አንዳንድ ሰዎች ቁማር ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ አደገኛ የሆነ ልማድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ቁማር መጫወት ስህተት ነው?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች ቁማር ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስከተደረገ ድረስ ምንም ጉዳት የሌለው መዝናኛ እንደሆነ ያስባሉ። መንግሥት እንደሚያዘጋጃቸው ሎተሪዎች ያሉ ሕጋዊ እውቅና የተሰጣቸው የቁማር ዓይነቶች ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም የሚያስችል ገቢ ያስገኛሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቁማር በቀጥታ አይናገርም። ይሁን እንጂ አምላክ ስለ ቁማር ምን እንደሚሰማው የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ይዟል።

ቁማር ሲባል በአብዛኛው በሌሎች ኪሳራ ገንዘብ ማግበስበስ ሲሆን ይህ ደግሞ “ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ጋር ይጋጫል። (ሉቃስ 12:15) እንዲያውም አንድን ሰው ቁማር እንዲጫወት የሚገፋፋው መጎምጀት ወይም ስግብግብነት ነው። ቁማር የሚያጫውቱ ድርጅቶች፣ ተጫዋቾቹ የማሸነፍ ዕድላቸው ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ ከመናገር ይልቅ ሊያገኙ ስለሚችሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ብቻ ያስተዋውቃሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ድርጅቶች፣ ሰዎች ሀብታም እሆናለሁ በሚል ምኞት ብዙ ገንዘብ እንደሚያስይዙ ያውቃሉ። ቁማር አንድ ሰው ራሱን ከስግብግብነት እንዲጠብቅ ከመርዳት ይልቅ በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት እንዲመኝ ያደርጋል።

ቁማር አንድን ሰው ራስ ወዳድ እንዲሆን ይኸውም ሌሎች ተጫዋቾች የሚያጡትን ገንዘብ ለራሱ ለማግበስበስ እንዲመኝ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “እያንዳንዱ ሰው ዘወትር የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” በማለት ያበረታታል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱ ደግሞ “የባልንጀራህ . . . የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” ይላል። (ዘፀአት 20:17) አንድ ቁማርተኛ አሸናፊ ለመሆንና ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሌሎች ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲከስሩ ይመኛል።

በተጨማሪም ዕድል፣ በረከት የሚያስገኝ ሚስጥራዊ ኃይል እንደሆነ አድርገን እንዳናስብ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። በጥንቷ እስራኤል በአምላክ ላይ እምነት ያልነበራቸው አንዳንድ ሰዎች ‘ዕድል ለተባለ ጣዖት’ ገበታ አዘጋጅተው ነበር። አምላክ ‘ዕድል ለተባለው ጣዖት’ የሚቀርበውን እንዲህ ያለ አምልኮ ተቀብሎት ነበር? በፍጹም፤ እንዲያውም አምላክ ‘በፊቴ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ የሚያስከፋኝን ነገር መርጣችኋል’ በማለት ተናግሯል።—ኢሳይያስ 65:11, 12

እርግጥ፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሕጋዊ እውቅና ከተሰጣቸው የቁማር ጨዋታዎች የሚገኘው ገቢ ለትምህርት፣ ለልማትና ለሌሎች ሕዝባዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ ይውላል። ይሁን እንጂ ገቢው ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ገንዘቡ የተገኘበትን መንገድ አይለውጠውም፤ ገንዘቡ የሚገኘው ደግሞ ስግብግብነትንና ራስ ወዳድነትን እንዲሁም አላንዳች ድካም አንድ ነገር ማግኘትን ከሚያበረታታ ጨዋታ ነው።

“የባልንጀራህ . . . የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።”ዘፀአት 20:17

 ቁማር መጫወት የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ [ሰዎች] ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) አንድን ሰው ቁማር እንዲጫወት የሚያነሳሳው ስግብግብነት ነው፤ “ስግብግብነት” ደግሞ መጥፎ ባሕርይ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንድናስወግዳቸው አጥብቆ ከሚመክረን በርካታ ባሕርያት መካከል አንዱ ነው።—ኤፌሶን 5:3

ቁማር የሚጫወት አንድ ሰው ያልደከመበትን ሀብት በቀላሉ ለማግኘት ስለሚመኝ የገንዘብ ፍቅር ያድርበታል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው” በማለት ይናገራል። ገንዘብ የማግኘት ፍላጎት የአንድን ሰው መላ ሕይወት ሊቆጣጠረው ይችላል፤ ይህም ግለሰቡ በጭንቀት እንዲዋጥና በአምላክ ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በገንዘብ ፍቅር የተጠመዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን ጉዳት በምሳሌያዊ አነጋገር ሲገልጽ “ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:10

ስግብግብነት፣ ሰዎች ባላቸው ገንዘብ እንዳይረኩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ደስታ ያሳጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም” ይላል።—መክብብ 5:10

በቁማር ጨዋታ ተስበው የገቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አደገኛ በሆነ የቁማር ሱስ ተጠምደዋል። ይህ ችግር እጅግ የተስፋፋ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቁማር ሱሰኞች እንዳሉ ይገመታል።

አንድ ምሳሌ “ከጅምሩ ወዲያው የተገኘ ርስት፣ በመጨረሻ በረከት አይኖረውም” ይላል። (ምሳሌ 20:21) በቁማር ሱስ የተያዙ ብዙ ሰዎች ለዕዳ ወይም ለኪሳራ የተዳረጉ ከመሆኑም ሌላ ሥራቸውን፣ ትዳራቸውንና ወዳጆቻቸውን ያጡም አሉ። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ ቁማር በሕይወታችንና በደስታችን ላይ ከሚያሳድረው ጎጂ ተጽዕኖ ይጠብቀናል።

“ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።”1 ጢሞቴዎስ 6:9