በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ነሐሴ 2014

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዓለም

“በየዓመቱ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በተወለዱ በመጀመሪያው ወር ይሞታሉ፤ ለዚህ መንስኤ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አብዛኞቹን መከላከል ይቻላል። ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት በተወለዱበት ዕለት ሕይወታቸው ያልፋል።”—ሴቭ ዘ ችልድረን ኢንተርናሽናል

ብሪታንያ

የኢንግላንድ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ቢሮ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በ2011 በ15 የለንደን ክፍለ ከተማዎች ውስጥ በአየር ብክለት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ናፍጣ ከሌሎች የነዳጅ ዓይነቶች ጋር ሲነጻጸር ኃይል የማያባክንና የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠኑም አነስተኛ ስለሆነ በአካባቢ ላይ ያን ያህል ጉዳት እንደማያስከትል ይታሰብ ነበር። ይሁንና በእነዚህ አካባቢዎች የአየር ብክለት ካስከተሉት መርዛማ ቅንጣቶች መካከል 91 በመቶ የሚሆነው ናፍጣ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የወጣ ነው።

ሩሲያ

የሩሲያ የሕዝብ አስተያየት ተቋም በ2013 ባካሄደው ጥናት መሠረት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እንደሆኑ ከተናገሩት ሩሲያውያን መካከል 52 በመቶ ገደማ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ አንብበው እንደማያውቁ የተናገሩ ሲሆን 28 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሚጸልዩት አልፎ አልፎ እንደሆነ ገልጸዋል።

አፍሪካ

የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦች የግብርና ምርት እንዲስተጓጎልና ድህነት እንዲስፋፋ እያደረጉ እንደሆነ የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት ይገልጻል። በዓለም ላይ ካለው ለግብርና አመቺ የሆነ ያልታረሰ መሬት መካከል ግማሹ ይኸውም 202 ሚሊዮን ሄክታር የሚያህለው መሬት የሚገኘው በአፍሪካ ውስጥ ነው፤ አፍሪካ በግብርና ረገድ ካላት አቅም ጥቅም ላይ የዋለው 25 በመቶው ብቻ እንደሆነ ይነገራል።

ዩናይትድ ስቴትስ

በርካታ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች፣ መማሪያ መጻሕፍትን በኤሌክትሮኒክ ታብሌቶች እየተኩ ነው፤ በእነዚህ ታብሌቶች ላይ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ጽሑፎች፣ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች እና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ይጫናሉ። ይህ ዘዴ ወጪ የሚቀንስ መሆን አለመሆኑ ግን አጠያያቂ ነው።