በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ሐምሌ 2014

 ንድፍ አውጪ አለው?

እንቁላሎቿን ሆዷ ውስጥ የምትታቀፈው እንቁራሪት የመራቢያ ሥርዓት

እንቁላሎቿን ሆዷ ውስጥ የምትታቀፈው እንቁራሪት የመራቢያ ሥርዓት

እንቁላሎቿን ሆዷ ውስጥ የምትታቀፈው የአውስትራሊያ የእንቁራሪት ዝርያ (ጋስትሪክ ብሩዲንግ ፍሮግ) ያልተለመደ ዓይነት የመራቢያ ሥርዓት አላት፤ የዚህች እንቁራሪት ዝርያ ከ2002 ጀምሮ እንደጠፋ ይታሰባል። እንስቷ እንቁራሪት በወንዴው ዘር የዳበሩትን እንቁላሎቿን ከዋጠቻቸው በኋላ ለስድስት ሳምንት ያህል ሆዷ ውስጥ ታቅፋ በማቆየት እንዲቀፈቀፉ ታደርጋለች። እንቁላሎቹ ሲፈለፈሉ እድገታቸውን የጨረሱት እንቁራሪቶች በአፏ በኩል ይወጣሉ።

እናቲቱ እንቁራሪት፣ እንቁላሎቹ ጨጓራዋ ውስጥ እንዳይፈጩ ለመከላከል መብላት የምታቆም ከመሆኑም ሌላ ጨጓራዋ አሲድ ማመንጨቱን ያቆማል። አሲድ እንዳይመነጭ የሚያደርገው እንቁላሎቹና ትናንሾቹ እንቁራሪቶች የሚያመነጩት ኬሚካል መሆን አለበት።

እናቲቱ ሁለት ደርዘን የሚያህሉ እንቁላሎችን ሆዷ ውስጥ ትታቀፋለች። ልጆቿ ለመወለድ በሚደርሱበት ጊዜ የጠቅላላ ክብደቷን 40 በመቶ ያህል ይሆናሉ። ይህም ከማርገዟ በፊት 68 ኪሎ ግራም ትመዝን የነበረች አንዲት ሴት እያንዳንዳቸው 1.8 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 24 ልጆች የተሸከመች ያህል ይሆናል ማለት ነው! እንቁራሪቶቹ እያደጉ ሲሄዱ የእናቲቱ ሆድ በጣም ስለሚለጠጥና ሳምባዎቿን ስለሚጫኗት በቆዳዋ በኩል ለመተንፈስ ትገደዳለች።

ትናንሾቹ እንቁራሪቶች ለመወለድ ሲደርሱ በቀናት ጊዜ ውስጥ በአፏ በኩል ይወጣሉ። እናቲቱ አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳለች ከተሰማት ግን ትተፋቸዋለች። ተመራማሪዎች አንዲት እናት እንቁራሪት ስድስት ልጆቿን 1 ሜትር ያህል እያስፈነጠረች ስትተፋቸው የተመለከቱበት ጊዜ አለ።

አንዳንዶች እንደሚሉት የዚህች እንቁራሪት የመራቢያ ሥርዓት በዝግመተ ለውጥ የመጣ ቢሆን ኖሮ በሰውነቷ አፈጣጠርም ሆነ በባሕርይዋ ላይ በአንድ ጊዜ ሰፊ ለውጥ ማድረግ ነበረባት። የዝግመተ ለውጥ አራማጅና የሳይንስ ሊቅ የሆኑት ማይክል ታይለር “በመራቢያ ሥርዓቷ ላይ አዝጋሚና በጊዜ ሂደት የተካሄደ ለውጥ ተከስቷል ብሎ ማሰብ ጨርሶ የማይመስል ነገር ነው” ሲሉ ጽፈዋል። “ይህ ሂደት ሙሉ በሙሉ ውጤታማ መሆን አለበት፤ ካልሆነ ጨርሶ ሊሠራ አይችልም።” ታይለር አሳማኝ የሚሆነው ብቸኛው ማብራሪያ “በአንድ ጊዜ ትልቅ ለውጥ ተካሂዷል” የሚለው እንደሆነ ይናገራሉ። አንዳንዶች ይህ ትልቅ ለውጥ ፍጥረት እንደሆነ ያምናሉ። *

ታዲያ ምን ይመስልሃል? እንቁላሎቿን ሆዷ ውስጥ የምትታቀፈው እንቁራሪት የመራቢያ ሥርዓት በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

^ አን.7 ቻርልስ ዳርዊን ኦሪጅን ኦቭ ስፒሺስ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ተፈጥሯዊ ምርጦሽ የሚካሄደው ተከታታይ የሆኑ ትናንሽ ለውጦችን በማድረግ ብቻ ነው፤ . . . እመርታዊ ለውጥ ሊኖር አይችልም።”