አምላክ አካላዊ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ይፈልጋል?

“ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”—2 ቆሮንቶስ 7:1

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ፈጣሪያችን ስለሚወደን ጥሩ ጤንነት፣ ረጅም ዕድሜና አርኪ ሕይወት እንዲኖረን ይፈልጋል። አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ትእዛዛቴን በልብህ ጠብቅ፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።” (ምሳሌ 3:1, 2) አምላክ ስለ ንጽሕና አጠባበቅ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው መመሪያዎች ለሰዎች ፍቅር እንዳለው ያሳያሉ። (ዘዳግም 23:12-14) እስራኤላውያን እነዚህን ምክንያታዊ የሆኑ መመሪያዎች ሲጠብቁ የተሻለ ጤንነት ይኖራቸው ነበር፤ እንዲሁም እንደ እነሱ ያለ የላቀ ሕግ ያልነበራቸውን እንደ ግብፃውያን ያሉ ሕዝቦችን ከሚያጠቁ የተለያዩ በሽታዎች ይጠበቁ ነበር።—ዘዳግም 7:12, 15

በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ እንደ ማጨስ፣ ከልክ በላይ መጠጣትና የዕፅ ሱሰኝነት ካሉ ‘ሥጋን የሚያረክሱ ነገሮች ራሳቸውን የሚያነጹ’ ሰዎች በአእምሮ ሕመምና በሌሎች በሽታዎች የመያዝ አጋጣሚያቸው አነስተኛ ነው፤ በተጨማሪም ያለዕድሜያቸው አይቀጩም። ከዚህም ሌላ የምንኖረው ከሌሎች ሰዎች ጋር እንደመሆኑ መጠን አምላክ ያወጣቸውን የንጽሕና ደንቦች መከተላችን ለእነሱ ያለንን አሳቢነት ያሳያል።—ማርቆስ 12:30, 31

 በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆናችን አምላክን ያሳስበዋል?

“በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የአምላክ ቁጣ ይመጣል።”—ቆላስይስ 3:5, 6

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን [እንድናነጻ]” ይመክረናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች አካላዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ የንጽሕና ደንቦችን ግን ችላ ይሉ ነበር። (ማርቆስ 7:1-5) ኢየሱስ “ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር [የለም] . . . ምክንያቱም የሚገባው . . . ወደ ሆዱ ነው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ ይገባል” በማለት ትክክለኛውን አመለካከት ገልጿል። ኢየሱስ አክሎም “ሰውን የሚያረክሰው ከሰው የሚወጣው ነው፤ ከውስጥ፣ ከሰው ልብ ክፉ ሐሳብ ይወጣል:- ዝሙት፣ ሌብነት፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ብልግና፣ ምቀኝነት፣ . . . ሞኝነት። እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ . . . ያረክሳሉ” ብሎ ተናግሯል።—ማርቆስ 7:18-23

አካላዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ የአምላክን የሥነ ምግባርና መንፈሳዊ ደንቦች ችላ የሚሉ ሰዎች ከላይ ሲታዩ ንጹሕ ቢመስሉም ውስጣቸው በጣም ከቆሸሸ ጽዋዎች ጋር እንደሚመሳሰሉ ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 23:25, 26

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ምክንያታዊ ናቸው?

“አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።”—1 ዮሐንስ 5:3

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሚክያስ 6:8 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” አምላክ ከእኛ ይህን መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። ከዚህም በላይ ፈጣሪያችን በፍቅር ተነሳስተን እንድንታዘዘው ይፈልጋል። እንዲህ ስናደርግ ታላቅ ደስታ እናገኛለን። (መዝሙር 40:8 NW) ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ደግሞ አምላክ መሐሪ መሆኑን ማወቃችን ያጽናናል። “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” በሌላ አባባል ደካሞች መሆናችንንና ፍጹም እንዳልሆንን ይረዳል።—መዝሙር 103:13, 14

ለማጠቃለል ያህል አምላክ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናን የሚመለከቱ መመሪያዎችን መስጠቱ እሱ ጥሩ እንደሆነና ለእኛ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። እነዚህን መመሪያዎች በጥብቅ ለመከተል ፈቃደኛ መሆናችን ጥበበኞች እንደሆንን እና አምላክን እንደምንወደው ይጠቁማል።