በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

‘ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ’

‘ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ’

ወፎች በሁሉም የምድር ክፍል የሚገኙ ሲሆን ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊመለከታቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ቅርጻቸው፣ ቀለማቸው፣ ዝማሬያቸው፣ እንቅስቃሴያቸውና ልማዳቸው የተለያየ በመሆኑ ወፎችን ማየት አዝናኝና አስደሳች የጊዜ ማሳለፊያ ነው።

ጨረባ

አንተም ቤትህ ውስጥ ሆነህ በመስኮት የወፎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማየት ትችል ይሆናል፤ ለምሳሌ ወፎች ትል ፍለጋ ሲቆፍሩ፣ ነፍሳትን ሲያድኑ፣ ተባዕቱ ወፍ እንስቷን ለማማለል ጥረት ሲያደርግ፣ ያለመታከት ጎጇቸውን ሲሠሩ ወይም የተራቡ ጫጩቶቻቸውን ሲመግቡ ልትመለከት ትችላለህ።

ጅግራ

እንደ ንስር፣ የሎስና ጭልፊት ያሉ አንዳንድ ወፎች ሰማይ ላይ ሲያንዣብቡ ማየት ያስደንቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ድንቢጦች ተሻምተው ምግብ ሲለቃቅሙ፣ ወንድ ርግብ ለእሱ ደንታ የሌላት መስላ የምትታየውን እንስት ለማማለል ደረቱን ሲነፋ አሊያም በኤሌክትሪክ ገመድ ላይ ተዘቅዝቀው የተንጠለጠሉ ወፎች ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ማየት ያዝናናህ ይሆናል። እንደ ሽመላ ወይም ዝይ ያሉ ወደ ሌላ ቦታ የሚፈልሱ ወፎችን ስትመለከትም መገረምህ አይቀርም። በእርግጥም ከበርካታ ሺህ ዓመታት በፊት አንስቶ እንዲህ ዓይነቱን ፍልሰት የተመለከቱ ሰዎች፣ ወፎቹ ምንም ሳይሳሳቱ ከፍተኛ ርቀት ተጉዘው የሚፈልጉበት  ቦታ መድረስ መቻላቸው አስደንቋቸዋል። እንዲያውም ፈጣሪ ራሱ “ሽመላ . . . በሰማይ፣ የተወሰነ ጊዜዋን ታውቃለች፣ ዋኖስ፣ ጨረባና ዋርዳም፣ የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል።—ኤርምያስ 8:7

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ወፎች

መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተላለፍ ወፎችን ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰጎን የምትባለውን አስገራሚ ፍጥነት ያላት ወፍ አስመልክቶ ለኢዮብ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “[ሰጎን] ለመሸምጠጥም ክንፎቿን ስትዘረጋ፣ በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች።” * (ኢዮብ 39:13, 18) በተጨማሪም አምላክ “ጭልፊት የሚበረው . . . በአንተ ጥበብ ነውን? ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው . . . በአንተ ትእዛዝ ነውን?” የሚል ጥያቄ ለኢዮብ አቅርቦለት ነበር። (ኢዮብ 39:26, 27) አምላክ ለማስተላለፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? ወፎች የእኛ እርዳታ ሳያስፈልጋቸው አስደናቂ ነገሮችን ያከናውናሉ። ስለዚህ እነዚህ ወፎች ያላቸው አስደናቂ ችሎታ የአምላክን ጥበብ የሚያሳይ ነው፤ የሰዎች ጥበብ ለዚህ ምንም አስተዋጽኦ አላደረገም።

ንጉሥ ሰሎሞን፣ ጸደይ መምጣቱን በዝማሬ ስለሚያበስሩ “ርግቦች” ጽፏል። (ማሕልየ መሓልይ 2:12) አንድ መዝሙራዊ በአምላክ ቤተ መቅደስ ለማገልገል ያለውን ናፍቆት ሲገልጽ ድንቢጥን ጠቅሷል። መዝሙራዊው በዚች ወፍ እንደሚቀና በሚያሳይ ስሜት እንዲህ ብሏል፦ “የሰራዊት አምላክ ሆይ፤ መሠዊያህ ባለበት ስፍራ፣ ድንቢጥ እንኳ መኖሪያ ቤት፣ ዋኖስም ጫጩቶቿን የምታኖርበት ጐጆ አገኘች” ብሏል።—መዝሙር 84:1-3

“በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?”—ማቴዎስ 6:26

ኢየሱስ ክርስቶስም ወፎችን በመጥቀስ ግሩም የሆኑ ትምህርቶችን አስተምሯል። ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 6:26 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተመልከት፦ “የሰማይን ወፎች ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” ይህ ልብ የሚነካ ምሳሌ የኢየሱስ ተከታዮች በአምላክ ዘንድ ውድ እንደሆኑና ለሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ስለ ማግኘት መጨነቅ እንደማይኖርባቸው አረጋግጦላቸዋል።—ማቴዎስ 6:31-33

በዛሬው ጊዜ ወፎችን መመልከት ተወዳጅ መዝናኛ ሆኗል፤ ምክንያቱም የወፎች አስገራሚ እንቅስቃሴ፣ ውበታቸው፣ ተጓዳኝ ለማግኘት የሚያደርጉት ነገር እንዲሁም ዝማሬያቸው አስደናቂ ነው። ከዚህም ሌላ ወፎችን በማስተዋል የሚመለከቱ ሰዎች ከእነሱ ስለ ሕይወት ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ታዲያ አንተስ ‘ወፎችን ልብ ብለህ ትመለከታለህ?’

^ አን.6 ሰጎን በምድር ላይ ካሉት የወፍ ዝርያዎች ሁሉ ትልቋ ስትሆን በጣም ፈጣን ሯጭ ናት፤ በሰዓት 72 ኪሎ ሜትር ገደማ መሮጥ ትችላለች።