ተፈታታኙ ነገር

“አንዳንድ ጊዜ ሴቶች የስልክ ቁጥሬን እንድሰጣቸው እንዲሁም ‘አብረን እንድንወጣ’ ይጠይቁኛል። እኔ ግን እምቢ ብያቸው እሄዳለሁ። በኋላ ላይ ግን ‘ስልኬን ብሰጣት ምን ችግር አለው?’ እያልኩ አስባለሁ። እውነቱን ለመናገር፣ የሚጠይቁኝ አንዳንድ ሴቶች በጣም ቆንጆ ናቸው። በዚህ ጊዜ ቶሎ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ‘ምን ችግር አለው?’ የሚለው ሐሳብ ነው።”—ካርሎስ፣ * የ16 ዓመት ወጣት

አንተም እንደ ካርሎስ ፈታኝ ከሆነ ስሜት ጋር እየታገልክ ነው? ከሆነ አይዞህ፣ ትግሉን ማሸነፍ ትችላለህ።

ማወቅ የሚገባህ ነገር

ፈታኝ ለሆኑ ስሜቶች መሸነፍ ትርፉ ጉዳት ነው

አዋቂዎችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ፈታኝ የሆኑ ስሜቶች ያጋጥሙታል። ደግሞም ፈታኝ የሆኑ ስሜቶች የሚመጡት ከተለያየ አቅጣጫ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ ወጣት ባይሆንም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮም 7:22, 23) ጳውሎስ ትግሉ ከባድ ቢሆንበትም ፈተናውን ማሸነፍ ችሏል፤ አንተም ማሸነፍ ትችላለህ። ደግሞስ ለገዛ ራስህ ምኞት ለምን ባሪያ ትሆናለህ? (1 ቆሮንቶስ 9:27) በወጣትነትህ ፈታኝ ስሜቶችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ካዳበርክ በአሁኑ ጊዜ ከብዙ ጭንቀት ትድናለህ፤ በተጨማሪም ይህ ችሎታ ወደፊት አዋቂ ስትሆንም በጣም ይጠቅምሃል።

መገናኛ ብዙኃን ፈታኝ የሆኑ ስሜቶችን ይቀሰቅሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ምኞቶች’ ይናገራል፤ እነዚህ ምኞቶች በራሳቸው ከፍተኛ ኃይል አላቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ይሁን እንጂ ለወጣቶች ታስበው የሚዘጋጁ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ሙዚቃዎችና መጻሕፍት ለምኞታችን መሸነፍ ምንም ስህተት እንደሌለው በመግለጽ ፈታኝ ከሆኑ ስሜቶች ጋር የምናደርገው ትግል ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋሉ። ለምሳሌ በአንድ ፊልም ላይ የሚታዩ ሁለት ገጸ ባሕርያት ‘የሚዋደዱ’ ከሆነ በአብዛኛው በፊልሙ ውስጥ የሆነ ቦታ ላይ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በእውኑ ዓለም ያሉ ወንዶችና ሴቶች ‘ከሥጋዊ ምኞቶች መራቅ’ እንደሚችሉ ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 2:11) ስለዚህ ከፈለግህ ፈታኝ የሆኑ ስሜቶችን መቋቋም ትችላለህ። ግን እንዴት?

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

ድክመትህ ምን እንደሆነ እወቅ። አንድ ሰንሰለት የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆን ቢያንስ አንዱ ቀለበት ከላላ ሰንሰለቱ በቀላሉ ሊበጠስ ይችላል። በተመሳሳይም ትክክል የሆነውን ለማድረግ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ብታደርግም አንድ ደካማ ጎን ካለህ ይህን አቋምህን ሊያላላብህ ይችላል። በንቃት መከታተል ያለብህ ደካማ ጎንህ የቱ ነው?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ያዕቆብ 1:14

ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥምህ እንደሚችል ጠብቅ። ፈታኝ የሆነ ስሜት ሊያጋጥምህ የሚችለው እንዴት ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ አስቀድመህ አስብ። እንዲህ ያለው ፈተና ቢገጥምህ ምን እንደምታደርግ ገና ከወዲሁ በደንብ አስብበት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 22:3

አቋምህን አጠናክር። ዮሴፍ ዝሙት እንዲፈጽም በተፈተነ ጊዜ “እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ብሎ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 39:9) ዮሴፍ ‘እኔ እንዴት ይህን አደርጋለሁ?’ የሚል መልስ መስጠቱ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ጠንካራ አቋም እንደነበረው ያሳያል። አንተስ እንዲህ ዓይነት አቋም አለህ?

አቋምህን የሚደግፉልህ ጓደኞች ምረጥ። ለጓደኝነት የመረጥካቸው ሰዎች የአንተ ዓይነት የሥነ ምግባር አቋም ያላቸው ከሆኑ ከብዙ ፈተና መዳን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 13:20

ፈታኝ ስሜትን መቋቋም ከባድ እንዲሆንብህ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ራቅ። ለምሳሌ ያህል፦

  • ከተቃራኒ ፆታ ጋር ብቻህን አትሁን።

  • ፖርኖግራፊ ለማየት እንድትፈተን በሚያደርግ ጊዜ ወይም ቦታ ላይ ሆነህ ኢንተርኔት አትጠቀም።

  • መጥፎ ነገር መፈጸም አስደሳች እንደሆነ በአነጋገራቸውም ሆነ በድርጊታቸው ከሚገልጹ ሰዎች ራቅ።

ወደ ፈተና እንዳትገባ የሚረዱህን የትኞቹን መመሪያዎች ለራስህ ማውጣት ትችላለህ?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 2 ጢሞቴዎስ 2:22

አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ወደ ፈተና እንዳትገቡ ሳታሰልሱ ጸልዩ’ ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:41) ይሖዋ አምላክ መጥፎ ነገር እንድትፈጽም የሚፈትኑ ስሜቶችን እንድታሸንፍ ይፈልጋል፤ እንዲሁም እንዲህ ማድረግ እንድትችል ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 10:13

^ አን.4 ስሙ ተቀይሯል።