በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ነሐሴ 2014

 የታሪክ መስኮት

ዊልያም ዊስተን

ዊልያም ዊስተን

ዊልያም ዊስተን የሳይንስና የሒሳብ ሊቅ፣ የሃይማኖት መሪ እንዲሁም ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ የተዋጣለት ጸሐፊ ነው፤ በተጨማሪም የፊዚክስና የሒሳብ ሊቅ የሆነው የእንግሊዛዊው የሰር አይዛክ ኒውተን የሥራ ባልደረባ ነበር። በ1702 ዊስተን ኒውተንን ተክቶ በኢንግላንድ፣ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሉኬዢያ የሒሳብ ፕሮፌሰር ሆነ። ይህን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ የላቀ ችሎታ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው።

ዊስተን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ ይበልጥ የሚታወቀው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረውን አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ይኸውም የፍላቪየስ ጆሴፈስን ጽሑፎች ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎሙ ነው። ዘ ዎርክስ ኦቭ ጆሴፈስ የተሰኘው ይህ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ስለ አይሁዳውያን ታሪክና ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖረን አድርጓል።

ዊስተን የሚያምንባቸው ነገሮች

ዊስተን ብሩሕ አእምሮ የነበረው ሲሆን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተለይ ደግሞ በሳይንስና በሃይማኖት መስክ ብዙ ምርምር አድርጓል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ትክክል እንደሆነ እንዲሁም በተፈጥሮ ላይ የሚታየው ንድፍ፣ ውበትና ሥርዓት መለኮታዊ ንድፍ አውጪ መኖሩን እንደሚጠቁም ያምን ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ብዙ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ሊፈጠሩ የቻሉት ቀሳውስቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የቤተ ክርስቲያን መማክርትና አባቶች ለደነገጓቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችና ልማዶች ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ እንደሆነ ያምን ነበር።

ዊስተን፣ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ እውነትን የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ስለተገነዘበ በገሃነም እሳት ውስጥ ለዘላለም ስለ መሠቃየት የሚገልጸውን ትምህርት አይቀበልም ነበር። ይህ ትምህርት ፈጽሞ የማይመስልና ጭካኔ የሚንጸባረቅበት አልፎ ተርፎም አምላክን የሚያሰድብ እንደሆነ ያምን ነበር። ከቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት ጋር ይበልጥ እንዲጋጭ ያደረገው ግን የሥላሴን ትምህርት አለመቀበሉ ነው፤ ይህ ትምህርት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የማይበላለጡና ዘላለማዊ እንደሆኑ ይገልጻል። ያም ቢሆን በዚህ ትምህርት መሠረት አምላክ ሦስት ሳይሆን አንድ ነው።

 ‘የተከበረው ምሁር ከምሁራኑ ማኅበረሰብ ተገለለ’

ዊስተን ጥልቅ ምርምር ሲያደርግ ሥላሴ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ያስተማሩት ትምህርት ሳይሆን ከጊዜ በኋላ ወደ ክርስትና ሰርጎ የገባ አረማዊ ፍልስፍና እንደሆነ ተገነዘበ። * የምርምሩን ውጤት ማሳተሙ አደገኛ እንደሆነ ጓደኞቹ ቢያስጠነቅቁትም ዊስተን፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅና ፍጡር ሆኖ ሳለ እውነተኛ ማንነቱ እንዲዛባ ያደረገውን የሥላሴ ትምህርትን ከማጋለጥ ወደኋላ ማለት አልፈለገም።

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ፣ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረው መሠረተ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ሐሳብ የሚያስተምርን ሰው ከሥራ ያግድ ስለነበረ ዊስተን ያደረገው ውሳኔ የነበረውን ማዕረግ ሊያሳጣው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ዊስተን ያመነበትን ነገር በመናገር ከኒውተን የተለየ አቋም ወስዷል፤ ምክንያቱም ኒውተን የሥላሴ ትምህርት ሐሰት እንደሆነ ቢያምንም የሚያምንበትን ነገር በይፋ ከመናገር ተቆጥቧል። ዊስተን “ምንም ዓይነት ዓለማዊ ፍላጎት ሐሳቤን ሊያስቀይረኝ አይችልም” በማለት ጽፏል።

አቋሙን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆኑ “ይህ የተከበረ ምሁር ከምሁራኑ ማኅበረሰብ ተገለለ”

በ1710 ዊስተን ከካምብሪጅ ተባረረ። አቋሙን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆኑ “ይህ የተከበረ ምሁር ከምሁራኑ ማኅበረሰብ ተገለለ።” እንደዚያም ሆኖ ዊስተን አላጎበደደም። እንዲያውም በመናፍቅነት ተከስሶ እያለም ፕሪሚቲቭ ክሪስቺያኒቲ ሪቫይቭድ ተብለው የተሰየሙ ተከታታይ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አዘጋጅቷል፤ ዊስተን ፕሪሚቲቭ (primitive) የሚለውን ቃል የተጠቀመው የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ይከተሉት የነበረውን እውነተኛ ክርስትና ለማመልከት ነው። ከጊዜ በኋላ ዊስተን የጥንት ክርስትናን የሚያራምድ ማኅበር ያቋቋመ ሲሆን የማኅበሩ አባላት ለንደን በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ይሰበሰቡ ነበር።

ዊስተን የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ያጣና ለተወሰነ ጊዜ የገንዘብ ችግር የገጠመው ቢሆንም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ማዘጋጀቱንና በለንደን በሚገኙ ሻይ ቤቶች ንግግር በማቅረብ ማስተማሩን ቀጥሎ ነበር። እንዲሁም ክርስትና በጀመረበት ወቅት ስለነበረው ሕይወት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሲል ወደ እንግሊዝኛ የተረጎማቸውን የጆሴፈስን ጽሑፎች በ1737 አሳተመ። ይህ የትርጉም ሥራ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሲታተም ቆይቷል።

ዊስተን በድፍረት የወሰደው አቋም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ባሉ ብዙ ሰዎች ዘንድ “ከሰው የማይገጥም ሰው” የሚል ስም እንዳተረፈ ጄምስ ፎርስ የተባሉት ደራሲ ተናግረዋል። ሌሎች ግን ዊስተንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሆኖ ባበረከተው አስተዋጽኦ፣ ሃይማኖታዊ እውነቶችን ለማግኘት በቅንነት ባደረገው ምርምርና በእምነቱ መሠረት ለመኖር በነበረው ቁርጠኝነት ያደንቁታል።

^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ማንነት በግልጽ ይናገራል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.org/am የተሰኘውን ድረ ገጽ ጎብኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ተመልከት።