አምላክ ለሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ በሕልም ይጠቀማል?

“[የአምላክ ነቢይ የሆነው] ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም አለመ፤ . . . የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው።”—ዳንኤል 7:1

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ለሰዎች አስፈላጊ መልእክቶችን ለማስተላለፍ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። በጥንት ዘመን፣ አልፎ አልፎ በሕልም ይጠቀም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ የሚያሳየው ሕልም እንደ አንድ ተራ ሕልም ግልጽ ያልሆነና ትርጉም የለሽ አልነበረም። ከአምላክ የመጡት ሕልሞች ግልጽ፣ ትርጉም ያላቸው እንዲሁም መልእክት ያዘሉ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ዳንኤል የተለያዩ አራዊትን በሕልሙ ተመልክቶ ነበር፤ እነዚህ አራዊት ከባቢሎን መንግሥት እስከ ዘመናችን ድረስ የተፈራረቁትን መንግሥታት ያመለክታሉ። (ዳንኤል 7:1-3, 17) አምላክ፣ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ለነበረው ለናዝሬቱ ዮሴፍ ሚስቱንና ልጁን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ በሕልም ነግሮት ነበር። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በጨካኙ ንጉሥ በሄሮድስ እጅ ከመገደል ድኗል። ሄሮድስ በሞተ ጊዜም አምላክ ይህን ለዮሴፍ የነገረው በሕልም ሲሆን ቤተሰቡን ይዞ ወደ አገራቸው እንዲመለስ አዞታል።—ማቴዎስ 2:13-15, 19-23

 በዛሬው ጊዜ አምላክ ለእኛ መልእክት ለማስተላለፍ በሕልም ይጠቀማል?

“ከተጻፉት ነገሮች አትለፍ።”—1 ቆሮንቶስ 4:6

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ሕልሞች አምላክ ለሰው ልጆች በጽሑፍ ያሰፈረው ቃል ክፍል ናቸው። ይህን የአምላክ ቃል በተመለከተ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 እንዲህ ይላል፦ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ሥነ ምግባር መሥፈርቶቹና ከምድር ጋር በተያያዘ ለእኛ ስላለው ዓላማ ማወቅ የሚያስፈልገንን ሁሉ ስለያዘ ‘በሚገባ ያስታጥቀናል።’ በመሆኑም አምላክ ለሰዎች መልእክት ለማስተላለፍ በሕልም መጠቀሙን አቁሟል። ስለ ወደፊቱ ጊዜና አምላክ ከእኛ ስለሚጠብቀው ነገር ለማወቅ ‘ከተጻፉት ነገሮች ማለፍ’ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ሌላ አያስፈልገንም። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ይህን መጽሐፍ ማግኘት እንዲሁም በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩትን አምላክ በሕልምም ሆነ በሌሎች መንገዶች ያስተላለፋቸውን ሐሳቦች ማወቅ ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ሕልሞችና ራእዮች ላይ እምነት ልትጥል የምትችለው ለምንድን ነው?

“ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:21

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት አብዛኞቹ ሕልሞችና ራእዮች ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክስተቶች የሚተነብዩ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነዚህን ትንቢቶች በጽሑፍ በማስፈራቸው የእነሱንም ሆነ የቅዱሳን መጻሕፍትን ተአማኒነት መርምረን ማረጋገጥ እንችላለን። ታዲያ የጻፏቸው ነገሮች ትክክለኛ መሆናቸው ተረጋግጧል? በባቢሎናውያን የግዛት ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተጻፈውንና በዳንኤል 8:1-7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ራእይ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

በትንቢቱ ላይ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው አንድ አውራ በግና አውራ ፍየል ተጠቅሰዋል፤ ከዚያም ፍየሉ አውራ በጉን በምድር ላይ ጥሎ እንደረጋገጠው ትንቢቱ ይገልጻል። ዳንኤል የራእዩን ትርጉም መገመት አላስፈለገውም። ከአምላክ ተልኮ የመጣ አንድ መልአክ “ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል። ጠጕራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ [ነው]” በማለት ለዳንኤል ነግሮታል። (ዳንኤል 8:20, 21) የሜዶ ፋርስ መንግሥት ባቢሎንን በመተካት የዓለም ኃያል መንግሥት እንደሆነ ታሪክ ያረጋግጣል። ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ ሜዶ ፋርስ የግሪክ ንጉሥ በሆነው በታላቁ እስክንድር ድል ተደረገ። ትንቢታዊ ይዘት ያላቸው ሕልሞችን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ፍጹም ትክክለኛ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ይህ እውነታ በራሱ መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች ሃይማኖታዊ መጻሕፍት ሁሉ የተለየና እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንዲሆን ያደርገዋል።