ሱዛን ስለ አምላክ መጠየቅ የጀመረችው ገና በሰባት ዓመቷ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የተፈጠረባት ጓደኛዋ የሆነው የዘጠኝ ዓመቱ አል በፖሊዮ ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ በሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ እርዳታ ይኖር ስለነበር ነው። የሱዛን ታሪክ በጥር 6, 2013 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እትም ላይ ወጥቷል።

ሱዛን አልን ሆስፒታል ሄዳ ከጠየቀችው በኋላ እናቷን “አምላክ በዚህ ትንሽ ልጅ ላይ እንዲህ የሚያደርገው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀቻት።

እናቷም “ቄሶች አምላክ ይህን ያደረገበት ምክንያት እንዳለው ይናገራሉ፤ እኔ ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላውቅም” ብላ መለሰችላት።

ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1954 ጆናስ ሳልክ የፖሊዮን ክትባት አገኘ፤ በዚህ ወቅት የሱዛን እናት ‘መድኃኒቱን ተመራምሮ እንዲያገኝ የረዳው አምላክ ሳይሆን አይቀርም’ በማለት ተናገረች።

ሱዛን ግን “አምላክ ቀድሞውኑም ቢሆን ሐኪሞቹን ቢመራቸው ኖሮ አል በሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ ለመጠቀም አይገደድም ነበር” ብላ መለሰች።

ሱዛን ስለ ልጅነት ሕይወቷ የጻፈችውን ሐሳብ ስታጠቃልል እንዲህ ብላለች፦ “[አል] ከስምንት ዓመት በኋላ ሞተ፤ በዚያን ጊዜ አምላክ የለም የሚል ጠንካራ አቋም ይዤ ነበር።”

እንደ ሱዛን አሳዛኝ ነገር የደረሰባቸው ወይም በሌሎች ላይ ሲደርስ ያዩ ብዙ ሰዎች አምላክን በተመለከተ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች በአምላክ መኖር አያምኑም። ሌሎች ደግሞ አምላክ መኖሩን ሙሉ በሙሉ ባይክዱም የአምላክን መኖር ይጠራጠራሉ።

በአምላክ መኖር የማያምኑትም ሆኑ የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ስለ ሃይማኖት ያውቃሉ። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲይዙ የሚያደርጋቸው በሃይማኖት ውስጥ የሚያዩት ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች በአእምሯቸው ውስጥ ለሚጉላሉ ከባድ ጥያቄዎች የሃይማኖት ተቋማት መልስ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ ይሰማቸዋል። የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? የሚገርመው፣ እነዚህ ሰዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎችም ያነሷቸዋል። እስቲ ብዙ ሰዎች አጋጣሚውን ቢያገኙ አምላክን መጠየቅ የሚፈልጓቸውን ሦስት ጥያቄዎችና መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንመልከት።

 1 “መከራ እንዲኖር የፈቀድከው ለምንድን ነው?”

ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች ‘አፍቃሪ የሆነ አምላክ ቢኖር ኖሮ አሳዛኝ ነገሮች እንዳይደርሱብን ይከላከልልን ነበር’ ብለው ይናገራሉ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ከእኛ የተለየ ባሕል ያላቸው ሰዎች የሚያደርጓቸው ነገሮች ለእኛ እንግዳ ሊሆኑብን አልፎ ተርፎም ሊያስደነግጡን ይችላሉ። የሚያደርጉትን ነገር በቀላሉ በመጥፎ ልንተረጉመው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ባሕል ውስጥ የሰዎችን ዓይን ዓይን እያዩ ማውራት የጨዋነት ምልክት እንደሆነ ይታያል፤ በሌላ ባሕል ደግሞ እንዲህ ማድረግ ጨዋነት የጎደለው ምግባር እንደሆነ ይቆጠራል። ሆኖም እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንደኛው ስህተት ሌላኛው ደግሞ ትክክል ነው ብለን መናገር አንችልም። ከዚህ ይልቅ ባሕሉን በደንብ ማወቅ ያስፈልገናል።

አምላክ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ለመረዳትም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ያስፈልገን ይሆን? ብዙ ሰዎች መከራ መኖሩ አምላክ እንደሌለ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች ግን አምላክ ስለመኖሩ እርግጠኞች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ የሚያስብበትና ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ከእኛ በጣም የተለየ ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) በዚህ ምክንያት እሱ የሚያደርገው ነገርና ቶሎ እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት መጀመሪያ ላይ ግራ ሊገባን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ የሚያደርጋቸውን ነገሮች መረዳት አንችልም” እንደሚሉት ያሉ አስተሳሰቦችን በጭፍን እንድንቀበል አያበረታታም። ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ መማራችንን እንድንቀጥል የሚያበረታታን ሲሆን አምላክ እርምጃ የሚወስደው ለምን እና መቼ እንደሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። * በተጨማሪም ወደ አምላክ መቅረብ እንችላለን።—ያዕቆብ 4:8

 2 “በሃይማኖት ውስጥ ግብዝነት የሚታየው ለምንድን ነው?”

ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች ‘አምላክ ቅንነትን የሚወድ ቢሆን ኖሮ እሱን እናመልካለን የሚሉ ሰዎች ይህን ያህል ግብዝ አይሆኑም ነበር’ ይላሉ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ አባቱ በጥሩ ሁኔታ የሚያሳድገውን አንድ ልጅ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር፤ ልጁ የአባቱን ቤት ትቶ በመውጣት መጥፎ አኗኗር ለመከተል ፈለገ እንበል። አባትየው የልጁን ሐሳብ ባይደግፍም የፈለገውን እንዲያደርግ ይፈቅድለታል። ልጁን በዚህ ሁኔታ ያየው ሰው አባቱ መጥፎ ሰው ነው ወይም ደግሞ አባት የለውም ብሎ ቢያስብ ተገቢ ነው? በፍጹም! በተመሳሳይም በሃይማኖት ውስጥ ግብዝነት የሚታየው አምላክ ሰዎች የፈለጉትን ጎዳና እንዲከተሉ ስለፈቀደላቸው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ በሃይማኖት ውስጥ የሚታየውን ግብዝነት ይጠላል። (ኤርምያስ 7:29-31፤ 32:35) ሰዎች ነፃ ምርጫቸውን ተጠቅመው የፈለጉትን ነገር እንዲያደርጉም ፈቅዷል። በአምላክ እንደሚያምኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች፣ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንና ራሳቸው ያወጧቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይከተላሉ።—ማቴዎስ 15:7-9

በአንጻሩ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ግብዝነት የለበትም። * ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) ይህ ፍቅር “ግብዝነት የሌለበት” መሆን አለበት። (ሮም 12:9) አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ይህን መሥፈርት አያሟሉም። ለምሳሌ ያህል፣ በ1994 በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ወቅት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖተኛ ሰዎች የእምነት አጋሮቻቸውን የተለየ ጎሣ ስላላቸው ብቻ ጨፍጭፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በዚህ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አልተካፈሉም፤ ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ሕይወት እንኳ አደጋ ላይ በመጣል የእምነት አጋሮቻቸውን እና የሌሎች ሰዎችን ሕይወት አትርፈዋል። እንዲህ ዓይነቱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ድርጊት ሃይማኖት ግብዝነት የሌለበት ሊሆን እንደሚችል ያረጋግጣል።

 3 “የተፈጠርነው ለምንድን ነው?”

ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች የሚከተለው ጉዳይ ያሳስባቸዋል፦ ‘ሰዎች 80 ወይም 90 ዓመት ብቻ የሚኖሩት ለምንድን ነው? እንዲህ በአጭሩ የሚቀጩትስ ለምንድን ነው?’

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ በአምላክ የማያምኑ ብዙ ሰዎች በተፈጥሮ ላይ የሚታየው ንድፍ የረቀቀ፣ የተወሳሰበና ሥርዓታማ መሆኑ ይህን ያዘጋጀ አካል እንዳለ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። በምድር ላይ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት ጨረቃ፣ የምንኖርባት ፕላኔትም ሆነች ሌሎች ፕላኔቶች በትክክለኛ ቦታ ላይ ስለተቀመጡ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ጽንፈ ዓለም የሚመራባቸው የተፈጥሮ ሕጎች በሚገባ የተስተካከሉና የታሰበባቸው በመሆኑ በጣም ትንሽ ለውጥ ቢደረግባቸው እንኳ በምድር ላይ ሕይወት ሊኖር እንደማይችል ያውቃሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ብዙ ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ዕድሜያችን አጭር መሆኑን አምላክ እንደሌለ የሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ይመለከቱታል፤ ይሁን እንጂ ተፈጥሮን በመመልከት ብቻ ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል። (ሮም 1:20) ፈጣሪ እነዚህን ነገሮች የሠራው በዓላማ ሲሆን እኛም የተፈጠርንበት ምክንያት ከዚህ ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው፤ ይህ ዓላማው አሁንም ቢሆን አልተለወጠም።—መዝሙር 37:11, 29፤ ኢሳይያስ 55:11

አምላክ መኖሩንና አንዳንድ ባሕርያቱን ከተፈጥሮ መገንዘብ የምንችል ቢሆንም አምላክ ስለ እሱ ዓላማ እንድናውቅ የሚፈልገው በዚህ መንገድ አይደለም። የአምላክን ዓላማና የተፈጠርንበትን ምክንያት ማወቅ የምንችለው አምላክ ራሱ ሲነግረን ነው። አምላክ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ነግሮናል። * የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንድትመረምር ይጋብዙሃል።

^ አን.17 አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ለማወቅ ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

^ አን.23 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

^ አን.29 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።