ስፔን ይህን አሳዛኝ ድርጊት የፈጸመችው በዋነኝነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ገፋፊነት እንደሆነ ይነገራል። ይህ ልታውቀው የሚገባ ታሪክ ነው።

የስፔን ንጉሣዊ መንግሥት ስፔንን በአንድ ሕግ የምትተዳደር ክርስቲያን አገር ማድረግ ፈለገ። ሞሪስኮዎች እንደ አረመኔ ይቆጠሩ ስለነበረ የእነሱ መኖር በአምላክ ዘንድ እጅግ የተጠላ ነገር እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። መፍትሔው ምን ነበር? ሞሪስኮዎችን ማባረር! *

በግዳጅ ሃይማኖትን ማስለወጥ

ሙዴሃር ተብለው የሚጠሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በስፔን የሚኖሩ ሙስሊም ሙሮች በካቶሊኮች ቁጥጥር ሥር በነበሩ አካባቢዎች ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሰላም ኖረዋል። ለተወሰነ ጊዜም በአንዳንድ አካባቢዎች የራሳቸውን ሕግ፣ ባሕልና ሃይማኖት እንዲከተሉ ሕጋዊ መብት ተሰጥቷቸው ነበር።

በ1492 ግን ዳግማዊ ፈርዲናንድ እና ኢዛቤላ የሚባሉ ካቶሊክ ነገሥታት በአይቤርያ ባሕረ ገብ መሬት በሙስሊሞች ቁጥጥር ሥር የቀረችውን ግራናዳ የተባለችውን የመጨረሻ ግዛት ወርረው ያዙ። ግዛቲቱ እጇን በሰጠችበት ወቅት የተደረገው ስምምነት በዚያ ይኖር ለነበረው የሙር ሕዝብ የሙዴሃሮች ዓይነት መብት የሚሰጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ካቶሊክ መሪዎች በግዛታቸው ሥር የሚኖሩ ሙስሊሞች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ የሚያሳድሩት ጫናና ስደት እየተባባሰ ሄደ። ሙሮች የሚፈጸምባቸው በደል ቀደም ሲል የተደረገውን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን በመቃወም በ1499 ዓመፁ። በዚህ ጊዜ የመንግሥት ወታደሮች ዓመፁን አዳፈኑት፤  ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን በየአካባቢው የሚኖሩ ሙስሊሞች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ካልሆነም አገር ለቀው እንዲወጡ ተገደዱ። ስፔናውያን፣ ሃይማኖታቸውን ቀይረው በስፔን የቀሩትን ሙስሊሞች ሞሪስኮ ብለው ጠሯቸው።

“ጥሩ ክርስቲያንም ሆነ ታማኝ ተገዢ” አልሆኑም

በ1526 የእስልምና ሃይማኖት በመላው ስፔን ታገደ፤ ያም ቢሆን ብዙ ሞሪስኮዎች ሃይማኖታቸውን በሚስጥር ያካሂዱ ነበር። በአብዛኛው ባሕላቸውን ጠብቀው ኖረዋል።

መጀመሪያ ላይ የሞሪስኮዎች የይስሙላ ካቶሊክነት ችላ ተብሎ ነበር። ደግሞም በዕደ ጥበብ፣ በጉልበት ሥራና በግብር ከፋይነት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። ሆኖም በአጠቃላይ ሲታይ ሞሪስኮዎች ከሌላው ሕዝብ ጋር ለመቀላቀል እምቢተኛ መሆናቸው እንዲጠሉ አደረጋቸው፤ በዚህም የተነሳ በመንግሥትም ሆነ በተራው ሕዝብ መድልዎ ይፈጸምባቸው ጀመር። እንዲህ ያለው መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዲፋፋም ያደረገው ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ሞሪስኮዎች ሃይማኖታቸውን የለወጡት ከልባቸው ስለ መሆኑ ያደረባት ጥርጣሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ሳይሆን አይቀርም።

ብዙም ሳይቆይ በቸልታ ማለፍ ቀረና ማስገደድ ተጀመረ። በ1567 ዳግማዊ ፊሊፕ የተባለው ንጉሥ የሞሪስኮዎችን ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ባሕልና ወግ የሚያግድ ሕግ አወጣ። ይህ እርምጃ በድጋሚ ዓመፅ እንዲቀሰቀስና ደም መፋሰስ እንዲከሰት አደረገ።

በደረሰባቸው ከፍተኛ ሥቃይ የተነሳ ወደ 300,000 ገደማ የሚሆኑ ሞሪስኮዎች ከስፔን ለመውጣት እንደተገደዱ ይገመታል

የታሪክ ምሁራን እንደገለጹት የስፔን ገዢዎች “ሞሪስኮዎች ጥሩ ክርስቲያንም ሆነ ታማኝ ተገዢ እንዳልሆኑ” ተሰማቸው። በዚህ የተነሳ ከስፔን ጠላቶች ማለትም ከባሕር ላይ ወንበዴዎች፣ ከፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶችና ከቱርኮች ጋር በማሴር ስፔንን ለወረራ እንዳጋለጡ ክስ ቀረበባቸው። ሞሪስኮዎች ውሎ አድሮ አገር መክዳታቸው አይቀርም የሚለው ፍርሃትና ለእነሱ የነበረው መሠረተ ቢስ ጥላቻ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ ሳልሳዊ ፊሊፕ በ1609 ከአገር እንዲባረሩ ወሰነ። * በቀጣዮቹ ዓመታት ሞሪስኮዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ስደት ደረሰባቸው። በዚህ አሳፋሪ መንገድ ስፔን ሙሉ በሙሉ የካቶሊክ አገር ሆነች።

^ አን.4 ሞሪስኮ ማለት በስፓንኛ “ትንሽ ሙሮች” ማለት ነው። የታሪክ ምሁራን ይህን ቃል የሚጠቀሙት እንደ ስድብ ሳይሆን የመጨረሻው ሙስሊም መንግሥት በ1492 ከወደቀ በኋላ ወደ ካቶሊክነት ተለውጠው በአይቤርያ ባሕረ ገብ ምድር የቀሩትን ሙስሊም የነበሩ ሰዎች ለማመልከት ነው።

^ አን.12 በተጨማሪም የታሪክ ምሁራን ከስፔን ገዢዎች መካከል ቢያንስ አንዱ የሞሪስኮዎችን ንብረት በመውሰድ ብዙ ጥቅም እንዳገኘ ይገምታሉ።