንድ ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡት ራሳቸውን ለማስተዳደር ዝግጁ ሳይሆኑ ነው። ብዙውን ጊዜ የሚሠሩት ሥራ ከጠበቁት በላይ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ራስን ችሎ መኖር በጉጉት የጠበቁትን ያህል አስደሳች እንዳልሆነ ሲገነዘቡ ተስፋ ይቆርጣሉ። ራስን ችሎ መኖር ይህን ያህል ከባድ ይሆናል ብለው እንዳልጠበቁ ግልጽ ነው።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

ወደ ቤት መመለስ እንደምትፈልግ ለወላጆችህ ንገራቸው። በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ አብራችሁ ተወያዩ፦ ቤት ለመቆየት ያሰብከው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ከእነሱ ጋር በምትኖርበት ጊዜ አንዳንድ የቤት ወጪዎችን በመሸፈን ረገድ ምን አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለህ? የትኞቹን የቤት ውስጥ ሥራዎች በመሥራት ማገዝ ትችላለህ? እንደገና ራስህን ችለህ ለመኖር ምን እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? ዕድሜህ ምንም ያህል ቢሆን ከቤተሰቦችህ ጋር እስከሆንክ ድረስ እነሱ ለሚያወጧቸው መመሪያዎች መገዛት እንዳለብህ አስታውስ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ዘፀአት 20:12

ስለ ገንዘብ አያያዝ ተማር። ዘ ኮምፕሊት ጋይድ ቱ ፐርሰናል ፋይናንስ፦ ፎር ቲኔጀርስ ኤንድ ኮሌጅ ስቱደንትስ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ገንዘብህን የምታወጣበት መንገድ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ስኬታማ መሆን አለመሆንህን ይጠቁማል። . . ‘የማያስፈልጉህን ነገሮች ለመግዛት ገንዘብ ማውጣት የለብህም’ የሚለውን ጠቃሚ መመሪያ ማወቅ ይኖርብሃል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሉቃስ 14:28

ምክር ለማግኘት ሞክር። ወላጆች ወይም ሌሎች ትላልቅ ሰዎች ከባንክ አጠቃቀም፣ ከበጀት አወጣጥና ወጪዎችን ከመክፈል ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። ማሪ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ሀ ብዬ መማር ነበረብኝ። አንዲት ጓደኛዬ አስፈላጊ የሆኑትንና ያልሆኑትን ወጪዎቼን በጽሑፍ እንዳሰፍር መከረችኝ። አብዛኞቹ ወጪዎቼ ፈጽሞ የማያስፈልጉ እንደሆኑ ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ! በተጨማሪም ራስን ችሎ ለመኖር በጣም ወሳኝ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 13:10

ዋናው ነገር የምትሠራው ምንድን ነው የሚለው ሳይሆን በሥራህ ምን ያህል ውጤታማ ነህ የሚለው ነው

ሥራ ለማግኘት ጥረት አድርግ። በሥራ ታሳልፈው የነበረውን ጊዜ ሥራ ለመፈለግ ተጠቀምበት። ሥራ መፈለግ ስትጀምር አንዳንዶች “የምትወደውን ሥራ መያዝ አለብህ” ሊሉህ እንደሚችሉ አትዘንጋ። ይሁን እንጂ ‘የምትመኘውን ሥራ’ ብቻ መፈለግ፣ ያሉህን አማራጮች ሊያጠብብህና ፊትህ ያሉ ሌሎች አጋጣሚዎችን እንዳታይ ዓይንህን ሊጋርደው ይችላል! ትኩረትህን በአንድ የተወሰነ የሥራ ዓይነት ላይ በማድረግ ጊዜ ከማባከን ይልቅ ሌሎች አማራጮችንም ለመመልከት ጥረት አድርግ። ዋናው ነገር የምትሠራው ምንድን ነው የሚለው ሳይሆን በሥራህ ምን ያህል ውጤታማ ነህ የሚለው ነው። እንዲያውም አንድ ሰው ልምድ እያገኘና በሙያው እየተካነ ሲሄድ ሥራውን ይበልጥ እንደሚወደው ማስተዋል ተችሏል። የምትሠራውን ነገር ለመውደድ የምትወደውን ነገር መሥራት አያስፈልግህም!

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.8 በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የኮሌጅ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው ከሆነ አንድ ተማሪ ሲመረቅ በአማካይ 33,000 የአሜሪካ ዶላር ዕዳ ይኖርበታል።