በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ንድፍ አውጪ አለው?

ብርሃን አመንጪው የሃዋይ ቦብቴይል ስኩዊድ

ብርሃን አመንጪው የሃዋይ ቦብቴይል ስኩዊድ

ምሽት ላይ ለአደን የሚወጣው የሃዋይ ቦብቴይል ስኩዊድ የራሱን ብርሃን ይፈጥራል፤ እንዲህ የሚያደርገው ሌሎች እንዲያዩት ለማድረግ ሳይሆን ራሱን ለመሰወር እንዲሁም በዙሪያው ካለው የጨረቃና የከዋክብት ብርሃን ጋር ለመመሳሰል ሲል ነው። የዚህ እንስሳ ሚስጥር ብርሃን አመንጪ ከሆኑ ባክቴሪያዎች ጋር ያለው ዝምድና ነው። እንዲህ ያለው ዝምድና ለእንስሳው ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር እኛንም የሚጠቅምበት መንገድ እንዳለ ይታመናል። ከጤንነታችን ጋር የተያያዘ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የሃዋይ ቦብቴይል ስኩዊድ የሚኖረው በሃዋይ ደሴቶች ዳርቻዎች በሚገኝ ጥርት ያለ ባሕር ውስጥ ነው። ይህ ስኩዊድ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃን ሲያርፍበት የሚፈጠረው ጥላ እንስሳው ከሥሩ ላሉ አዳኝ እንስሳት በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ቦብቴይል ስኩዊድ በኃይሉም ሆነ በሞገድ ርዝመቱ ከምሽቱ ብርሃን ጋር የሚመሳሰል ብርሃን ከሆዱ አካባቢ እንዲፈነጥቅ ያደርጋል። ይህም እንስሳው ጥላ እንዳይኖረው ስለሚያደርግ ከእይታ ይሰወራል። የስኩዊዱ “የተራቀቀ መሣሪያ” ብርሃን የማመንጨት ችሎታ ያላቸው ባክቴሪያዎችን የያዘው የአካል ክፍል ሲሆን እነዚህ ባክቴሪያዎች እንስሳውን ለመሰወር የሚያስችል ትክክለኛ መጠን ያለው ብርሃን ያመነጫሉ።

በተጨማሪም ባክቴሪያዎቹ ስኩዊዱ የሚተኛበትንና የሚነቃበትን ጊዜ ለማስተካከል ይረዳሉ ተብሎ ይታሰባል። በባክቴሪያዎችና ሰውነት ጊዜ ጠብቆ በየዕለቱ በሚያከናውናቸው ነገሮች መካከል ያለው ይህ ዝምድና በቦብቴይል ስኩዊድ ላይ ብቻ የሚታይ አለመሆኑ የተመራማሪዎችን ቀልብ ስቧል። ለምሳሌ በአጥቢ እንስሳት ውስጥ ከምግብ መዋሃድ ጋር የተያያዘ ሚና ያላቸው ባክቴሪያዎች፣ ሰውነት ጊዜ ጠብቆ በየዕለቱ ከሚያከናውናቸው ነገሮች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ይታሰባል። በሰውነታችን ውስጥ የሚከናወኑት ነገሮች ጊዜያቸው መዛባቱ የመንፈስ ጭንቀት፣ የስኳር በሽታ፣ ከልክ በላይ የሆነ ውፍረትና የእንቅልፍ ችግር ያስከትላል። በመሆኑም የስኩዊድ ባክቴሪያ በሚሠራበት መንገድ ላይ የሚደረገው ጥናት ከሰው ልጆች ጤንነት ጋር በተያያዘ አዲስ እውቀት ይፈነጥቃል ተብሎ ይታመናል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሃዋይ ቦብቴይል ስኩዊድ ብርሃን አመንጪ አካል በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?