ብዙ ሰዎች ማስረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ ሕይወት የላቀ የማሰብ ችሎታ ካለው አካል እንደተገኘ ደምድመዋል። በአንድ ወቅት አምላክ የለሽነትን በጥብቅ ይደግፉ የነበሩትና የፍልስፍና ፕሮፌሰር የሆኑት አንተኒ ፍሉ ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል። እኚህ ምሁር ሕይወት እጅግ ውስብስብ መሆኑን ሲገነዘቡና አጽናፈ ዓለም ስለሚመራበት ሕግ ሲያውቁ አመለካከታቸውን ለውጠዋል። የጥንት ፈላስፎችን አመለካከት በመጥቀስ “የትም ያድርሰን የት ማስረጃው ወደሚመራን መሄድ አለብን” በማለት ጽፈዋል። በመሆኑም ፕሮፌሰር ፍሉ ማስረጃው የመራቸው፣ ‘ፈጣሪ አለ’ ወደሚለው መደምደሚያ ነው።

ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ዠራርድም ተመሳሳይ ወደሆነ ድምዳሜ ደርሰዋል። ከፍተኛ ትምህርት የተከታተሉና በነፍሳት ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ቢሆንም እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር በአጋጣሚ እንደሆነ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ አላገኘሁም። ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚታየው ሥርዓታማነትና ውስብስብነት አንድ አደራጅና ንድፍ አውጪ ሊኖር እንደሚገባ አሳምኖኛል።”

አንድ ሰው የአንድን ሠዓሊ ሥራዎች በመመርመር ስለ ሠዓሊው ሊያውቅ እንደሚችል ሁሉ ዠራርድም ተፈጥሮን በመመርመር የፈጣሪን ባሕርያት ሊያስተውሉ ችለዋል። በተጨማሪም ዠራርድ ፈጣሪ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ የሚታመነውን መጽሐፍ ቅዱስን ጊዜ ወስደው መርምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህን በማድረጋቸውም ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚያረኩ መልሶችን አግኝተዋል፤ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ በሰው ልጆች ፊት ለተደቀኑ ችግሮች መፍትሔው ምን እንደሆነ ተረድተዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ያስጻፈው መጽሐፍ መሆኑን ሊያምኑ ችለዋል።

በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ መልሶች ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው፤ ዠራርድም ይህን ተገንዝበዋል። አንተም መልሶቹን እንድትመረምር እናበረታታሃለን።