በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ቃለ ምልልስ | ወንሎንግ ሄ

የኤክስፐርመንታል ፊዚክስ ሊቅ ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

የኤክስፐርመንታል ፊዚክስ ሊቅ ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

ወንሎንግ ሄ፣ ፊዚክስን መጀመሪያ ያጠናው በቻይና ጃንግሱ ግዛት በሱጆ ከተማ ነበር። በአንድ ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ የጥናት መጽሔት ዝግጅት ላይ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን በደርዘን የሚቆጠሩ የጥናት ጽሑፎችን በሳይንሳዊ ጽሑፎች ላይ አውጥቷል። ወንሎንግ በአሁኑ ጊዜ የሚሠራው በስኮትላንድ በሚገኘው ስትራትክላይድ ዩኒቨርሲቲ ነው። በወጣትነቱ በዝግመተ ለውጥ ያምን የነበረ ቢሆንም አሁን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ንቁ! ስለሚያምንበት ነገር ጠይቆታል።

እስቲ ስለ አስተዳደግህ ንገረን።

የተወለድኩት በ1963 ነው፤ ያደግኩት በቻይና ጃንግሱ ግዛት፣ ከያንግሲ ወንዝ በስተ ደቡብ በሚገኝ መንደር ነው። የአየሩ ሁኔታ ከፊል ሞቃታማ ሲሆን አካባቢው በምግብ ምርቱ የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ብዙ ጊዜ የሩዝና የዓሣ አገር ተብሎ ይጠራል። በልጅነቴ ‘ተፈጥሮ ይህን ሁሉ ጣፋጭ ምግብ የሚሰጠን ለምንድን ነው? እነዚህ ምግቦች እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው? ከዶሮና ከእንቁላል ቀድሞ የተገኘው የቱ ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር። አምላክ የለሽነት በቻይና በጣም የተስፋፋ በመሆኑ በትምህርት ቤት ስለ ዝግመተ ለውጥ ተማርኩ።

ቤተሰብህስ?

ወላጆቼ አምላክ የለሾች ነበሩ። እናቴ በግብርና ሥራ ተሰማርታ ነበር፤ አባቴ የሥነ ሕንፃ ባለሙያ ሲሆን የግንባታ ኩባንያ አቋቁሟል። በቤተሰባችን ውስጥ ያለነው አምስት ወንድ ልጆች ስንሆን እኔ የበኩር ልጅ ነኝ። የሚያሳዝነው ከወንድሞቼ ሁለቱ ገና በልጅነታቸው ሞቱ። በዚህ በጣም ስላዘንኩ ‘ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው? ወንድሞቼን ዳግመኛ አገኛቸው ይሆን?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።

ሳይንስ ያጠናኸው ለምንድን ነው?

ፊዚክስ ለማጥናት የፈለግኩት ፍጥረት ያስደንቀኝ ስለነበረ እና ከልጅነቴ ጀምሮ ለሚያሳስቡኝ ጥያቄዎች ፊዚክስ መልስ ይሰጠኝ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ነው።

ምርምር የምታደርግበት መስክ ምንድን ነው?

ኤሌክትሪክ ተሸካሚ የሆኑ ቅንጣቶችን ከብርሃን ፍጥነት ጋር በሚቀራረብ ፍጥነት ማስኬድ ስለሚቻልበት መንገድ ምርምር አደርጋለሁ። ይህን የማደርገው የአተሞችን አወቃቀር ለማጥናት ነው። በተጨማሪም በማይክሮዌቭና በኢንፍራሬድ  ጨረሮች መካከል የሚገኝ ከፍተኛ ኃይል ያለው ጨረር ማመንጨት ስለሚቻልበት መንገድ እመረምራለሁ። ጥናቴ በንግዱ ዓለም ጠቀሜታ ቢኖረውም አጽናፈ ዓለም እንዴት እንደተገኘ ለመረዳት ከሚደረገው ጥረት ጋርም የተያያዘ ነው።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያደረብህ እንዴት ነው?

በ1998 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ መጡ። ለጥያቄዎቼ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ሊያሳዩኝ እንደሚችሉ ነገሩኝ። የሳይንስ ሊቅ የሆነችው ባለቤቴ ህዋቢም አብራኝ ማጥናት ጀመረች። ከዚያ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አይተን የማናውቅ ብንሆንም ይህ መጽሐፍ በሚሰጠው ጠቃሚ ምክር በጣም ተገረምን። ወደ ቤታችን የሚመጡት የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ተግባራዊ በማድረጋቸው ምን ያህል እንደተጠቀሙ አስተዋልን። እነዚህ ባልና ሚስት ደስተኞች ሲሆኑ ኑሯቸውም ያልተወሳሰበ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገረው ነገር፣ ‘አጽናፈ ዓለም የተገኘው በፍጥረት ይሆን?’ ብዬ እንደገና እንዳስብ አደረገኝ። የፊዚክስ ሊቅ እንደመሆኔ መጠን ሥራዬ ተፈጥሮን መረዳት ነው። ስለሆነም መረጃዎቹን በጥንቃቄ ለመመርመር ወሰንኩ።

የፊዚክስ ሊቅ እንደመሆኔ መጠን ሥራዬ ተፈጥሮን መረዳት ነው። ስለሆነም መረጃዎቹን በጥንቃቄ ለመመርመር ወሰንኩ

የትኞቹን መረጃዎች መረመርክ?

በመጀመሪያ፣ አንድ ላይ የተቀመጡ የተወሰኑ ነገሮች ያለ ሌላ አካል ጣልቃ ገብነት በራሳቸው ይበልጥ ሊደራጁ ወይም እንደተደራጁ ሊቆዩ እንደማይችሉ አውቃለሁ። ይህ የተርሞዳይናሚክስ ሁለተኛው ሕግ ነው። አጽናፈ ዓለሙና በምድር ላይ የሚገኘው ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ በመሆኑ ይህን ያደረገ አንድ አካል ይኸውም ፈጣሪ መኖር አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። ትኩረቴን የሳበው ሁለተኛው ሐቅ ደግሞ አጽናፈ ዓለምና ምድር፣ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ለማኖር ታስቦባቸው የተዘጋጁ የሚመስሉ መሆኑ ነው።

እነዚህ ነገሮች ታስቦባቸው የተፈጠሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አገኘህ?

በምድር ላይ የሚኖር ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ ማለት ይቻላል ሕልውናው ከፀሐይ በሚገኘው ኃይል ላይ የተመካ ነው። ይህ ኃይል፣ ሕዋን አቋርጦ በጨረር መልክ ወደ እኛ ይደርሳል። ወደ ምድር የሚጓዘው የተለያየ የሞገድ ርዝመት ባላቸው ጨረሮች መልክ ነው። አጭር የሞገድ ርዝመት ያለው ገዳይ የሆነው ጋማ ጨረር ነው። ከዚያ በመቀጠል ኤክስ ሬይ፣ አልትራቫዮሌት ሬይ፣ በዓይን የሚታየው ብርሃን፣ ኢንፍራሬድ፣ ማይክሮዌቭና ከሁሉም የሚረዝመው የሬዲዮ ሞገድ ይገኛሉ። ከባቢ አየራችን ብዙዎቹ ጎጂ ጨረሮች ወደ ምድር እንዳያልፉ በማገድ ተፈላጊ የሆኑት ጨረሮች ብቻ ወደ ምድር እንዲደርሱ የሚያደርግ መሆኑ በጣም የሚያስደንቅ ነው።

ይህ በጣም ያስደነቀህ ለምንድን ነው?

ስለ ፍጥረት የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መግቢያ እንዲሁም ስለ ብርሃን የሚናገረው ነገር አስገርሞኝ ነበር። ዘገባው “እግዚአብሔር ‘ብርሃን ይሁን’ አለ፤ ብርሃንም ሆነ” * ይላል። ከፀሐይ ከሚመጡት በርካታ ጨረሮች መካከል በዓይናችን ልናየው የምንችለው ብርሃን በጣም የተወሰነው ነው፤ ይሁን እንጂ ብርሃን ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነው። ዕፅዋት ምግብ ለመሥራት የፀሐይ ብርሃን ያስፈልጋቸዋል፤ እኛም ማየት የምንችለው ብርሃን ካለ ብቻ ነው። ከባቢ አየር ብርሃን ማስተላለፍ የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ሊሆን አይችልም። ወደ ምድር ገጽ የሚደርሰው በጣም አነስተኛ የሆነው አልትራቫዮሌት ብርሃን ደግሞ ይበልጥ አስደናቂ ነው።

ይህ ትኩረትህን የሳበው ለምንድን ነው?

መጠነኛ የሆነ አልትራቫዮሌት ጨረር እጅግ አስፈላጊ ነው። ቆዳችን መጠኑ አነስተኛ የሆነ አልትራቫዮሌት ብርሃን ያስፈልገዋል፤ ይህም ለአጥንታችን ጤንነት እንዲሁም ካንሰርንና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል አስፈላጊ የሆነውን ቪታሚን ዲ ለመሥራት ይረዳል። ይሁን እንጂ ይህ ጨረር ከበዛ የቆዳ ካንሰርና የዓይን ሞራ ግርዶሽ ያስከትላል። ከባቢ አየር የተዘጋጀው በጣም አነስተኛ የሆነ የአልትራቫዮሌት ጨረር ብቻ ወደ ምድር እንዲያሳልፍ ተደርጎ ሲሆን ይህም ለምድር የሚያስፈልገው ትክክለኛ መጠን ነው። ይህ ሐቅ፣ ምድር ሕይወት ያለው ነገር እንዲኖርባት ታስባ የተሠራች መሆኗን የሚያሳምን ማስረጃ እንደሆነ ይሰማኛል።

ቀስ በቀስ እኔና ህዋቢ ፈጣሪ እንዳለና መጽሐፍ ቅዱስንም ያስጻፈው እሱ እንደሆነ አመንን። በ2005 የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን፤ አሁን መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች በማስተማሩ ሥራ እንካፈላለን።